Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ወንጀልን መከላከል የሚቻለው በየመንገዱና በየሠፈሩ ጠብመንጃ ይዞ በመቆም አይደለም››

‹‹ወንጀልን መከላከል የሚቻለው በየመንገዱና በየሠፈሩ ጠብመንጃ ይዞ በመቆም አይደለም››

ቀን:

የፌዴራል የፍትሕ አካላት

ኅብረተሰቡን በማሳተፍ፣ መረጃ በመለዋወጥና በቅርበት ነገሮችን በጋራ በመከታተል የፍትሕ ሥርዓቱን ማስጠበቅና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ካልተቻለ በስተቀር፣ በየመንገዱና በየሠፈሩ ጠብመንጃ ይዞ በመቆም ብቻ ወንጀልን መከላከል እንደማይቻል የፌዴራል የፍትሕ አካላት ተናገሩ፡፡

አንድ ላይ በመቀናጀት ‹‹የፍትሕ አካላት›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ባለሥልጣናት ሐሙስ ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፣ አንዱ ተቋም ለሌላው ተቋም ሥራ ስኬት አጋዥና ደጋፊ ነው፡፡ ዓላማቸውም ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ያገኙ የሕዝቦችና የዜጎች መብቶችን ማስከበር፣ እንዳይጣሱ መከላከል፣ ተጥሰው ሲገኙ ደግሞ ተጠርጣሪዎችን በሕግ እንዲጠየቁና ሕጋዊ ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የፍትሕ አካላቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳኜ መላኩ እንዳስረዱት፣ የፍትሕ አካላቱ የየራሳቸው ተቋማዊ ህልውናና ነፃነት ያላቸው፣ በአዋጅ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት ይዘው ለመወጣት የተለያዩ የለውጥ ፕሮግራሞች ዘርግተው እየሠሩ ያሉ ተቋማት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ፍትሕን በሚመለከት በጋራ ተናበው መሥራት ቢችሉ፣ ዜጎች ፍትሕ በማጣት እንዳይጉላሉና የተቀላጠፈ ፍትሕ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ አክለዋል፡፡ የፍትሕ አካላቱ በጋራ መሥራት በመቻላቸው ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ ሕፃናትና ሴቶች የሚያጋጥማቸውን ችግር በተፋጠነና በተቀላጠፈ ሁኔታ ማገዝና ዕርምጃ ለመውሰድ መቻሉን አቶ ዳኜ አስረድተዋል፡፡

