- ሰማያዊ ፓርቲና ኦፌኮ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተወስኗል
- ከመጠን ያለፈ ኃይል የተጠቀሙ ፀጥታ አስከባሪዎችም እንዲጠየቁ ተብሏል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ተከስተው የነበሩትን ሁከትና ብጥብጦች አስመልክቶ ያቀረበውን የምርመራ ሪፖርት ያዳመጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ወስኗል፡፡
የፓርላማው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብም ፓርላማው በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡ በሕግ እንዲጠየቁ ከተባሉት መካከል በኦሮሚያ ክልል የኢሬቻ በዓል ከመከበሩ አስቀድሞ ሁከት እንደሚነሳ እየታወቀ፣ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ የክልሉ መንግሥት የማመለከታቸው ኃላፊዎች ይገኙበታል፡፡
በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ ሰላማዊ ሠልፍ ጠርቶ የነበረው ሰማያዊ ፓርቲ ሠልፉ ሰዓታት ሲቀሩት መሰረዙን ቢገልጽም፣ ሰላማዊ ሠልፉ እንደተካሄደና ወደ ብጥብጥ እንደተቀየረ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት መረዳት በመቻሉ ፓርቲው በሕግ እንዲጠየቅ ሲል ፓርላማው ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሱት ረብሻዎች የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባላት ተሳትፎ መገኘቱ በሪፖርቱ በመረጋገጡ ፓርቲው እንዲጠየቅ ፓርላማው ወስኗል፡፡ በሦስቱም አካባቢዎች በነበሩት ግጭት አዘል ተቃውሞዎች 669 ሰዎች መሞታቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ከእነዚህ ሟቾች ውስጥ 606 የሚሆኑት ሲቪሎች ሲሆኑ፣ 63 የሚሆኑት ደግሞ የፀጥታ አስከባሪዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት በተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ አስከባሪዎት ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀማቸውን፣ በዚህም ሳቢያ በሰዎች ላይ የሕይወት ህልፈትና የአካል ጉዳት መፍጠራቸውን ገልጿል፡፡
ይህንኑ ከግምት ያስገባው ፓርላማው ከመጠን ያለፈ ኃይል የተጠቀሙ የፀጥታ አስከባሪዎት በሕግ እንዲጠየቁ ሲል ወስኗል፡፡
በአማራ ክልል ለተነሳው ግጭት ከወልቃይት የወሰን ጥያቄ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች የአማራና የትግራይ ክልል አመራሮችን ለዚሁ ግጭት ሲወቅሱ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ለነበረው ግጭት መነሻ የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች መሆናቸውን ኮሚሽኑ በዋና መንስዔነት የጠቀሰና የወልቃይት ጉዳይ አባባሽ በመሆኑ፣ የሁለቱ ክልል አመራሮች በሕግ ሊጠየቁ እንደማይገባ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ጉዳዩን አስመልክቶ ፓርላማው ውስጥ ለተነሳው ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