Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትስፖርቱና ፖሊሲው የሚናበቡት መቼ ነው?

ስፖርቱና ፖሊሲው የሚናበቡት መቼ ነው?

ቀን:

በ1990ዎቹ መጀመርያ በአገር አቀፍ ደረጃ ዕውን የሆነው የስፖርት ፖሊሲ ዛሬም ከወረቀት ሊያልፍ አለመቻሉ ለስፖርቱ ዕድገት ውሱንነት እንደምክንያት ይጠቀሳል፡፡ በስፖርት አደረጃጀት ውስጥ ያለውን ችግር በውል ለይቶ ለማወቅ የችግሩ አካል ራሱ ችግሩን መለየት የሚያስችል አቅም ማጣቱ በራሱ ሌላ ችግር እየሆነ ስለመሆኑም ይነገራል፡፡ አንዳንዶች ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት የአስፈጻሚ አካል የአቅም ውስንነት እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርቱ ዘርፍ አዲሱ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በስፖርቱ ዙሪያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከደረጀ ጠገናው ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የስፖርት አደረጃጀቶችን በሚመለከት በፖሊሲው እንዳስቀመጠው የስፖርት ማኅበራት በሒደት ሕዝባዊ አደረጃጀት እንደሚኖራቸው ያምናል፡፡ መሬት ላይ ያለው ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ሆኖ ይገኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አቋምና እምነት ምንድነው?

አቶ ተስፋዬ፡- የሚኒስቴሩ አቋም የመንግሥት አቋም ነው፡፡ ከየትም ሊመነጭ አይችልም፡፡ ተልዕኮውም የሚመጨነው አገሪቱ ስፖርቱን በሚመለከት ካስቀመጠውና ከቀረፀው ፖሊሲ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አጠቃላይ የአገሪቱ መንግሥታዊ ሥርዓት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የራሱ ባህሪያት አሉት፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ መንግሥት ስፖርቱን ጨምሮ የገበያ ክፍተት ባለበት ሁሉ ጣልቃ ይገባል የሚል ይገኝበታል፡፡

- Advertisement -

መንግሥት በፌዴሬሽኖች አደረጃጀት ውስጥ ተልዕኮውን መነሻ አድርጎ ካልሆነ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሌላው በአገሪቱ በማናቸውም ደረጃ ለሚፈጠሩ አደረጃጀቶች ዋናው ገዥ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ፌዴሬሽኖች ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ነገር እስካልፈጸሙ ድረስ ለስፖርቱ በሚጠቅም አግባብ መደራጀት ይችላሉ፡፡ ሚኒስቴሩም ከዚህ በመነሳት ነው አደረጃጀቶችን የሚያየውና የሚመዝነው:: በአሁኑ ወቅት በፌዴሬሽኖች አካባቢ ሲነገር የሚደመጠውን ጣልቃ ገብነት መመልከት የሚኖርብን ከዚሁ በመነሳት ነው፡፡ የሚገርመው በአገሪቱ ከሚገኙ የስፖርት ተቋማት መካከል አቅም አለው ተብሎ የሚታመነው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጭምር ከውጭ ለሚያስመጣቸው ከትጥቅ ጀምሮ ማናቸውም ዕቃዎች ቀረጥ የሚከፍለው መንግሥት ነው፡፡ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲኖሩት የፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ለስፖርቱ ቀጣይ ዕድገት ሲባል ሰንዳፋ የአትሌቲክስ መንደርንና ለሌሎችም መሠረተ ልማቶች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ስታዲየሞችንና አካዴሚዎችን ይገነባል፣ ገንብቷልም፡፡

መንግሥት ጣልቃ ገብቷል ከተባለ በዚህ መልኩ ያደረገውን ነው፡፡ በፖሊሲውም መንግሥት ይደግፋል፣ ስለሚል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በፌዴሬሽን የውስጥ ሥራ ገብቶ መሥራት ያለብህ እንዲህና እንዲያ ብሎ ጣልቃ የገባበት ሁኔታ ካለ ትክክልም አይደለም፣ አልተደረገምም፡፡ እርግጥ ነው ከመንግሥት አመራሮች ጀምሮ ይህንን በሚመለከት የተሳሳተ ግንዛቤ ያላቸው እንዳሉ እናምናለን፡፡ በተረፈ ሚኒስቴሩና ፌዴሬሽኖች በምን አግባብ ተናበውና ተጣጥመው መሥራት እንዳለባቸው በአገሪቱ ሕገ መንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ ማኅበራት በግልጽ የተቀመጡ መርሆች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ከምርጫ ጀምሮ የተለያዩ አሠራሮችን ለመከወን ሲያስቡ ሚኒስቴሩ ‹‹የመንግሥት አቅጣጫ ነው›› በሚል ጣልቃ የሚገባበት አጋጣሚ እንዳለ ያለፉ ተሞክሮዎችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል?

