Sunday, April 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የምኞት ፈረስን መጋለብ አይቻልም!

 መመኘት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ምኞት ደግሞ በቀላሉ ሊገኝ የማይችል ነገርን የራስ ለማድረግ በስሜት የተጠናከረ ፍላጎት መግለጫም ነው፡፡ ምኞት ምናልባትም ፈፅሞ ሊገኝ የማይችል ነገርን የመፈለግ በስሜት የተሞላ ደመነፍሳዊ እሳቤ ነው፡፡ ‹‹ደግ ተመኝ ደግ እንድታገኝ›› የሚል ዕድሜ ጠገብ ብሂል ቢኖርም፣ ምኞት ዕውን የሚሆነው በስሜት ሳይሆን በተግባር በተደገፈ ጥረት ብቻ ነው፡፡ ይህ ጥረት ‹‹በእርስዎም ይሞክሩት›› መንገድ ሳይሆን በሳይንስ ሊታገዝ ይገባዋል፡፡ በጥናትና በምርምር የሚታገዝ ጥረት መኖር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የተማረ የሰው ኃይልን በሚገባ መጠቀም፡፡ በዕውቀት፣ በክህሎትና በልምድ የበለፀጉ ባለሙያዎችን ከያሉበት ማፈላለግ፡፡ ሥራና ሠራተኛን ማገናኘት፡፡ ያኔ ውጤቱ በራሱ ይናገራል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ከግለሰብ ሕይወት ጀምሮ በማኅበረሰብ ደረጃ፣ በግሉ ዘርፍ፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ተግባራዊ ሲሆን አገር ጤና ሁሉም ደህና ይሆናል፡፡ አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮችን አንስቶ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡

በ16ኛው ክፍለ ዘመን እንደተነገረ የሚወሳለት አንድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ አባባል፣ ‹‹ምኞት ፈረስ ቢሆን ኖሮ ምንዱባን ይጋልቡት ነበር›› ይላል፡፡ ይህ አባባል ምኞት ነገሮችን ማሳካት ቢችል ድሆች የፈለጉትን ማድረግ ይችሉ እንደነበር የሚያሳስብ ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓለም እውነታና ምኞት የተለያዩ ናቸው፡፡ ከግለሰባዊ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጀምሮ እስከ አገር አጠቃላይ ጉዳይ ድረስ በጎ በጎውን መመኘት መልካም ቢሆንም፣ በተደራጀ ዕቅድ ላይ ተመሥርቶ ሥራዎችን አለማከናወን ህልመኛ ነው የሚያደርገው፡፡ የአገር ጉዳይ ሲሆን ደግሞ ከብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ጀምሮ እስከ ሕዝብ መሠረታዊ መብቶችና ፍላጎቶች ድረስ፣ በተቻለ መጠን በጥናትና በምርምር ላይ የታገዙ አሠራሮችን መከተል በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ መደነባበርና አሰልቺ የዘመቻ ሥራዎች ውስጥ መዘፈቅ የሚከተለው፣ እውነታንና ምኞትን ለያይቶ ለማየት ባለመቻል ወይም በደንታ ቢስነት ሳቢያ ነው፡፡ በምኞት ብቻ የፈለጉትን ማግኘት እንደማይቻል ሁሉ፣ በባለሙያዎች ያልታገዘ ጥረት የትም አያደርስም፡፡ ‹‹ልፋ ያለው ገለባ ይወቃል›› እንደሚባለው ሁሉ ከምርቱ ይልቅ ግርዱ ይበረክታል፡፡

በአገራችን ከመንግሥት ስንጀምር ብዙ ጉድለቶች ይታያሉ፡፡ አንደኛው ለበርካታ ዓመታት ለምሁራንና ለባለሙያዎች የሚሰጠው የተሳሳተ ግምት ነው፡፡ ሁለተኛው በጥናትና በምርምር ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማትን ለማደራጀትም ሆነ በራሳቸው ጊዜ እንዲመሠረቱ ፍላጎት አለመኖር ነው፡፡ ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ደግሞ ለሙያና ለሲቪክ ማኅበራት አለመኖር ወይም መሽመድመድ መንስዔ መሆን ነው፡፡ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ዕቅድ አውጥተውና በጀት ተይዞላቸው የሚሠሩ ቢሆንም፣ ከአስተቃቀዳቸው ጀምሮ እስከ አፈጻጸማቸው ድረስ በጥናት ላይ የተመሠረተ ቁጥጥርና ክትትል ስለማይደረግላቸው ከአቅም በታች ይሠራሉ፡፡ በጀታቸውን እንኳ በአግባቡ ሲያወራርዱ አይታዩም፡፡ ለባለሙያዎችና ለባለ ክህሎቶች የተሰጠው ሥፍራ አናሳ በመሆኑ፣ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት በአቅም አልባዎች ስለሚመሩ ውጤታቸው ‹‹ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ›› እንደሚባለው ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አሠራራቸው ለሕዝብ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዳለበት ቢደነገግም፣ ብዙዎቹ ምን እንደሚሠሩ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ማጣፊያው ሲያጥር ግን በሐሰተኛ ሪፖርቶች ታጅበው አደባባይ ብቅ እያሉ ግራ መጋባት ይፈጥራሉ፡፡ የፋይናንስም ሆነ የሥራ አፈጻጸማቸው በጥልቀት ሲጠና ግን ‹‹ዱባና ቅል ለየቅል›› ሆነው ይቀርባሉ፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መዛባትና በሙስና ምክንያት መቸገሩን አሳውቆ ዕርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ቢገልጽም፣ ችግሩ ገደቡን ጥሶ ደም አፋሳሽ አመፅ ተከስቶ ነበር፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የደረሰው የዜጎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ እንግልትና የንብረት ውድመት ለአገርና ለሕዝብ ሥጋት ሊፈጥር የቻለው መፍትሔው ቀላል ሆኖ ተግባራዊ ለማድረግ ባለመቻል ሳቢያ ነው፡፡ ሕዝብ በደልና ሰቆቃ ደረሰብኝ ሲል ለማዳመጥ ፈቃደኛ አለመሆን ትልቁ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ ፍትሕ የተዛባበት ዜጋ ሕግ የሚያስከብርለትና ከለላ የሚሰጠው መንግሥት ሲያጣ እንደሚያምፅ ማንም አይስተውም፡፡ ሰብዓዊ ፍጡር በመሆኑ ብቻ የተቀዳጃቸውን መሠረታዊ መብቶች የተነፈገ ማንም ወገን፣ መጀመሪያ ሕግ እንዲከበርለት የሚጠይቀው መንግሥትን ነው፡፡ መንግሥት እያንዳንዱን ዜጋ የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ፣ አሠራሩ ደግሞ በሕግ ተጠያቂነት አለበት፡፡ ይህንን ዓይነቱን በዓለም የተለመደ አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች የፀደቁ ሕጎች አሉ፡፡ የሕግ የበላይነት ተከብሯል የሚባለውና በሕዝብም አመኔታ የሚያገኘው ሕጎች በአግባቡ ሲከበሩ ብቻ ነው፡፡ ይህንንም የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት አፅድቆ ቁጭ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም ሕጎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተጣጣሙ መሆን እንዳለባቸው የማስፈጸም ግዴታ አለበት፡፡ ሕጎች ዜጎችን መጠበቂያ እንጂ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆኑ መከላከል የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ መንገድ ኃላፊነትን መወጣት ባለመቻሉ ምክንያት ብቻ የማይወጡበት ቀውስ ውስጥ ይገባል፡፡ ሕግ በምኞት አይከበርም፡፡ ይልቁንም በባለሙያዎች በመታገዝ ተገቢው ክትትል፣ ቁጥጥርና እርማት ሲደረግ ሰላም ይሰፍናል፡፡

ሌላው ችግር የአገር ተረካቢ የሆኑ ወጣቶችን የሚመለከት ነው፡፡ ወጣቶችን አቅም በፈቀደ መጠን ተንከባክቦ ማሳደግ፣ ማስተማርና ለወግ ማዕረግ ማብቃት የቤተሰብ፣ የማኅበረሰቡና የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ወጣቶችን በአዕምሮ፣ በአካልና በሥነ ልቦና በማጎልበስ ከአደንዛዥ ዕፆች፣ ከተለያዩ ሱሶችና ከመጤ የባህል ወረርሽኞች መከላከል ሌላው ዋነኛ ተግባር ነው፡፡ ራሳቸው ወጣቶች፣ ቤተሰቦች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ መንግሥት፣ ወዘተ በባለቤትነት መንፈስ የሚነጋገሩባቸው መድረኮች ያስፈልጋሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነት መድረኮች ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ተቋማትና ምሁራን ችግሮችን ያለምንም ይሉኝታ እንዲያሳውቁ ተደርጎ፣ በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ማምጣት የአገር ወግና ባህል ሊሆን ይገባዋል፡፡ በይስሙላ ዓውደ ጥናቶች በለብ ለብ የተሠሩ ጥናት ተብዬዎችን ይዞ በመቅረብ መወዛገብ ሊበቃ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ወጣቶችን የሥራ ፈጠራና ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት፣ ከፕሮፓጋዳና ከአስመሳይነት ሊላቀቅ የሚችለው ወጣቶችንና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያማከለ ውሳኔ ላይ መድረስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ‹‹ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል›› እንዲሉ በዘመቻና በሆይ ሆይታ ውጤት መጠበቅ ዘበት ነው፡፡ ከንቱ ምኞት፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ መልክዓ ምድሮች ውስጥ እየኖረ በዘር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በአመለካከትና በመሳሰሉት ልዩነቶች ቢኖሩትም፣ ለዘመናት አብሮ በመኖሩና በመዋለዱ ሥነ ልቦናው አንድ ዓይነት ወይም ተቀራራቢ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓደዋ አንፀባራቂ ድል ጀምሮ በተለያዩ መስተጋብሮቹ ከልዩነቱ ይልቅ አንድነቱ እጅግ በጣም የተጠናከረ ነው፡፡ ይህንን አኩሪና ድንቅ የታሪክ ባለቤት የሆነ ሕዝብ ይዞ አገርን ለታላቅ ደረጃ ማብቃት ይቻላል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ መጀመሪያ ሕግ የበላይ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቃል፡፡ አላስፈላጊ ድርጊቶችን (ሕዝብ ማማረር፣ ፍትሕ መንፈግ፣ አገር መዝረፍ፣. . .) በማስወገድ በሕዝብ ሁለተናዊ ተሳትፎ ላይ የተመሠረተች ዴሞክራሲያዊት አገር ዕውን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ትውልድ ያልፋል፡፡ ታሪክ ግን ክንውኖችን ይመዘግባል፡፡ ይህ ዘመን ደግሞ ዕድለኛ ነው፡፡ በቴክኖሎጂ ግስጋሴው በአቋራጭ ዕድገት ማስመዝገብ ያስችላል፡፡ ‹‹የዘመኑን ጉዳይ ለዘመኑ ትውልድ›› እንዲሉ ወጣቶች ዕምቅ ክህሎታቸውን አውጥተው ለአገር አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ፣ በዕውቀትና በልምድ የበሰሉ ዜጎች ድጋፋቸው ያለገደብ ጥቅም ላይ ይዋል፡፡ ደመነፍሳዊ እንቅስቃሴዎችና ብቃት አልባ አሠራሮች ይወገዱ፡፡ አገራቸውን ከልብ ለማገልገል የሚችሉ የዕውቀትና የልምድ ባለቤቶች በተግባር ይፈለጉ፡፡ በመከባበርና በመርህ ላይ የተመሠረተ አሠራር ይዳብር፡፡ ባዶ ወሬና መፈክር የትም አያደርሱም፡፡ የምኞት ፈረስን መጋለብ አይቻልምና! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...

የአገሪቱ ባንኮች የመጭበርበር ተጋላጭነት እየጨመረ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ2 ቢሊዮን ብር መጭበርበሩን ገልጿል ቀሲስ በላይ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

እንደገና ያገረሸው ግጭት መፍትሔ ይፈለግለት!

ሰሞኑን በራያና አካባቢው እንደገና ያገረሸው ግጭት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው፣ አድማሱ ሰፍቶ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ አያጠራጥርም፡፡ በራያ በኩል የተጀመረው ትንኮሳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ ተጨማሪ...

ስልታዊ መፍትሔን የሚሻው የኪነ ጥበቡ ዘርፍ

የኪነ ጥበቡ ዘርፍ በተለይም ፊልምና ሙዚቃ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ሲስተም በአግባቡ አልተበጁለትም፡፡ ስለሆነም ይህ ችግር ከመሠረቱ እየተፈታና እየተቀረፈ ካልሄደ ከዓመት...

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...