Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊብቁ ሐኪም ወይስ ጋዋን ለባሽ ማፍራት?

ብቁ ሐኪም ወይስ ጋዋን ለባሽ ማፍራት?

ቀን:

በሆስፒታሉ የተለያዩ ዋርዶች ላይ ከተገኙ በብዛት ወዲያ ወዲህ ሲሉ የሚመለከቱት መደበኛ ሐኪሞችን ሳይሆን በልምምድ ላይ ያሉትን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ክሊኒካል አታችመንት (Clinical Attachment) ላይ ያሉ እንደ ሦስትና አራተኛ ዓመት ተማሪዎች በቡድን በቡድን ሆነው በዋና ሐኪም እየተመሩ ታማሚዎችን ሲጎበኙ ይስተዋላል፡፡ ይህ በየካቲት 12 ሆስፒታል ብቻ ሳይሆን እንደ ጥቁር አንበሳ፣ ጳውሎስ፣ ዘውዲቱና ሌሎችም የመንግሥት ሆስፒታሎች የሚታይ ነው፡፡  

አገሪቱ ያለባትን የሐኪም እጥረት ችግር ለመፍታት ባለፉት የተወሰኑ ዓመታት የሕክምና ተማሪዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር መንግሥት  እንደ መፍትሔ የወሰደው ዕርምጃ ነው፡፡ በርግጥ ይህ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ተማሪዎች ቁጥር መጨመር የታገዘ ዕርምጃም ነው፡፡ በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የመንግሥት ሆስፒታሎች እየተስፋፉና ማስተማሪያ ሆስፒታሎች (Teaching Hospitals) እየሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሕክምና ትምህርት መስጠት በግሉ ዘርፍም እየተስፋፋ መሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችን ቁጥር የመጨመር ዕርምጃውን የሚያጠናክር ሌላው ነገር ነው፡፡

የሕክምና ተማሪዎች ቁጥር መጨመር፣ እንዲሁም የሕክምና ትምህርት በመንግሥት በግሉም ዘርፍ መሰጠት አዎንታዊና ይበል የሚባል ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ አጠቃላይ ውጤት ወይም ተፅዕኖ መልካም ይሆን ዘንድ ሊታዩ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የሕክምና ተማሪዎች የተግባር ሥልጠና ወይም ልምምድ ከቁጥራቸው መብዛትና ልምምድ ከሚያደርጉባቸው ሆስፒታሎች አቅም ውስንነት አንፃር እንዴት ይታያል? በተደጋጋሚ በሕክምና ተማሪዎችና ለማጅ ሐኪሞች ከመጎብኘት አንፃር የበሽተኞች ድካምና ጫናስ? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችም ይነሳሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሕክምና ተማሪዎች የተመደቡበትን ትምህርት ቤት እንደተቀላቀሉ ሁለት ዓመታት ከታማሚ ጋር ሳይገኛኙ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፡፡ ሦስተኛ ዓመት ላይ ከታማሚ ጋር መገናኘት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ መልኩ በንድፈ ሐሳብ በተግባርም (Clinical Attachment) ዘልቀው የመጨረሻ ዓመት ማለትም ሰባተኛ ዓመት ላይ የበቁ ነገር ግን የብቃት ማረጋገጫ የሌላቸው (Qualified but note Certified) በልምምድ ላይ ያሉ ሐኪሞች ሆነው ይንቀሳቀሳሉ፡፡

ነህምያ አንዳርጋቸው ትምህርቱን የተከታተለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሕክምና ትምህርት ቤት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰባተኛ ዓመት (intern) ሲሆን ልምምዱን እያደረገ ያለው በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ነው፡፡ ነህምያ የኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማኀበር ቅርንጫፍ የሆነው አዲስ አበባው የሕክምና ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ነው፡፡

ካለው የተማሪዎች ቁጥር፣ የትምህርት ቤቶችና የሆስፒታሎች አቅምና ሁኔታ አንፃር የሕክምና ተማሪዎች ልምምድ ምን ያህል እንደሚፈለገው እየሄደ ነው ትላለህ? የሚል ጥያቄ አቅርበንለት ነበር፡፡ በጣም ብዙ ተማሪዎች፣ በጣም ትንሽ በሽተኞች እንዲሁም የሆስፒታሎች (የትምህርት ቤቶች) አቅም ውስን በሆነበት ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ ልምምድ መሆኑን በመግለጽ ለጥያቄያችን መልስ ሰጥቷል፡፡

ከነህምያ ቀደም ብለው የሕክምና ትምህርት ቤትን የተቀላቀሉ እንደገለጹልንም የተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የሕክምና ትምህርት ይሰጥ የነበረው በጥቁር አንበሳ፣ በጅማና በጎንደር ዩኒርሲቲዎች ነበር፡፡ እያንዳንዳቸው ለማሠልጠን የሚቀበሉት በዓመት ከአርባ ተማሪ የሚበልጥም አልነበረም፡፡

የዳግማዊ ምኒልክ ድንገተኛ ክፍል ኃላፊ የነበሩትና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በነርሲንግ፣ ሁለተኛውን በኢመርጀንሲ ሜዲሲንና ክሪቲካል ኬር በጥቁር አንበሳ የሠሩት አቶ አለሙ ዳንኤል የተማሪነት ጊዜአቸውን በማስታወስ ዛሬ ላይ የተሪማዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ይገልጻሉ፡፡ ይህም በልምምዳቸው በሕክምና አገልግሎት አሰጣጡ ላይም ተፅዕኖ እንዳለው ያስረግጣሉ፡፡ የታካሚዎች በተደጋጋሚ በተማሪዎች መጎብኘት መሰላቸትና መድከምንም ያነሳሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት የሕክምና ትምህርት ሃያ ስድስት በሚሆኑ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና አምስት በሚሆኑ የግል ተቋማት በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

ነህምያ የቅርብ ጊዜውን እንደሚያስታውሰው እንኳ ጥቁር አንበሳ ሕክምና ትምህርት ቤትን ሲቀላቀል የተማሪዎች ቅበላ በዓመት ከሶስት መቶ ያልበለጠ ነበር፡፡ የዚህ ዓመት የትምህርት ቤቱ ቅበላ ግን አራት መቶ የሚጠጋ እንደሚሆን ይገልፃል፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ኮሌጅን ብንመለከት በአሁኑ ወቅት 796 የሚሆኑ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች አሉት፡፡ እንደ ነህምያ ያሉ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች፣ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ነርሶችና ቡድኑን የሚመራው ሐኪምን ጨምሮ የታማሚዎች ጉብኝት ላይ አንድ ታማሚን ከ25 እስከ 30 የሚሆኑ ባለሙያዎች ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡ ይኼ በራሱ ችግር ነው ባይባል እንኳ የተማሪዎች የልምምድ ጥራት እንዲሁም የታማሚዎች በአግባቡ አገልግሎት ማግኘት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ የግድ ይላል፡፡

በመደበኛ ሐኪም በሚመራ የተለማማጅ ሐኪሞችና ሕክምና ተማሪዎች መጎብኘት ብቻም ሳይሆን ለሁለት ወይም ለሦስት የሚሰጡ አሳይመንቶችን ለመሥራትም ተማሪዎች ታማሚዎችን ይጎበኛሉ፡፡ ‹‹ለሕመምተኛው ሰላምታ ሰጥተንና ራሳችንን አስተዋውቀን የታማሚውን ካርድ በሚገባ አጢነን እንመረምራለን፤›› የሚለው ነህምያ በተደጋጋሚ በተማሪዎች በመጠየቅ ታማሚዎች ሊሰለቹ፣ ሊደክሙም እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡

በደም መርጋትና በማህፀን ዕጢ ይሰቃዩ የነበሩ እናቷን ይዛ በየካቲት 12፣ ጳውሎስና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች ያለፉት ጥቂት ሳምንታትን (እናቷን በተመላላሽና አልጋ ይዘው ለማሳከም) አሳልፋለች፡፡ ‹‹መለማመዳቸው አስፈላጊ ነው፡፡ ግን የደከመው፣ እያመመው ያለና የተኛ በሽተኛ ብሎ ነገር አያውቁም፡፡ የተኛ ሁሉ ቀስቅሰው  ያናግራሉ፡፡ አቀራረባቸውም ትህትና የተሞላበት አይደለም፡፡ የሚፈልጉትን ማድረግ እንጂ የታማሚ ሁኔታ ግድ የሚሰጣቸው አይመስልም›› በማለት የተለማማጅ ተማሪዎች ብዛት ታማሚ ላይ ያለውን ጫናና የሥነ ምግባር ጥሰት ትገልጻለች፡፡    

ሁኔታው ታማሚዎች ላይ ከሚፈጥረው ጫና ባሻገር ነህምያን ጨምሮ ብዙዎች እንደ ትልቅ ችግር የሚያነሱት በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የተማሪዎች በቂ ልምምድ ማድረግ ያለመቻል ሰፊ ዕድልን ነው፡፡ ነህምያ እንደሚለው በሕክምና ትምህርት ቤት ካደረገው ረዥም ቆይታ ከሕመምተኛው ጋር የተገናኘበት ጊዜ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ ይህ ጊዜ ለእሱ ብቻም ሳይሆን ለሕክምና ተማሪዎች በሙሉ ወሳኝ ጊዜ መሆኑ በምንም መልኩ ለክርክር የሚቀርብ አይደለም፡፡

በሕክምናው ዘርፍ አንቱ የተባለው ካናዳዊ ሠር ዊሊያም ኦስለር የሕክምና ተማሪዎችን የተግባር ልምምድ እጅግ አስፈላጊነት ‹‹የበሽታዎችን ሁኔታ ካለመጽሐፍ ለማጥናት መሞከር ካርታ የሌለው ባህርን እንደመቅዘፍ ሲሆን መጽሐፎችን ካለበሽተኛ ለማጥናት መሞከር ደግሞ ጨርሶ ወደ ባህሩ አለመሄድ ነው፤›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ ነህምያም የተማሪዎች ልምምድ በምንም ሊካካስና ሊተካ የማይችል እንደሆነ ይናገራል፡፡

ያለውን ውስንነት ከግምት በማስገባት የሕክምና ተማሪዎች ልምምድ በምስለሰብ (simulation)፣ እንዲሁም ተማሪ በተማሪ ላይ እንዲለማመድ ማድረግን ጨምሮ ክፍተቶችን ለመሙላት የተለያዩ ጥረቶች በሕክምና ትምህርት ቤቶች እየተደረጉ መሆኑ አዎንታዊ ዕርምጃ ቢሆንም ይህም በቂ ሊባል የሚችል እንዳልሆነ ይሰማዋል፡፡ የአገሪቱ የባለሙያ ፍላጎት፣ የሕክምና ተማሪዎች ሥልጠና ጥራትና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ከግምት ገብተው የተወሰነ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ የሚገልጸው ነህምያ ‹‹እንደ እኔ ምልከታ የተማሪ ብዛት በ25 ወይም በ30 በመቶ ቢቀንስ ነገሮች ይሻሻላሉ ብዬ አምናለሁ፤›› ይላል፡፡

በሌላ በኩል የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ትምህርት ቤት ዲንና አሁንም በዩኒቨርሲቲው ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አበበ በቀለ የተማሪዎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን የሕክምና ተቋማት አቅምም ከብዙ ነገሮች አንፃር ለመጨመሩ አጽንኦት ይሰጣሉ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ብቻም ሳይሆን ስፔሻላይዝ የሚያደርጉ፣ ሁለተኛ ዲግሪና ሰብስፔሻላይዝ የሚያደርጉም ቁጥር እየጨመረ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡ አሁን የሕክምና ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች አቅም ከሰው ኃይልም ይሁን ከአገልግሎት አንፃር የተገነባ ቢሆን የተማሪ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ የሕክምና ተማሪዎች የተግባር ልምምድ እንደሚፈለገው እንደ ቀድሞ (እንደ እሳቸው ጊዜ) አለመሆኑን ግን ያምናሉ፡፡

‹‹ከአራት እስከ ስድስት ሺሕ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ያስፈልገናል፡፡ ያለን ግን ከአራት መቶ የሚበልጥ አይደለም፡፡ የምንፈልገው ላይ ለመድረስ ገና ሩቅ ነን፤›› የሚሉት ዶ/ር አበበ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ የሆነ ትውልድ ዋጋ መክፈል እንደሚኖርበት ያስረዳሉ፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ግን ብዙ የሕክምና ባለሙያዎችን ለማውጣት በተለያየ መንገድ ሁሉም የበኩሉን ዋጋ ከፍሎስ በመጨረሻ ብቁ የሕክምና ባለሙያዎችን ማፍራት ይቻላል ወይ? የሚል ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ማፍራት የሚቻለው ብቁ የሕክምና ባለሙያዎችን ሳይሆን ነጭ ጋዋን ለባሾችን ነው በማለት የሕክምና ተማሪዎች ቁጥር ዳግም ሊጤን ይገባል የሚል ክርክር የሚያነሱ ጥቂት አይደሉም፡፡    

መንግሥት የአገሪቱን የሕክምና ባለሙያ ፍላጎት ለመሙላት የተማሪዎችን ቁጥር መጨመር ይፈልጋል፡፡ መምህራን ተማሪዎቹ እንደሚገባቸው ሳይሠለጥኑ የሚል ቅሬታ ያነሳሉ፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸው ምንም እንኳ ረዥም ዓመታትን በሕክምና ትምህርት ቤት ቢያሳልፉም በቂ ዕውቀት ሳያገኙ ይላሉ፡፡ ሕመምተኞችና አስታማሚዎች ደግሞ የተማሪዎች መብዛት ታካሚዎች ላይ ጫና አሳደረ ይላሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሚዛን መጠበቅ ያለበት እንዴት ነው?

‹‹እንደ ድሮው ጥራት ቢባል አይታሰብም፡፡ እንደ ዛሬውም ዝም ብሎ ቁጥር ይጨምርም ቢባል የሚሆን አይደለም›› የሚሉት ዶ/ር አበበ ሚዛን ጠብቆ የመሄድ አማራጩ በጣም ቀጭን መስመር እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ስለዚህ የሕክምና ትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ላይ በጣም መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከሕክምና ተማሪዎች የብቃት ፈተና፣ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ስታንዳርድ ጋር በተያያዘ የተሠሩ ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህም ቢሆን ግን የወጡ ስታንዳርዶች በአፋጣኝ ተግባር ላይ ካለመዋል እንዲሁም ወደ ሚፈለጉ አሠራሮች ለመሻገር ከመዘግየት ጋር በተያያዘ ብዙ ክፍተቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡

የሕክምና ተማሪዎች ቁጥር መጨመሩም፤ እዚህ ነገር ላይ የሚነሳውም ቅሬታ ትክክል እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር አበበ ‹‹አሁንም ግን በጉዳዩ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ባለድርሻዎች ሁሉ ቁጭ ብለን የምንፈልገው ላይ ለመድረስ መሄድ ያለብን እንዴት ነው በሚለው ላይ መነጋገር ይኖርብናል›› ይላሉ፡፡

የተማሪዎች ቁጥር እንዲሁ እየጨመረ እንደማይቀጥል ይልቁንም የሚፈለገው ቁጥር ላይ ሲደረስ እንደሚቆም የሚናገሩት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የአካዴሚክና ሪሰርች ምክትል ፕሮቮስት ዶ/ር ወንድምአገኝ ገዛኸኝ የተማሪ ቁጥር ከፍተኛ፤ አልጋ ይዞ የሚታከም ታካሚ ቁጥር ደግሞ አነስተኛ መሆኑ በብዙ መልኩ ተፅዕኖ መፍጠሩ እንደማይቀር ይገልጻሉ፡፡ ኢንተርን ወይም በልምምድ ላይ ያሉ ሐኪሞች ብዙም የታካሚ የሕክምና ዝርዝር ስለማይወስዱ የእነሱ ልምምድ ታካሚዎች ላይ ጫና እንደማያሳድር ነገር ግን ክሊኒካል አታችመንት ላይ ካሉ ተማሪዎች ጋር በተያያዘ ችግር መኖሩን ያምናሉ፡፡ ይህ ተማሪዎች ልምምድ ላይ እንዲሁም የታካሚዎች ደኅንነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳውን የለማጅ ተማሪዎች ቁጥር ብዛት ለመቀነስ ሆስፒታላቸው የራሱ ኮሌጅ ተማሪዎች እንጂ ከሌሎች የግል የሕክምና ትምህርት ቤቶች ተለማማጆች እንዳይመጡ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡

ምንም እንኳ ባለው በርካታ የሕክምና ባለሙያዎችን የማውጣት ፍላጎትና በተማሪዎች የልምምድ ጥራት መካከል ሚዛን መጠበቅ ላይ ሥራ መሠራት ቢኖርበትም አሁንም በተለይም ተለማማጅ ሐኪም (Intern) የሚባሉት ሰፊ ተግባር ልምምድ አድርገው የምዘና ፈተና ያለፉ ተማሪዎች መሆናቸው ሊዘነጋ እንደማይገባ ዶ/ር ወንድምአገኝ ይናገራሉ፡፡

ተለማማጅ ሐኪሞችም ሆኑ ክሊኒካል አታችመንት ላይ ያሉ ተማሪዎች ራሳቸውን ማስተዋወቅን ጨምሮ ምን እንደሆኑ የመናገር ሐዘኔታና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ሕመምተኞችን መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ የሚታየው ነገር ግን ከዚህ የተለየ መሆኑን አንድ ሁለት ሆስፒታል ሄዶ መመስከር ይቻላል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ተለማማጅ ተማሪ ወይም ሐኪም የሚል የሚጻፈው በእንግሊዝኛ እንጂ በአማርኛ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ተለማማጅ ተማሪዎችም ይሁኑ ተለማማጅ ሐኪሞች ራሳቸውን አስተዋውቀው ማንነታቸውን ከመግለጽ ይልቅ እንደ መደበኛ ሐኪም በቀጥታ ሕመምተኛውን መጠየቅ ብሎም አገላብጦ ማየትን ይመርጣሉ፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ያሉ ደግሞ በሆስፒታሉ የሚገለገለውን ሰው ታሳቢ በማድረግ የሕክምና ባለሙያዎች መግለጫ በኦሮምኛም ጭምር እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ አማርኛም፣ እንግሊዝኛም የሚያደርጉም አሉ፡፡ ነገር ግን እዚህ ድረስ የሚሄዱ የሕክምና ትምህርት ቤቶችም ብዙ አይደሉም፣ ይህንን የሚመለከት የተቀመጠ ስታንዳርድም የለም፡፡ 

የሕክምና ተማሪዎቹ ቁጥር እንዲሁ እየጨመረ አይቀጥልም አንድ ቦታ ላይ ይቆማል የሚለው አስተያየት ካለው እውነታ አንፃር ሲመዘን አሁንም አቅጣጫ ጠቋሚው ወደ መጨመር እንጂ ወደ መቀነስ አለመሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ስለዚህም የሕክምና ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ ሲባል ብቻ መቀነስ ሳይሆን ብቁ የሕክምና ባለሙያዎችን ማፍራትን የሚያረጋግጥ መንገድን መቀየስ ግድ የሚልበት ወሳኝ ጊዜ ላይ መደረሱን ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...