Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊግንባታ ሳያጠናቅቅ ከሥራ ተቋራጩ ጋር ጠፍቷል የተባለው አማካሪ ድርጅት አለሁ አለ

ግንባታ ሳያጠናቅቅ ከሥራ ተቋራጩ ጋር ጠፍቷል የተባለው አማካሪ ድርጅት አለሁ አለ

ቀን:

ሚያዝያ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የቁም እንስሳት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ለመገንባት ስምምነት ፈጽመው ግንባታውን ሳይጨርሱ የተሰወሩ ካሉዋቸው መካከል፣ ከሥራ ተቋራጩ ጋር ስሙ አብሮ የተነሳው በለስ ኮንሰልቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጠፍቷል መባሉን አስተባበለ፡፡

በእሑድ ሚያዝያ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ዕትም መንግሥት የቁም እንስሳት ለውጭ ገበያ ከመቅረባቸው በፊት የጤንነታቸው ሁኔታ የሚፈተሽበት ጣቢያ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አልመሃር በተባለ ሥፍራ፣ ግንባታውን እንዲያከናውን የግንባታ ውል የተፈራረመው ቱሊፕ የተባለው ተቋራጭና በለስ ኮንሰልቲንግ ግንባታውን ሳያጠናቅቁ በመሰወራቸው፣ ለሕግ ለማቅረብ እየተፈለጉ መሆናቸውን ለፓርላማ መግለጻቸውን፣ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስትሩ ፍቃዱ በላይ (ፕሮፌሰር) ዋቢ ተደርገው መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ አማካሪ ድርጅቱ ጠፍቷል፣ ሪፖርት አላደረገም መባሉን ያልተቀበሉት የድርጀቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ አዳሙ ከበደ (ኢንጂነር)፣ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን በተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በማማከር መደበኛ ሥራ ላይ መሆናቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ተጨማሪ ጨረታዎችን በመከታተል በመደበኛ ሥራቸው ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተርም በቢሯቸው ተገኝቶ በአነጋገራቸው ወቅት፣ ‹‹ድርጅቴም ሆነ እኔ መቼም ጠፍተን አናውቅም፡፡ የበርካታ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ኮንትራት ወስደን እየሠራን ባለንበት ወቅት አገር ጥለን የሚያስጠፋን ጉዳይ የለም፤›› በማለት ሚኒስቴሩ የራሱን ችግሮች ለማድበስበስ ሲል ፓርላማ ድረስ ስም ማጥፋት አይገባውም ነበር ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

ነገር ግን በሥራ ተቋራጩ ችግርና የአቅም ውስንነት ምክንያት ፕሮጀክቱ ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ የሚኒስቴሩን ሥጋት ቢጋሩም፣ አማካሪው የችግሩ አካል ሆኖ ሊያስወቅሰው የሚችል ጥፋት አልነበረበትም ብለዋል፡፡ ይልቁንም ድርጅታቸው ቀደም ብሎ ሥራ ተቋራጩ በታሰበው መሠረት ለመገንባት እንደተሳነውና የአቅም ችግር ውስጥ መግባቱን ደጋግሞ በመጥቀስ ለሚኒስቴሩ ማስታወቁን፣ ሊወስድ የሚገባቸውን ዕርምጃዎች በተደጋጋሚ ተናግሮ ሊሰማ ባለመቻሉ፣ ግንባታው እንዲጠናቀቅ ታቅዶ ከነበረበት ከሰኔ 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ለዓመታት መጓተቱንና በጅምር ስለመቅረቱ አውስተዋል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ ለክትትልና ለማማከር አገልግሎት ሊከፈላቸው የሚገባው ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው አቶ አዳሙ አክለዋል፡፡

‹‹በመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ መሠረት ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በቅርበት የሚከታተሉት ፕሮጀክት በመሆኑ፣ በነፃ ጭምር ለአራት ዓመታት አገልግሎት ስንሰጥ ቆይተናል፤›› ብለዋል፡፡

ከሥራ ተቋራጩ እኩል የአማካሪ ኩባንያው ስም መነሳት እንዳልነበረበት የሚገልጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ለሚኒስትሩ ሪፖርት አለማቅረባቸውን በተመለከተ ለተነሳላቸው ግን ሪፖርቱን አለማቅረባቸውን አልካዱም፡፡ ነገር ግን፣ ‹‹ለግንባታው መጓተትም ሆነ መቋረጥ አማካሪው አለመሆኑ እየታወቀ እንዴት ሪፖርት ላስገባ እችላለሁ?›› በማለት ለድርጅታቸው የሚገባው ክፍያ ተሟልቶ እንዳልተከፈለ ተናግረዋል፡፡

