የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሊመክሩ እንደሆነ ታወቀ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚመራ የልዑካን ቡድን ከረቡዕ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በግብፅ ይፋዊ ጉብኝት የሚያደርግ ሲሆን፣ ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በሁለትዮሽና በአካባቢ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር የተላከው መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱን የሚያደርጉት ከግብፅ አቻቸው ሳሜህ ሹክሪ በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት ነው።
ኢትዮጵያ በቅርቡ የመሠረተ ድንጋይ የተቀመጠበት ስድስተኛ ዓመቱ የተረከበውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረች አንስቶ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት አወዛጋቢ ጉዳዮች እየገጠሙት ሲሆን፣ ሱዳንን ጨምሮ በግድቡ ላይ የሚካሄደው የሦስትዮሽ ምክክር አሁንም ድረስ አልተጠናቀቀም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ በተከሰተው ሁከትና አለመረጋጋት ጀርባ የግብፅ አንዳንድ ተቋማት እጅ ስለመኖሩ የኢትዮጵያ መንግሥት መክሰሱ ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብፅ ለጠየቀው ማብራርያ አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘቱም አይዘነጋም። እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ በደቡብ ሱዳን የግብፅ ወታደራዊ ኃይል እንዲሠፍር ደቡብ ሱዳን ተስማማች የሚል ያልተረጋገጠ ወሬ መናፈሱ ይታወሳል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአቻቸው ጋር በእነዚህና በሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮችና በአካባቢው ደኅንነት ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮ-አልጄሪያ የጋራ ኮሚሽን አራተኛው ስብሰባ ከሚያዚያ 4 እስከ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በአልጀርስ ተካሂዶ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአልጄርያ አቻቸው ሚስተር ራምታኔ ላማምራ ጋር በጋራ ስብሰባውን መምራታቸው ታውቋል።
ኢትዮጵያና አልጄርያ እ.ኤ.አ በ2013 የጋራ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መፈራረማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ እስከ ዛሬ ከ25 በላይ ስምምነቶች መፈራረማቸው ተገልጿል።
ሚኒስትሮቹ ከዚህ በፊት በተፈረሙ ስምምነቶች አፈጻጸም ላይ መወያየታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በዚህ ስብሰባም በንግድ፣ በዕፅዋት እንክብካቤና በሚዲያ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ሦስት ስምምነቶች መፈራረማቸው ታውቋል።