Saturday, May 25, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ታሪካዊና ምሁራዊ ማረጋገጫ ያጣው መጽሐፍ

ግምገማ፣ በኘሮፌሰር ጳውሎስ ሚልክያስ አመያ

ክፍል ሁለት

ይህ ክፍል ሁለት ቅኝት፣ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ በክፍል አንድ ያቀረብኳቸውን አያሌ ጥያቄዎችን በተመለከተ በድረ ገጽ የሰነዘሩትን የእንካ ስላንትያ ድንፋታ በሰከነና በምሁራዊ ማስረጃ ይዳስሳል። ዶ/ር ፍቅሬ ራስን በማዳን ደመ ነፍስ የወነጨፏቸውን ወደ ኋላ ትተን፣ በታሪክ ስም የሸመኑትን እንግዳ ተረት በጥሞና ስንቃኝ ሥራው እውነትን፣ ልብወለድን፣ ሃይማኖትንና ኮከብ ቆጠራን የሚያደባልቅ ለመረዳት እጅግ አስቸጋሪ የሆነ አባባል ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህም ምክንያት እውነት አስመስለው ለሸረቧቸው ነገሮች ማስረጃ የሚሆኑ፣ ላነሳኋቸው አሥራ ሁለት ጥያቄዎች አንድም እንኳ ተጨባጭ ማረጋገጫ አላቀረቡም፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ፣ ለተጠቀሙባቸው አጠራጣሪ ምንጮች ለግልጽና የተደላደለ ውይይት ኃላፊነት በመውሰድ ፈንታ፣ ለሚያገለግላቸው ውዥንብርና ራስን በመከላከል ድብብቆሽ ችግሩን ወደሌላ ለማላከክ ይዳክራሉ፡፡ ከመጀመሪያው ግልጽ እንዲሆንላቸው የምፈልገው ማረጋገጫ የመስጠቱ የኃላፊነት ሸክም በእኔ ላይ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም እኔ እንግዳ ነገርና ተሰምተው የማይታወቁ ትረካዎችን አላፈለቅሁም፡፡ ይህ ድርጊት የተፈጸመው በዶ/ር ፍቅሬ ስለሆነ፣ ወለም ዘለም ብለው ለማምለጥ አይችሉም፡፡ አገርን ለሚያክል ለመለያውና ለመታወቂያው ፈር እቀዳለሁ የተስተካከለ ታሪኩን አስተምራለሁ ብሎ በድፍረት የተነሳ ማንም ሰው ታማኝና ብረት ለበስ ማስረጃ ማቅረብ ግዴታው ነው፡፡

መልስ ካልተሰጠባቸው ከደርዘን ጥያቄዎቼ በተጨማሪ የሚቀጥሉትን ይመልሱ ዘንድ አሁንም ዶ/ር ፍቅሬን እጠይቃለሁ። አንደኛው አማራና ኦሮሞ የሚወለዱት የሰላም ንጉሥና በምድር የእግዚአብሔር ከፍተኛ ካህን ተበሎ በታወቀው የኢየሩሳሌም መሥራችና፣ አብርሃምና ሌሎች ነገሥታት የሰገዱለት አሥራትም ካወጡለት ከመልከ ጼዴቅ ነው ይሉናል። ሌላው ደግሞ ቀዳማዊ ምኒልክ በአገሩ ውስጥ የሠፈሩት የተለያዩ ብሔረሰቦች ሲሸፍቱበት የአጋዚ (የግእዝ ተናጋሪ) ብሔረሰብ ሰዎችን ከእሱ ጦር ጋር ተመሳጥረው ይዋጉለት ዘንድ ከጋዛ ወደ ኢትዮጵያ አመጣቸው ይላሉ፡፡ ምኒልክንም ክልስ ብለው በአግቦ እንደወረፉት ይጠቅሳሉ። ይህን የአማርኛ ቃል በምን ተዓምር ከሦስት ሺሕ ዓመታት በፊት ለመጠቀም እንደቻሉ ጸሐፊው ብቻ ናቸው የሚያውቁት።