ቀደም ብሎ በሚኒስቴሩ ኃላፊዎችና በአማካሪ ድርጅቱ መካከል የተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦችን ሪፖርተር የተመለከተ ሲሆን፣ ታኅሳስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚኒስቴር ዴኤታዋ ዶ/ር ምሥራቅ መኮንንን የተፈረመ፣ ግዴታን ባለመወጣት በመካከላቸው የነበረው ውል መቋረጡን የሚያመለክት ደብዳቤ ለበለስ ኮንሰልቲንግ ተጽፎለታል፡፡ በዚህም ደብዳቤ፣ ‹‹ኮንትራክተሩና የመሥሪያ ቤታችን መሐንዲስ በግንባታው ቦታው ተገናኝተው የግንባታው ሥራ ስላለበት ደረጃ መረጃዎችን ሰብስበው፣ ከኮንትራክተሩ ላይ ቦታውን ተረክበው ተመልሰዋል፡፡ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት አማካሪ ድርጅቱ በቀጣይነት የፊዚካል ሥራው ያለበትን ደረጃ ለኮንትራክተሩ እስከ ውል መቋረጥ ጊዜ ድረስ የተከፈለውን ክፍያና ቀሪ ሒሳብ በማስላት አጠቃላይ ሪፖርት ማቅረብ ሲገባው አላቀረበም፡፡ አማካሪ ድርጅቱ ይኼን ሪፖርት አጠናቅሮ ባለመቅረቡ መሥሪያ ቤታችን ቀሪ የግንባታ ሥራ አጠናቆ ጣቢያውን ወደ ሥራ ማስገባት አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት መሥሪያ ቤታችን የቁም እንስሳት ወደ ውጭ ልኮ ማግኘት የሚገባው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከአንድ ዓመት በላይ በሚሆን ጊዜ ማግኘት አልቻለም፤›› በማለት የውል ማቋረጥ ደብዳቤ ሚኒስቴሩ ጽፏል፡፡

አማካሪው በበኩሉ ታኅሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሚኒስቴሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹የእኛ ኮንትራት ያለቀው በሰኔ 2004 ዓ.ም. በመሆኑ በወቅቱ ኮንትራቱ ታድሶ ሥራው እንዲጠናቀቅ በተደጋጋሚ ብናሳስብም፣ ኢንቴንት ኦፍ ክሌም (Intent of Claim) ብናስገባም፣ በተጨማሪ ክሌም (Claim) ብናደርግም ከነገ ዛሬ በሚል ምክንያት ሊስተካከል አልቻለም፤›› ሲል ገልጿል፡፡ ‹‹በተጨማሪም እንዲስተካከል ተስማምተን ከወጣን በኋላ፣ ኮንትራክተሩ ገብቶ ሥራውን ባለመሥራቱ ምክንያት ሳይስተካከል ቀርቷል፤›› ሲሉም የአማካሪው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

‹‹ይኼ ሁሉ ሳይሆን በመጀመሪያ ኮንትራክተሩ በወቅቱ ሥራውን መጨረስ አለመቻሉን ጠቅሰን ኮንትራክችዋል የሆነ ዕርምጃ (Contractual Measure) እንዲወስድ ሪከመንድ (Recommend) ብናደርግም ምንም ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቶ በመጨረሻ የእኛ ኮንትራት ያለበት ሁኔታ ሳይታወቅ የኮንትራክተሩ ውል እንዲቋረጥ ተደርጓል፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹በዚህ ላይ ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም (ከግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2004 ዓ.ም.) ድረስ እንድንሠራ ተደርጎ ውላችን ቢቋረጥ ኖሮ እኛም የሠራተኛ ውል አቋርጠን ሥራውን አናቆምም ነበር፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ይኼ ባልሆነበት ሁኔታና የእኛ በየወቅቱ የሥራና የደብዳቤ ግንኙነት ባልተቋረጠበት ክፍያ ተከልክለን የቆየን መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶልን፣ ከሰኔ 2004 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2007 ዓ.ም. ማለትም የሦስት ዓመት ከሁለት ወር ቫትን ጨምሮ ከ 3.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፈለን፤›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ‹‹እኛም በዚህ ሁኔታ የፕሮጀክቱን የመጨረሻ ሪፖርት ሠርተን ያዘጋጀን ቢሆንም፣ የውሉን መሻሻልና መታደስ ባላወቅንበት ሁኔታ ሪፖርቱን ማስገባት ያስቸገረ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ያልተከፈለን ክፍያ እንዲከፈለን እንጠይቃለን፤›› በማለት አማካሪ ድርጅቱ ለሚኒስቴሩ በጻፈው ደብዳቤ መግለጹን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ውዝግቡን አስመልክቶ ከሚኒስቴሩ ጋር በድጋሚ ለመወያየት አማካሪ ድርጅቱ ማቀዱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...