አቶ ተስፋዬ፡- በዚህ ጉዳይ የመንግሥት አቋምና አቅጣጫ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት ስፖርቱን በሚመለከት ሁሉም ነገር እንዲሄድ የሚፈልገው በፖሊሲው መሠረት ነው፡፡ በፖሊሲው ከተቀመጠው አንዱና ዋናው ነገር ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የስፖርቱ መሪዎች ናቸው፡፡ ይኼ ማለት ፌዴሬሽኖች ከምርጫ ጀምሮ ነፃነት ያላቸው መሆኑንና ስፖርቱም እንደሌላው ሴክተር ሁሉ በአቅምና በዕውቀት እንዲመራ ሙሉ እምነት ያለው መሆኑን ነው፡፡ ፖሊሲውም ይህንኑ በግልጽ አስቀምጧል፡፡

መንግሥት አንድን አካል አቅም ኖሮት ስፖርቱን ይደግፋል ብሎ ካመነና ሒደቱን ጠብቆ ከመጣ አመራር እንዳይሆን አይከለክልም፡፡ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ከሆነ ማለት ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ፌዴሬሽን ትልቁ የሥልጣን አካል ተብሎ የሚታመነው ጠቅላላ ጉባኤ ነው፡፡ ይህ አካል ያመነበት መንግሥት ይቀበላል፡፡ ተልዕኮውም ይኼው ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ለስፖርቱ ዕድገት እስከሆነ ድረስ መድረኩ ነፃ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ተጠያቂነትና ግልጸኝነት አይኖርም ማለት እንዳልሆነም ሊወሰድ ይገባል፡፡ 

ሪፖርተር፡- መንግሥት ጣልቃ እንደሚገባ ማሳያ ተደርጎ የሚነሳው የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ላይ የቀድሞዎቹ ሚኒስትሮች የወሰዱት ቢሮ የማሸግ ዕርምጃን ነው፡፡ ስለዚህስ የሚሉት ይኖርዎታል?

አቶ ተስፋዬ፡- ሚኒስቴሩ ሊያደርግ የሚችለውና ተደርጓል ብዬ የማምነው ለውኃ  ስፖርቶች ፌዴሬሽን ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ ማቋረጡን ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዕለት ተዕለት ሥራውንና ከተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳይቀጥል አላደረገም፡፡ ፌዴሬሽኑም በዚህ ረገድ ደርሶብኛል ያለው ነገር የለም፡፡ እንደሚታወቀው የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ከጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቅጥር ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች የሚደረጉለት ከሚኒስቴሩ ነው፡፡ መንግሥታዊ አካሉ በፌዴሬሽኑ ክፍተቶች ሲኖሩና አለ ብሎ ሲያምን እንዲያስተካክልም ጭምር ከመመኘት ድጋፉን አቋርጧል፡፡ ድጋፍ በሌለ መልኩ የሰጥቶ መቀበል መርህም ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡ መርሁ አልተሟላም ብሎ የሚያምን አካል ድጋፉን ሲያቋርጥ ምክንያቱ ምንድነው? ብሎ ከማጥራት ይልቅ ሌላ ትርጉም በመስጠት ወደ አላስፈላጊ እሰጣ ገባ መሄድ ለተቋሙ ብቻ ሳይሆን ለስፖርቱም ጥቅም የሚሰጥ አይመስለኝም፡፡ ሥራውን ያገደ አካል ግን የለም፡፡ በእርግጥ ሥልጣንን ባልተፈለገ መልኩ ለመጠቀም የሚሞክሩ አመራሮች አይኖሩም የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዚህ ረገድ ችግሮች ሊፈጠሩ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ይኼ ደግሞ የሥልጣን ገደብን ካለማወቅ የሚመጣ ሊሆን እንደሚችልም እገምታለሁ፡፡ ይህ የመንግሥታዊ ሥርዓቱ ክፍተት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ግለሰቦች ከመንግሥት ተልዕኮ ውጭ የሚሆኑበት አግባብ ስለሚኖር ለይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይም መንግሥት ጣልቃ ገብነትን አያበረታታም መርሁም አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከታገደ ፌዴሬሽን ለብሔራዊ ኦሊምፒክ ምርጫ ተወካይ ቀርቧል በሚል  ትችቶች ሲቀርቡ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ እዚህ ላይ የሚኒስቴሩ አቋም ምንድነው?