ዶ/ር ፍቅሬ ኤቴል ወደ ኢትዮጵያ ሔዶ፣ ዛሬ ጐጃም ተብሎ በሚጠራው በሠፈረበት ጊዜ፣ ዘጠኝ ልጆች እንደነበሩት በስም ይዘረዝራሉ። ከእነዚህ አንዱ ቶሎሳ ነበረ ይሉና በተጨማሪ ‹‹በነገራችን ላይ የአጎቴ፣ ማለት የአባቴ ወንድም ስም ቶሎሳ ነው›› ይላሉ፡፡ ዶ/ር ፍቅሬ! እንኳን ለአጎትዎ ሞክሼ አገኙ፤ ነገር ግን እነዚህ እንግዳ መልዕክቶች ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይስ ከሌላ የሃይማኖት ድርሳናት የተጠቀሱ ናቸው? እርስዎስ ራስዎ ይህን በተመለከተ እውነት ለመሆኑ ማስረጃ ለሌለው በፈጠራ ለተቀነባበረ ትረካ የተዓማኒነት ሚዛን ይሰጣሉ ወይ? አዝናለሁ፤ ፈጠራና ሃይማኖታዊ እንጂ በምንም ተዓምር ሥራው ተጨባጭ ታሪክ ነው ተብሎ የሚቆጠር አይደለም፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ፣ ታሪክ ሳይንስ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ይጠይቃሉ፡፡ አዎ፣ ታሪክ ሳይንስ ሊሆን ይችላል፤ እናም ነው። ለምን ቢባል፣ ታሪክም እንደሌሎች የማኅበረሰባዊ የጥበብና የዕውቀት መስኮች በአስተማማኝ መረጃ ላይ በመመሥረት የተፈጥሮን የዓለም ታሪክ ለማስረዳት፣ የሰው ልጅ ባለፈው ጊዜ ምን እንዳከናወነ በምንስ አኳኋን የዘመን ኑሮውን እንዳሳለፈ ጎልጉሎ፣ አበጥሮ ንጥረ ፍሬውን በሥርዓት ለመዘርዘርና ለመቃኘት የተዘጋጀ የምሁር መሣሪያ ነው።

ትክክለኛ ታሪክ ለብርቱ የሰው ጥረትና ግረት ምቹ መዝገብ ሲሆን፣ በጥበብ ሒደቱ ከሃይማኖት፣ ከፈጠራ ወሬና ከአፈ ታሪክ ተረት በአያሌው ይለያል፡፡ ለሚያቀርባቸው ሐሳቦች ሁሉም መውጫ አንቀጽ አሉት። ማስረጃው ወይም የመረጃ ጥርቅሞቹ ከገመቱት ሐሳብ ጋር በጥብቅ የሚመሳሰል ካልሆነ በስተቀረ ተመራማሪ ጠቢባን ወይም ሊቃውንት ሐሳባቸውን ሙሉ በሙሉ ይለውጣሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት እንግዲህ የመረጃን አንድምታዎች ለመቀበል ላላቸው የአሠራር ዘዴ ተገዥነታቸውን ለማረጋገጥ ሲሉ ነው፡፡

ከተሰነዘረው የይሆን ይሆናል ግምት ጋር የሚጣጣመውን መቀበል ወይም ተቃራኒ የሆነውን እርግፍ አድርጐ መተው የሰከነ ሊቅ ተግባር ነው፡፡ የምሁራዊም ጥበብ ምርምር መሠረቱ ይህ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሳይንስን በሚመለከት በአርስጣጣሊስ ሥነ አመክንዮ አስተሳሰብ (ሲሎጅዝም) መሠረት ከዳሰስነው ከአጠቃላይ ወደ ዝርዝር ውሩድ አመክንዮ የሚራመደው (ዲደክቲቭ ሎጅክ) አለዚያም ከዝርዝር ወደ አጠቃላይ የሚራመደው ገንቢ አመንክዮ (እንደክቲቭ ሎጅክ)፣ ወደ ትክክለኛ አስተሳሰብ በሚያደርስ ሥሌት ሊረጋጋጥ በሚችል እውነታ ነው፡፡ ገንቢ አመክንዮ ትክክለኛ መሆኑ የሚታወቀው የመነሻው እውነታ የመደምደሚያውን እውነታ የሚያረጋግጥ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። ስለሆነም ከዝርዝር ሁኔታዎች ወደ አጠቃላይ ሁኔታዎች የሚራመደው ሥነ አመክንዮ፣ አንድ ማሟላት ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ በዚህ ሒደት የሁሉም ከሁሉም የሆነው የዋናው ፅንሰ ሐሳብ መንስዔ እንከን የለሽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ውሩድ አመክንዮ ግን የእምነት ጉዳይ ስለሆነ የማረጋገጫ አቅራቦት ግዴታ የለበትም፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ በመረጡት እውነተኛነቱ ባልተረጋገጠ የብራና ጽሑፍ ላይ በተመሠረተው አፈ ታሪክ ተረት ተመርተን፣ እንደ ሃይማኖት በጭፍን የፈጠራን ሐሳብ በእምነት መቀበል፣ ከአጠቃላይ ወደ ዝርዝር የሚተነተነው ሥነ አመክንዮ ምቹ የሆነለት ሲሆን፣ በሁለቱ አማራጮች መካከል ግን የማይታለፍ ልዩነት አለ፡፡ የመጀመሪያው የሳይንስ ምርምር መንገድ ሆኖ ሳለ ሁለተኛው ግን የዕምነት ማረጋገጫ ዓምድ ነው። ምሁራዊ ታሪክ የመጀመሪያውን ሒደት ሲከተል የዶ/ር ፍቅሬ ዓይነቱ የሁለተኛውን መንገድ ተከታይ ነው። በአጭሩ ዶ/ር ፍቅሬ የኢትዮጵያ ምሁራዊ ታሪክ ጸሐፊ ሳይሆኑ እመኑልኝ ብለው ለሚማጠኑለት የፈጠራ ተረት ጥብቅና የቆሙ የልብ ወለድ ደራሲ ናቸው።

ዶ/ር ፍቅሬ  ለአብዛኞች መደምደሚያዎቻቸው የሚተማመኑበት ጃን ሸዋ  የተሰኘው መጽሐፍ፣ እሳቸው እንደሚሉት እውነት የጥንታዊ ቅርስ ግኝት መሆኑ  አልተረጋገጠም፡፡ ስለዚህ ለሚተቿቸው ነገሮችና ሐተታዎች አስተማማኝ ዋቢ ሊሆን  አይችልም፡፡ በሥነ አመንክዮ አነጋገር ይኸን በተመለከተ ደራሲው “ጥያቄውን የመለመን” (ቤጊንግ  ኲዌስሽን) ተግባር ውስጥ ገብተዋል ማለት ነው። ስለ ሥነ አመንክዮ ለማወቅ ለሚፈልጉት  አንድ ክርክር ጥያቄውን ይለምናል የሚባለው  አስቀድሞ የክርክሩን መደምደሚያ ሲቀበል ነው፡፡  የአንድ ምሁር ዋና ኃላፊነት በመሠረታዊ እውነትና በሐሳዊ መረጃ መካከል ያለውን ልዩነት ፍንትው አድርጐ ማሳየት፣ አስተማማኝ ምንጮችን ከአጠራጣሪዎች ለመለየት የሚያስችሉ ምሁራዊ ውጤቶችን ማስገኘት ነው፡፡ በዚህ  አንፃር የዶ/ር ፍቅሬ ምንጮች ምሁራዊ ማስረጃ ከመሆን የራቁ የሐሰት ፈሊጦች ናቸው፡፡

ደራሲው በመሪራስ ሰነድ በሰፊው መመካታቸው ግልጽ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ቴዎድሮስ ለተባለ የኢቢኤስ ጋዜጠኛ በርዕዮት ቪዲዮ ፕሮግራም ቃለ ምልልሳቸው (ttps://www.youtube.com/watch?v=vOgiBKbvPl0 ይመልከቷል) ይህንን የሚመኩበትን ጃን ሸዋ የተባለ የብራና ግኝት ጭራሽ አላየሁትም ብለው በግልጽ ተናዘዋል። ተዓምር ነው! ምሁር ነኝ የሚል ሰው እንዴት ያላየውን ሰነድ ዋቢ አድርጎ  ያቀርባል?

‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ዶ/ር ፍቅሬ በኩራት እንደ ምሁራዊ  መረጃ ከዘረዘሯቸውና ዋቢ አድርገው ካቀረቧቸው ማረጋገጫዎች ውስጥ ማንም ሊጽፈውና  ማንም ሊገድፈው የሚችለው ዊኪፒዲያ መጣጥፍ ይገኝበታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም። ጀርመን ባለው ሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት በፕሮፈሰር ባይሩ ታፍላ አንደተጠቀሰው፣ የዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ የሌሎችን ደራሲዎች ሥራ በቅንፍ ውስጥ አለማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ እንዲያውም የግርጌ ወይም የመጨረሻ ማስታወሻ ምስክርነት ሳያክሉ (ገጽ 207ን ይዩ) ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከተባለው የንቡረዕድ ኤርሚያስ ከበደ መጽሐፍ ስለ ንግሥተ ሳባ ታሪክ ቃል በቃል ተጠቅመዋል (ኢትዮሚዲያ ጃኑዋሪ 12 ቀን 2017)። እንዲሁም ፕሮፌሰር ባይሩ እንዳሳሰቡት፣ የአብርሃም ክንፈ ጽሑፍ በዶ/ር ፍቅሬ ‹‹የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ›› መጽሐፍ ውስጥ ያለቅንፍና ያለ አጣቃሽ ማስታወሻ ቃል በቃል ሰፍረው ተገኝተዋል፤ (በዚያው ቦታ ይዩ)

በዓይናቸው አዩትም አላዩትም ዶ/ር ፍቅሬ በድረ ገጽ ሐተታቸው፣ ወሳኝ ምንጭ የሆነውን የመሪራስ የብራና ጽሑፍ መጽሐፈ ጃን ሸዋን በተመለከተ ጀበል ኑባ (ኑቢያ) ተገኘ የሚሉትን ጥንታዊ የብራና ግኝት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዘክር ስለመስጠት  ጉዳይ ዶ/ር ጳውሎስ ደኅንነቱን ማረጋገጥ ከቻሉ አግኚው መሪራስ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው ብለዋል፡፡ አሁን ነፍሳቸውን ይማረውና እኚህ ሰው በቅርብ ቀን ስላረፉ ወራሻቸው መጽሐፉን ለቤተ መዘክሩ ገፀ በረከት ካደረጉ ከድንቅነሽ ቅሪት ያላነሰ ልዩ ጥበቃ ይደርግለት ዘንድ ማረጋገጫ ለመስጠት እደፍራለሁ። ችግሩ መጽሐፉ ይህን ያህል እንክብካቤ የማያሻው ተዓማኒ በማስመሰል በመሪራስ የተቀነባበረ የደባ ጥንስስ መሆኑን በግዕዝና በሴም ቋንቋዎች ሊቅነት ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ የተመሰከረላቸው ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ ጥርጣሬያቸውን ከሰነዘሩ እነሆ ጊዜው ከርሟል። ይሁንና ዶ/ር ፍቅሬ የግል አባባሎቻቸውን ለመደገፍ ሁለት የግርጌ ማስታወሻዎችን ሲያሠፍሩ በአንደኛው ከ63ቱ 31፣ ከሁለተኛው ከ56ቱ 30 ምንጮች፣ በመሪራስ ምሁራዊ ሥልጣን ስም የሠፈሩ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ የዶ/ር ፍቅሬ ግራ የሚያጋቡ አባባሎች ተቀባይነት ይኖራቸው ዘንድ ከሁሉ በፊት የመሪራስ የብራና መጽሐፍ እውነተኛነት መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የመሪራስ ታላቅ ግኝት መጽሐፈ ጃን ሸዋ ተገኘ የተባለበትን ቦታና ጊዜ ጠለቅ ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የተጻፈበት ጊዜ የተጻፈበት ፊደላት መልክና ቅርጽ መመርመር አለበት፡፡

ስለ መጽሐፈ ጃን ሸዋ  ተዓማኒነት ለምን ይህን ያህል መጨነቅ ያስፈልጋል? የመሪራስ ሥራ አቀራረቡ እውነት መሳይ፣ ግን ሐሳዊ ቢሆንሳ? ምሁራዊ መቋሚያው  ምኑ ላይ ነው? ለዚህ ችግር ማሳያ ምሳሌ እንመልከት። እ.ኤ.አ. በ1983፣ ከ1932  እስከ 1945 ያሉትን ዓመታት የሚሸፍን የሂትለር የቀን ማስታወሻ ደብተር ተገኘ ተብሎ ወሬው የዘመናችን ታላቅ የታሪክ ግኝት ተብሎ በዓለም የመገናኛ አውታሮች  ተሰራጭቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ባለሙያዎች  በጥሞና መርምረው ሐሳዊ ግኝት ነው ሲሉ አሰናበቱት፡፡ በምርምር ጠቢባኑ ፍረጃ ዕፁብ ድንቅ ግኝት ተብየውን ለማቀነባበር በጥቅም ላይ የዋሉት ንጥረ ነገሮች እስከ ሂትለር  መጨረሻ ድረስ እንዳልነበሩ፤ አሁንም በተጨማሪ ሲፈትሹት ዘመናዊ አብራሂ አልትራ የሌት ብርሃን በተጻፈበት ወረቀት ላይ ተስተውሎ ተገኘ፡፡ ከዚህም በላይ የቀን ማስታወሻው መጠረዣ ናሙና በአንድ አቅጣጫ የብርሃን ማጉያ ሲፈተሽ፣ ዘመናዊ ሰው ሠራሽ ንጥረ ነገርን መያዙ ተደርሶበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ይህ አጠራጣሪ የመሪራስ መጽሐፍ እንደ አስተማማኝ ዋቢ ሆኖ ሊጠቀስ ይገባው ዘንድ ጥብቅ ምርመራ እንዲደረግበት መፈለጉ።

በአጭሩ ዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፋቸውን ለመጻፍ ያነሳሳቸው ምክንያት ምንም ይሁን ምን አጣቃሽ ምንጮቻቸው እውነታን ለማረጋገጥ ሠፈሩም አልሠፈሩም የአንጦርጦስ መቀመቅ ድክመቶች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

አንድ ነጥብ ልብ እናድርግ፡፡ በምሁራዊ አስተሳሰብ አግባብ ያለው ጠንካራ መከራከሪያ በማቅረብ ፈንታ ዶ/ር ፍቅሬ አዎንታዊ ስሜቶችን በመቀስቀስ፣ እንዲሁም ፍላጐቶችን በማነቃቃት፣ ከሕዝብ ስምምነት ለማግኘት አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ይህ ግን በአመንክዮ እይታ፣ አንድ ነገር እውነት ነው ብለው ብዙዎች ሰዎች ስለሚያምኑበት እንዲሁ በዘወረደ መቀበልና መሠረታዊ አስተሳሰብን የማዛባት ስህተትን የሚጋብዝ ነው፡፡ በደራሲው አመለካከት በቀረበው ሐሳብ ላይ ሰዎች ጥያቄ እስካላነሱ ድረስ ነጥቡ እንደ እውነት ተደርጎ መወሰድ አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይን እያየ፣ ጆሮ እየሰማ፣ አዕምሮ እያወጣና እያወረደ አደገኛ የማስተዋል ግድፈት መፈጸም ነው፡፡

ለምሳሌ ከኮርፐርኒከስና ከጋሊሊዮ ጋሊሊዮ በፊት፣ መሬት ዝርግና  የማትንቀሳቀስ የኮስሞስ ማዕከል መሆኗን፣ ለሕዋሶቻችን እንደሚመስለው ሁሉ ፀሐይ በዙሪያዋ እንደምትሽከረከር ምዕመኖቻቸው ይቀበሉ ዘንድ የሃይማኖት መሪዎች አጥብቀው ይለፍፉ ነበር፡፡ ለዚህ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ አቀራረብና በነበረው እምነት ኢያሱ እግዚአብሔርን ፀሐይ ባለችበት እንድትቆም ያደረገውና ልመናው የተሳካለት፡፡ በዚያም እግዚአብሔር ፀሐይን ቀጥ ብላ ካለችበት እንድትቆም ሲያዛት እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል በቁ ተብሎ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሠፍሯል፡፡ (መጽሐፈ ኢያሱ 10፥13)፡፡  በጊዜው የነበሩ ከ90 በመቶ የሚሆኑት እስራኤላውያን በአገላለጹ ያመኑትና በሱም ደስተኞች እንደነበሩ በቀላሉ ልንገምተው እንችላለን፡፡ እስራኤላውያን በአገላለጹ  በማመናቸው ግን መሬት ዝርግና የማትንቀሳቀስ የኮስሞስ ማዕከል፣ ፀሐይም በዙሪያዋ ትሽከርከር ነበር ማለት አይደለም፡፡ ፀሐይ በመሬት ዙሪያ እንደምትሽከረከር የጥንት  ሰዎች ስላመኑም ይህ ግምት እውነት ሆነ ማለት አይደለም፡፡ በዚህ አመክንዮ ከሔድን ዘንዳ ብዙ ሰዎች ስላመኑበት በዶ/ር ፍቅሬ የቀረበውና ዒላማውን የሳተ አስተሳሰብ የመጽሐፉን መግለጫዎች ተገቢ ያደርጋቸዋል ማለት ተላላነትና የአዕምሮ መናዘዝ ምልክት ይሆናል፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ የመጽሐፋቸው አንድምታ በምሁራን ዘንድ እንደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተቆጥሯል ይላሉ፡፡ በዚህ ብቻም አልተወሰኑም፡፡ ‹‹እውነተኞቹ ምሁራን›› መጽሐፉ በኢትዮጵያ ዜና መዋዕል በአርአያነት ነባር እምነትን ከመሠረቱ የፈነቀለ አዲስ የታሪክ ብልጭታ ነው በማለት ገምግመውልኛል እስከማለት ደፍረዋል፡፡ ዶ/ር ፍቅሬ ይህን የሚሉት እውነት ከልባቸው ነው? በእርግጥ እውነተኞቹ ምሁራን የእሳቸው መጽሐፍ የኢትዮጵያ ታሪክ አቀራረብ ፈር ቀዳጅና ተራራን የሚያንቀጠቅጥ ብለው ከጠረጠሩት፤ ያ ለውጥ ከእውነታ ወደ ልብ ወለድ፣ ከታሪክ ወደ ተሸመነ ተረት ማሸጋገሩን ሲጠቁሙ መሆን አለበት፡፡ እስቲ ይህን ለማረጋገጥ ታዋቂ የኢትዮጵያ ታሪክ መምህራንን ከብዙው በጥቂቱ እንጥቀስና የሳቸውን ሐሳቦች ይደግፉ እንደሆነ እንጠይቅ። ቀጥሎ የተጠቀሱት ምሁራን እውነት የዶ/ር ፍቅሬን ታሪካዊ ልብ ወለድ በመስካቸው ፈር ቀዳጅ ብለው ያምኑ ይሆን? እስቲ ተጠየቁ ኘሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፣ ኤፍሬም ይስሐቅ፣ መሳይ ከበደ፣ መሐመድ ሀሰን፣ ተሰማ ታኣ። አዎ፣ እስቲ ተጠየቁ! እናንተ የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁራን ፣ ስለዚህ የተዛባ ሥራ ዝምታችሁን ሰብራችሁ ሐሳባችሁን ለግሱ። ይህን ማድረግ ደግሞ ኃላፊነታችሁም ነው።

ዶ/ር ፍቅሬ እኔ ለዘመናት ከኢትዮጵያ ውጭ እንደኖርኩና በዚሁም ምክንያት ኢትዮጵያ ካለው እውነታ በእጅጉ እንደራቅኩ ይተርካሉ፡፡ ነገሮችን በትክክል ለማስቀመጥ ያህል፣ እውነት ከአገሬ ርቄ ብዙ ዓመታት መቀመጤ አይካድም። በእኔ ግምት ዶ/ር ፍቅሬም ቢሆኑ እንዲሁ ለብዙ ዓመታት ውጪ ከርመዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ከሳቸው የበለጠ ካገሬ የራቅኩ አይመስለኝም። ለምሳሌ በ1981 ዓ.ም. ጎብኚ ኘሮፌሰር ሁኜ እንዳስተምር በተባበሩት መንግሥታት ተልኬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎቴን አበርክቻለሁ፤ በዚያም ምሁራዊ ጥናት አድርጌያለሁ፡፡ እንዲሁም በስዊድን መንግሥት ድጋፍ በዚያው ዩኒቨርሲቲ ጐብኚ ኘሮፌሰር ሆኜ በ2004 ዓ.ም. አስተምሬያለሁ፡፡ በተጨማሪም፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጋብዤ ኤም  የፒኤችዲ. የድኅረ ምረቃን ፕሮግራም ለማቋቋም በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ካሉት ብዙ ተሰጥዎ ካላቸው ታዋቂ ምሁራን ጋር በሰፊው ተካፍያለሁ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የምሁር አበል እየከፈለኝ የፖለቲካ ሳይንስ የፒኤችዲ ተመራቂዎችን ውጤት እንድገመግም ተመድቤ ሠርቻለሁ። ዩኒቨርሲቲዬ እየከፈለኝ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ በርካታ ምርምሮችን አካሂጃለሁ፡፡ ይህንንም ለማሟላት በዓመት ቢያንስ ሦስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሄጃለሁ፡፡ እናም በ2008 ዓ.ም. ለአራት ወራት አዲስ አበባ ነበርኩ፡፡ ይህም በዌስተርን ሚሽገን በተደገፈና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ምሁራዊ ስብሰባ ላይ የጥናት ወረቀት ለማቅረብ ነበር፡፡ በዚያም በማኅበረሰብ ጥናት ፎረም ግቢ ሳለሁ ዶ/ር ፍቅሬ በሌላ ቦታ መጽሐፋቸውን እየፈረሙ በመሸጥ ተጠምደው በነበረበት ሰዓት፣ ባለፈው የግምገማ መቅድም እንደጠቀስኩት፣ እኔ ደግሞ ከኘሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ጋር ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ እየተወያየሁ ነበርኩ፡፡ ስለዚህ እኔም ከአገሬ እውነታዎች ከእሳቸው በበለጠ የራቅኩ አይደለሁም፡፡

ለወጣትና በማቆጥቆጥ ደረጃ ላይ ላሉ ምሁራን የሰጠሁትን ምክር በተመለከተ አዎ እነሱን ያልተረጋገጠ መረጃ ተጠቂዎች ከመሆን ለማዳን ስል በምርጫ ሞግዚታዊ ሚናን ለመጫወት ወስኛለሁ፡፡ ለበርካታ አሠርት መምህር ሆኜ የኖርኩ እንደመሆኑ መጠን፣ በዚህ ጊዜ የማስተማር ዓላማዬን አለማቋረጤን አንባቢዎች እንዳትስቱት በማያቋርጥ ዘዴ በማንኛውም ረገድ ወጣቱን በጥብቅ ለመምከር ቆርጫለሁ፡፡

