Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርመንግሥት በደሌን ተገንዝቦ መፍትሔ ይስጠኝ

መንግሥት በደሌን ተገንዝቦ መፍትሔ ይስጠኝ

ቀን:

በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት በአንጋፋነቱ የሚታወቀው በአሁኑ አጠራር የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ እ.ኤ.አ. በ1912 በግል ባለሀብት ተቋቁሞ እነሆ ለ104 ዓመታት ያህል አገልግሎት እየሰጠ ያለ ድርጅት ነው፡፡ እኔ የዚሁ ፋብሪካ ባለሀብት አቶ ብርሃኔ ገብረ መድህን ሀብቱ በደርግ መንግሥት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ አማካይነት ሐምሌ 5 ቀን 1969 ዓ.ም. በደንብ ቁጥር ወ/መ/4/8/4106/09 ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጻፉት ቀላጤ ደብዳቤ መሠረት ከሕግ ውጭ ድርጅቴን ተወስዶ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የደርግን በመመርያ የተወሰደባቸው የግል ባለሀብቶች እየተጣራ ንብረቶቻቸው እንዲመለስ ለማድረግ የካቲት 8 ቀን 1987 ዓ.ም. አዋጅ ቁጥር 110/87 እና የአዋጁን አፈጻጸም ቁጥር 001/88 እና 002/89 መመርያ በማውጣት ከ250 በላይ ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለንብረቶች ንብረታቸው እንዲመለስላቸው ተደርገዋል፡፡

መንግሥት ይህን አዋጅ ማውጣቱ ኢትዮጵያን ለተሻለ የዕድገት ጎዳና ከሚያደርሳት አንዱና ዋነኛ እንደሆነ ይታመናል፡፡ እኔ ለ16 ዓመታት በስደት አሜሪካን አገር ቆይቼ ወደ አገሬ ኢትዮጵያ ተመልሼ ከመጣሁ በኋላ በደርግ መንግሥት ከአዋጁ ውጭ በቀላጤ የተወሰደብኝ ድርጅቴ የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን እንዲመለስልኝ የካቲት 22 ቀን 1987 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ አቤቱታ አቀረብኩ፡፡ ኤጀንሲው አቤቱታየን በመቀበል ለሦስት ዓመታት ያህል ጊዜ ወስዶ ከመረመረ በኋላ ከውሳኔ ሐሳብ ጋር ለሥራ አመራር ቦርድ በማቅረብ ቦርዱም ከአዋጁና ከመመርያው ጋር አገናዝቦ መጋቢት 30 ቀን 1990 ዓ.ም. በቃለ ጉባዔ ቁር 61 መሠረት የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን እንዳለ ሳይነጣጠል እንዲመለስልኝ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡

የኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ባሻህ አዝምቴ የሥራ አመራር ቦርዱ ድርጅቴን በመርህ ደረጃ እንደሚመልስልኝ የወሰነ መሆኑን በደንብ ቁጥር 20/ነ2/196/3709/90 ሚያዝያ 8 ቀን 1990 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ገልጸውልኛል፡፡ ማስረጃው በእጄም አለ፡፡ በቦርዱ ውሳኔው ቅር የተሰኘ ወገን በኖር በአዋጁ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 001/88 አንቀጽ 13.4 መሠረት ይግባኝ የማቅረብ መብት እንደሚሰጥ በተደነገገው መሠረት የቦርድ ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ በ60 ቀናት ጊዜ ውስጥ የቀረበ የይግባኝ ቅሬታ ባለመኖሩ የቦርዱ ውሳኔ እንደ ፀና ይገኛል፡፡ ይህ የቦርድ ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ ነው፡፡

ቀጥሎ ኤጀንሲው የድርጅቱን የንብረት ቆጠራ፣ የዋጋ ትመናና የሒሳብ ማጠቃለያ ዝርዝር እንዲሠራ አስደርጎ ዝርዝሩ ጥቅምት ወር 1991 ዓ.መ. ተሠርቶ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ በድርጅቱ አመላለስና ገንዘብ አከፋፈል በመለየት ሁለት አማራጮች አስቀምጧል፡፡

  1. የቀድሞ ባለሀብት ድርጅቱን ባለበት ሁኔታ ለመረከብ ፈቃደኛ ቢሆኑ ለመንግሥት መክፈል የሚገባቸው ብር 26.4 ሚሊዮን እንዲከፍሉ የሚል፤
  2. የቀድሞ ባለሀብት ድርጅቱን ባለበት ሁኔታ ለመረከብ ፈቃደኛ ባይሆኑ መንግሥት ሊከፍላቸው የሚገባቸውን ዋጋ 2.8 ሚሊዮን ተገምቷል የሚል ነው፡፡

እኔም ከቀረቡልኝ ከእነዚህ ሁለት አማራጮች መካከል አማራጭ አንድ በመቀበል ብር 26.4 ሚሊዮን ከፍዬ ድርጅቴን መረከብ እንደምችል ታኅሳስ 30 ቀን 1991 ዓ.ም. ፈቃደኛ መሆኔን በጽሑፍ በማረጋገጥ አቀረብኩኝ፡፡

በቦርድ ውሳኔ መሠረት ንብረቴን ለመረከብ በዝግጅት ላይ እያለሁ ከሦስት ቀናት በኋላ ጥር 3 ቀን 1991 ዓ.ም. በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ግጭት ሰበብ ምክንያት በማድረግ ንብረቴን እንዳልረከብ ተደርጎ ከአገር እንድወጣ ተደረገ፡፡ በሕጉ አግባብ እንዲመለስልኝ የተወሰነውን ፋብሪካ እንዳልረከብ ከአገር ሆን ተብሎ እንድወጣ ከተደረገም በኋላ ይኼው ድርጅቴን ከሌሎች 41 የመንግሥት ኢንተርፕራይዞች ጋር በጨረታ እንዲሸጥ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1992 ዓ.ም. ወጥቶ በዝግጅት ላይ እያለ የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባለው የቆየ መልካም ግንኙነት መሠረት ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስት አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በመነጋገር በእሳቸው በጎ ፈቃድ አማካይነት ድርጅቴን ከሽያጭ እንዲሰረዝ ተደርጎ እኔም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ንብረቴን እንድከታተል ተፈቅዶልኝ ነሐሴ 10 ቀን 1994 ዓ.ም. ተመልሻለሁ፡፡ ከተመለስኩ በኋላ በቦርዱ ውሳኔ መሠረት ንብረቴን እንድረከብ በተደጋጋሚ ጊዜ በአካልም ሆነ በጽሑፍ አቤቱታ ለኤጀንሲው፣ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያቀረብኩ ቢሆንም ድርጅቴን እንዳልረከብ ተደርጎ ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ እነሆ ለ18 ዓመታት ያህል በመንገላታት ላይ እገኛለሁ፡፡

ድርጅቴን እንዳይመለስ በኤጀንሲውም ሆነ በኢንዱትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እየተሰጡ ያሉ ምክንያቶች መንግሥት ሆነ ኅብረተሰቡ ሊገነዘበው እንዲችል፡-

  1. በቦርድ ውሳኔው ንብረታቸው እንዲመለስ ሳይሆን ብር 2.8 ሚሊዮን ካሳ እንዲከፍላቸው ነው የሚል፤
  2. መንግሥት በፋብሪካው ላይ ብዙ ገንዘብ ስላወጣበት ድርጅቱን ለሽያጭ ለጨረታ ሲያቀርብ እንደማንኛውም ሰው በጨረታ ከሚሳተፉ በስተቀር ንብረቱን ለመመለስ አይቻልም የሚሉ ናቸው፡፡

ሀቁና እውነታው ግን የኤጀንሲ ሥራ አመራር ቦርድ የወሰነው ውሳኔ ንብረቱ እንዳለ ሳይነጣጠል ለባሀብቱ እንዲመለስላቸው በሚል በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ሰጠ እንጂ ካሳ እንዲከፈል አልወሰነም፡፡ ካሳ እንዲከፈል የተሰጠ የቦርድ ውሳኔ የለም፡፡

ንብረቴን እንዲመለስልኝ ከወሰኑ ስድስት የሥራ አመራር ቦርድ አባሎች መካከል አንዱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ክቡር አቶ ሱፊያን አህመድ ናቸው፡፡ ካሳ እንዲከፈል በቦርድ እንደተወሰነ በማስመሰል የድርጅቴን ማኅደር ከኤጀንሲው ወስደው ለአሥር ዓመታት ያህል አቆይተው እንዲጓተት ካደረጉ በኋላም ሁኔታው ሕጋዊ እንዳልሆነ ተገንዝበው በደንብ ቁጥር በ208/ከካ/2005 በ23/05/2005 ዓ.ም. በተጻፈ ባለሀብቱ ካሳ እንዲቀበሉ በመንግሥት የተወሰነው ውሳኔ ጥረት ተደርጎ ስላልተቻለ በሚል ካሳ መከፈሉን ቀርቶ በኤጀንሲው ሕግና መመርያ በአገሪቱ ሕግ መሠረት መፍትሔና እልባት እንዲሰጥበት ሲሉ በአዳራሽ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በግልባጭ ለኤጀንሲው አሳውቀዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ካሳ መከፈሉን ቀርቶን ንብረቴን በሕግና በደንብ እንድረከብ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጻፈው መሠረት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መኮንን ማንያዘዋል ይህን ደብዳቤ መሠረት በማድረግ ካሳ ከመፈሉን ቀርቶ በኤጀንሲ መመርያና ደንብ እንዲሁም በአገሪቱ ሕግ መሠረት እልባትና መፍትሔ እንዲያገኝ በማለት በደንብ ቁጥር 02/27.20/18 የካቲት 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ለኤጀንሲው የገለጹ ሲሆን፣ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረ መስቀል ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ድርጅቶቼን በሕጉና መመርያ መሠረት እንዲመለስልኝ በደብዳቤ ከተገለጸላቸው በኋላ ንብረቴን እንዳልረከብ ምንም ምክንያት በሌለበት ሁኔታ የጻፉት ምላሽ አቶ ብርሃኔ ገብረ መድህን ለቀጣዩ ፋብሪካው ወደ ግል ለማዛወር በሚኖር ጨረታ እንደማናቸው ተወዳዳሪ ሊሳተፉ ከሚችሉ በቀር በኤጀንሲያችን ሊስተናገዱ የሚችሉበት ሌላ የሕግ አግባብ የሌለ መሆኑን በሚል በደንብ ቁጥር ተኤ-215/513/10 የካቲት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. በተጻፈ በራሳቸው ሥልጣን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

መንግሥት የአገርና የውጭ ባለሀብቶችን በኢትዮጵያ ገብተው በልማት እንዲሳተፉ ሲያደርግ እኔም እንደማንኛው ባለሀብት ድርጅቴን እንዳልረከብ ለምን ተነፈገኝ? እንዲሁም መንግሥት በልዩ ልዩ ምክንያት ከሕግ ውጭ የተወረሱና የተወሰዱ የግል ንብረት ወደ ግል ባለሀብት ማስተላለፉ እጅግ የሚያበረታታ ቢሆንም አንዱን ሰጥቶ ሌላውን መከልከሉ ተገቢ አይደለም፡፡

በቀድሞ በመንግሥት ተይዘው የነበሩ ድርጅቶች ወደ ግለሰብ እንዲዛወር ካደረጋቸው ፋብሪካ እንደ ምሳሌ ማየት ከተፈለገም የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ከ65 ዓመታት በላይ በመንግሥት እጅ በቆየበት ጊዜ በድጎማና በኪሳራ ላይ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት የት ደረጃ እንደደረሰ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ወደ ግለሰብ የተዛወሩ ድርጅቶች በለውጥ ደረጃ ላይ እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በመንግሥት እጅ ሆኖ ለ25 ዓመታት ያህል ማሽኑ በእርጅና ስለተዳከመ በቂ ንፁህ አልኮል ሊያመርት አቅም አጣ እየተባለ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር በቂ የምርት ሽያጭ አለማቅረቡ ግልጽ ነው፡፡ በዓመት የሽያጭ ምርቱ እያመረተ ያለው ከአንድ ቢሊዮን በታች ነው፡፡ ፍላጎትና አቅርቦት እጅግ በመራራቁ ምክንያት በአገሪቱ የገበያ ፍላጎት ማርካት አልቻለም፡፡ ድርጅቱ በአግባቡ ቢያዝ በዓመት የሽያጭ ውጤት ቢያንስ ከ3.5 እስከ 4 ቢሊዮን የሽያጭ ምርት ማከናወን የሚችል አቅም ያለው ነው፡፡ ድርጅቴን እንዲመለስ ከተወሰነ በኋላ በመንግሥት እጅ እንዲቆይ የተደረገበት ዋናው ምክንያት መንግሥት ነጋዴ ሆኖ መቀጠሉ ፍላጎቱ አይደለም፡፡ ድርጅቴን እንዳልረከብ በእንጥልጥል ማቆየቱን እጅግ አሳዛኝና ግፍ ነው፡፡

መንግሥት የልማት መንግሥት መሆኑን የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ በዕድገት ጎዳና መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት የድርጅቴን ጉዳይ ለመፍታት በቂ አቅምና ሥልጣን እንዳለው ምንም የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ከባዱን ችግር መፍትሔ እየሰጠ ሲሆን፣ ለአንድ ግለሰብ ያውም በግፍ ንብረቴ የተወሰደብኝ በሕጉ አግባብ እንደሌሎች ንብረታቸው እንዲመለስ እንደተወሰነላቸውና እንደተረከቡ ባለሀብቶች ድርጅቴን በውሳኔ መሠረት እንድረከብ ያለመደረጉ ግፍና በደል አሳዛኝ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ካሳ እንዲከፈል ሳይወሰን ካሳ እንዲከፈል የቦርዱ ሥራ አመራር እንደወሰነ ተደርጎ ድርጅቴን እንዳይመለስ በምክንያትነት ማስቀመጡና በዚሁ ምክንያት እኔን ማንገላታቱና መፍትሔ ያለመስጠቱ ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ ኤጀንሲው የድርጅቴ ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጥበት ለረዥም ዓመታት በማቆየቱ በቦርዱ ውሳኔ መሠረት መፍትሔና እልባት እንዲሰጥኝ በቅርቡ ጊዜ ለተቋቋመው ለመንግሥት የልማት ድርጅት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አቤቱታ ባቀርብም መፍትሔ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም፡፡

ኤጀንሲ በአዋጅ ቁጥር 110/87 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ድርጅቶቼ በቀላጤ ደብዳቤ መወሰዱን አረጋግጦ መጋቢት 30 ቀን 1990 ዓ.ም. የወሰነውን ውሳኔ በአፈጻጸም መመርያ አንቀጽ 9.6 መሠረት የመጨረሻ የፀና የማይለወጥ ውሳኔ ሆኖ እያለ 17 ዓመታት ያህል መጉላላቴ የመንግሥት ፍላጎትና ዓላማ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም እልባት ሳይሰጥበት ለ19 ዓመታት ያህል ግፍ ተፈጽሞብኝ ሰሚ ባለማግኘቴ ምክንያት መንግሥት በደሌን ተገንዝቦ መፍትሔና እልባት ይሰጥልኝ ዘንድ እጠይቃለሁ፡፡

ከብርሃኔ ገብረ መድህን ሀብቱ፣

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...