አቶ ተስፋዬ፡- ከታገደ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ለኦሊምፒክ ምርጫው ዕጩ ሆኖ የቀረበ አካል ስለሌለ የምለው ነገር የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በተደረገው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ በዕጩ አቀራረብ ሒደት ሚኒስቴሩ ጣልቃ ይገባ እንደነበር፣ ይሁንና ጉዳዩ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና በክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች ጥንካሬ ምርጫው ነፃ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መደረጉ ተሰምቷል፡፡ ይቀበሉታል?

አቶ ተስፋዬ፡- በሚኒስቴሩ የስፖርቱ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ እኔ ነኝ፡፡ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ በተደረገበት አዳማም ነበርኩ፡፡ ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ የመገናኛ ብዙኃን አካላትም ነበሩ፡፡ በዕለቱ በተከናወነው ጉባኤ ላይ የታደሙ ከሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ነበሩ፡፡ ጣልቃ ገብነትን በተመለከተ በምርጫው ዕለትም ሆነ ከምርጫ በፊት በነበረው ሒደት ሚኒስቴሩ ላይ የቀረበ ተቃውሞ አልነበረም፡፡ ክልሎች ሆኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ባላቸው መብት ተጠቅመው ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት ነው ምርጫቸውን ያከናወኑት፡፡ በጉባኤው ዕለት መክፈቻና መዝጊያ ንግግር ካልሆነ በምርጫው ሒደት ሚኒስቴሩን በመወከል በግሌ የተናገርኩት የለም፡፡ ክርክሮች ሲደረጉ ነበር፣ የተለያዩ የሕግና የመመርያ ጉዳዮች ተነስተው ጉባኤተኛው ውይይት አድርጎባቸዋል፡፡

 በአጠቃላይ ጉባኤው የተጠናቀቀው ያለአንዳች ተፅዕኖና ጫና ነበር፡፡ የመንግሥት ፍላጎት ይኼ ዓይነቱ አሠራር እየጎለበተ እንዲሄድ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ በነፃ ምርጫ የመጣን አካል የቱንም ያህል አሠራሩ ባይመቸውም ሕዝባዊ አካሉ የወከለው እስከሆነ ድረስ የመቀበል ግዴታ ይኖርበታል፡፡ የሆነውም ይኼው ነው፡፡ ጉዳዩ የግለሰብ ሳይሆን ፖሊሲን የማስፈጸም ጉዳይ ነው፡፡ የግል ስሜት ለግል ጉዳይ እንጂ እዚህ ጋ ቦታ አይኖረውም፡፡ እዚህ ላይ ፌዴሬሽኖችስ ይህን እየተጠቀሙበት ነው ወይ? የሚለውም መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ስፖርቱ የሚፈልገው አደረጃጀት ሲኖረው ዕድገቱም በዚያው ልክ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በጣም ብዙ ውስንነቶች በፌዴሬሽኖችና ክልሎች የለም? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ሕገ ደንባቸውን ሳይቀር በውል የማያውቁ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አሉ፡፡ በሕገ ደንባቸው መሠረት ለምርጫ የሚቀርቡ ዕጩዎች መቼና በምን አግባብ ቀርበው ለኃላፊነት እንደሚበቁ በግልጽ ተቀምጦ እያለ ድንገት ተነስተው ጉባኤ ጠርተው ምርጫ የሚያደርጉ ፌዴሬሽኖች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ምን ማለት ነው? ይኼን አሠራር ትክክል አይደለም የሚል መንግሥታዊ አካል ቢመጣ ጣልቃ ገብነት ተብሎ ሊወሰድ ነውን? አይመስለኝም፡፡ ነፃ ምርጫ ከተባለ ሚዲያውና ሕዝቡ ማን ምን ዓይነት አቅም አለው የሚለውን ሊተቹት ይገባል፡፡ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖቻችን ይኼ ተለምዷል? በፍፁም፡፡ የተመራጮች ግለ ታሪክ ኃላፊነት ከመቀበላቸው አስቀድሞ አስተያየት ተሰጥቶበት ያውቃል? በፍፁም፡፡

ስፖርቱ ጠንካራ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ ምክንያቱም ውጤቱን ለማወቅ እሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ሜዳ ላይ የሚታይ በመሆኑ ማለት ነው፡፡ በአገሪቱ በተለይም በአሁኑ ወቅት ስፖርቱ አካባቢ የሚታዩት በትንሽ ነገር የመታጠርና የመርካት ዓይነት አካሄድ ነው፡፡ ይኼ የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ ስፖርቱ አትሌቲክስና ኦሊምፒክን ጨምሮ ከመንግሥት ድጋፍና ድጎማ አልወጣም፡፡ ፌዴሬሽኖቻችንም ሆኑ ክለቦቻችን ለስፖርቱ ዘላቂ ህልውና ማረጋገጫ የሚሆን ስትራቴጂክ ዕቅድ አንድና ሁለት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ነገር የላቸውም፡፡ በግልጽ እንነጋገር ከተባለ ከፌዴሬሽኖቻችን ስንቶቹ ናቸው ከመንግሥት ጥገኝነትና ጠባቂነት ለመውጣት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ያላቸው?

ፖሊሲው የስፖርት ተቋማት በጊዜ ሒደት ራሳቸውን እየቻሉ ሕዝባዊ አደረጃጀት ይኖራቸዋል ይላል፡፡ በምንመለከተው ሁኔታ የዚህ መርህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ቀርቶ ሐሳቡስ ያለ ይመስላል? ከዚህ ለመውጣትና ወደ ትክክለኛው አደረጃጀት ለመምጣት ስፖርቱንና ገንዘቡን አጣጥመው መሔድ ወደሚችሉ አካላት መምጣት ያስፈልጋል፡፡ የሚገርመው የፌዴሬሽኖቻችን መሪዎች ዜጎችን በስፖርተኛ ስም የሚያስኮበልሉ አሉ፡፡ ይኼ ከምን የመነጨ ነው? ግልፅ ስላልሆነ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መምጣት ያስፈልጋል፡፡ ሚኒስቴሩ በእያንዳንዱ ተቋማት የሚያውቃቸው በርካታ ክፍተቶች አሉ፡፡ ከአትሌቶች ምርጫ፣ ከሙያተኛ ቅጥርና ምደባ ጋር ተያይዞ ማስረጃ ሊቀርብባቸው የማይችሉ የአሠራር ጉድለቶች ብዙ ናቸው፡፡ ይኼ ሁሉ ባለበት እንኳን ሚኒስቴሩ ጣልቃ አይገባም፡፡  

ሪፖርተር፡- የወጣቶችና ስፖርት የቀድሞ ሚኒስትር፣ ስፖርቱ መንግሥትና ኅብረተሰቡ በሚፈልጉት መጠን ዕድገት እንዲያመጣ ከተፈለገ በአመራርም ይሁን በሙያተኛ ደረጃ መምጣት ያለባቸው ሰዎች በስፖርቱ የሚጠቀሙ ሳይሆኑ ለስፖርቱ የሚጠቅሙ መሆን እንዳለባቸው ተናግረው ነበር፡፡ አባባሉን በተመለከተ የአሁኑ ኃላፊዎች አስተያየት ምንድነው?

