Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊስድስት በካይ የተባሉ የቆዳ ፋብሪካዎች እንዲታገዱ የተላለፈው ውሳኔ ታገደ

ስድስት በካይ የተባሉ የቆዳ ፋብሪካዎች እንዲታገዱ የተላለፈው ውሳኔ ታገደ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የኢንዱስትሪ ብክለት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው የተባሉ ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎች እንዲታገዱ ውሳኔ ቢተላለፍም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጉዳዩን አመዛዝኖ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የተላለፈውን ውሳኔ ተፈጻሚ እንዳይሆን አገደ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ሰባት የቆዳ ፋብሪካዎች ውስጥ ከኢትዮ ሌዘር ኢንዱስትሪ ኩባንያ (ኤሊኮ) በስተቀር ስድስቱ ፋብሪካዎች እንዲታገዱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ውሳኔው ከመጋቢት መጨረሻ ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን ቢገባውም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔው ላይ ተነጋግሮ የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ያስፈልጋል በማለት የባለሥልጣኑ ውሳኔ ተፈጻሚ እንዳይሆን አግዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲታገዱ ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ድሬ፣ አዲስ አበባ፣ አዋሽ፣ ኒው ዊንግ፣ ባቱና ዋልያ ቆዳ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ፍሳሻቸውን በቀጥታ ወደ ወንዝ በመልቀቅ በአካባቢ፣ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ብክለት እየደረሱ በመሆናቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲታገዱ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ተፅዕኖና ግምገማና ብክለት ቁጥጥር ዋና የሥራ ሒደት መሪ አቶ አዱኛ ለሜሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ ባካሄደው ጥናት እነዚህ ፋብሪካዎች ፍሳሻቸውን በቀጥታ ወደ አካባቢ በመልቀቅ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡

‹‹ባለሥልጣኑ እንዲታገዱ ውሳኔ ቢያስተላልፍም የከተማው አስተዳደር ማወቅና መወሰን ያለበት ጉዳይ በመኖሩ ለጊዜው እገዳው እንዲቆይ አድርጓል፤›› ሲሉ አቶ አዱኛ ገልጸው፣ ‹‹ፋብሪካዎች የሚታሸጉት በግብር ኃይል በመሆኑና በተለይ በግብረ ኃይሉ ዋነኛ ተሳታፊ የሚሆኑት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የክፍላተ ከተሞች ሥራ አስፈጻሚዎች ተጠሪነታቸው ለከንቲባው በመሆኑ፣ ከንቲባው ሊያውቁትና ውሳኔ ሊሰጡበት ይገባል፤›› ሲሉ አቶ አዱኛ ዕርምጃው የዘገየበትን ምክንያት ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ለቆዳ ፋብሪካዎች ጽፎት የነበረው ደብዳቤ በኋላ ተፈጻሚ መሆን ባይችልም እንደገለጸው፣ በአዋጅ ቁጥር 35/2004  በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት የከተማውን ውበትና ፅዳት የሚበክሉ፣ ደረቅም ሆነ ፍሳሽ በካይ ነገሮችን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥልጣን  እንዳለው አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የብክለት ቁጥጥር ደንብ  ቁጥር 25/2000 ዓ.ም እና አዋጅ ቁጥር 300/1995 ዓ.ም.፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ብክለት ቁጥጥር ደንብ ቁጥር 158/2001 ዓ.ም. የወጡትን ሕግጋት መሠረት በማድረግ ሥራቸውን በማያከናወኑ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ላይ በሕግ አግባብ እንደ ጥፋቱ ዓይነትና ጉዳት መጠን ፈቃድ መሰረዝ፣ ከቦታ ማዛወርና እስከ መዝጋት ድረስ ያሉ የቅጣት ውሳኔና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚችልም አስታውሷል፡፡

ነገር ግን እነዚህ ፋብሪካዎች በኅዳር 2009 ዓ.ም በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በተደረገ ውይይት ፋብሪካዎቹ በኅብረተሰቡና በአካባቢ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን እንዳመኑ፣ የተሻለ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ እንደሚገነቡ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ባለሥልጣኑ በጻፈው ደብዳቤ አስታውሷቸዋል፡፡

‹‹ድርጅታችሁ እያደረሰ ያለውን ብክለት እንዲያቆም የማስተካከያ ዕርምጃ እንድትወስዱ በተደጋጋሚ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ቢጻፍላችሁም ለማስተካል ፈቃደኛ አልሆናችሁም፡፡ በሰኔ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በቁጥር 171/18-01 182 17 በተጻፈ ደብዳቤ ለመጨረሻ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣችሁም ማስተካከል አልቻላችሁም፤›› ሲል ባለሥልጣኑ ትዕግሥቱ ማለቁን አመልክቷል፡፡

በዚህ ምክንያት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የኢንዱስትሪ ብክለት መከላከያ ደንብ ቁጥር 159/2001 ዓ.ም. እና የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ  300/1995 ዓ.ም. አንቀፅ (4) መሠረት ከመጋቢት 17/2009 ዓ.ም. ጀምሮ ፋብሪካዎቹ እንዲታሸጉ ባለሥልጣኑ ትእዛዝ በማስተላለፍ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ፋብሪካዎቹን በማሸግ ሒደት እንዲተባበሩ ጠይቋል፡፡

ነገር ግን የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር የባለሥልጣኑ ውሳኔ ተግባራዊ ሳይሆን በፊት አግዶታል፡፡ ፋብሪካዎቹ በካይ በመሆናቸው ለዓመታት ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ሊያስተባብሉ ስላልቻሉ፣ አስተዳደሩ ዕርምጃ ይወስዳል ብለው እንደሚጠብቁ አቶ አዱኛ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲዘጉ ከወሰነባቸው መካከል የድሬ ቆዳ አክሲዮን ማኅበር አንዱ ነው፡፡ ድሬ ቆዳ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ዊንጌት አካባቢ ይገኛል፡፡ የድሬ ቆዳ ፋብሪካ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሐጂ በዳዳ ጫሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የእሳቸው የቆዳ ፋብሪካ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው፡፡ ሐጂ በዳዳ ፋብሪካቸው በካይ ነው ብለው አያምኑም፡፡ ምክንያቱም 1.2 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ሁለተኛ ደረጃ የፍሳሽ ማጣሪያ በመግጠም ንፁህ የሚባል ፍሳሽ ወደ ወንዝ እንደሚለቁ ገልጸዋል፡፡ ድሬ እ.ኤ.አ. በጥር 2004 የአይኤስኦ 14001 ሠርተፊኬት አግኝቷል፡፡ ይህ ሠርተፊኬት በምርት፣ በአስተሻሸግና በመጋዘን ክምችት ሒደት መልካም አሠራር መኖሩን የሚያመለክት ነው፡፡

ድሬ ቆዳና እህት ኩባንያው ድሬ ጫማ ፋብሪካ በድምሩ 1,300 ሠራተኞች እንዳሉት ሐጂ በዳዳ ገልጸው፣ ፋሪካው የሚዘጋ ከሆነ እነዚህ ሁሉ ሠራተኞች ይበተናሉ ብለዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ጉዳዩን በጥሞና ቢመለከተው፣ ጉዳዩንም በጥልቀት አጥንቶ መልስ ቢሰጥ መልካም ነው፤›› ሲሉ ሐጂ በዳዳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የቆዳ ፋብሪካዎች በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ 76 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ሞጆ ከተማ ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የቆዳ ፋብሪካዎቹ ደንበኛ የፈሳሽ ማጣሪያ የሌላቸው በመሆናቸው ፈሳሻቸውን በቀጥታ ወደ ወንዝ ይለቃሉ፡፡

አዲስ አበባና ዙሪያዋ የአዋሽ ተፋሰስ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደመሆናቸው፣ የአካባቢ ብክለቱ ሰፊ ቦታ የሚሸፍንና በበርካታ ሰዎች የዕለት ጉርስ የሚያገኙባቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ማሳዎች ያሉበት፣ በርካታ የእንስሳ ሀብት ያለበት በመሆኑ እየተከሰተ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በተለይ ከቆዳ ፋብሪካዎች የሚወጣው ክሮም የተባለ ንጥረ ነገር ለጤና አደገኛ ነው፡፡ ካንሰርና በሰው ልጆና በእንስሳት ላይ የተዛባ ዕድገት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በአትክልትና በፍራፍሬዎች ውስጥ በመዋሀድ የመቀመጥ ባህሪ ያለው በመሆኑ፣ አደገኛነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ባለሙዎች ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩትና ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሰ፣ እነዚህን ፋብሪካዎች በመዝጋት የአዲስ አበባ ወንዞች ንፁህ ይሆናሉ ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የእግዱ ጉዳይ ወደ እሳቸው መሥሪያ ቤት እንዳልመጣ፣ ነገር ግን ፋብሪካዎች በኢኮኖሚው ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ እንዲገባ አቶ ወንዱ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡    

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...