ሕፃናት መንገድ ላይ ሲሄዱስ ወላጆች እንዴት አድርገው ይዟቸዋል? ኃላፊነት የሚሰማቸው መኪና ከሚሽከረከርበት በተቃራኒ በእጃቸው ይዘው ይመራሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹ተከተዪኝ›› እያሉ እንዳሻቸው የሚሄዱ፤ ዞር ብለው ሳያዩ ወደፊት ብቻ ያመራሉ፡፡ መሰንበቻውን ነው ካዛንቺስ ዑራኤል አካባቢ አንዲት ሕፃን ዓይኗ ይንከራተታል፤ እናቷ ቀድማት ሄዳለች፤ ከሰዎች መሃል ተቀላቅላለች፡፡ ሕፃኗ እንደመሮጥ ያደርጋታል፡፡ በመሃል ብቅ ያለ ጎልማሳ መንገዱን ቢከልላት አልፋው ትሄዳለች፡፡ ተመሳሳይ ቀሚስ የለበሰችውን እናቷን ታይና ትደርስባታለች፡፡ እናቲቱ ምንም አልመሰላትም፤ ስትፈጥንባት ሕፃኒቱ ነጠላዋን እየጎተተች፡፡ ትራመዳለች፣ ባካባቢው ያለፉ አንዲት እናት በሐዘን ቅላፄ ‹‹አቤት እናትነት¡›› ሲሉ ሌሎችም በመስማማት ይመስላል ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡
***
በፀረ ትራፊክ አደጋ ዘመቻው ሰሞን
ባለፈው ሳምንት አጋማሽ (ሚያዝያ 4) ነበር፡፡ ራስ ደስታ ሆስፒታል አካባቢ አንዲቷ አራት ሕፃናትን ጭና መታጠፊያዎች ላይ እንኳን ያለዕርጋታ በፍጥነት ስታሽከረክር፣ አንዱን ሕፃን ዕረፍት እንዲያደርግ ያደረገችው፣ እንዲህ ነበር (ፎቶ)፡፡ ‹‹ሴት አሽከርካሪዎች ጥንቁቅ ናቸው›› ቢባልም፣ እንዲህም እንኳን ለእግረኛ ለጫኑት ሕፃን የማይጨነቁ አይጠፉም፡፡
***
‹‹የንጉሥ ግብር››
በቀድሞ ዘመን ነገሥታቱ፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ እስከ 1967 ዓ.ም. የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ እስከወረዱበት ድረስ ሰውን ደግሰው ያበሉ ያጠጡ ነበር፡፡ በዘመኑ መጠሪያው ‹‹ግብር›› ነበር፡፡ ብላልኝ ጠጣልኝ ለማለት ጥሪ የሚያስተላልፉትም ነጋሪት እያስመቱ ነው፡፡ ያንን የግብር ገጽታ አንድ አንጓ በሐዲስ ዓለማየሁ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› (1958 ዓ.ም.) ልቦለድ እንዲህ በምልልስ ተገልጾ ነበር፡፡
. . . ደብተራ መንበሩና በዛብህ ወደ ግቢ ሲሄዱ ገና ከሩቅ ነጋሪት እያስተጋባ ‹‹ገብር፣ ገብር›› ሲል በዛብህ ሰማና ‹‹የምን ነጋሪት ነው የምንሰማው?››
‹‹ሰውን ለግብር የሚጠራ ነው፡፡
‹‹ሁልጊዜም ሰው ግብር የሚበላው እንዲህ በነጋሪት እየተጠራ ነው?
‹‹ከዚህ ቀደም አይተህ አታውቅም?››
‹‹የለም አይቼ አላውቅም፤››
‹‹ማየቱ ጥሩ ነው፤ መብላቱን ግን አልወደውም›› . . .
ለዚህ ማስታወሻ መነሻ የሆነን አንድ የኢትዮ ጁቡቲ ምድር ባቡር ታሪክን በፎቶዎች ያጀበ የባሕር ማዶ መጽሐፍ ውስጥ ያገኘነው የግብር ፎቶ ነው፡፡ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክና በንጉሥ ተፈሪ ዘመን (1909-1923) ባንድ የግብር አዳራሽ ታዳሚው ከቀረበለት የሥጋ ዓይነት ጋር ይታያል፡፡
***