አቶ ተስፋዬ፡- በመሠረታዊነት የብሔራዊ ፌዴሬሽኖቻችን መሪዎች አማተር አገልጋዮች ናቸው ብለን ስንል ግለሰቡ በራሱ ዕውቀትና ገንዘብ ጭምር ለተቋሙ ተጨማሪ አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው፡፡ ኮታና ተዋጽኦ የሚባለውም መታየት ያለበት በዚህ አግባብ መሆን ይገባል፡፡ ዕውቀትና አቅም ለድርድር የሚቀርቡ ነገሮች አይደሉም፡፡ እንደ አገር ብዝኃነትን የምንከተል ነን፡፡ ይህን አጣጥመን ለመሔድ ደግሞ ሙያተኞች እንዲበቁ መሥራት፣ ከዚያም በአቅምና በዕውቀት ኃላፊነትን መስጠት የሚለው መለመድ ይኖርበታል፡፡ ብዝኃነትን እንቀበላለን ስንል የበቁ ሰዎችን በማፍራት ተገቢውን ቦታና ኃላፊነትን ጭምር መስጠት ነው፡፡ የሁሉም ፌዴሬሽኖች የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በትንሹም ቢሆን ሕዝብን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ይኼ አካላቱ ያመኑበት ከሆነ ሚኒስቴሩም ሊያምንበት ግድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  በብዙዎቹ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ምርጫን ጨምሮ ያለው አሠራር የአገሪቱን የበጀት ዓመት መነሻ ያደረገ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ ሒደት መመልከት ይቻላል፡፡ እንደነዚህ የመሰሉ የአሠራር ክፍተቶች እንዲስተካከሉ ኃላፊነትና ድርሻችሁ ምንድነው?

አቶ ተስፋዬ፡- እውነቱን ለመነጋገር የሚኒስቴሩ ድጋፍና ክትትል የሚመራው የአገሪቱን የበጀት ዓመት መነሻ አድርጎ ነው፡፡ ምናልባት በተለየ ሁኔታ እንዲታይ አስገዳጅ የሚሆነው የኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ነው፡፡ ምክንያቱም ኦሊምፒክ ምርጫም ሆነ ጉባኤ እንዲያደርግ የሚገደደው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ሁሉም ጉባኤያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ነው፡፡ እየሆነ ያለውም ይኼው ነው፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ግን የአገሪቱን የበጀት ዓመት እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ይገደዳሉ፡፡ ስለዚህ አሁንም በዚህ ረገድ ውስንነት እንዳለ እንረዳለን፡፡ እስከነአካቴው ጉባኤም የማያደርጉ ጭምር አሉ፡፡

እዚህ ላይ የሚኒስቴሩ ድርሻ የሚሆነው የዕውቅና አሰጣጥ ጉዳይ ነው፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በደንብና መመሪያዎቻቸው መሠረት ማድረግ ያለባቸው የአገሪቱን የበጀት ዓመት መነሻ ያደረገ አሠራር ሊከተሉ እንደሚገባ ነው፡፡ ያን ጊዜ ተገቢውን ዕውቅና ይሰጣል፡፡ ለዚህም የማኅበራትን አደረጃጀት በሚመለከት በ2003 ዓ.ም. የወጣ መመርያ አለ፡፡ በመመርያው መሠረት ፌዴሬሽኖች አሠራራቸውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተቋማቱ የሕዝብ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የመንግሥት ዋና ኦዲተር ጭምር አፈጻጸማቸውን ኦዲት ያደርጋል፣ ተደርጓልም፡፡ እግር ኳስንና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ተቋማቱ ፓርላማ ቀርበው አፈፃፀማቸውን እንዲያስረዱ የተደረገበት አግባብ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ተጠያቂነትን በተመለከተ ካለው ተሞክሮ እስካሁን ዕርምጃ ሲወሰድ አልታየም?

አቶ ተስፋዬ፡- መንግሥት ከዕርምጃ በፊት ማስተማር በሚለው ያምናል፡፡ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ስፖርቱ አካባቢ ያሉት የአሠራር ክፍተቶች ብዙ ናቸው፡፡ በክፍተቱ መጠን ወደ ዕርምጃ መገባት አለበት ከተባለ ስፖርቱ ወደ ባሰ ችግር ውስጥ ስለሚከት ሚኒስቴሩ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያምናል፡፡ ሌላው የሚዲያው ጉዳይ ነው፡፡ ሚዲያው ባለው ተደራሽነት የመንግሥትም ሆነ የግሉ እንዲሁም የማኅበረሰብ ሚዲያውን ጨምሮ ዕርምጃ አወሳሰዱን የሚመለከቱበት ሚዛን ብዙ የሚቀረው ነው፡፡ እርግጥ ነው እነዚህን ነገሮች አጣጥሞ መሄድ የሚያስችል ሥራ ላይ ከእኛ ጀምሮ የሚቀር ነገር አለ፡፡ ሚዲያ ለምንከተለው የለውጥ መንገድ ትልቁ መሣሪያ እንደሆነ ግን እናምናለን፡፡ ለዚህ ሁሉ አስታራቂ የሚሆን ግልጽ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች እንዲኖሩ መሥራት ነው፡፡ እስካሁን ግን እንደሌለ ገምግመናል፡፡

ሪፖርተር፡- መፍትሔ የሚሉት?

