Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትድርድርና የኢትዮጵያ ዕድል

ድርድርና የኢትዮጵያ ዕድል

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

የመንቦጫረቅም ወግ አለው

አስፈሪ የቅያሜ ስሜቶች፣ ምሬቶችና የጥፋት ሥራዎች በታዩበት የሕዝብ ቁጣ ማግሥት ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎቹ የመደራደርን ነገር አንስተው፣ በስንት መንቀራፈፍ ከተገጣጠሙ በኋላ ንግግርና ቀጠሮን እያፈራረቁ የወራት ጊዜ መፍጀታቸውና በተለይ በአደራዳሪ ነገር ብዙ መድከማቸው ያልተጠበቀም፣ ያስገረመም ነበር፡፡ የመጨረሻውን ነጥብ እስኪ ትንሽ እናፍተልትለው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኢሕአዴግ የያዘው ከተቃዋሚም ከእኔም ያልሆነ ገለልተኛ ብሎ ነገር የለም የሚል አቋም፣ የሚያምንበትና ሲሠራበት የኖረ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰቡ በተግባር እንዳየነው ድፍን መቶ ሚሊዮን ዜጋን የአንድ ኢሕአዴግ ደጋፊ እስከ ማድረግ የሚቃጣው ነው፡፡ የዚህ ተግባሩ ግብ ደግሞ በቀጥታ ከሥልጣን አለመንሸራተትን የሚመለከት ነው፡፡ ያለ እሱ ለሕዝብ መድኅን የሚሆን እንደሌለ፣ እሱ ተራማጅና የልማት ፓርቲ፣ ሌላው የጥፋትና የዘረፋ ፓርቲ እንደሆነ ሲነግረን መኖሩም ከዚሁ ሥልጣንን ከማጥበቅ ጋር በቀጥታ ይገናኛል፡፡

ከታሪክ እንደምንረዳው የፓርቲዎች ባህርይ እንደ ምድር ሰሜናዊና ደቡባዊ ዋልታዎች በነበረበት ሁሌም የሚገኝ አይደለም፡፡ ተራማጅነት ሊያረጅና ወደ ወግ አጥባቂነትና ወደ ፀረ ሕዝብነት ሊያረጅ፣ ሊያፈጅ ይችላል፡፡ ዓይንና አፈር ሆነው የምናያቸው ፓርቲዎች በውስጣዊ ባህርያቸው ተመሳሳይ ሆነውም ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ሕዝቡና ልማቱ ካለኔ መሪ የለሽ ይሆናል የሚለን ኢሕአዴግ እስከ ዛሬ ድረስ የሕዝብን ሁለንተናዊ እሰየውና ፍቅር ተጎናፅፎ አያቅም፡፡ ሲጀመር አንስቶ አገዛዙ ከሮሮና ከኑሮ መፋለስ ጣጣዎች ጋር የሚላፋ ነው፡፡ ከሥራ በገፍ ማባረር፣ ሠራተኛን ላይ ታች ማድረግና የዘመቻ ሹምሽር በገዢነት ታሪኩ ውስጥ ተመላልሰዋል፡፡

እህልና ጥራጥሬ ወደ ውጭ እስከ መላክ የዘለቀው ላኪነትና የመንግሥት የውጭ ምንዛሪ ረሃብ በአንድ ፊት፣ በግል ንግድ ውስጥ ያለው የዶረየ ትርፍ አሳዳጅነት በሌላ ፊት በዋጋ ንረት ኑሮን ማዳቀቁ እንደቀጠለ ነው፡፡ ምርት በሚበዛበት ወቅት ያስቤዛ ዋጋ ይረክሳል ተብሎ ተስፋ እንዳይደረግ እንኳ፣ የግል ነጋዴም መንግሥትም በየፊናቸው ዋጋ ከሚፈልጉት ደረጃ በታች ዝቅ እንዳይል በዘዴ ይቆጣጠራሉ፡፡ የኑሮ ድቀቱም ቤተሰብ እየሸረፈ መንገድ ዳር ያወጣል፡፡ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ፣ ከገጠር ወደ ከተማ ያሳድዳል፡፡

ወንዞቿን ከፋብሪካና ከፍሳሽ ምረዛ መጠበቅ ያቃታት “የአፍሪካ መዲና” እየተባለች የምትሞካሸዋ አዲስ አበባ፣ የተበከለ የወንዝ ዳርና የየመስክ አትክልት ልማትን መከልከል እንጀራ የለሽነትን ማባዛት ሆኖባት እንዳላየ በማየት ወጥመድ ተይዛ ትገኛለች፡፡ ጤናማ የሆኑት ገለባማ የጥራጥሬ ምግቦች ከመንገድ ዳር እየተመናመኑ በምትካቸው ጠንቀኞቹ የእነ ድንች እንጭርጭሮች በአሮጌ ወረቀት እየተሰፈሩ ግራ የተጋባ ዘበናይነትን ያረካሉ፡፡ ደጉ ጤፍ ከደሃ ማጀት የሚታጣበት ጊዜም የቀረበ ይመስላል፡፡

በቴሌቪዥን ስብሰባዎች ላይ ብዙ ዓይነት የፕሮፓጋንዳ ዋጋ ያላቸው የባህል አልባሳት ሲጋፉ እናያለን፡፡ በእውነተኛዋ ኑሮ ውስጥ ግን ሥር ሰዶ የኖረ የሴቶች የሐበሻ ልብስ ባህል በዋጋ ንረት ተመትቶ ባለፀጎችና ፈረንጆች (ቢበዛ ከማን አንሼዎች) የሚዋቡበት ውድ ነገር ሆኗል፡፡ ተራው ዜጋ በደህናው ጊዜ የገዛውን የክት አድርጎ ዕድሜውን በማራዘም፣ ያለቀበትም እንደምንም ነጠላ ገዝቶ በፈረንጅ ጨርቅ ላይ ጣል በማድረግ እየተንገዳገደ ይገኛል፡፡

ተወዝፎና መፍትሔ ጠብቦት ለኖረው የመጠለያ ችግር ኢሕአዴግ በስተኋላ ያመጣው በመንግሥት በኩል የሚገነባ የጋራ ቤት መፍትሔነቱ ከጭልፋ ያላለፈ ነው፡፡ ከደርግ ወደ ኢሕአዴግ ጊዜ የተሻገረውና የቤት ዕጦትን ማምለጫም በአቋራጭ መክበሪያም የሆነው ሕገወጥ ግንባታም በድብቅብቅና በጉርሻ የቀጠለ ቢሆንም፣ ግንባታው ተስፋፍቶ ከተንሰራፋ በኋላ የሚመጣ የማፍረስ ዘመቻ ቤት የነበረውን ቤት እየነሳ፣ ወደ ተጨናነቀ ጥገኝነትና ወደ ላስቲክ መጠለያ ይገፈትራል፡፡ ለልማትና ለመልሶ ግንባታ መነሳትም ቢሆኑ የሚያስከትሉት የሥፍራ ለውጥ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ገመዶች ተደጋግፎ የቆመ የኑሮ አቋምን የሚያናጋ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ኢሕአዴግ በግንባታ ያጌጠውን ያህል ከላይ በተዘረዘሩት ገመናዎች ሁሉ ‹ያሸበረቀ› ነው፡፡ ለተቃዋሚዎች ይሰጠው የነበረው ሥልጣንን የግል መበልፀጊያ የማድረግ ኃጢያት እሱም ቤት ውስጥ መትረፍረፉን የ2008 እና 2009 ዓ.ም. ፍንዳታ ካንባረቀበት በኋላ አምኗል፡፡ በዚህ እንከናምነቱ ከየትኛውም የነቀዘ ሕዝበኛ ገዢ ጋር አንድ ላይ ሊመደብ የሚችል ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ  እንኳን ከዛሬ ተቃዋሚዎቹ ጋር ይቅርና ከትናንቶቹ የኃይለ ሥላሴና የደርግ አገዛዝ ጋር የሚዛመድባቸው፣ አፄውንና ደርግን በብዙ ነገር እንደበለጣቸው ሁሉ ከእነሱ ያነሰባቸውም ነገሮች  (ለምሳሌ በአካዳሚዊ ነፃነት ከአፄው፣ የግል ቤት ግንባታን በመሰነግ ከደርግ) አሉ፡፡ ይህንን ማየት ከተሳነውና ራሱን ከየትኞቹም የማይደራረስ ተፃራሪ አድርጎ የሚያምን ከሆነ፣ ወይም “ገለልተኛ የለም” ባይነቱን ብልጠት ብሎት ከሆነ ከጥፋቱ ተምሮ በተባበረ ጥረት የምር የሆነ ዴሞክራሲን ለመገንባት ተስፋ አይሆንም፡፡ ይህን ደግሞ ደጋግሞ እንዲያደምጠው፣ እንዲያስተነትነው፣ ደግሞ ደጋግሞ እንዲጮህበት እፈልጋለሁ፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ያሉ አቋሞችን በኢሕዴግና በተቃዋሚዎቹ ረድፍ ብቻ መመደብ የሚጠባቸው ናቸው፡፡ በዚያው ልክ በጭፍኑ ተቃዋሚዎችን አንድ ላይ መፈረጅ፣ የኢሕአዴግንም ሰዎች በአሁኑ ደረጃ በልሙጡ ባለ አንድ አቋም አድርጎ መውሰድ ስህተት ነው፡፡ ተቃዋሚዎችንና ኢሕአዴግን አንቅሮ የተፋ (ለሁለቱም ድምፁን የማይሰጥ) እንዳለ ሁሉ ከሁለቱም ወገኖች የሚጠላባቸውና የሚወድላቸው ነገሮች የሚታዩት፣ ከሁለቱም የተውጣጣ ወይም የተወሰኑ ባህርዮቻቸውን ወስዶ ያዳቀለ ስብስብ የሚፈጠርበትን ቀን የሚመኝ ሁሉ አለ፡፡ ኢሕአዴግ እነዚህ ዝንባሌዎች ባይታዩትና ገለልተኛ የለም ባይነቱ ላይ ቢደርቅ እንኳ፣ ለድርድር ለጠራቸው ተቃዋሚዎቹ ክርክሩን እንተወውና እናንተ ገለልተኛ የምትሉትን አምጡና ድርድሩን እንዲመራ አድርጉ ቢላቸው ኖሮ ምን ይቀነስበት ነበር?

በተቃዋሚዎቹ ውስጥ በገለልተኛ ሰው ድርድሩ ካልተመራ በማለት የታየው መንገታገት ራስን እስከ ማግለልና ለብቻ እደራደራለሁ እስከ ማለት መሄዱ የባሰ አታምጣ ያሰኘ ነበር፡፡ አደራዳሪ ከተመድ ቢያስመድቡስ እንኳ ምንድነው የሚያተርፉት? ከኢሕዴግና ከሚመራው መንግሥት ጋር ያላቸው ጉዳይ አደራዳሪ ገለልተኛ ካልሆነ ያዳላብኛል የሚያስብል የርስት ወይ የንብረት ሙግት አይደል፡፡ ወይም በአዳራዳሪ/ሽማግሌ የታየ ጉዳይ ሰነድ ይዞ እንደ ባልና ሚስት ክርክር ወደ ፍርድ ቤት የሚሄድበትን የመሰለ ነገር የለበት፡፡ የሕዝብ ውክልና በሚጠይቁ ወይም ሕዝቦች በመነጋገርም ሆነ በድምፅ ሊጨርሷቸው በሚገቡ ጉዳዮች ውስጥ ገብተው ቢደራደሩም፣ የድርድራቸው ውጤት ለሚመለከተው ውሳኔ ሰጪ አካል ሐሳብ ከማቅረብ አይዘልም፡፡ (አሁን ባለው የተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ውሳኔ በሚያገኙ ጉዳዮች ላይ የሚደረስ ስምምነት የውሳኔ ያህል የሚሆነውም ምክር ቤቱ በኢሕአዴግና በአጋሮቹ በመያዙና ኢሕአዴግ በድርድር የተስማማበት ነገር በምክር ቤትም ያለቀለት ያህል ስለሆነ ነው፡፡) ፓርቲዎቹ ኢሕአዴግን ጨምሮ በደንብ አጢነውት ከሆነ ድርድር የተባለው ነገር፣ በመሠረቱ በአሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ዓይንን ገልጦ በመወያየት የጋራ መግባባት መፍጠርና በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሰላም ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን መከራ የማቅለል ተልዕኮ ነው፡፡ ተቃዋሚዎቹ በየፊናቸው የሚኖራቸው የታሰሩ አባላትንና መሪዎችን የሚመለከቱ አቤቱታዎች በቶሎ እንዲቃለሉ የሚያስችለውም ይኸው የጋራ መግባባት ጥርጊያ ነው፡፡

በዚህ ዓብይ ነጥብ ላይ የተግባባን ከሆነ አደራደሪ የተባለው ሰው ተግባር ማስተናበር መሆኑ አያከራክረንም፡፡ አስተናባሪው የስብሰባ አመራርን የሚያውቅ ከሆነ፣ ተሰብሳቢዎቹ የስብሰባ አካሄድንና አስተናባሪ መንገድ ሲስት ማቃናትን የሚያውቁ ከሆነ፣ እየተቧደኑ የመናገር ዕድልን በየቡድን ቤቶች መሀል እንዲሆን አድርገው ካቀላጠፉት የአስተናባሪው ገለልተኛ መሆን አለመሆን ልዩነት አያመጣም፡፡

አደራዳሪ የተባለው ሰው ገለልተኛ መሆኑ የተፈለገው፣ መግባባት የተደረሰባቸውና ፊርማ ያረፈባው ነጥቦች በተለይ ከምርጫ በፊት የአሁኑ መንግሥት እንዲያሻሽላላቸው/እንዲያከብራቸው የተባሉ ተፈጻሚ ባይሆኑ፣ ለእነ አሜሪካ ተዓማኒ ምስክርነት በመስጠት ገዥውን ፓርቲና መንግሥቱን የማያጋልጥ ሰው ለማግኘት ከሆነ፣ በዛሬው ጊዜ ኢትዮጵያና አካባቢዋ፣ ሌላውም ዓለም ያሉበት አሳሳቢ ሁኔታ አልተጨበጣቸውም ማለት ነው፡፡

ገለልተኛ ሰው የተፈለገው የተቀረፀ መረጃ በእጅ ባይገኝና መካካድ ቢመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የገለልተኛ ሰው ምስክርነት እንዳያጣ ታስቦ ይሆን? የዚያ ዓይነት አሳቢነት ብቅ ብሎ ከነበረም ዋናው ባለጉዳይ ተዘንግቷል ማለት ነው፡፡ አንደኛ የውይይት/የድርድር ርዕሶቹ ብቻ ሳይሆኑ ፓርቲዎቹ ራሳቸው (ለሥልጣን ይወዳደራሉና) የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሕዝብ ክሳትና ጉልምስናቸውን መዝኖ ማወቅ መብቱ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ዕውቀት ደግሞ ክርክር ያለበት ውይይት ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ከፓርቲዎቹ መሀል “የሐሰት ተቃዋሚ/የኢሕአዴግ ጭፍሮች” እየተባሉ የሚታሙ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሐሜቱ እውነት ቢሆን እንኳ በውይይት ጊዜ ወዲህም ወዲያም ብለው በየረድፋቸው ዞሮ ከመግባት ባለፈ ውጤት ላይ የሚያመጡት ነገር አይኖርም፡፡ ምክንያቱም ድርድርና መግባባት በድምፅ ብልጫ መሸናነፍ የሚያልቅ ሳይሆን፣ የሁሉንም ተደራዳሪ መስማማት የሚሻ ነውና፡፡ ሁለተኛ በሕዝብ ውስጥ ያለውን ኩርፊያና የረገበ ውጥረት ወደ አዲስ ተስፋ የሚጠመዝዘው ፓርቲዎች በዚህ በዚህ ላይ ተስማሙ የሚል መግለጫ ሳይሆን፣ በውይይቱና በድርድሩ ጉዞ ሲፈልቅ የታየ ለውጥ የማምጣት ልባዊ ፍላጎትና ዝግጁነት ነው፡፡

ስለዚህ አስቂኝ አተካራ ውስጥ ሰበር ሰካ ከማለት ይልቅ ይበልጥ ይጠቅም የነበረው፣ ሌሎች ተጋባዥ ተሳታፊዎች የተካተቱበትና በቀጥታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚደርስ የምክክር ጉባዔ የማሰናዳትና የማካሄድ ተግባር ላይ ማተኮር ነበር፡፡ የሕዝብ ጥቅም ከእኛ ጋር ነው/ሀቀኛ ተቃዋሚ እኛ ነን ብለው የሚያስቡና ማን ምን እንደሆነ ሕዝብ እንዲያውቅ የሚፈልጉ ፓርቲዎችም፣ ከሞላ ጎደል የውይይቱ ሒደት ሳይጎማመድ ለሕዝብ መቅረቡን መደገፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተሟላ መረጃን ማግኘት በሚፈልግ ትልቅ የሕዝብ ጉዳይ ላይ የሚዲያ መገኘትና አለመገኘት በውስን ፓርቲዎች (ያውም ምርጫና የይፋ ስብሰባ አጋጣሚ ሲመጣ ብቅ ከማለት በቀር በፖለቲካ እንቅስቃሴ የት እንዳሉ በማይታወቁ ጭምር) ፍላጎት ላይ መንጠልጠሉ እንደምንስ አግባብ ይሆናል!

የፓርቲ ፕሮግራሞች ላይ መወራከብ በሌለበትና የሁሉም ጉዳይ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ችግሮች በሆኑበት ይሻሻሉ፣ ይጨመሩ፣ ይቀነሱ የሚባሉ ሕጎች (ሌላው ቀርቶ የታሰሩ የየፓርቲ አባላትና መሪዎች ጉዳይም) እዚሁ ውስጥ የሚካተቱ ሆነው ሳለ፣ ጥያቄዎችን ደምሮ እንደ አንድ ቡድን (ከዚህ ቢያንስ ሦስትና አራት ቡድን ሆኖ) ከኢሕአዴግ ፊት ለፊት ለመቀመጥ አለመቻል የሚያሳዝን ነው፡፡ ከማበር ይልቅ መፈነጋገጥ ከባድ በሚሆንበት (ያለ አንድ ክርክር እያንዳንዱ ፓርቲ ባቀረባቸው የመደራደሪያ ነጥቦች ላይ የሚፈልጋቸውን ውጤቶች አስቀምጦ በተፈላጊ ውጤቶች ተመሳሳይነት መሠረት ለውይይት የሚያመች ጊዚያዊ ቡድን መፍጠር እየተቻለም) አሥራ ምናምን ሆኖ መኮልኮል የበለጠባቸው፣ ለመፎካከር ተሰባስቦ መጠንከርን በሚጠይቀው የምርጫ ውድድር ላይ ምን ሊያተርፉ? ማንንስ ሊማርኩ? በዚህ ደረጃ ራሳቸውን “ተፎካካሪ ፓርቲ” ያሉ የሚጠሩ ከሆነ መቼም ታሪክ ነው! ዕውቅና ለመሸመት እኔም አይቅርብኝ ባዮች እየተንዘባዛቡ ተሳታፊንም ሆነ ዕድሉ ከተገኘ በመገናኛ ሒደቱን የሚከታተለውን ወገን ማታከትስ የአድልዎ አልባነት ማረጋገጫ ሆኖ ይመጣ ይሆን? ለመሆኑ ደጅ የቀሩት እነ መድረክና ሰማያዊ፣ ኢሕአዴግ ከሌሎቹ ጋር የሚግባባውን ተግባብቶና የሚያቃናውን አቃንቶ ዝም ቢላቸው ምን ሊያደርጉ? ደጅ መቅረት እንደ ‹ማሞ ቂሎ› ከመዘንጋት በቀር የሚያስገኘው የፖለቲካ ትርፍ ምንድን ነው? ኢሕአዴግስ ብዙ ድጋፍ ያላቸውን ውጭ ትቶ ከአንድ ኢዴፓ በቀር በቁንጥርጣሪዎች ከተሞላ አጅብ ጋር ሽር ብትን ብሎ ከተቃዋሚዎች ጋር ስኬታማ መግባባት ላይ ደረስኩ ሊልና ጎሽ ሊባል ነው? አገራችንና አካባቢያችን ለሚገኙበት ሁኔታ የተጨነቀ ህሊና ካለ፣ እንኳን በአዳራሽ ውስጥ በጋዜጣ ዓምድም ላይ ተወያይቶና ተከራክሮ መግባባት ቀላል እንደሆነስ እነዚህ አካላት ታስቧቸው ያውቅ ይሆን!

ስብሰባ የመምራት ዕድል ማግኘትና አለማግኘት በሕዝብ ዕውቅና መብለጥና መበለጥ ሆኖ ማነጋገሩን፣ ከዚህም አልፎ “የድርድር” ክብደትን ከመሰብሰቢያ አዳራሽ ላይ ለማግኘት የመልፋት ገመናንም እንለፈው፡፡ የተወሰኑ ቡድኖች ደጅ መቅረት ለሁላቸውም የሚያጎድል ጉዳት መሆኑን አጢኖ መጠራራት ሲገባ፣ ለእሙልኝ ባይ “የጋዜጠኛ” ጥያቄ እየተበለጡ ትችት ውስጥ መግባትን ግን ምን እንበለው? አንዳቸውም ለትዝብትና ለመመፃደቅ የሚሆን አፍ እንደሌላቸው ነጋሪ ያስፈልጋቸዋል? አንዲት ሙሽሪት ባሏ ቤት የገባች ዕለት ግድግዳ ላይ የሆነ ቆዳ የውጥር ተሰቅሎ አየችና “ይኸ ምንድነው?” ስትል፣ “የበፊቷ ሚስቴ አመሏ አስቸግሮኝ ገደልኳትና ቆዳዋን እንዲህ አኖርኩት፤” በማለት ባል ይመልስላታል፡፡ አዲሷ ሚስት እንዴት ያለ ጠንቅ ሊያገኛት እንደሚችል በማስተዋል ፈንታ ከፊተኛዋ በምን እልቃለሁ የሚል ግብዝነት በለጠባትና “አንተዬ እንዴት ያለችውን አርበ ጠባብ ኖሯል ያገባኸው!” አለች አሉ፡፡ በዚሁ ወደ ዋናው ጉዳይ እንሻገር፡፡

“ለራስ ምታት ጩህበት” መድኃኒት አይሆንም

“ፓርቲዎቻችን” አዳራሽ ውስጥ በአዳራዳሪ፣ በመሰብሰቢያ ሥፍራና በሥነ ሥርዓት ላይ ሲትረከረኩ፣ በዋናው የጋራ ጉዳይ ላይ የመነጋገሩ ሥራ ከእነሱ ቀጥተኛ ተሳትፎ ውጭ ጅማሬ አሳይቷል፡፡ በቅርቡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናት ላይ ተንተርሶ ያካሄደውና በቴሌቪዥን የቀረበ ውይይት፣ ያንንም ተመርኩዘው የተካሄዱ ሌሎች ውይይቶች የዚህ ምሳሌ ናቸው፡፡ በእነዚህ ውይይቶች ከሞላ ጎደል ሥራ አስፈጻሚው (በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ) በሚያሳየው ተግባራዊ እንቅስቃሴው በምክር ቤቶች ሥር አለመሆኑ፣ በግልጽም ሆነ በሥውር እጅ መሥራቱ፣ ሕግ ለመተላለፍ፣ ለዛቻና ለጣልቃ ገብነት ባይተዋር አለመሆኑ፣ እንዲያውም ያልፈለጋቸውን የምክር ቤት አባላት ሕዝብን በመጠቀም ውክልናቸውን እስከ ማስነሳት ሲሄድ መታየቱ፣ ምክር ቤቶች የመቆጣጠርና የመጠየቅ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸውና የመሳሰሰሉት ተወስተው ሥራ አስፈጻሚው የሥልጣን አጠቃቀሙ ገደብ አጥቷል የሚል ድምዳሜ እስከ መስጠት ተደርሷል፡፡ ለ25 ዓመታት ፊት ለፊት ሲታይ የኖረ ተራ እውነት ይመስገነውና በ26ኛው ዓመት ላይ ሊታመን በቃ፡፡

“ሥራ አስፈጻሚው ገደብ አጥቷል” ማለት ደግሞ ባህርይው ‹ሥራ አስፈጻሚነት› ከሚገልጸው ደረጃ ተላልፏል ማለት ነው፡፡ ድምዳሜውን በሌላ ገጽታው እንመልከተው፡፡ የምክር ቤቶች አባላት እንዲያፀድቁ የቀረበላቸውን ከማፅደቅና አስቀድሞ ውጤቱ ለታወቀ ውሳኔ እጅ ከማውጣት ያልራቀ ሚና እየተጫወቱ ሳለ እንዲያውም ለሕገ መንግሥት፣ ለሕዝብና ለህሊናቸው ከመታመን ይልቅ ለፓርቲ (ለዚያውም ለፓርቲ ቀጭን ትዕዛዝ) የሚታመኑ ሆነው ሳለ፣ በዚህ ባህርያቸው ሕዝብ በነፃ ፍላጎቱ ጠይቋቸውና አውርዷቸው አያውቅም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ፣ ሥራ አስፈጻሚው በምክር ቤት አማካይነትም ሆነ በሌላ ሕጋዊ መንገድ የሕዝብ ተቆጣጣሪነትና ጠያቂነት የለበትም ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ለመጥማጣ አቤቱታ ከማቅረብ አልፎ በተቆጣ ጊዜ፣ አማራጩ ወይ በሆነ ማሻሻያ ነገር ተደልሎና ተደቁሶ መኮራመት ወይም የነበረውን መንግሥት እስከ ማፍረስ መሄድ የሚሆነውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በአጭሩ ሕዝቡ በ‹ተወካዮቹ›ም ላይ ሆነ በሥራ አስፈጻሚው ላይ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በተቀመጡት ጎዳናዎች ተፅዕኖ እያደረገ ባለመሆኑ፣ ሕዝብ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ነው የሚባለው ነገር (የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብ ሪፐብሊክነት) ከወግ ያለፈ አልሆነም፡፡

