ከአሥር ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌላው ጊዜ በተለየ ከፍተኛ የሲሚንቶ እጥረት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል የነበረው ክፍተት የሲሚንቶ ዋጋን በከፍተኛ ደረጃ በማናሩ፣ ለግንባታ ኢንዱስትሪው እንቅፋት እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡ በወቅቱ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ይሸጥበት የነበረው ዋጋ በዓለም ከፍተኛው የመሸጫ ዋጋ እንደነበር ይነገራል፡፡
የችግሩ አሳሳቢነት በአገሪቱ ፓርላማ ሳይቀር እንደ አገራዊ አንገብጋቢ ጉዳይ ሲመከርበት እንደነበርም ይታወሳል፡፡ አገሪቱ እያካሄደች ካለችው የግንባታ ሥራዎች አንፃር የተፈጠረው ክፍተት የግንባታ ዘርፉን ዕድገት ሊገታ እንደሚችል በመታመኑ፣ የሚፈለገውን የሲሚንቶ መጠን ለማሟላት አማራጩ ከውጭ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ ከሌሎች የገቢ ሸቀጦች በተለየ ለሲሚንቶ በፍራንኮ ቫሉታ ተፈቅዶ እንዲገባ መደረጉ በወቅቱ የነበረውን አሳሳቢ ችግር ሊያመለክት ይችላል፡፡ ይህ አማራጭ ግን ዘላቂ መፍትሔ አልነበረም፡፡
ችግሩን ለዘለቄታ ለመፍታት ሲሚንቶ ፋብሪካዎችን መገንባት፤ ያሉትንም ወደ ማስፋፊያ እንዲገቡ ማድረግ ግድ መሆኑ ይታሰብ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ሦስት ግለሰቦች፣ ዛሬ በአገሪቱ የአክሲዮን ኩባንያዎች ምሥረታ ታሪክ ውስጥ በርካታ ባለአክሲዮኖችን በማሰባሰብ ተጠቃሽ የሆነውን ሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበርን ለመፍጠር የሚያስችል ጥንስስ የጠነሰሱት፡፡
አቶ ግዛው ተክለ ማርያም (ኢንጂነር)፣ አቶ መስፍን አቢ (ኢንጂነር) እንዲሁም አቶ እስክንድር ደስታ የሲሚንቶ ፋብሪካ ለማቋቋም በማሰብ የአክሲዮን ኩባንያ የማደራጀት ሥራቸውን አንድ በማለት የጀመሩት በ2001 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከሥራው ጋር ያላቸውን ቅርበት ተጠቅመው ሐሳቡን ለቅርብ ወዳጆቻቸው በማቅረብ ከእነርሱ ጋር 30 ሆነው ሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ኩባንያ እንዲመሠረት አደረጉ፡፡
በወቅቱ እያንዳንዳቸው ሃያ ሺሕ ብር በማዋጣት ኩባንያውን መሥርተው ወደ አክሲዮን ሽያጭ የገቡት ሦስቱ ግለሰቦች፣ የጀመሩት ጥምረት አድጎ በአሁኑ ወቅት 16,500 ባለአክሲዮኖችን በሐበሻ ሰሚንቶ ሥር ማሰባሰብ ችለዋል፡፡ ሁለት የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎችንም ወደ ኋላ ላይ አካተዋል፡፡ በዚህ መንገድ ሲጓዝ የቆየው አክሲዮን ማኅበሩ፣ በዘጠነኛው ዓመቱ ረቡዕ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ማምረቻ ፋብሪካውን ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡ የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፋብሪካው በተገነባበት ሆለታ ከተማ ተገኝተው መርቀውታል፡፡
በዓመት 1.4 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካው፣ ዘጠኝ ዓመታትን ከጠበቀ በኋላ ለሥራ ብቁ ይሁን እንጂ፣ ዓላማው ግን ፋብሪካው በሦስት ዓመት ቢበዛ በአራት ዓመት ውስጥ ማምረቻ ፋብሪካውን ዕውን ማድረግ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደታሰበው ሊሆን አልቻለም፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን አቢ እንደሚገልጹት፣ ዛሬ ፋብሪካው ዕውን ይሁን እንጂ ብዙ ውጣ ውረድ ማለፍ ነበረበት፡፡ ሲጀመር በ300 ሚሊዮን ብር ለመገንባት የታሰበው ፋብሪካ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የኢንቨስትመንቱ ወጪ እያሻቀበ እንደመጣ ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ተጨማሪ ካፒታል ለማሰባሰብ የተደረጉ ጥረቶችም ጊዜ ወስደውበታል፡፡ ትልቁ ፈተና ግን ካፒታሉ ሲያድግ ገንዘብ ለማግኘት የነበረው እልህ አስጨራሽ ጥረት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ፕሮጀክቱ አዋጭ መሆኑ ባይጠረጠርም፣ በጉዞው ሒደት አንዳንድ የአክሲዮን ኩባንያዎች ቀውስ ውስጥ መግባታቸው በሐበሻ ሲሚንቶ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደራቸው፣ ተጨማሪ አክሲዮን ማሰባሰቡ ፈተና ሆኖበት እንደነበር አቶ መስፍን ይገልጻሉ፡፡
በሦስት ዓመት ዕውን ይሆናል የተባለውም ፕሮጀክት ዘጠኝ ዓመት ለመውሰድ ተገደደ፡፡ ይህን የተረዱ አንዳንድ ባለአክሲዮኖችም ገንዘባችን ተበላ እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ሰልችተው ገንዘባቸውን ያስመለሱና አክሲዮኖቸውን ያስተላለፉም አሉ፡፡
በአንዳንድ ወገኖች ደግሞ ብዙ ሲባልለት የነበረው የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር ከያዘው ባለአክሲዮኖች ብዛት አንፃር ውጤት ካላመጣ የአክሲዮን ኩባንያ መሥረታ በሕዝቡ ዘንድ ወደፊት ተዓማኒነት ያጣል የሚል ፍራቻም አሳድሮ ነበር፡፡
ፋብሪካው በተቀመጠለት ጊዜ ውስጥ ዕውን ላለመሆኑ ከሚጠቀሱ ችግሮች አንዱ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል የገጠመው ችግር እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ ባንኩ የፈቀደውን ብድር በግማሽ መቀነሱ ብቻም ሳይሆን፣ የተፈቀደውንም መጠን አዘግይቶ መልቀቁ የፕሮጀክቱን ወጪ በ30 ሚሊዮን ዶላር እንዲጨምር ሊያደርግ ችሏል ተብሏል፡፡ አቶ መስፍን ኩባንያውን ለዚህ ወጪ የዳረገው የብድሩ መዘግየት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ካፒታሉን ለመሙላት የነበረበት ፈተና ከፍተኛ እንደነበር የሚገልጹት አቶ መስፍን፣ ካፒታሉን ለማሳደግ ከነባር ባለአክሲዮኖች የሚፈለገውን ማግኘት ባለመቻሉና አማራጭም በማጣቱ የውጭ ኩባንያዎች ገብተውበት፣ ከፍተኛውን የ53 በመቶ ድርሻ ሁለት የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች በበላይነት እንዲይዙት ግድ ሆኖበታል ብለዋል፡፡ እንደ ኃላፊዎቹ ገለጻ፣ በወቅቱ ለኩባንያው ህልውና የነበረው አማራጭ ይኸው ብቻ ነበር፡፡ አጠቃላይ የባለቤትነት ድርሻው በኢትዮጵያውያን ቢያዝ ምኞታቸው ነበር፡፡
ከዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ ዕውን መሆኑ ግን በጣሙን እንዳስደስታቸው ይናገራሉ፡፡ አጠቃላይ የፋብሪካው ግንባታ 3.24 ቢሊዮን ብር ወይም 155.26 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በቀን 3,000 ቶን ክሊንከርና 4,500 ቶን ፖርትላንድ እና ፖዞናላ የተባሉ የሲሚንቶ ዓይነቶችን ያመርታል፡፡
ይህ ፋብሪካ ለኢንቨስትመንቱ ካዋለው ገንዘብ ውስጥ ከኮሜሳው የንግድና ልማት ባንክ (የቀድሞው ፒቲኤ ባንክ) የ50.1 ሚሊዮን ዶላር ብድር፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክም የ690 ሚሊዮን ብር በመበደር ያገኘው ሲሆን፣ ቀሪውን የደቡብ አፍሪካ ባለአክሲዮኖች፣ ፕሪቶሪያ ፓርትላንድ ሲሚንቶ ፋብሪካና ኢንዱስትሪያል ዴቨሎፕመንት ኮርፖሬሽን የተባሉት ሁለት ኩባንያዎች ያዋጡት ገንዘብ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሆለታ ከተማ የተገነባው ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ 500 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡ ፋብሪካውን የመረቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንደገለጹት፣ ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ የአገሪቱን የሲሚንቶ ምርት መጠን ከማሳደግ በላይ ከ16 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን አቀናጅተው የፈጠሩት፣ በሌሎች ዘርፎችም በተመሳሳይ መንገድ መሥራት ከተቻለ ውጤት እንደሚገኝ ማሳያ ነው፡፡
ከአሥር ዓመታት በፊት የአገሪቱ ዓመታዊ ሲሚንቶ ምርት መጠን 1.8 ሚሊዮን ቶን እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ግን የሐበሻ ሲሚንቶን ጨምሮ የአገሪቱ የሲሚንቶ ምርት 16.5 ሚሊዮን ቶን ላይ መድረሱ ከፍተኛ እመርታ ለማሳየቱ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ፣ በዓመት 27 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ለማምረት የተያዘውን ግብ ለማሳካት በዕለቱ የተመረቀው የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ መስፍን ከሆነ፣ ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሲሚንቶ አምራችነት ብቻ ሳይወሰን ተጨማሪ የሲሚንቶ ውጤቶች ማምረቻዎችን በማምረት ይቀጥላል፡፡ ለዚህም የኩባንያው ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አለመዘጋቱንና ቀጣይ ሥራዎችንም እንደሚያስፋፋ ጠቁመዋል፡፡
የሲሚንቶ ፋብሪካውን ግንባታ ያካሄደው የቻይናው ኖርዘን ሔቪ ኢንዱስትሪያል ግሩፕ የተባለ ኩባንያ መሆኑ ታውቋል፡፡ አጠቃለይ የፋብሪካውን ግንባታና የማሽነሪ ተከላ በማካሄድ የተዋዋለበት ዋጋም 79 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