አቶ ተስፋዬ፡- በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ለስፖርቱ ዕድገት ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት ትልቅ ሀብት አለ፡፡ ይህ አካል ወደ ስፖርቱ የሚመጣበትን በማመቻቸት ተዋናይ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች አሁን አሁን መታየት ጀምረዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢሾፍቱ ላይ ዕውን ያደረገው የእግር ኳስ አካዴሚን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው ውስንነቶች አሉ፡፡ ብልጭታው ግን ተስፋ ሰጪ እየሆነ ነው፡፡ የነበረውና የቆየው አሠራር የትም እንደማያደርሰን፣ በመንግሥት በጀት ከነማ ተብለው የሚቋቋሙ ክለቦች በተቋቋሙበት ዓመት ብቅ ብለው በዓመቱ ዝናብ የሚሆኑበት ሁኔታ እየተመለከትን ነው፡፡  የስፖርት ተቋማት ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡-  ስፖርቱ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ የራሱን አሉታዊ ድርሻ እየተወጣ የሚገኝ ሁለት ጫፍ የደረሰ አለመግባባት አለ፡፡ የንድፈ ሐሳብ ዕውቀትና የተግባር ዕውቀት ያላቸውን አካላት ማጣጣም አልተቻለም፡፡ ለነዚህ ሁለት ፅንፎችና አስተሳሰቦች አስታራቂ የሚሆነው አማራጭ በእርስዎ ምን ሊሆን ይገባል ብለው ያምናሉ?

አቶ ተስፋዬ፡- እንደ እኔ ሁሉም ሙያዎች ደረጃ ሊወጣላቸው ይገባል፡፡ ይኼ በየትኛውም ዓለም የተለመደና ያለ አሠራር ነው፡፡ ምክንያቱም በልምድ ሜካኒክ የሆነ ይኖራል፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ተምሮ ሜካኒክ የሚሆን አለ፡፡ መፍትሔው ለሁለቱም ዕውቀቶች ደረጃ አውጥቶ ዕውቅና መስጠት ነው፡፡ በስፖርቱም የዚህ ዓይነት አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ ብሔራዊ የወጣቶች አካዴሚ ውስንነቱ እንዳለ ሆኖ የሙያ ደረጃ ላይ የሚሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ዕውቀት በክህሎት፣ ክህሎትም በተመሳሳይ በዕውቀት መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ዕውቀት ንድፈ ሐሳብ ነው፡፡ ክህሎት ደግሞ ሁለቱንም ያካትታል፡፡ ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ሁለቱም ማቀናጀት የግድ የሚልበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ይኼ የቆየውንና ነባሩን አሠራር ለማዘመን ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ረገድ ክፍተቱ እንዳለ እናውቃለን፣ ግን ደግሞ ለመፍትሔው እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የብዙዎቹ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች  ደንቦችና መመርያዎች ትውልደ ኢትዮጵያውያን በስፖርቱ ያላቸውን ዕውቀትና ልምድ እንዳያካፍሉ ምክንያት እየሆኑ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ ስለገደቦች የሚሉት ይኖርዎታል?

አቶ ተስፋዬ፡- መንግሥት የስፖርት ሴክተሩን ጨምሮ የተሻለ ዕድገትና ውጤት ለማመጣት የዓለም ምርጥ ተሞክሮዎችን ጭምር በማሰብ እየሠራ ይገኛል፡፡ ዓለም አንድ መንደር በሆነበት በዚህ ዘመን የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግሮች እንደሚያስፈልጉ ያምናል፡፡ በዚህ መነሻነት ማንኛውም ትውልደ ኢትዮጵያዊ ቢመጣ ለምን የምንልበት አግባብ አይኖርም፡፡ አሁን በምንገኝበት ደረጃ እንኳ እግር ኳሱን ጨምሮ በሌሎችም ስፖርቶች ዕውቀትና አቅሙም ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያ ወገኖችን በማቅረብ አብረን የምንሠራባቸው አካሄዶች አሉ፡፡ ይኼ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...