የሕዝብ ሪፐብሊክነቱ ከወግ ማለፍ ለምን ተሳነው? ሕዝብ “ተወካዮቹን”፣ “ተወካዮቹም” “ሥራ አስፈጻሚውን” መግራት ለምን ተሳናቸው? ይህንን የሚመለከቱ ጥያቄዎች በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በኩልም ሆነ በኢኤንኤን (የኢትዮጵያ የዜና መረብ) የተባለ ቴሌቪዥን ባቀረበው “ኦዳ” በተሰኘ የውይይት ፕሮግራም ላይ ተነስተው ነበር፡፡ ሁነኛ ምክንያቶቹን ለይቶ ማወቅ የመፍትሔውንም ትክክለኛት ይወስናል፡፡ የተገለጠልን ምክንያት ከወለል የማያልፍ ከሆነ መፍትሔያችንም የላይ ገላ የሚያክክ ይሆናል፡፡ የምክር ቤት በጀት ማነስ፣ የምክር ቤት አባላት ኃፊነታቸውን ሳይፈጽሙ ሲቀሩ አለመጠየቃቸው፣ በፍርኃት መታሰር፣ የአባላት ጥራት ማነስ፣ ከአሮጌ ባህልና አስተሳሰብ አለመውጣት፣ የሕግና የአሠራር ክፍተት፣ ከምክር ቤት አባልነት ጋር የሥራ አስፈጻሚነትን ሥራ ደርቦ መያዝ፣ በሕዝብ በኩልም በመብት አለመጠቀምና ከንቁ ተሳትፎ መራቅ የሚሉ ነገሮች ሲደረደሩ ሰምተናል፡፡ ርጋፊና ግለሰባዊ ነገሮችን የሚለቃቅሙ ወይም የእውነታ ገጽታዎችን እንደ ምክንያት አድርገው የሚሾሙ ምልከታዎች ያሳስቱ እንደሆን እንጂ ወደ ወሳኞቹ ምክንያቶች አያደርሱንም፡፡ ሕዝብም ሆነ ምክር ቤቶችና አባሎቻቸው ለሥራ አስፈጻሚው አጎንብሶ ማደራቸው የለመድነውና የሚጠበቅ ነገር ለምን ሆነ? በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ከተከማቹት የኢሕአዴግ ሰዎች መሀል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነቱን አልተወጣም የሚሉ ቢከሰቱ ከሰማይ የሆነ ነገር ዱብ ያለ ያህል ያስደነግጣል፡፡ “ጉድ መጣ! … አለ ነገር!… ተከፋፍለዋል ማለት ነው …” ያስብላል፡፡ ለምን? በዚህ አቅጣጫ ካልመረመርን በ ‹ኦዳ› ውይይት ላይ አንዱ እንዳለው “እነ ዓባይ ፀሐዬ ተመልሰው የምክር ቤት አባል ቢሆኑ” የሚል “መፍትሔ” እስከ መሰንዘር ሊዞርብን ይችላል፡፡

እስከ ዛሬ በምናቀው የአገዛዝ እውነታ፣ ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ ምክር ቤቶችም ሆኑ ሥራ አስፈጻሚዎች ግንባር/አጋር ከሚባሉ ማድጋዎች የሚቀዱ፣ ኢሕአዴግነት/ኢሕአዴጋዊነት የጋራ ባህርያቸው ነው፡፡ የአንድ ፓርቲነት የሥልጣን የደረጃ ከፍታ ከሥራ አስፈጻሚ የደረጃ ከፍታ ጋር አብሮ የሚያሸቅብ ነውና ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚነት ከከፍተኛ የፓርቲ ባለሥልጣንነት ጋር በጥቅሉ ይገጥማል፡፡ እንዲያም ሆኖ በዚህ ጥቅል ውስጥ ሽቅብ ተጉዘን ሁሉ ነገር በጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ እንደሆነ አድርገን ብናስብ ከስህተት ላይ ልንወድቅ እንችላለን፡፡ በአቶ መለስ ዜናዊ ዘመን ሥልጣን እነማን ወይም እማን ዘንድ እንደሚሰበሰብ ማንበብ ቀላል ነበር፡፡ አሁን ግን ለበስበስ ያለ ነገር ያለው ይመስላል፡፡ ምንም ይምሰል ወደ ውስጥ መግባት ለጉዳያችን ስለማያስፈልገን ፍልፈላ ውስጥ አንገባም፡፡ የጉዳያችን አንዱ ዋና ፍሬ ነጥብ የሥራ አስፈጻሚዎችም ሆነ የምክር ቤቶች ስብስብ የፓርቲ ስብስብ መሆኑን፣ አለቃቸውም የፓርቲ መረብ መሆኑን ማጤናችን ነው፡፡ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ፣ በኢሕአዴጋዊ ፓርቲዎች ውስጥ የተያዙ አቋሞችን/ደንቦችን ለፓርቲው አይበጁም ወይም ሕግ መንግሥታዊ ኃላፊነትን ለመወጣት አያስችሉም ብሎ በይፋ የመቃረን ድፍረት በፓርቲ አባልነትና በሥራ ኃላፊነት ውስጥ ከመቆየት ጋር እንደተጎዳኙ ሲከሰቱ አልታዩም፡፡ ምክንያቱም የፓርቲን ውሳኔና አቋም መቃረን ፓርቲን ከመቃረን፣ፓርቲን መቃረንም ፓርቲን ከመጉዳት ጋር አንድ ተደርጎ ነው የሚታሰበው፡፡ ፓርቲን መጉዳት ደግሞ በዝምታ አይታለፍምና የፓርቲያቸውን ውሳኔዎችና ዕርምጃዎች የሚሞግቱ የምክር ቤት አባላት ሲከሰቱ የማየቱ ዕድል ዝግ ነው፡፡

የፓርቲ ሥልጣን እስከ መንግሥታዊ ልዩ ልዩ ዘርፎች ድረስ ዘልቆ ህሊናን በመግዛትና አውታራትን የዓላማ ታማኝ አድርጎ በማነፅም ይገለጻል፡፡ እንዲያውም የፓርቲው ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ውጦሽ በሁሉም መስክ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሁሉ የሚስፋፋ ነው፡፡ አቶ ሸፈራው ሽጉጤ በፓርቲዎች “ቅድመ ድርድር” ውይይት ላይ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ጉዳይ ላይ ገለልተኛነት ብሎ ነገር (ከኢሕአዴግ ወይም ከተቃዋሚ ያልሆነ) የለም ብለው የኢሕዴግን አቋም ሲያሳውቁ፣ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት ኢሕአዴግ ወገንተኛ መሆን የለበትም ብሎ የተወው/የሚተወው ተቋም እንደሌለም እያመኑ ነበር፡፡ የዚህ ዓይነቱ በአንድ ፓርቲ ህሊና እፍንፍን ስልቅጥቅጥ የተደረገ እውነታ፣ ከዘረፋ እስከ ጋጠወጥ የመብት ረገጣ ድረስ ለሰፉ ብዙ ሥውር ሥራዎች የሚስማማ ሙቀትና እርጥበት የሚገኝበት ዳስ ከመሆኑ ሌላ፣ ያለ ፍርክስና ያለ ሴራ በሰላም የሥልጣን ወንበር ከአንድ ፓርቲ ወደ ሌላ መተላለፍ ላለበት የዴሞክራሲ አገዛዝ ፈጽሞ የማይስማማ (ብዙ የማሻሻያ ሥራ የሚጠይቅ) ነው፡፡ ገዢ ፓርቲ የሥራ ማስፈጸሚያ አውታራትን ሕጋዊ የሥራ ኃላፊነታቸው በሚፈቅድላቸው ልክ ከማንቀሳቀስ አልፎ፣ ካቦተለካቸው (በፓርቲ ወገነዊነት ካጠናቸው) ሕዝብን በፖለቲካ መርታትና ለሕዝብ የምርጫ ካርድ መስገድ ብቸኛ መተማመኛው መሆኑ ቀርቶ በጉልበትና በሸፍጥ ሊኖር የሚችልበትንም አቅም ፈጠረ ማለት ነው፡፡ ሳያስበው በአመፅ ቢወገድ እንኳ መንግሥታዊ አውታራቱ ውስጥ በተረፉ ርዝራዞቹ በኩል አድብቶ በግልበጣ ራሱን ወደ ሥልጣን የመመለስ ቀዳዳ ይኖዋል፡፡ የፓርቲ ወገናዊነት በነበራቸው መንግሥታዊ አውታራት ላይ የወጣ ገዢም ከመገልበጥ አደጋ ለመትረፍ አውታራቱን ማተራመስና ማጠብ ውስጥ ለመግባት ይገደዳል፡፡ የዴሞክራሲ አውታራት ተበጁ የሚባለው እንዲህ ያለው እያመሱ ማደራጀት የማያስፈልገው አስተናነፅ ሲሟላ ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ድረስ በመውረድ በኢትዮጵያ የመንግሥት አገነባብ ውስጥ ያሉ ችግሮችንና የሚሹትን ማስተካከያ፣ የሕግና የአሠራር መጠበቂያ፣ እንደሁም ያስተናነፅ ጥራት እየመረመሩ መወያየትና መግባባት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

በዚህ ረገድ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የተፍረጠረጠረ ጥናትና ውይይት ማድረግ ገና ገና ይቀረዋል፡፡ “ኢኤንኤን” የተባለው ቴሌቪዥንም ለሳምንታዊ የውይይት ፕሮግራሙ መጠሪያ ያደረገው “ኦዳ” ተምሳሌትነቱ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ ገብቶት ከሆነ፣ በቁም ጎረስረስ አድርጎ መሮጥን የመሰለ ከላባ ውይይት ከማቅረብ ፈንታ፣ የጥያቄና የአስተያየት ድርሻ ባላቸው ታዳሚዎች የታጀቡ የአዳራሽና የስቱዲዮ ትልልቅ ውይይቶችን (የብቻ አቅም ባያስችል በትግግዝ) ማሰናዳት ይጠበቅበታል፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ሕዝቦችና በየትኛውም የፖለቲካ ወገን መከበርንና መታመንን ለመቀዳጀት የሚሻ መገናኛ ብዙኃን፣ እዚህ ስኬት ላይ የሚደርሰው በብልጣ ብልጥነት ሳይሆን፣ ወደ የትኛውም ፓርቲ ሳያጋድልና በማድበስበስ ውስጥ ሳይገደብ፣ እውነታን በመበርበርና እውነትን በመፈልቀቅ መንገድ መሆኑን እግረ መንገዴን ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ሁነኛ ችግሮችንና መፍትሔዎችን እያሳዩ ወደ መግባባት የሚያደርሱ፣ ትልልቅ ግን ቅልጥፍ ያሉ ውይይቶችን የማካሄድ ኃላፊነት በፓርቲዎች ላይ ማመዘኑም መረሳት የለበትም፡፡ ድርድር የተባለው ነገር ፍሬያማ የሚሆነው ከሁሉ በፊት በክርክርና በውይይት የኢትዮጵያን የፖለቲካና የአገዛዝ ጣጣዎች መጀመሪያ ጎልጉሎ ማየትና ማሳየት ከቻለ ብቻ ነው፡፡

የፖለቲካ ሾኬ ሠራሽ የሆነ ክስ ተመሠረተብኝ፣ በምርመራ/በማረፊያ ቤት አያያዝ ድብደባና ማሰቃየት ተፈጸመብኝ የሚሉ ሮሮዎች ምን ያህል እውነትነትና ሐሰትነት እንዳላቸው መቼና በማን ነው የሚገላለጡት? የሚያጓጓ ዕቃ እያስቀመጡ “ሰራቂ”ን እንደመያዝ የመሰለ የአገራችን እንቆቅልሽ እንዴት ነው የሚፈታው? ዘረፋን የሚያደፋፍሩ ሁኔታዎችን የሚያለማ ብልሽትን የፈጠረና ዕድሜ የሰጠ አካል ከግለሰብ ሌቦች ይበልጥ ተጠያቂነት የለበትም? ከዚሁ ጋር በሚመሳሰል አኳኋን ብሶትና በደል አደባባይ እንዳይወጣ እያፋፈነ የቁጣ ፍንዳታን የጠራ አጥፊ እንደገና በሃያ ሺዎች ሰዎችን እያሰረ “ሥልጠና” ለመስጠት የሚበቃው ጉልበት ከእሱ ጋር ስላለች ነው? ወይስ የሞራል ልዕልና ከሰማይ ወርዶለት? የኢሕአዴጋዊ ፓርቲዎች የምሥረታ ክበረ በዓላት ክንዋኔዎች ከመሥሪያ ቤቶች፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከትምህርት ቤቶች ጋር የተጣበቁት በምን አግባብነት ነው? የመድረክ በድርድር መሳተፍና አለመሳፈፍ የግል ጉዳያቸው ነው? ወይስ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የፖለቲካ ሰላም የሚመለከት ጉዳይ? የኢትዮጵያና የኤርትራ መጠማመድና መኮራኮም መርዘሙ፣ የጋራ ዕጣ ያላቸው ሕዝቦች ጥቅምና ዝምድና ጉዳት አይደለም? የኤርትራ መንግሥት በቀጥታም በእጅ አዙርም ኢትዮጵያን ለማበጥ ለሚያደርገው መፍጨርጨር እኛስ በማስገለል “ስኬታችን” የእልህ አስቤዛ እየሰፈርን አይደለንም? የኢሳያስ አፈወርቅ አምባገነንነትን ውድቀት የምናቀርበው በፍጥጫ ወይስ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን በቶሎ አሳክተን ጠበኛ ፖለቲካን ስናመክንና ይኼ ድላችን ክፉኛ መሳጫው ሲሆንAnchor? ወዘተ …  የተብላላ ውይይትን የሚሹ ሁነኛ ጉዳዮቻችን መገለጫዎቻቸው ብዙ ናቸው፡፡

ገዢው ፓርቲ ውይይቱና ድርድሩ እንዲሳካ ፅኑ ፍላጎት ካለው ሕዝብ ገብ የአደባባይ ስብሰባዎችና ሠልፎች ላይ ጊዜያዊ እገዳ ከማሳረፍ በቀር የሐሳብ ነፃነት ላይ በሽብር ሕግም ሆነ በተራዘመው አዋጅ አማካይነት ጠለፋ እንደማይኖር ዋስትና መስጠት ይኖርበታል፡፡ የችግሮች መፍረጥረጥ፣ ተማምኖ ለመተጋገዝና ወደ መፍትሔ ለማምራት ጠንካራ መሠረት ከመፍጠሩም በላይ፣ ለዴሞክራሲ የሚስማሙ አውታራትን የመገንባት የመጀመሪያ ጥርጊያ ነው፡፡ እዚህ ጥርጊያ ውስጥ ለመግባት ከደፈርን ያለ ጥርጥር ዛሬ ችግር የሆነብን የሕዝብና የመገናኛ ብዙኃን ንቁና ስል ተሳትፎ ይጎርፋል፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለመራመድ የማይመቹ አስተሳሰቦችና የአደረጃጀት ቅርፆች የመናጋት ፈተና ውስጥ መግባታቸው፣ እዚያም እዚህም የታጀሉ ዴሞክራቶች እየተሳሳቡ ለመገናኘት ምቹ ሜዳ ማግኘታቸውም ሌላ ብሥራት ነው፡፡

ዴሞክራሲን፣ እኩልነትን፣ ሰላምንና ግስጋሴን የምታበራ አገር ትኖረን ይሆን?

የፓርቲዎች “ድርድር” የጓዳ ሥራ ካልሆነና ሕዝብን በአቀፈ የተብላላ ውይይት አማካይነት ከቀጣዩ ምርጫ በፊት በመንግሥትና በፓርላማ በኩል መሟላት የሚገባቸውን ተግባራትና ባህርያት፣ ከፓርቲዎች በኩል በጋራና በግል የሚጠበቁ አደራዎችን፣ በይደር መቆየትና የበለጠ መመርመር የሚገባቸውን ጉዳዮች መለየት ተሳክቶልን ወደፊት መራመድ ከቻልን ያለጥርጥር ተስፋ ይኖረናል፡፡ የፍትሕ ሥራ በግልጽም ሆነ በሥውር ጣልቃ ገብነት የማይጎድፍበት፣ ሥራ አስፈጻሚው በሕግና በሕዝብ እንደራሴነት ሥር የሚውልበት፣ ሁለቱም አካላት ሕዝብን የሚያፍሩበት፣ ዜጎችም በነፃነታችን የምንመካበት ቀን ላይ መድረስ ሩቅ አይሆንም፡፡

በነፃነት፣ በተነሳሳ አዲስ ስሜትና በሕዝብ አቀፍ መተባበር ውስጥ ሆነን የማይገፋ ምን ቋጥኝ ይኖራል! ዴሞክራሲን ከማዝለቅ ጋር ከብዙ በጥቂቱ፡-

  • በየትኛውም የዓለም ጥግ የሚገኙ በፖለቲካ ኩርፊያና ጠብ ውስጥ የነበሩ የኢትዮጵያ ተወላጆች ለአገራቸውና ለሕዝባቸው በሩቅም ሆነ በቅርብ አስተዋፅኦ የሚያደርጉበትን በር መክፈት፣
  • ለጥላቻና ለግጭት የሚያጋልጡ፣ የአንድ ወይም የሌላ አካባቢ ሰዎች እየቦጠቦጡን ነው ያሰኙና የሚያሰኙ ቅሬታዎችን የሚዘጉና ኅብረ ብሔራዊ መተማመንና አብሮ መሥራትን የሚያጠናክሩ መፍትሔዎችን ሥራ ላይ ማዋል፣
  • በየትኛውም ኅብረተሰብ ኑሮ እያጮለ የሚያዘቅጣቸው አባላት መኖራቸው የታወቀ ቢሆንም፣ ሒደቱ እንዳይጋሽብ የሕዝብ ኑሮ ዋስትናን የሚያጠነክሩ ሥልቶችን ማደራጀት፣ በተለይም ድርቅ በጠኔ ሕይወትንና የህልውና ምንጭን በገፍ የሚያሳጣበትን ጥቃት መመከት፣ በከተሞችም የሰው ልጅ ከገንዳ እስከ መመገብ ከሰውነት ዳር የሚወጣበትን ውድቀት እስከ መጨረሻው መድፈን፣ ባትሎ አደሮችንና ዝቅተኛ ጡረተኞችን ከዋጋ ግሽበት ምች መታደግና መጠበቅ፣
  • መልካም አስተዳደርንና የመብት ጥበቃን የሁሉም ሥፍራ በማድረግና የልማትን አድማስ በማስፋት፣ እስከ ዛሬ አዲስ አበባና የጎሉ ከተሞች ከገጠራማ አካባቢዎች በደልና ሥውር ችጋር ያበረራቸው ሰዎች መሸሺያ የሆኑበትን ታሪክ መቀየር፣ እንዲሁም የከተሞች የሕዝብ ክምችት ዕድገት በኢንዱስትራያዊ ግስጋሴ ከሚፈጥሯቸው የሥራ ዕድሎች ጋር በአያሌው የተራከበ እንዲሆን አድርጎ መግራት፣
  • በመኖሪያ ቤት ግንባታና በኪራይ ቤት አቅርቦት ረገድ ማነቆ ሆነው የኖሩ መሰናክሎችን ከየትኛው ከተማ መበጣጠስ፣
  • በልማት ምክንያት የሚመጣ የኗሪ ተነሺነት አስቀድሞ ተገቢ መሰናዶ ሳይሟላ እንዳይፈጸም ማድረግ፣ ሲፈጸምም ለውጡ ከበፊቱ በእጅጉ ከተሻለ አኗኗር ጋር የሚያገናኝ (ተመስገን የሚያሰኝ) መሆኑን ማረጋገጥ፣
  • በኢትዮጵያ ሕዝቦች የመንግሥት አገናባብ ታሪክ ላይ መሠረታዊ መግባባት ፈጥሮ በሁሉም ቦታዎች ከፓርቲ መዳፍ በወጣ የታሪክ ግንዛቤ ዜጎች የሚታነፁበት ምዕራፍ ውስጥ መግባት፣
  • በባላባታዊው ሥርዓት ረዥም ዘመን ውስጥ ሥር የሰደደውና ዛሬም ድረስ ሕዝቦችን ተብትቦ የሚገኘውን በአማላጅ፣ በደጅ ጥናትና በእጅ መንሻ ጉዳይን የማቃናትና ደንቃራን የመግፋት ባህልን መብትና ግዴታ በሚስተናበሩበት ዴሞክራሲዊ ባህል መበጣጠስ፣
  • ተግባራዊ ለማድረግም ሆነ ከወሰንተኛ ሕዝቦች ፍላጎት ጋር ለማገናኘት ያስቸገረውን የኢትዮ-ኤርትራ የወሰን ጉዳይን በተመለከተ ወሰን የማካለልን ጉዳይ ለጊዜው እንደዘገየ አቆይቶ፣ ጉድጓድ ከመማማስ ይልቅ ወደ ትግግዝ መሸጋገር የሁለቱም አገሮች ጥቅም መሆኑን በመተማመን፣ የጋራ ጥቅምና መተሳሰብ እየሰመረ ሲሄድ የወሰን ነገር ቀላልና ትንሽ ነገር የሚሆንበትን መጪ ጊዜ (ብሎም የአፍሪካ  ቀንድን የጋራ ዕጣ) በማስተዋል በቅኝ ካርታ ጣጣ የተለያዩትን ዘመዳም ሕዝቦች መልሶ ለማገናኘት እንዲቻል ያለመታከት በጋራ ወዳጅ አገርም ሆነ በፊት ለፊት ግንኙነት ጥረት ማድረግ፡፡

በዚህ አቅጣጫ መራመድ ከሰመረልን ሁለት ነገሮችን እንጨብጣለን፡፡ 1ኛ) በታሪክ ጉዞ ውስጥ ያመለጡ ዕድሎችን ከመቁጠርና እንዲህ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ከማለት የወጣ አዲስ ታሪክ እንጽፋለን፡፡ 2ኛ) ለቀጣናችን የዴሞክራሲ፣ የፍትሐዊ ልማትና የሰላም ፈርጥ እንሆናለን፡፡

ከዚህ ውጤት ጋር ተዘማምዶ ኢትዮጵያን ከአፍሪካም ባለፈ የመላ ጥቁሮች የኩራት አምባ ማድረግ የሚያስችል፣ ግን የዘነጋነው የታሪክ ሀብትም አለን፡፡ ኢትዮጵያ በዓድዋ ድሏ አፍሪካውያንንና የዓለም ጥቁሮችን በኩራትና በድል ጧፍ ሞሽራለች፡፡ በአምስት ዓመቱ የፀረ ፋሽስት ትግል ጊዜ ደግሞ የዓለም ጥቁሮችና አፍሪካውያን (ለኢትዮጵያ የተቆረቆሩ ነጮች ጭምር) ጩኸቷንና ትግሏን በመጋራት ኢትዮጵያን ሞሽረዋታል፡፡ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በካሪቢያን ደሴቶች፣ በአፍሪካ የተጮሁ ጨኸቶች፣ የተካሄዱ የቅዋሜ ግብግቦች፣ ከጣሊያን በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የተካሄደ አድማ፣ ድጋፍ በማሰባሰብና በፀሎት የማገዝ እቅስቃሴዎች፣ እንዝመት ብሎ እስከ መነቃነቅ የሄደ ተቆርቋሪነት፣ በተግባርም የታዩ የዘመቻ ተሳትፎዎች ታሪኮቻቸውና የሰነድ ቅጂዎችቻቸው ተሰባሰበው፣ እኛም ያለብንን ታላቅ ውለታ እንድናስታውስና ምሥጋናችንን እንድንገልጽ ያስቻሉ፣ ባለውለታዎቻችንም የታሪክ አጋርነታቸውን መጥተው እንዲያዩ ከሩቅ የሚጣራና አይረሴ መዘክርና መታሰቢያ የተገነባው የቱ  ነው? ይህን ውለታ በቃል እንኳ ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነትን ተወጥተናል? የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ይህንን ሁሉ ዕዳ ተሸክመን መተኛታችን ብቻ አይደለም፡፡ ለዘመናት የኖረውን አሮጌ ሥርዓት መሸኘት ላስቻለው ለትናንትናው የ1966 ዓ.ም. አብዮትና ወጣት አብዮተኝነት የሚመጥን የአክብሮት ማስታወሻ እንኳ ለማስቀመጥ አለመቻላችንም ነው፡፡

መሆን ያለበትና ሆኖ የሚገኘው ላይገናኝ ቢችልም፣ የሥልጣን ጥቅም ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም በታች መዋል እንዳለበት ዕውቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን ላይ መቀመጥ ደግሞ ከዚህም ያለፈ ኃላፊነት ያለበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለችም፡፡ ዕጣዋ የአፍሪካ ቀንድንም ዕጣ ይወስናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ኢትዮጵያ፣ አፍሪካውያንና ጥቁሮች አነሰም በዛ የለፉባት አገር መሆኗ መቼውንም መረሳት የለበትም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...