Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊታዳጊዋ የኮምፒውተር አውራ

ታዳጊዋ የኮምፒውተር አውራ

ቀን:

ቤተልሔም ደሴ 17 ዓመቷ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ናት፡፡ ብዙዎች እሷ በምትገኝበት ዕድሜ ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች በላቀ በኢንፈርሜሽን ኮሙዩኒኬሸን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ)  ዘርፍ ብዙ ሠርታለች፡፡ ወጣቶችን በሮቦቲክስና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚያሠለጥነው የአይኮግ ኤኒዋን ካን ኮድ የፕሮጀክት ኃላፊ ናት፡፡ አሜሪካ ኤምባሲ ሴቶችን በአይሲቲ ዘርፍ ለማብቃት የዘረጋው ገርልስ ካን ኮድ አሠልጣኝም ናት፡፡ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ያሠለጠነች ሲሆን፣ ለዩኒቨርሲቲው የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት  (ኢኦን ዲጂታል ላይብረሪ) አፕልኬሽን ሠርታለች፡፡ ለቴክኖ የሞባይል አፕልኬሽኖች እንዲሁም ተማሪዎች እርስ በርስ የሚገናኙበት አስኳላ የተባለ አፕልኬሽን ሠርታለች፡፡ ለመንግሥትና ለግል ተቋማት ከሠራቻቸው አፕልኬሽኖች መካከል እነዚህ ጥቂቱ ሲሆኑ፣ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጓደኞቿ ጋር ‹‹ሬሙስ›› የተባለ የአይቲ ኩባንያም አቋቁማለች፡፡

ከቤተልሔም ጋር ቆይታ ያደረግነው በአይኮግ ኤኒዋን ካን ኮድ ቢሮዋ ውስጥ ነበር፡፡ ስናገኛት ቀለል ያለ ካናቴራ በጂንስ ሱሪና ሸራ ጫማ አድርጋ ነበር፡፡ ፈገግታ የማይለያት ባለ አፍሮዋ ታዳጊ በላፕቶፕ ኢሜሎቿን እያነበበች ነበር፡፡ ሳምንታዊ ክንውኖቿን መዝግባ እንቅስቃሴዎቿን የምትመራበት አጀንዳ በአቅራቢያዋ ይገኛል፡፡ በቢሮዋ ለታዳጊዎች ስለ ሮቦቲክስ የምታስተምርባቸው ሮቦቶችም ይታያሉ፡፡ ሮቦቶቹ  ታዳጊዎች ስለ 21ኛው ክፍል ዘመን ቴክኖሎጂ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለማስተማሪያነት እንደሚውሉ ገልጻልናለች፡፡ ሮቦቶቹ አምና በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሮቦ ሶከር ካፕ በተዘጋጀበት ወቅት ጥቅም ላይ ውለውም ነበር፡፡  

የቤተልሔም መነሻ ተወልዳ ባደገችበት ሐረር ከተማ የሚገኘው ቤቲ ኤሌክትሮኒክስ የተባለው የአቧቷ ሱቅ ነው፡፡ ሞባይልና ሌሎች ኤሌክትሮኒክሶች ለገበያ የሚያቀርበው ሱቁ በከተማው ታዋቂ ነበር፡፡ እሷም ሱቁን ታዘወትራለች፡፡ አባቷ ከመደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንድትሳተፍ ያበረታቷት ነበርና የሙዚቃና ሌሎችም ሥልጠናዎች ወስዳለች፡፡

ዘጠኝ ዓመት ሲሆናት የኮምፒውተር ሥልጠና ወሰደች፡፡ ከዚያ ቀደም ከተማረቻቸው ትምህርቶች በበለጠ ወደደችው፡፡ ይህን ያስተዋሉ አባቷ ኮምፒውተር ገዙላትና ራሷን በራሷ ታስተምር ጀመር፡፡ ኮምፒውተሩ ሲበላሽባት ኤሌክትሮኒክስ የሚጠግኑ ባለሙያዎች ጋር ወስዳ ሲሠራ ትመለከት እንደነበርም ትናገራለች፡፡ ዝንባሌዋን የሚደግፉት አባቷ በእጅጉ ያበረታቷት ስለነበረ ለዛሬ ማንነቷ መሠረት መጣላቸውንም ታክላለች፡፡

ሐረር ውስጥ በሚገኝ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት የሚያስተምር ህንዳዊ መምህር ስለ ኮምፒውተር ግንዛቤ የሚያስጨብጡ መጻሕፍት ይሰጣት ነበር፡፡ ፈጣን ተማሪዋ ቤተልሔም፣ ያገኘችውን የኮምፒውተር ዕውቀት በአካባቢዋ ለሚኖሩ የዕድሜ እኩዮቿ ማካፈል ጀመረችና በትውልድ ቀዬዋ ዕውቅናን አተረፈች፡፡ ከሥልጠናዎቹ በተጨማሪ የኮምፒውተር ዕውቀቷን ወደ ቢዝነስ ለመለወጥ የተነሳሳችበት አጋጣሚ ዘጠነኛ ዓመት ልደቷን ያከበረችበት ወቅት እንደነበረ ትናገራለች፡፡

ልደቷን ለማክበር ዝግጅት ስታደርግ አባቷ ገንዘብ ስላልሰጧት የልደቷን ወጪ በራሷ ለመሸፈን አሰበች፡፡ ‹‹የሰርግ ቪዲዮ ከሙዚቃ ጋር አዋህዶ ኤዲት በማድረግ ያገኘሁትን ገንዘብ ልደቴን አከበርኩበት፤›› ትላለች፡፡ ከዛ በኋላ ኮምፒውተሯን ወደ ገቢ ማግኛነትም ለወጠች፡፡ ከአይሲቲ ዘርፎች በአንዱ መካን (ስፔሻላይዝ ማድረግ) እንዳለባት አሰበችና ‹‹በወቅቱ ትልቅ የነበረና ለወደፊትም እንደሚያድግ ያመንኩበት፤›› ያለችውን ኮዲንግ መረጠች፡፡ ‹‹በኮምፒውተር አንዳች ነገር የመፍጠር ሒደት ስለሚያስደስት ኮዲንግን መርጫለሁ፤›› ስትልም ትገልጻለች፡፡ ድረ ገጽና የሞባይል አፕልኬሽኖች በመሥራቱ ዛሬም ገፍታበታለች፡፡  

በአሥር ዓመቷ ሕይወቷን ባልተጠበቀ አቅጣጫ የሚለውጥ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል ድሬዳዋ ከተማ በተገኙበት ወቅት የከተማው መስተዳድር ከቤተልሔም ጋር እንዲተዋወቁ አደረገ፡፡ ችሎታዋን ከግምት በማስገባት አዲስ አበባ መጥታ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ሥልጠና የምትወስድበት መንገድም ተመቻቸላት፡፡ ቤተሰቦቿ ጓዛቸውን ሸክፈው አዲስ አበባ ከተሙና ሥልጠናውን ትከታተል ጀመር፡፡

‹‹ሐረር በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ቢኖሩም አዲስ አበባ በመምጣቴ በርካታ ባለሙያዎችና የምሳተፍባቸው ፕሮጀክቶች አግኝቻለሁ፤›› ትላለች፡፡ ኢንሳ ውስጥ እየሠለጠነች በተለያዩ ተቋማት ፕሮጀክቶች ትሠራ ነበር፡፡ ከፕሮጀክቶቹ መካከል ከትምህርት ጋር የተያያዙት ከምትደሰትባቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ከዘጠነኛ እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ያሉ መጻሕፍትን በድምፅ እንዲገኙ (ኦዲዮ ቡክ) ለማድረግ የተሠራውን አፕልኬሽንና ለባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሠራችው ያለ ኢንተርኔት ኮኔክሽን (ኦፍላየን) የሚሠራ ዲጂታል ላይብረሪን ማንሳት ይቻላል፡፡ አፕልኬሽኑን ለመሥራት ሁለት ዓመት የወሰደባት ሲሆን፣ ባህር ዳር በነበራት ቆይታ ቤተሰቦቿም ኑሯቸውን ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር አዙረው እንደነበር ትናገራለች፡፡

ሰዎች ለሚገጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ አፕልኬሽኖች ለመሥራት ቅድሚያ ትሰጣለች፡፡ እንደ ምሳሌ የምትጠቀሰው ለአማራ ክልል ዋና ኦዲተር የሠራችው ዲጂታል መረጃ ማስቀመጫ (ዶክመንት ማኔጅመንት ሲስተም) ነው፡፡ ፋይሎችን በአግባቡ የማስቀመጥ (አርካይቪንግ) ሰፊ ክፍተት እንዳለ ያስተዋለችው ቤተልሔም፣ እንደ መፍትሔ ያቀረበችው ዲጂታል የመረጃ ክምችት ሥርዓትን ነው፡፡

ከተጠቀሱት አፕልኬሽኖች መካከል ለብቻዋ የሠራቻቸውና ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር የተጣመረችባቸውም አሉ፡፡ እንደየምትሠራው አፕልኬሽን የሚወስድባት ጊዜ ቢለያይም፣ ከሦስት ሳምንት እስከ ሁለት ዓመት የቆየችባቸው አሉ፡፡ የምትሠራቸውን አፕልኬሽኖች የኮፒ ራይት መብቷን ለመጠበቅ ታስመዘግባቸዋለች፡፡ ሶፍትዌሮችን የማስመዝገብ ሒደት በቅርቡ ቢጀመርም፣ በዘርፉ የጎላ ችግር እንዳልጠገማት ትናገራለች፡፡

ከኮፒ ራይት ጥሰት ጋር የተያያዘ እንቅፋት ባይገጥማትም የምትሠራቸው አፕልኬሽኖች በአግባቡ ጥቅም ላይ የማይውሉበት ጊዜ እንዳለ ታስረዳለች፡፡ ‹‹አፕልኬሽን የሚያሠሩ ሰዎች በመጀመሪያ የሚፈልጉትን ነገር በአግባቡ አያሳውቁም፡፡ ከተሠራ በኋላም በሚፈለገው መጠን ላይጠቀሙበት ይችላሉ፤›› ትላለች፡፡ ለግለሰቦችም ይሁን ለመንግሥት ተቋማት የምትሠራቸው አፕልኬሽኖች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መሥራት እንደሚያስፈልግም ታምናለች፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫውን አፕልኬሽኖች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከማድረግ ጎን ለጎን ታዳጊዎች የአይሲቲ ዘርፍን የመቀላቀል ሰፊ ዕድል እንዳላቸው በማመላከት ረገድም መሥራት እንደሚገባ ትናገራለች፡፡ ‹‹ኮምፒውተርና ኢንተርኔት ካለ ማንኛውም ነገር መፍጠር ይቻላል፤›› የምትለው ቤተልሔም፣ በርካታ ታዳጊዎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ስለምትፈልግ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሥልጠና እንደምትሰጥ ትገልጻለች፡፡

እሷና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች በሚያሠለጥኑበት አይኮግ ኤኒዋን ካን ኮድ የሚሰጧቸው የሮቦቲክስና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሥልጠናዎች ብዙ ተማሪዎችን ማዳረስ ባይችሉም፣ በየትምህርት ቤቱ የአይሲቲ ቡድኖች በማቋቋም ትምህርቱ እንዲዳረስ ያደርጋሉ፡፡ ‹‹ባለን ውስን ግብዓት ማሠልጠን የምንችለው ጥቂት ተማሪዎች ብቻ ነው፡፡ ካለው ፍላጎት አንፃር በቂ አይደለም፤›› ስትል ክፍተቱን ታስረዳለች፡፡ ለተማሪዎቹ ጽንሰ ሐሳቡን ካስተማሩ በኋላ የሚያቀርቡላቸውን መሣሪያ በመጠቀም ፕሮጀክቶች እንዲሠሩ ያደርጋሉ፡፡ ይህን እንቅስቃሴ ‹‹እኔ ያገኘሁትን ዕድል ለሌሎችም ለማካፈል ነው፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡

ቤተልሔም እንደምትለው፣ የምታሠለጥናቸው ልጆች አንዳች ቦታ ደርሰው ማየት ያስደስታታል፡፡ ተማሪዎች የማትሪክ ፈተና ጥያቄዎች በመሥራት ለፈተና የሚዘጋጁበት አፕልኬሽን የፈጠሩ ሠልጣኞቿን እንደ ምሳሌ ታነሳለች፡፡ በዘርፉ ጥሩ ደረጃ የመድረስ ተስፋ እንዳላቸው ያስመሰከሩ ታዳጊ ሴቶች ቢኖሩም፣ ሴቶች በሚፈልጉት መጠን እንዳይሠሩ እንቅፋቶች መኖራቸው ፈታኝ እንደሆነም ሳትናገር አላለፈችም፡፡ በሷ በኩል ግን ልጅ መሆኗ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እንድታገኝ አስችሏት ነገሮችን እንዳቀለለላትና ብዙ ፈተናዎች እንዳልገጠሟት ትገልጻለች፡፡ አያይዛም በአይሲቲ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች መሰናክሎችን አልፈው ትልቅ ደረጃ የደረሱ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን እንደምታደንቅ ትናገራለች፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ደግሞ እንደ ኤለን መስክ ያሉ ስኬታማ ባለሙያዎችን ታደንቃለች፡፡

በአይሲቲ ዘርፍ ለታዳጊዎች ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱ ለወደፊት እንደ ጉግልና ፌስቡክን የመሰሉ ቴክኖሎጂዎችን የሚፈጥሩ ኢትዮጵያውያን እንዲፈልቁ ያግዛል ብላ ታምናለች፡፡ የአይሲቲ ክለቦች፣ ሰመር ካምፖች (የክረምት መቆያ)፣ የአይቲ ውድድሮችና ሥልጠናዎች ብዙ የኮምፒውተር ልሂቃን እንደሚፈልቁባቸውም ተስፋ ታደርጋለች፡፡ እሷ ከአይሲቲ ጎን ለጎን ሕግ አጥንታ ፍትሕ ያጡትን የመታደግ ህልም አላት፡፡ ‹‹በሕይወቴ ቦታ የምሰጠው ደስተኛ መሆንን ነው፤›› የምትለው ቤተልሔም፣ ሐሴት የሚሰጣትን እያደረገች ጠንካራ ሴት ሆና መኖርም  ትሻለች፡፡

የሕይወቷን አብዛኛውን ዓመታት ከኮምፒውተር ጋር ለተያያዙ ሥራዎች ቅድሚያ በመስጠት ብታሳልፍም ከዕድሜ እኩዮቿ ጋር ለመዝናናት ጊዜ እንደምትሰጥም ትናገራለች፡፡ የሳምንቱን መጨረሻ ቀናት ከጓደኞቿ ጋር በመገናኘት ወይም ፊልም በማየት ታሳልፋለች፡፡ ‹‹ቁጥብ ነኝ፡፡ ሥራዬ ላይ ቆፍጣና ነኝ፡፡ ሰዎችን ብዙ ጊዜ የማገኘው ከሥራ ጋር ለተያያዘ ጉዳይ ቢሆንም የምዝናናበት ጊዜም አለ፤›› ትላለች፡፡

ቤተልሔም ለሥራዎቿ ከመንግሥትና የግል ተቋሞች ሽልማቶች ተበርክቶላታል፡፡ ከነዚህም በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር፣ ቤስት ፕረዘንተር አዋርድ በሚል ተሸልማለች፡፡ ቤስት ኢኖቬትስ አዋርድና ቤስት ፕሮጀክት ኦፍ ዘ ይር በሚል የተሸለመቻቸውም አሉ፡፡ በቅርቡ አውትስታንዲንግ ገርል ኦፍ ዘ ይር በሚል ዊንግስ ኢዱኬሽን ኤንድ ሚዲያ ከአፍሪካ ኅብረትና ዩኔሴፍ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ዕውቅና ተሰጥቷታል፡፡ በዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ስም የተሰጠው ሽልማት በሴቶች ዙሪያ የሚሠሩ እንደ ኢትዮጵያን ውሜን ሎየርስ አሶሴሽንና የኛ  የተሸለሙበትም ነበር፡፡ እሷም ስለ ሽልማቶቹ የተሰማትን ስትገልጽ ‹‹እንደዚህ መታወቁ ትልቅ ዕድል ነው፤›› ትላለች፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...