ሟቹ ሱማሌያዊ ወዳጄ፣ የረትገርስ ዩኒቨርሲቲ ኘሮፌሰር የነበረው ሰይድ ሳመታር፣ እናንተ የኢትዮጵያ አስተማሪዎች ወጣቶቻችሁን የብዙ ሶማሌ ወንዶች አንጐልን ካቃወሰው ጫት ማራቅ አለባችሁ ይል ነበር፡፡ ምሁራዊ የሥነ ጥበብ ጥናቶች እንደደመደሙት ጫት የአንጐል ነቀርሳ ብቻ ሳይሆን ብዙ ተጨማሪ የጤና ጠንቅ እንደሚያስከትል ተረጋግጧል። ይበልጥ የሚያሳዝነው አስተማሪዎች በጥንቃቄ ካለመከታተላቸው የተነሳ፣ ከወዲሁ ብዛት ያላቸው ከባድ የጫት ሱሰኞች የአንጐል የደም ሐረግ የተዛባባቸውና ትስስሩ የተቃወሰባቸው ለክፉ የአዕምሮ ደዌ ተዳርገዋል፡፡ ከእነዚህ ጥቂቶች ያሉት የአገሪቱን ሆስፒታሎች ያጨናንቃሉ፤ የቀሩት ስድ ተለቀው በመረንነት ተግባር ላይ ተሰማርተዋል፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ እንገንዘብ፡፡ ምክንያቱም የሚኖሩት በሁለመናው በተለየ ኮስሞስ፣ ያለ የሚመስል ግን የሌሉ ድምጾችን የሚሰሙበት የዝንጋኤ ዓለም ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ምሁር ነኝ ባዮች ከመካከላቸው ፈንጠር ብለው የቆጡን የባጡን የሚቀባዥሩት። ሌላ ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩ የሚሉትን ሁሉ ያምኑበታል። ችግሩ ሌሎችን ግራ ያጋባሉ። ዋና መድኃኒቱ ታዳጊዎችን በጨቅላ ዕድሜአቸው ከጫት ማራቅ ብቻ ነው። አስተማሪዎች እንደመሆናችን እኛ ወጣቶቻችን ከዚህ ዓይነቱ አዋኪ አደጋ ለመጠበቅ በብርታት መሥራት ይኖርብናል፣ ይህን ማድረግም ኃላፊነታችን ነውና፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ የኦሮሞና የአማራ ጥንታዊ የጋራ ቋንቋቸው ‹‹ሱባ›› ነው ይሉናል፡፡ ግን ይህ ጭራሽ ያልነበረ መቶ በመቶ የመሪራስና የዶ/ር ፍቅሬ ፈጠራ መሆኑ አያጠራጥርም። ወደ መሠረቱ እንሒድና በትክክል እንገንዘብ። ምሁራዊ ጥናት እንደሚያሳየው ኩሽና ሴም ከአንድ አባት የሚወለዱ ሁለት ቅርንጫፎች የሆኑት ከአራት ሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ ነው። የፈለቁትም ከአፍሪቃ ነው። በምሥራቅ፣ በሰሜን በአፍሪቃ ቀንድ እንዲሁም በምዕራብ ኤስያ ያሉት ቋንቋዎች በሙሉ አንድ ግንድ እንዳላቸው ከተረጋገጠ መቶ ዓመታት አልፈዋል። እነዚህም ቋንቋዎች አፍሮ-ኤሲያቲክ ይባላሉ። የኢትዮጵያም ቋንቋዎች በሙሉ እዚህ ውስጥ ይጠቃለላሉ። የካም ወይም የኩሽ ቋንቋዎች የጥንቱን የግብፅ ቋንቋ ጨምሮ፣ ኑቢያ በርበር፣ አገው፣ ቤጃ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሊ፣ አፋር ሳሆ፣ ብሌን የማሊ ቱኣሬግ ታሜሼክ፣ የቶጎ ካቢዬ፣ ቻሚርን፣ ያጠቃልላል። የሴም ቋንቋዎች ደግሞ ግእዝ፣ ትግረ፣ ትግርኛ፣ አማርኛ፣ ጉራግኛ፣ ዓረብኛ፣ ዕብራይስጥ፣ አራማይስጥ፣ ባቢሎናዊና ኣሶራዊ፣ አዶማዊ ሞኣባዊ፣ ካነዓናዊና ፊንቂኣዊን ያጠቃልላል። ዛሬ አራት አምስተኛ የኩሽ ቋንቋና የሴም ቋንቋ ተናጋሪዎች በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ነው የሚኖሩት። የኩሽ ቋንቋ በአፍሪቃ ብቻ ሲወሰን የሴም ቋንቋ በአፍሪቃም በደቡብ ኤሲያም ተስፋፍቷል። የቋንቋ ጠቢባን አንደሚሉት ሁለቱም ቅርንጫፎች የተኮተኮቱት ኢትዮጵያን ማዕከል ባደረገ በአፍሪቃ ቀንድ ነው። ሁለቱም ቋንቋዎች ከኢትዮጵያ አካባቢ ተነስተው ነው ወደ ሰሜን አፍሪቃና ወደ ኤሲያ የተስፋፉት።

ከዚህ በላይ የተዘረዘረው ሁሉ የማይካድ እውነታ ሲሆን፣ ዶ/ር ፍቅሬ አንድ ከባድ ክህደት ፈጽመዋል፡፡ በፈጠራ ሥራቸውም የአገርን ታሪክ በአያሌው አዛብተዋል። አንባቢዎች በሕዝብ ላይ የተወነጨፈውን ቧልት የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ ተብሎ የተጻፈውን የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን መጽሐፍ ገጽ 67 ግለጡና ተመልከቱ። አስገራሚና አስቂኝ በሆነ ዘዴ ትግሬዎችን ከአክሱም ሥልጣኔ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን፤ ምንም የጽሑፍ ሆነ የአፈታሪክ ትውፊት በሌለበት በግድየለሽነት የተፈጠሩ፣ ተሰምተው የማይታወቁትን እንደ ጉራጌዎች አደርጋለሁ ብለው ሰባት ልብ ወለዳዊ ነገድ ፈጥረውላቸዋል፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያን ፊደል ‹‹ረ››ን መሠረት በማድረግ የተራቡ አዲስ የጐሳ ስያሜ ናቸው፡፡ በዚህ አሳሳች ፈጠራ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ፊደላት፣ ማለት (ትግ)ን እንዳሉ በመጠቀም የግዕዙን አራቢ 7 ፊደል ተራዎች ማለት፣ ግዕዝ፣ ካዕብ፣ ሣልስ፣ ራብዕ፣ ምስ፣ ሳድስ፣ ሳብዕ የመጨረሻዎቹን በመለወጥ ብቻ ከዚያም ‹‹ትግ›› እና     ሪ፣     ር፣  እያለ በዚሁ ቅደም ተከተል ተሰምተው የማይታወቁ ሰባቱን ብርቅዬ የትግሬ ጎሣዎች ፈጥረው አርፈዋል፡፡ በዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ የተዘረዘሩት፣ ከላይ ለመግለጽ በተሞከረው ሁኔታ የሰባቱ የፈጠራ የትግሬ ጐሳዎች፡ ትግረ፣ ትግሩ፣ ትግሪ፣ ትግራ፣ ትግሬ፣ ትግር እና ትግሮ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ዶ/ር ፍቅሬ ሆይ ይህ አስቂኝ የነገድ ራዕይ መሐደምት እንዴት ነው የተገለጠልዎት? ለመሆኑ የአንዱን ታላቅ የኢትዮጵያ ነገድ ብሔራዊ ታሪክ በሚያስገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ ሲያመሰቃቅሉ ስመ ገናናውንና ታላቁን የአገራችንን ሕዝብ እንዴት ቢንቁት ነው? ቁጭ ብለው የፈጠራ ነገድ የፈጠሩለት እንዴትስ ተገቢውን ክብር ለመንፈግ ቢነሳሱ ነው? ምን ዓይነት ትምክህት ነው በሕዝብ ላይ መቀለድ?

የሚገርመው ነገር ደራሲው ‹‹የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ›› በተባለው መጽሐፋቸው አዲስ ጐሳ ሲፈጥሩ በዚህች ትንሽ ዘዴ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የምሁራኑን አዕምሮአዊ ብቃትና የአመክንዮ ደረጃ ለመፈታተን መሞከራቸው ነው፡፡ እንዲሁ በአጭሩ ለመደምደም በዚህ ዕርምጃቸው ብንመዝናቸው ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ ግጉይ ግለሰብ ናቸው ለማለት ያስደፍራል። አለዚያ ደግሞ ከመጠን ያለፉ ደፋር ሰው በመሆናቸው ሳይውል ሳያድር የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል!

ይቀጥላል

ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው በካናዳ ሞንትሪያል በሚገኘው ኮንኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

በኘሮፌሰር ጳውሎስ ሚልክያስ አመያ

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles