Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከብክለት ነፃ በሆነው የባቡር ትራንስፖርት ምክንያት አዲስ አበባ ተሸለመች

ከብክለት ነፃ በሆነው የባቡር ትራንስፖርት ምክንያት አዲስ አበባ ተሸለመች

ቀን:

በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ቁጥጥር ላይ የሚሠራውና ‹‹ሲ-40 የአየር ንብረት ፎረም›› የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም፣ በአየር ንብረት ጥበቃ በተለይም ከብክለት ነፃ በሆነው የኤሌክትሪክ ባቡር ትራንስፖርቷ ሳቢያ እ.ኤ.አ. በ2016 ውድድር አዲስ አበባ ከተማ ማሸነፏ ተገለጸ፡፡

ሐሙስ ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ቃሊቲ በሚገኘው የአዲስ አበባ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ግቢ ውስጥ ተገኝተው ሽልማቱን ሲቀበሉ እንደተናገሩት፣ በአዲስ አበባ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ እየተሠራ ያለው ሥራ ምቹና አካባቢን የማይበክል ነው፡፡ እንዲሁም የባቡር ትራንስፖርት ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የሚገለገሉበት በመሆኑም ጭምር አዲስ አበባ ውድድሩን ለማሸነፍ እንዳስቻላት ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌታቸው በትሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የአካባቢ ብክለትን በመቆጣጠርና በካይ ጋዞችን በማስወገድ ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ያለውም ሆነ ወደፊት የሚገነባው የባቡር ትራንስፖርት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም በመሆኑ፣ በአካባቢ ላይ ብክለት አያስከትልም፤›› በማለት አክለዋል፡፡

- Advertisement -

‹‹የሲ-40›› የአየር ንብረት ፎረም የአፍሪካ ዳይሬክተር ሃሰቲንግስ ቺኮኮ  የአዲስ አበባ የባቡር ትራንስፖርት አካባቢን የማይጎዳና ለዜጎችም ምቹ አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ, አዲስ አበባ ውድድሩን እንድታሸንፍ እንዳበቃት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለአንድ ከተማ ማደግና አካባቢያዊ ጥበቃ መጎልበት አመራሮች ከፍተኛ ዋጋ አላቸው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹መሪነት ማለት ቃል መግባት፣ ዕቅድና ፖሊሲ ማውጣት ብቻ አይደለም፡፡ ማውራት ቀላል ነገር ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካላት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለዚህ ሽልማት ሊበቁ ችለዋል፤›› ሲሉም አስተዳደሩን አሞካሽተዋል፡፡

‹‹ሲ-40›› የተሰኘውና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሠራው ተቋም አባል ከተሞች አካባቢን በመጠበቅ ረገድ ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይ ሪፖርት በየሁለት ዓመቱ እንደሚለቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አዲስ አበባም የውድድሩ አሸናፊ ልትሆን የቻለችው እ.ኤ.አ. በ2016 ሜክሲኮ ላይ በተካሄደው ውድድር እንደነበር በመድረኩ ተገልጿል፡፡ በዚህ ውድድር ከ100 በላይ ከተሞች ተሳትፈው እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ቺኮኮ እንደተናገሩት፣ በመላው ዓለም ካሉ ከተሞች ውስጥ 160 ያህሉ በተቋሙ ለመካተት የአባልነት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንዱን ከተማ ባቡር የአዲስ አበባ ከተማ እህት በሆነችው የጀርመኗ ላይፕዚሽ ከተማ ስም ሰይሟል፡፡

ረቡዕ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ቃሊቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ቅጥር ግቢ ውስጥ በነበረው ሥነ ሥርዓት ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ድሪባ፣ ‹‹ከዚህ በፊት በጀርመኗ ላይፕዚሽ ከተማ ውስጥ ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ያገለገለና አሁንም በማገልገል ላይ ያለ አንድ ባቡር በአዲስ አበባ ከተማ ስም ተሰይሟል፡፡ እኛ ደግሞ አንዱን ባቡራችንን እነሆ ዛሬ በላይፕዚሽ ከተማ ስም ሰይመናል፤›› ብለዋል፡፡

ከንቲባው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ ከሃያ በላይ የውጭ ከተሞች ጋር የእህትማማችነት ግንኙነት ቢኖራትም ከላይፕዚሽ ጋር ያለው ግንኙነት ግን የበለጠ ተጠናክሯል፡፡ በዚህ ግንኙነት የተነሳም ፒኮክ አካባቢ ለሚገነባው የእንስሳት ፓርክ ባለሙያዎችን በመላክ የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌታቸው በትሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ይህች የአዲስ አበባ ከተማ አንዷ ባቡር በላይፕዚሽ ከተማ ስም መሰየሟ በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የላይፕዚሽ ከተማ ከንቲባ በርክሃርድ ጃንግ በበኩላቸው፣ ‹‹አዲስ አበባና ላይፕዚሽ የተለየ ትስስር አላቸው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የከተማችሁን ስም የእኛ የአንዷ ባቡር ስያሜ እንዲሆን አድርገናል፡፡ እናንተ ደግሞ አንዷን ባቡራችሁን በእኛ ከተማ ስም ሰይማችኋል፡፡ ይህ ሁለቱንም ከተሞች ለማስተዋወቅ ያለው ፋይዳ ጉልህ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከንቲባው አያይዘውም ሁለቱ እህት ከተሞች በባህልና በቋንቋ ያላቸው ግንኙነትም መልካም የሚባል እንደሆነ ገልጸው፣ ወደፊት በበለጠ ሁኔታ ይጠናከራል ብለዋል፡፡

አዲስ አበባና ላይፕዚሽ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩት እ.ኤ.አ በ2004 እንደነበር ተወስቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...