Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉሙስናን በተግባር እንጂ በቃላት ድርደራ መከላከል አይቻልም

ሙስናን በተግባር እንጂ በቃላት ድርደራ መከላከል አይቻልም

ቀን:

በጎይቶም ተክሌ

የዓለም ባንክ ጽሕፈት ቤት ሙስናን የራስ ያልሆነውን የሕዝብ ሀብት ለግል መጠቀም ማዋል ወይም ሌሎች እንዲጠቀሙ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር በሚል ይተረጉማዋል፡፡ ሌሎችም ጸሐፊያንም ከዓለም ባንክ ጽሕፈት ቤት ብዙ ያልታየውን ትርጓሜ ሰጥተውታል፡፡ ሙስና ባለበት አገር ውስጥ የዜጎች የእኩል ሀብት ተጠቃሚነትን ያሳጣል፡፡ ጥቂቶች ሀብታም ሲሆኑ ብዙኃኑ በድህነት አረንቋ ሥር እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡ ሙስና የኢኮኖሚ ልማት ዕድገትን ያቀጭጫል፡፡ ኢንቨስትመንትን ይጎዳል፡፡ ዜጎች የራስ መብታቸውን በጥሪት ገንዘባቸው እንዲገዙ ያደርጋል፡፡ ዜጎችን በመንግሥት ላይ እንዲያምፁና የመንግሥት ንብረት የተባለውን እንዲያወድሙ ያነሳሳል፡፡ በአጠቃላይ ሙስና በአገር ሰላም እንዳይኖር ያደርጋል፡፡

የሙስና ዓይነቶች ብዙ ናቸው፡፡ ጉቦ መቀበል፣ ማዳላት፣ ማጭበርበር፣ መስረቅ፣ ማታለል፣ በሥልጣን ያላግባብ መጠቀም፣ ወዘተ ናቸው፡፡ በተለይም ጉቦ መቀበል፣ ማዳላትና በሥልጣን ያላግባብ መጠቀም ዜጎችን በመንግሥት ላይ እንዲመራሩ፣ የራስ መብታቸውን በጥሪት ገንዘባቸው እንዲገዙ ስለሚጠየቁ በአገር ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር ያስከትላል፡፡ ሕዝቡ የልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን፣ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶች ከሥራቸው እንዲሸሹ፣ በአጠቃላይ የሕዝብ ኑሮ እንዳይሻሻል መንስዔ ይሆናል፡፡

እንደ አገር የሕግ የበላይነት የማይረጋገጥ ከሆነ፣ የተጠያቂነትና የግልጽነት አሠራር ከሌለ፣ በአገር ጉዳይ የዜጎች ተሳትፎ ከተገደበ፣ በአገር ጉዳይ የጋራ መግባባት ካልተያዘ፣ ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ካልተሰጠ በዚያች አገር ሙስና ተንሰራፍቷል ማለት ነው፡፡ ይህ ባለመሆኑ የመንግሥት ሠራተኞችና ኃላፊዎች እንዲሁም የመንግሥትን ሀብት ያላግባብ መጠቀም የሚፈልጉ ባለሀብቶች ሙስናን በስፋት ያካሂዳሉ፡፡ በአገራችን የመልካም አስተዳደር መርሆዎች እንደሚጠበቁ በቃላት ደረጃ ሁሉም የመንግሥት ኃላፊና ሠራተኛ ያወራል፣ የመልካም አስተዳደር ችግር የልማትና የዴሞክራሲ ዕድገት እንቅስቃሴ ፀር እንደሆነ ሁሉም በየፊናው መፈክር ያስተጋባል፡፡ ይህ ፉከራ በቃላት እንጂ በተግባር ባለመሆኑ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ በጣም እንዲመረር እያደረገ ይገኛል፡፡

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በሙስና ትግል ላይ ቁርጠኛ አቋም እንዳለ እየገለጹ ነው፡፡  ለዚህም ማሳያ የፌዴራልና የክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በማዋቀር ሙስናን የመከላከልና የመዋጋት ሥራ ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡ በዘጠኙም ክልሎች የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ተደራጅተዋል፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በየዓመቱ በጀት እየተፈቀደላቸው ሙስናን የመከላከልና የመዋጋት ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ አውቃለሁ፡፡ የሥራ ውጤቶቻቸውን በየጊዜው በሪፖርት ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ተቋማት ብቃትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ይህንን መንግሥት ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡

ተቋማቱ ለሠራተኞቻቸው በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ከሚከፈለው ደመወዝ በአብዛኛው ያነሰ ደመወዝ ስለሚከፍሉ ብቃትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል አይቀመጥላቸውም፡፡ ይቀጠራል፣ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለቆ ይወጣል፡፡ ሌለው ተቋማቱ የራሳቸው የሚዲያ ፕሮግራም የላቸውም፡፡ ከደቡብ ክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በስተቀር (ፋና ሬዲዮ ጣቢያን በግዥ ይጠቃማል)፡፡ ሚዲያ በፀረ ሙስና ትግል ውጤታማነት ያለው ፋይዳ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ቢታወቅም፣ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ተቋማት እንደ ማንኛውም ድርጅት (ዘይት፣ ሳሙና፣ ቢራ፣ ዳይፐር፣ ፓስታ….. ማስታወቂያ ክፍያ ዓይነት) እየከፈሉ መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ፡፡ በዚያ ላይ የማስተላፊያ ሰዓት በገንዘብ ምረጥ መባል አለ፡፡ ሚዲያዎች መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ከፍተኛ ዋጋ ስለሚጠይቁ መልዕክት ማስተላለፍ የሚችሉት በቂ ገንዘብ ካላቸው ብቻ ነው፡፡ በቂ በጀት ከሌላቸው አይፈቀድላቸውም፡፡ እነሱም አይሞክሩም፡፡ የመንግሥት ኅትመት ሚዲያም ቢሆን የልማት ጉዳይ ይቅደም ስለሚል በሙስና ጉዳይ ላይ ብዙም ትኩረት አይሰጥም፡፡ ስለሆነም መንግሥት የፀረ ሙስና ትግል ላይ ቁርጠኛ አቋም ካለው የእነዚህን ተቋማት አቅም በትክክል ማሳደግ ይገባው ነበር፡፡ በእርግጥ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የፀረ ሙስና ትግል ለሚያካሄዱ ተቋማት የደመወዝ ጥያቄ ለማስተናገድ የሚያሳየውን ከፍተኛ ዳተኝነትና በሥውር የማዳከም ሥራ ሳንረሳ፣ መንግሥት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በማስገደድ ጭምር ይህንን በተግባር ሊያሳይ ይገባል፡፡ በቃላት ብቻ እናጠናክራለን ማለት አይሠራም፡፡ ካልሆነ ሕዝብ ማታለል ይሆናል፡፡

ሌላው መንግሥት ለሙስና ትግል ቁርጠኛ አቋም አለኝ ቢልም የመንግሥት ተሿሚዎች ቁርጠኞች አለመሆናቸው ነው፡፡ በቃላት ቁርጠኛ ነን ይላሉ እንጂ አይደሉም፡፡ በአደባባይ ባይሆንም በሥውር የሙስና ትግሉን በፅናት ይቃወማሉ፡፡ ለማጥፋት ተግተው ይሠራሉ፡፡ ለዚህ መገለጫ ደግሞ ችግር አለባቸው የተባሉት ተሿሚዎች ባሉበት ተቋማት ውስጥ ሙስና እንደሚከናወን ዜጎች በስፋት ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ ሙስና ውስብስብና በተማረ አካል በጥንቃቄ ስለሚሠራ ማስረጃ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ተሿሚዎች ሕይወታቸው ሲቀየር ይታያል፡፡ በጣም ዘመናዊ ቤት ይገነባሉ፡፡ እንደ ሀብታም ልጆቻቸውን ውጭ አገር ልከው ያስተምራሉ፡፡ በጣም ውድ የሆኑ ዕቃዎችን ይገዛሉ፡፡ ገንዘብ ውጭ አገር ያስቀምጣሉ፡፡ ከየት አመጣህ ብሎ የሚጠይቅ አካል ግን የለም፡፡ ቢጠይቅም ማስረጃ አይገኝም፡፡

ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ ተሿሚዎች ለፖላቲካ ድርጅታቸው በጣም ታማኝ ናቸው፡፡ የድርጅት መዋጮ በወቅቱ ይከፍላሉ፡፡ በየመድረኩ እየተገኙ ስለፖለቲካቸው ያወራሉ፡፡ ሙስናን ይረግማሉ፣ ያስረግማሉ፡፡ ተሃድሶ ሲባል እነሱን የሚቀድማቸው የለም፡፡ ታድሰናል ይላሉ፣ ግን በተግባር አልታደሱም፡፡ በአንድ ሥልጣን ቦታ ላይ የሕዝብ ጥያቄ ቢነሳባቸው፣ ሌላ ቦታ ተቀይረው ይሾማሉ፡፡ ምክንያቱም ሙስና ስለመፈጸማቸው ማስረጃ የለም፡፡ ደግሞ ለፖለቲካ ድርጅታቸው በጣም ታማኝ ናቸው፡፡ ታድሰዋል ተብለዋል፡፡ የፖለቲካ ታማኝታቸው ያበቃ ዕለት ግን ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ እነሱም ቀድመው ካወቁ  ውጭ አገር ሄደው ይቀራሉ፡፡ የመንግሥት ተቀውሞ መግለጫ በሚዲያ ላይ ይሰጣሉ፡፡ ራሳቸውን እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነን እያሉ ዲስኩራቸውን ይነዛሉ፡፡ ወደ ተቃዋሚ ድርጅት በር ማንኳኳት ይጀምራሉ፡፡ እውነት ነው አገር ውስጥ ከሆኑ ደግሞ ‹ሸቤ› ይገባሉ፡፡ ይህ በተግባር ያየነው ጉዳይ ስለሆነ እውነት ነው፡፡ ከ‹ሸቤ› ንስሐ ገብተው ይወጣሉ፡፡ የለየት ፓስተር ወይም ወንጌላዊ ወይም ነቢይ እስከመሆን ይደርሳሉ፡፡ በራሳቸው ላይ ለውጥ ያደርጋሉ፡፡ ስለጌታ ይሰብካሉ፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በሰረቁት ገንዘብ ኑሮአቸውን በትክክል ይመራሉ፡፡

ኅብረተሰቡ በሙስና ላይ የአመለካከት ብዥታን የፈጠረ ይመስላል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለሙስና ጉዳት ያወራሉ፣ ይራገማሉ፡፡  ነገር ግን የገቢ ምንጫቸው ደመወዝ ብቻ ሆኖ የተንደላቀቀ ኑሮ ይመራሉ፡፡ ይህን የተንደላቀቀ ኑሮ ለመምራት ገቢው ከየት የተገኘ ነው ቢባል ግን ማስረጃ የለም፡፡ ባለሥልጣኑ ደግሞ ስለሙስና ክፋት በሰፊው ያወራል፣ ያወግዛል፡፡ ይህ ደግሞ ኅብረተሰቡን ግራ እያገባ ይገኛል፡፡ እንዴትስ ይታማል? መረጃስ እንዴት ይገኛል? ኅብረተሰቡ ግን ‘እከሌ በሚስቱ ስም ቤት ገነባ፣ እከሌ የተባለ ባለሥልጣን ኩባንያ በመመሥረት አስመጪና ላኪ ሆኗል፣ የእዚህ ክፍለ ከተማ ባለሥልጣን የሁለት ልጆች እናት ፈትቶ የአንድ ልጅ እናት የሆናችሁን ከባሏ ቀምቶ አገባ፣ በጣም ቆንጆ ቤት ሠራ፣ በሚስቱ ስም ድርጅት ከፈተ፡፡’ ይህ ሁሉ የባለሥልጣኑን ስም እየጠራ በታክሲ፣ በለቅሶ ቤትና በመሳሰሉት ቦታዎች ሲገኙ ይወራል፡፡ የሚወራው በአብዛኛው እውነት ስለመሆኑ ደግሞ አመልካች ነገር አለ፡፡ነገር ግን ባለሥልጣኑ ገንዘቡን ከየት እንደመጣ ማስረጃ የለም፡፡ ማስረጃ የማይኖረው ደግሞ ሙስና የሚከናወነው በሁለት ሰዎች ስምምነት ስለሆነና በደረሰኝ የገንዘብ ቅብብሎሽ ስለማይደረግ ነው፡፡ ዛሬ ለቴክኖሎጂ ምሥጋና ይግባውና በማስተር ካርድ ወይም በቪዛ ካርድ ሙስና መፈጸም ይቻላል፡፡ ገንዘብ የሚሰጣው ሰው ገንዘቡን በውጭ አገር በተለይም በአውሮፓና በእስያ አገሮች ባንኮች በባለሥልጣኑ ስም ገንዘብ ተቀማጭ በማድረግ የገንዘብ መጠቀሚያ የማስተር ካርድ አምጥቶ ይሰጣል፡፡ ባለሥልጣኑም ውጭ ካሉ ወንድም ወይም እህት እንደተላከለት በማስመሰል አገር ቤት እያስላከ ይጠቀማል፡፡ አስረዳ ቢባልም ከውጭ ካሉ ወንድምና እህት የተላከትን ደረሰኝ ማሳየት ይችላል፡፡

ባለሀብቱ ቤት ሠርቶለት በባለሥልጣኑ አባት ወይም እናት ስም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ይሰጣል፡፡ ይህን የሙስና ወንጀል ማስረጃ ማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም ተቋማትን የሚመሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወይም ኃላፊዎች በቃላት ሙስናን ይታገላሉ እንጂ በተግባር የሉበትም፡፡ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖችም በእነዚህ ባለሥልጣናት በሚመሩዋቸው ተቋማት ውስጥ ሙስናን ለመከላከል ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ነገር ግን የሚፈልጉትን ድጋፍ አያገኙም፡፡ አይሰሟቸውም፡፡ ስለዚህ ኮሚሽኖቹ በተደጋገሚ ይለፋሉ እንጂ የተፈለገውን ውጤት ግን አያመጡም፡፡ ሙስናም በተፈለገው ልክ አይቀንስም፡፡ እንዲያውም መልኩን ቀይሮ በአገሪቱ እንደ ወረርሽኝ በጣም እየተሠራጨ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተቋማት ባለሥልጣናት ወይም ኃላፊዎች የቃላት እንጂ የተግባር ሰዎች አለመሆናቸው ነው፡፡

እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት በጣም ምሥጉኖች፣ ለሕዝብ የቆሙ፣ ለሕዝብ የሚሠሩ የመንግሥት ባለሥልጣነትንና የሥራ ኃላፊዎችን ይህ አስተያየት አይመለከታቸውም፡፡ ብዙ ጥሩ ሰዎች አሉን፡፡ ሙስና ተበዳይ የሆነ ባለቤት ስለሌለው ጉዳቱ ቆይቶ እንጂ ወዲያው አይታወቅም፡፡ ስለሆነም ኅብረተሰቡ በሙስና ላይ ብዥታ ያለው አመለካከት ስለያዘ ለመታገል ብዙ ፍላጎት አያሳይም፣ በራሱ ካልደረሰበት በስተቀር፡፡ የሚፈልጉትን ያጡ ወይም አንድን ነገር ለማግኘት ዓላማ አድርገው የሚቀንቀሳቀሱ ሰዎች ግን በሙስና ትግል ላይ ያላቸው ተሳትፎ በጣም የላቀ ነው፡፡ ሌሎች ኅብረተሰብ አካላት ግን ሙስና ይጎዳናል ብለው ትግል ባያካሂዱም፣ አጋጣሚውን ሲያገኙ የራሳቸውን ዕርምጃ ከመውሰድ አይመለሱም፡፡ የሕዝብ አመፅ ሲነሳ የመንግሥት ንብረት ላይ ውድመት ያደርሳሉ፡፡ ጥቂቶች ተንደላቀው የሚኖሩበት ተቋም የሚል አስተሳሰብ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስላለ፣ የመንግሥትን ንብረት ለማጥፋት ቅድሚያ ይወስዳሉ፡፡ ኅብረተሰቡ ተቋማት የእኔ ናቸው ብሎ እንዲያስብ የማድረግ ሥራ ስላልተሠራ፡፡ የፀረ ሙስና ተቋማትን ውስጣዊ ችግራቸውን በትክክል ሳይረዱ በስማ በለው ብቻ ስሙን የሚያጎድፉ፣ የሚኮንኑ፣ ተምረው እንዳልተማሩ ሆነው የስሚ ስሚ አስተያየት የሚሰጡና አዋቂ ነን ባይ ወገኖችም፣ የኮሚሽኖችን ችግር በቅርበት በመረዳት ዕገዛና ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

ሚዲያ በፀረ ሙስና ትግል ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተለያዩ ምሁራን ጽሑፎች ያስረዳሉ፡፡ እውነትም ነው፡፡ በአሜሪካ የወተርጌት ቅሌትን ያጋለጠው ሚዲያ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በሌሎች አገሮች ሚዲያዎች ለፀረ ሙስና ትግሉ የሚያደርጉት ድጋፍና ዕገዛ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በጎረቤታት ኡጋንዳ ሚዲያ በፀረ ሙስና ትግል የሚሰጠው ድጋፍ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በእርግጥ አንድ ሚዲያ ሙስናን በተጨባጭ የሚታገል ከሆነ ከመንግሥት ባለሥልጣን የሚደርስበትን እንግልት እረዳለሁ፡፡ ምክንያቱም ሚዲያውን እስከ ማስዘጋት ድረስ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ስላለ፡፡ የሚዲያ ሠራተኞች ራሳቸው ሙስና መፈጸማቸው ደግሞ ሌለው አስቀያሚ ነገር ነው፡፡ ሙስና የፈጸመን ሰው ከማጋለጥ ይልቅ አስፈራርቶ ገንዘብ መቀበል፣ ግልጽ የሙስና ችግሮችን አዛብቶ ለሕዝብ ማቅረብ፣ ሊተላለፍ የማይገባውን ዘገባ በገንዘብ ማስተላለፍ ወይም ማተም፣ ሚዲያ በእጁ ስላለ ብቻ ኅብረተሰብን ማታለል፣ ለምሳሌ በዓመት በዓል ወቅት ለዘመዶች ቀደሞ ጥያቄውንና መልሱን በመንገር ስልክ ራሱ እየደወለ ጥያቄ በመጠየቅ ‘አሸናፊ ነህ’ እያሉ ሽልማት መስጠትና ሌላው ሕዝብ ወደ ጣቢያ ስልክ እንዳይደውል ስልኩን ተይዟል የሚል ቶን እንዲሰጥ ማድረግ፣ እንዲሁም ዘመዶችን መንገድ ላይ እንዲጠብቁ በማድረግ ጥያቄዎችን በመጠየቅ የተሰጠውን አስተያየት የሕዝብ አስተያየት ብሎ መዘገብ ለአብነት የሚጠቀስ በጣም ጥቂት የሚዲያ ሙስና ወንጀሎች ናቸው፡፡

የመንግሥት ሚዲያ በእርግጥ በልማት ላይ ብቻ እንዲያተኩር ትዕዛዝ የሚሰጥ ስለመሆኑ ግምት ቢኖረኝም፣ በውስጡ ካሉት ባለሙያዎች ውስጥ የልማት፣ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ጉዳዮችን ለመዘገብ ዝግጅቱና ብቃቱ የሚያንሳቸው አሉ፡፡ በሥነ ምግባርና በፀረ ሙስና ዙሪያ ዜናና ዘገባ ሥሩ ሲባሉ ‘የሚያጮህና የማያጮህ ዜናና ዘገባ’ እያሉ ስለሚሠሩ በጣም ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ የኅብረተሰቡን ሥነ ምግባር የሚያሳድግ ዜናና ዘገባ ከመሥራት ይልቅ፣ የማያገባቸውንና ኅብረተሰቡን የማይወክለውን ትርኪሚርኪ ጉዳዮችን በመሰብሰብ ዜናና ዘገባ በሚዲያ ማሳየትንና ማስተላለፍን ይመርጣሉ፡፡

ሙስና በድብብቆሽ ሊጠፋ አይችልም፡፡ ሙስና በቃላት ድርደራ አይጠፋም፡፡ ሙስና እየፈጸሙ ሙስና ማውገዝ ተገቢ አይደለም፡፡ መንግሥትም ሆነ የመንግሥት ኃላፊዎች ሙስናን ለማውገዝ የሚናገሩትን ልክ ቃላቸውን ወደ ተግባር  በመቀየር በሙስና መከላከል ሥራ ለውጥ ሊያሳዩ ይገባል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሕዝብ መኖር ስላለበቸው ከሚያገኙት ገቢ በላይ በመኖር መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሙስናን እንዲታገሉ የተደራጁት ተቋማት የበጀትና የቁሳቁስ አቅም በትክክልና በተገቢ መንገድ ተገንብቶና የሙያ ነፃነታቸው ተጠብቆላቸው ሥራቸውን በኃላፊነት ስሜት እንዲሠሩ ለማድረግ የመንግሥት ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ደግሞ ብቃትና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማቆየት በቂ ደመወዝ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ለሕዝብ እዚህ ግባ የማይበል ሥራ ለሚሠሩ ለአንዳንድ ተቋማት ከፍተኛ ደመወዝ መጠን ሲፈቅድ፣ የአገር ትልቅ አጀንዳ የሆነውን ችግር ለመፍታት ለሚንቀሳቀሱ ተቋማት በቂ ደመወዝ እንዳይከፈል የሚያደርገውን የዳተኝነትና ተቋማትን በሥውር የማዳከም ሥራ በመተው ለተቋማቱ ቅድሚያ ሰጥቶ በቂ ደመወዝ እንዲመደብ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የሌሎች አገሮችን ተሞከሮ በመውሰድ መንግሥትን በዚህ ዙሪያ ማመከር አለበት፡፡

የመንግሥትም ሆኑ የግል ሚዲያዎች ራሳቸውን ከሙስና በማፅዳት በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ ሚናቸውን በተገቢ ሁኔታ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲሁም ሕዝቡ በመንግሥት ኃላፊዎች የገቢ ምንጭ ላይ በቂ ዕውቀት ኖሮት ሳይሸማቀቅ ሙስናን እንዲዋጋ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር፣ ለጠቋሚዎችና ለምስክሮች በቂ ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህን ካደረግን ሙስና ከአገራችን ሙሉ በሙሉ ባይጠፋም ሊቀንስ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ መንግሥትም በየጊዜው ከማያሳምን የቃላት ድርደራ ወጥቶ የተግባር መንግሥት እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...