ላለፉት ስድስት ዓመታት በተለያዩ መሪ ቃላት የፍትሕ ሳምንታት መከበራቸውን የገለጹት አቶ ዳኜ፣ በዚህ ዓመት ከሚያዝያ 30 ቀን እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የሚከበረው የፍትሕ ሳምንት፣ ‹‹የሕግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላምና ለሕዝቦች አንድነት›› በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር አስረድተዋል፡፡ ቅንጅታዊ አሠራሩ ላለፉት ስድስት ዓመታት ያስገኛቸው ጥቅሞች መኖሩን ጠቁመው፣ በቀጣይም እየዳበረና እየተሻሻለ የሚሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ የፍትሕ አካላቱ በጥምረት መሥራታቸው የመልካም አስተዳደር ዕጦትን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሌሎች ብልሹ አሠራሮችን ከመቆጣጠር አንፃር ወደር የሌለው ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የፍትሕ ሳምንት እንዲከበር በዋናነት ያስፈለገው፣ ለፍትሕ አካላቱ የማይታዩትን ወይም ሆን ተብለው የታለፉና በአቅም ማነስ ያልተተገበሩ አፈጻጸም ችግሮችን ከኅብረተሰቡ ጋር በመወያየት፣ ኅብረተሰቡ አሉ የሚላቸው የፍትሕ ችግሮች ላይ በመወያየትና ችግሮቹን ነቅሶ በመውሰድ ለማስተካከል፣ ለማረምና ከአቅም በላይ የሆኑት ላይ ዕርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር መሆኑን አቶ ዳኜ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በበኩላቸው፣ በየዓመቱ የሚከበረው የፍትሕ ሳምንት ግልጽ ተልዕኮ ያለው፣ የፍትሕ ተቋማቱንና ኅብረተሰቡን የሚያቀራርብ፣ የሚያወያይና የሚያገናኝ ትልቅ ድልድይ ነው ብለዋል፡፡ የፍትሕ አካላት የሕግ የበላይነት የማረጋገጥም ሆነ መልካም አስተዳደር የማስፈን ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉት አሳታፊ፣ በተገልጋዮች ዘንድ ተዓማኒነት ያተረፈና ግልጽነት የተላበሰ የፍትሕ ሥርዓት መገንባት ሲቻል ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ ያለ ኅብረተሰቡ ቀጥታ ተሳታፊነትና ባለቤትነት ውጤታማና ስኬታማ መሆን እንደማይቻል የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ኅብረተሰቡ በፍትሕ ጉዳይ ላይ ‹‹ያገባኛል›› ብሎ የራሱን እምነት እንዲያንፀባርቅ፣ በፍትሕ አገልግሎት ላይ የሚታዩ ችግሮችን፣ ቅሬታዎችንና በደሎችን በግልጽ እንዲያቀርብ በማድረግ የፍትሕ ሳምንቱን ማክበር ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በሁሉም አስፈጻሚ ተቋማት ውስጥ ሕግን የመተርጎምና የመፈጸም ሚና የሚኖራቸው አተያይና አረዳድ የተለያየ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ አመለካከታቸውን በመቅረጽ አገሪቱ የምትመራበትን ፖሊሲና ስትራቴጂ አውቆ መፈጸም የሚችል አመራር፣ ብቁ ዳኛ፣ ብቁ ፖሊስ፣ ብቁ ዓቃቤ ሕግ፣ ብቁ የማረሚያ ቤት ኃይል እንዲኖር ለማድረግ ጠንክረው እየሠሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

‹‹ኅብረተሰቡ በፍትሕ አካላቱና ተቋማቱ ላይ ያለውን ቅሬታና መልካም ሥራዎች ለይቶ ሊነግረን ይገባል፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ከሚያዝያ 30 ቀን እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚከበረው የፍትሕ ሳምንት መሪ ቃል ‹‹የሕግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላምና ለሕዝቦች አንድነት›› ተብሎ የተመረጠው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከታዩት ሁከትና የብጥብጥ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የሕግ የበላይነት፣  የአካባቢ ሰላምና ደኅንነት ከተጣሰበት ሁኔታ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለመግለጽ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሰላም እንዲናጋ፣ ኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባና ለዘመናት ተፋቅሮና ተናቦ የሚኖረው ኅብረተሰብ የጥርጣሬ ዘር እንዲዘራ ያደረገ ሁኔታም ስለነበር፣ መሪ ቃሉ ይህንን ሁሉ በማገናዘብ የተመረጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የመሪ ቃሉ ፍቺ በአጭሩ ‹‹የሕግ የበላይነት ይከበር›› የሚልና ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የሚኖረውን ጥያቄ የሕግ የበላይነትን አክብሮ በአግባቡ ማቅረብ የሚችል መሆኑን የሚያስረዳም እንደሆነ አቶ ጌታቸው አክለዋል፡፡ ከሁለት ሳምንታት በኋላ መከበር የሚጀምረው ሰባተኛው የፍትሕ ሳምንት ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ ካሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተውጣጡ ከ80,000 በላይ ዜጎች የሚሳተፉበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

ባለሥልጣናቱ ስለሰባተኛው የፍትሕ ሳምንት አከባበር ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ከመገናኛ ብዙኃን ጥያቄዎች ቀርቦላቸዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተከበሩ የፍትሕ ሳምንታት ላይ ኅብረተሰቡ ያነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች ምላሻቸውና የተወሰዱ ዕርምጃዎች ስለመኖራቸው፣ አመራሮች ስለሕግ የበላይነትና ፍትሕን ከማረጋገጥ አኳያ ምን ሠሩ? የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝ ስለማይፈጽምበትና ታራሚዎች (በክስ ሒደት ላይ የሚገኙ) በፍርድ ቤቶች ተደጋጋሚ አቤቱታዎች ስለማቅረባቸው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ዜጎች አለመከሰሳቸው ወይም አለመለቀቃቸው ለምን እንደሆነ፣ ኅብረተሰቡን ያማረሩ ትንንሽ ዝርፊያዎች ላይ በተለይ ዓቃቤ ሕግና ፍርድ ቤቶች ግዴለሽነት የተመላበት አሠራር መኖር፣ የበላይ ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች በሥር ፍርድ ቤቶችና በማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ጭምር እየተሻሩ ስለመሆኑ፣ በማረሚያ ቤት ታስረው ሳይፈቱ ወይም ሳይከሰሱ ስለቀሩ በርካታ ዜጎች ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥያቄ ተነስቶላቸዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ለተነሱት የተወሰኑ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፣ ኅብረተሰቡ ያነሳቸው ጥያቄዎችና ጥያቄዎቹ የተነሱባቸው ተቋማት አሉ፡፡ ጥያቄውን መሠረት በማድረግ ተቋማቱ ውስጣቸው እንዲፈተሽ በማድረግ የማስተካከል፣ የማስተማርና ዕርምጃም የመውሰድ ድርጊት መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡ ለቀጣይ ሥራቸውም እንደ ግብዓት መውሰዳቸውንም አክለዋል፡፡

የፍትሕ አካላት ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል ሚኒስቴር ካወረደው የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ ውጪ የተለየ ጥልቅ ተሃድሶ መደረጉን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በጥልቅ ተሃድሶው ያላዩዋቸውን ለማወቅና ለማስተካከል፣ ከከተማ እስከ ወረዳ ኅብረተሰቡ እንዲሳተፍ በማድረግና ተደራሽነቱን በማስፋት፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች የታሰሩ ቢሆንም፣ ጥፋተኞቹ ተለይተው ክስ እንደተመሠረተባቸው ገልጸው ዝም ብሎ የታሰረ የለም ብለዋል፡፡ ነገር ግን ከአራት ወራት በላይ  የታሰሩ ዜጎች እንዳሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ትዕዛዝ አልፎ አልፎ ማረሚያ ቤቶች የማይፈጽሙበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ይህንን የሚያደርግ ኃላፊም ሆነ ሌላ አካል ከሕግ ተጠያቂነት ሊያመልጥ እንደማይችል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ቅሬታ ካለው ደረጃውን ጠብቆ ውሳኔውን ሊያስቀይር ይችላል እንጂ፣ ትዕዛዝ አልፈጽምም ሊል እንደማይችል አክለዋል፡፡ ማንም ሊያድነውና ሊከላከልለት የሚችል አካልም እንደማይኖር ጠቁመዋል፡፡

የማረሚያ ቤቶች አስተዳደርን ወክለው የተገኙት የታራሚዎች ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አስቻለው መኮንን ግን በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ሳይከሰስ የተረሳ እስረኛ እንደሌለ፣ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የሚታሰር ታራሚ እንደሌለ፣ አንድም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይከበር እንዳልቀረና ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ይፈታ ያለውን ትዕዛዝ በዕለቱ እንደሚያስፈጽም በመግለጽ ጥያቄውን ተቃውመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይህደጎ ሥዩምና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አማካሪ ረዳት ኮሚሽነር ሓኔታ ገብረ መድኅንም ስለፍትሕ አከባበር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ውጥን

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት...

በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን...

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት...