Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እጅ አልገባም እንጂ መቁጠር መቼ አቃተን?

ሰላም! ሰላም! ዓለም ሰላም አጥታ በእኛ ‘ኬፍ’ መባባል የሚቆጣ ይኖራል እኮ። ምን ይታወቃል? ከፀባችን ብዛት ሰላምታችን ሁሉ ሰላምን በማረጋገጥ ላይ መመሥረቱ ራሱ ቁጣ ማብረድ ነበረበት እኮ። ግን ምቀኛ አያሳጣን ነው መቼስ። የቅናት ዛር የሰፈረበት ሁላ እንኳን በሰው ሰላም በሰው ኪስ ይቃጠል የለ። አንዳንዴ እኮ አለመፈጠርን የሚያስመኘኝ ከተፈጠርኩ ያየሁት ትርጉም የለሽ ክፋት ተቆጥሮ የማይልቅ ሲሆንብኝ ነው። ዘንድሮ ቆጥራችሁ አይደለም ገና ሳትጀምሩት የሚያልቀው ገንዘብ ብቻ ሆኗል። በተረፈ ሌላው ጉድ የሚያልቅ አይደለም። እና ሰላም በራቀን ልክ እኛም የምንመፃደቀው እንደ ግዳይ መቁጠር የጀመርነው እኩይ እኩዩን ሆነ። የትንሳዔው ሰሞን ደግሞ ይብስብናል። መቼ ዕለት አንድ ወዳጄ ከአንዱ ወደ አንዱ ድለላ ስከንፍ አግኝቶኝ ‹‹ጫረው!›› አለኝ። ‘ፀብ አጫሪ መንገዱን አጣቦ ዓለምን አስጨንቆ ይዟት ሳለ ሌላ ፀብ ጫር ነው የሚለኝ?’ ብዬ ልሸሸው ስል፣ ‹‹የት ነው የምትሸሸው? ና ቢራ ልጋብዝህ፤›› አለኝ። ሰው እንደሆነ ሰበብ ሆኗል የሚፈልገው።

ከኑሮ መክበድ ጋር እያያዙ የቢራ ‘ኮርኪ ኮሌክት’ የማድረጉ ጉዳይ ግን ሊገባኝ አልቻለም። ጎበዝ ሳይታወቀን እኮ እያመረርን ነው። በተለይማ በበዓል? ጉድ እኮ ነው። ብቻ እሺም እንቢም ሳልል፣ ምንም ሳልመልስ ጥዬው ሄድኩ። ክፉም ደግም ሳይወጣኝ አንገቴን ነቅንቄ ጥዬው ሄድኩ። አንዳንዴ ብዙም የማይገባ ነገር ሲገጥማችሁ ፈቀቅ ማለትን የመሰለ ነገር የለም እሺ። ስጓዝ ተኝቶ መታከም ያለበት ሰው ቁጥር ከኢኮኖሚ ዕድገት አኃዙ በእጥፍ እየጨመረ እንደሆነ እርግጠኛ ሆኛለሁ። አሁን እስኪ ጦርነት ያላየ ትውልድ ልንተካ ለሰላም እየዘመርን፣ ዓባይን እየገደብን፣ ቢሰምርም ባይሰምርም የዴሞክራሲ ጭቃ እያቦካን፣ ማገር እየማገርን በጎን የምንንደውና የምናጠፋው ዋናውን እኔን መሆኑ አሳዝኖኝ ሊያዞረኝ ፈለገ። ግን በስንቱ ይዙርብን! 

 ወትሮ ‹‹እውነት የሚናገር ሰው ጓደኛ የለውም›› አላሉም አፍሪካውያን ጠቃሾች? እውነቴን ነው የምላችሁ ይህቺን ጥቅስ እስከ ሸመደድኩባት ቀን ድረስ የመንጋነት እንጂ የመሪነት መንፈስ እንዳለን አላውቅም ነበር። ከነበር አፈንግጦ ‘የለም በዚያ አይደለም! ኑ በዚህ!’ ያለ አፍሪካዊ ‘ሶቅራጥስ’ እንዳለ ከድለላ በሚተርፈኝ ሰዓት መርምሬ ለማግኘት አንዳንድ መጻሕፍትን ሳገላብጥ ማንጠግቦሽ ታዝባኝ፣ ‹‹ተው ብዙ አታንብብ። ታብዳለህ! እኔ ኋላ ከኅብረተሰቡ የተገለለ ባል አልፈልግም። አርፈህ ቅስቀሳ አዳምጥ። ‘አሸነፍን’ ሲሉ ‘አበጃችሁ’ በል። ‘አልተሸነፍንም’ ሲሉ ‘እንዳላችሁ’ ብለህ እለፍ። ነገር አታምጣብኝ…›› ብላ አስፈራራችኝ።  ያነበበና የተመራመረ ሁሉ የሥልጣን ሽሚያ ውስጥ ይገባል ያላት ማን እንደሆነ አላውቅም። ትንሽ ሰነባብታ ደግሞ፣ ‹‹እዚህ ቤት መጽሐፍ የሚባል ነገር ባይ የእኔና አንተ ነገር አከተመ፤›› አለችኝ። ካልለመድኩት ብቸኝነት የለመድኩት፣ ምኑ ጣፍጦኝ እንደ ለመድኩትም እንዳላጣራ የተከለከልኩት አብሮነት ይሻለኛል ብዬ ለአንዱ አዟሪ ሸጥኳቸው። ደግሞ ለመሸጥ። እንኳን የራሴን የስንቱን ንብረትና እውነት ሳሻሽጥ አይደል እንዴ የኖርኩት? ታዲያስ!

እንዲያው እርሜን በተጋመሰ ዘመኔ እውነትን ፍለጋ ቆርጬ ብነሳ ተቃውሞ ከቤቴ መጀመሩ አስገርሞኝ ገመናዬን ለባሻዬ ልጅ ሳዋየው፣ ‹‹ደግ አደረገች!›› አለኝ። ‹‹ምነው አንተ የተማርክ ሰው አይደለህ? እንዴት እንዲህ ይባላል?›› ስለው በከፊል ይኼ የትምህርት ጥራት ጉድለት እንኳን በሚኒስትር ሹም ሽረትና በርዕዮተ ዓለም ለውጥ፣ በእንዶድ ቢያጥቡትም አይፀዳ እያልኩ፣ ‹‹መጻሕፍት ውስጥ ሐሳብ እንጂ እውነት ተገኝታ አታውቅማ። ‘በተማረው ባሰ’ ‘ባነበበው ከረረ’ ሲባል የምትሰማው እኮ ሐሳብ ሸምድደን በሐሳብ ስለምንለያይ ነው። እውነት ግን አብራህ የተፈጠርች ናት። ህሊናህን ስትጠይቀው እውነትን ይጠራልሃል፤›› ብሎ  የሚገባኝን አሳንሶ ያልገባኝን አብዝቶ አብራራልኝ። ‘ሐሳብ የሌለባት እውነት እንዴት ያለች ትሆን?’ ስል የሚያበላኝን ደላላነት ትቼ የሚያስርበኝን ፍልስፍና ሙጥኝ ልለው ሆነና ነገሩን ተውኩት። በባሻዬ ልጅ አስተያየት ግን ባይዘመርላቸውም ብዙ ሺሕ ሶቅራጥሶች አፍሪካ እንዳሉዋት አረጋገጥኩ። ማሰብና መናገር እየተነፈጉ አይመስላችሁም ያልዘመርንላቸው? 

በነገራችን ላይ አንድ ጥሩ ይዞታ ላይ የነበረ ‘ካሚዮን’ ካጋዛሁት ደንበኛዬ ጋር እንዲሁ በወሬ በወሬ ለልጆች ተረት ስለማውራት ልምድ አንስተን ስንጫወት፣ ‹‹የአሁን ዘመን ልጆች እኮ ተበድለዋል። ከእራት በኋላ ቴሌቪዢን ማየት ይፈቀድልን ብለው መነትረክ ነው የሚያውቁት። አፍ የሚያስከፍት ተረት እንዳልሰማን ኑሮውም ነው መሰል አፍ የሚያስከፍት ተረት ሆኖብን፤ የልጅነት ጣዕማቸውን ወላጆች እያበላሸነው ነው፤›› አልኩት። ‹‹አይ አንተ! የዘንድሮ ልጅ እንኳን ለተረት መቼ ለወተት ይመቻል? አጥንት ብቻ እኮ ነው፤›› አለኝ። ‘ምንድነው የሚለኝ? ቋንቋና ምናብ በመለጠጥ ሳንበደል አድገናል ብለን ተኩራርተን ሳንጨርስ በአማርኛ ላንግባባ ነው?’ ብዬ ስደነግጥ ቀጠለ። የአስደንጋጩ ብዛት!

‹‹ይኼውልህ እኔ የአምስት ዓመት ልጅ አለኝ። አንድ ቀን አጠገቤ ተቀምጦ የሆነ ነገር እየጎረሰ አስነጠሰው። ‘እደግ’ እንደማለት ‘ይማርህ!’ ማለት። መውለዴን ብቻ እንጂ ስለልጅ አስተዳደግ ያልተማሩትን ወላጆቼን ያህል እንዳላሰብኩበት ያወቅኩት ያኔ ነው። ያዘኛ። ‘ማን ነው የሚምረኝ?’ ብሎ ጀመረ። አንዴ ስቻለሁና ‘ፈጣሪ!’ ብዬ መለስኩለት። ‘ምን አጥፍቼ ነው የሚምረኝ?’ አለኝ። ብዙ ላስረዳው ሞከርኩ። ስላልተዋጠለት አንድ ጥያቄ ብቻ ጠየቀኝ። ‘አልምርህም ቢለኝ ዝም ትለዋለህ?’ አለኝ። ‘ፈጣሪ መሐሪ ነው። እንቢ አይልም’ ስለው ‘እንቢ ካላለ ታዲያ መጀመሪያም ጥፋት የሚባል የለም ማለት ነዋ’ ብሎ ተነስቶ ሄደ።  ይኼውልህ የዛሬ ልጅ…›› ብሎ ያጫወተኝ ትዝ ይለኛል።

እኛም እንዲህ ነበርን ወይስ እንጀራ፣ እንጀራ ስንል ‘ሎጂክ’ ተነነብን? ምን ያልተነነብን ነገር አለ ዘንድሮ ብዬ እኮ ነው። የማዳበሪያው ትውልድ ነገር ከተነሳ ራሱን በራሱ ማንበብና መጻፍ ያስተማረ ጩጬ ያለውን ልመርቅላችሁ። አንድም በልማትና በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተባባሪ በመሆን፣ አንድም በፈጣን አላቂ ዕቃዎቻቸው የወረሩንን ሰዎች ዕቃዎች እያነሳ ጽሑፋቸውን ያነባል። ሲያነብ ‘ሜድ ኢን ቻይና’ ነው። ቢል ያው ‘ቻይና’ ነው። እና ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹እኔንም የሠራኝ ቻይና ነው እንዴ?›› — ሆሆ! ይቀራል ብለህ ነው ትንሽ ከቆየን? ማሙሽ . . .  ይቀራል?

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ሥራዬን ጨራርሼ ድክም ብሎኝ በጊዜ ገብቼ ልተኛ ስንደፋደፍ ባሻዬ ደወሉልኝ። የት እንዳለሁ ስነግራቸው፣ ‹‹ቶሎ ብለህ ቤት ና!›› አሉኝና ቤታቸው ሄድኩ። ለባብሰው ተዘገጃጅተው ይጠብቁኛል። ‹‹የት ልንሄድ ነው ባሻዬ?›› ስላቸው፣ ‹‹የዛሬ ጊዜ ሰው መጨካከን ከልክ እያለፈ ነው። ኖሮት ባይሰጥህ፣ ባያበድርህ፣ ተርፎት ባያጎርስህ ምናለበት ከወዳጅ ከዘመድ ስትጣላና ስትኳረፍ ምን ሆንክ ብሎ ቢያስታርቅ? ነውር አይደለም ግን?›› አሉኝ አትኩረው እያዩኝ። ምን እንደሚያወሩ ስላልገባኝ፣ ‹‹ደግሞ ማን ተጣላ?›› ብዬ እንዲያብራሩልኝ ስጠይቃቸው፣ በቅርብ የሚያውቋቸው ሊጋቡ የሚጠበቁ ጥንዶች ተኳርፈው እነሱን ሊሸመግሉ እንደምንሄድ ነገሩኝ። ተስማምቼ ሄድን። መቼም ትልቅ ሰው ትልቅ ነው!

ባሻዬ ሰውዬውን አስቀድመው ውጭ ቀጥረው አግኝተውት መክረውና ገስፀውት ሲያበቁ፣ እጮኛው ቤት እንደ ደረስን ጥንዶቹ ምንም ሳይነጋገሩ እንደተያዩ ዘለው ተቃቅፈው ይላቀሱ ጀመር። ‹‹ባሻዬ ምን ጉድ ነው?›› ብለው እኔን ያዩኛል። እኔም እሳቸውን አያለሁ። እሪታና ለቅሶውን እንዲያበርዱት ገስፀን ሁለቱንም ካረጋጋን በኋላ፣ ‹‹ለካ መተያየት ብቻ በቂያችሁ ኖሯል?›› ብለው ባሻዬ በነገር ጠቅ ሲያደርጓቸው ‹‹አይ ባሻዬ! ጓደኛ፣ ወዳጅ፣ ዘመድ የሚባለውንማ አየነው። አንድ ሰው ምን ሆናችሁ ብሎ እንኳ ሳይጠይቀን ይኼው እሱም እሷ ትምጣ፣ እኔም እሱ ይቅርታ ይጠይቀኝ ስል ተለያይተን መቅረታችን ነበር። ምነው ሰው ይህን ያህል የራሱን እንጀራ ብቻ አብሳይ ሆነ?›› አለችን።

ቤት ያፈራውን ቀማምሰንና ቡና ጠጥተን ‘የዓለም የሲሳይ ቤት ያድርገው! ውለዱ ክበዱ! ፍቅራችሁን እስከ መቃብር ያፅናው!’ ብለን ስንወጣ ባሻዬ፣ ‹‹አየህ ልጅ አንበርብር! ምን አገባኝ ስንት ነገር እያበላሸ እንዳለ? ስንት ቤተሰብ ሲበተን፣ እህት ወንድም እንደ ደመኛ ሲተያይ፣ አባት እናት ሲለያይ፣ ሁሉ እንደፈለገው ሲጓዝ፣ ኅብረተሰብ ፈር ሲስት ‘ተው ምን ሆናችሁ? ወዴት እየሄድን ነው?’ የሚል ሸምጋይ አስታራቂ ማጣት የሚሠራንን? ከሚያቀራርበው የሚያራርቀው፣ ልዩነትን ከሚያጠበው የሚያሰፋው መብዛቱ አያስፈራህም? አይበጀንም አንበርብር! አይበጀንም!›› እያሉኝ፣ ብዙ ስንጫወት አምሽተን ተለያየን። ‘ያስታራቂ ያለህ?’ እንበል ወይስ ‘ማን ይሆን ትልቅ ሰው?’ ለትውስታ ያህል አነሳሁት እንጂ መልሱን ታውቁታላችሁ። ብቻ ስንትና ስንት እሴቶቻችን ማንቀላፋታቸው ስለሚቆጨኝ ነው። ሰው መሆን እኮ ከምንም ይቀድማል። አይደለም እንዴ? ታዲያ በዚህ ዓይነት ዳግም ውልደት ዳግም ትንሳዔ የሚያስፈልጋቸው ማኅበራዊ እሴቶቻችንን ቁጠሩ እስቲ። እጅ አልገባም እንጂ መቁጠር መቼ አቃተን ያለው ማን ነበር? ረሳሁት፡፡ መልካም ዳግማዊ ትንሳዔ! መልካም ሰንበት!     

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት