Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርበመልካም አስተዳደር ዕጦት ዓመት የዘለቀ የተበዳዮች አቤቱታ

በመልካም አስተዳደር ዕጦት ዓመት የዘለቀ የተበዳዮች አቤቱታ

ቀን:

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገብረ መስቀልና የብሥራት ኤፍኤም 101.1 ሬድዮ ጣቢያ፣ ግንቦት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ከ12፡30 እስከ 2፡00 ባለው ጊዜ ውስጥ በተሰራጨውና ‹‹ምንጊዜም ጊዮርጊስ›› በተሰኘው የሬድዮ ፕሮግራም ወቅት ለፈጸሙብን የማንቋሸሽ ተግባር የብሮድካስት ባለሥልጣን ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ተከብሮ በሕጉ መሠረት እንድንስተናገድ ሰኔ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ከዚህ በታች ስማችን የተመለከተው ሰዎች አቤቱታ አቅርበን ነበር፡፡

መሥሪያ ቤቱም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ሐምሌ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በቁጥር 4016/2140 በተጻፈ ደብዳቤ፣ ብሥራት ሬዲዮ ጣቢያ የእኛን ምላሽ በተመጣጣኝና በተመሳሳይ ሰዓት እንዲያስተናግድ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሬዲዮ ጣቢያውም ሆነ የክለቡ አመራሮች ውሳኔውን ባለመቀበል እንቢተኝነታቸውን በጽሑፍ በማረጋገጣቸው፣ እስከዛሬ ድረስ የባለሥልጣኑ ውሳኔ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

እንደውም የስፖርት ማኀበሩ ቅሬታችንን በሬዲዮ ፕሮግራሙ ወቅት እንዲያስተናግድ በጽሑፍ ተጠይቆ ከሦስት ጊዜ በላይ ውሳኔውን እንደማይቀበልና እንደማያስተናግድ ማረጋገጫ መስጠቱን የሬድዮ ጣቢያው ታኅሳሰስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥር አያ/1609/09 በተጻፈ ደብዳቤ ለባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በበኩላችን ሬድዮ ጣቢያው ከክለቡ ጋር ያለውን ኮንትራት እንደሚሰርዝ ለባለሥልጣኑ ያሳወቀበትን ደብዳቤ ቅጅ ደርሶን ሐሳባችንን ለመስጠት እንድንችል ታኅሳስ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠይቀን ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ መሥሪያ ቤቱ ሊያስተናግደን ባለመቻሉ እየተጉላላን እንገኛለን፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግራ በሚያጋባና በማይታመን አሠራር ባለሥልጣኑ የሰጠውን ውሳኔ አላስተናግድም በማለት እንቢተኝነቱን ለገለጸው የክለቡ አመራር ጥያቄን በመቀበል በሌላ ሬድዮ ጣቢያ ፕሮግራሙን እንዲያሰራጭ ፈቃድ ሰጥቶ ይኸው ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ይህ ተግባር መንግሥት ለመልካም አስተዳደር ዕጦት የጥልቅ ተሃድሶ ጥሪ ለመሥሪያ ቤቶችና ለዜጎች ባደረገበት አፍላ ወቅት መፈጸሙ እጅግ አሳዝኖናል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን ለማስከበርና አቤቱታችን ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ እስከ መጨረሻው የበላይ አካል በመሔድ ትግላችንን እንድንቀጥል ሁኔታው አስገድዶናል፡፡ ስለዚህም፡-

1ኛ. ብሥራት ሬድዮ ጣቢያና የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለባለሥልጣኑ የጻፏቸው ደብዳቤዎች ቅጅ እንዲሰጡን፤

2ኛ. መሥሪያ ቤቱ የራሱን ውሳኔ ባልታወቀና ወደፊት በሚጣራ ምክንያት በመጣስ የአገሪቱን ሕግ አላከብርም ምንም አታመጡም በሚያስብል መልኩ እንቢተኛነቱን የገለጸው አካል ያዘጋጀው ፕሮግራም በሸገር 102.1 ሬድዮ ጣቢያ እንዲሰራጭ ፈቃድ በመስጠት አስተናግዷል፡፡ ይህ አሠራር ያጠፉ አካላት ከጥፋታቸው እንዲታረሙ ከማስተማር ይልቅ በተቃራኒው የሰውን ሰብዕናና ነፃነት ወይም ሥነ ምግባርን የሚፃረሩ ይዘቶች ያላቸው ፕሮግራሞች እንዳይተላለፉ የሚደነግገውን የብሮድካስት አዋጅ ቁጥር 533/99 አንቀጽ 30/4ሀ እንዲጥሱ፣ ለሕግ ተገዢ እንዳይሆኑ፣ አዋጆችና መመሪያዎችን በማስፈጸም ሕዝብን ለማገልገል የተቋቋሙትን የመንግሥት ተቋማት የሚገባቸውን ክብር እንዲነፈጉ የሚያበረታታ ለመሆኑ ማንም ቀና ህሊና ያለው የሚፈርደው ነው፡፡

ይህን ሁኔታ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር ‹‹በሕዝብ ሚዲያ›› ተዋርደን፣ ተዘልፈን፣ በሐሰትና ሚዛናዊ ባልሆነ የግለሰቦች መግለጫ ስማችን ጠፍቶ ሳለ፣ ይባስ ብሎ ምላሽ የመስጠት መብታችን በግለሰቦች በአደባባይ ተረግጧል፡፡ ጉዳዩን ለማረም የሚመለከተው መሥሪያ ቤት የማያሻማውን የአዋጁን ድንጋጌ መሠረት አድርጎ ራሱ የወሰነውን ውሳኔ ለ11 ወራት ተግባራዊ ባለማድረጉ ሐዘናችንን አባብሶታል፡፡ ያስላለፈውን ውሳኔ ሕጉን አክብሮ ከመተግበር ይልቅ ከጣቢያው ጋር ያለውን ውል መሠረዝ የመረጠው የክለቡን አመራር ጥያቄ ተቀብሎ ፕሮግራሙን በሌላ ሬድዮ ጣቢያ እንዲያሠራጭ ፈቃድ መስጠቱም በደላችንን እጥፍ ድርብ አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም በባለሥልጣኑ ላይ የነበረን እምነት እጅጉን ሸርሽሮታል፡፡ በአቤቱታችን ዙሪያ የተቀነባበረ ሴራ አለ ብለን በእርግጠኝነት ለመናገር ብንቸገርም ምክንያትን መሠረት ያደረገ ጥርጣሬ እንዳሳደረብን ግን ሳንደብቅ ማሳወቅ እንፈልጋለን፡፡

የሆነው ሆኖ የሕግ የበላይነት ለድርድር የማይቀርብ፣ በኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ላለው የዴሞክራሲ ሥርዓት የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን አበክረን ለማስገዘንብ እንወዳን፡፡ ማንም ሰው ሀብቱንም ሆነ ታዋቂነቱን ተመክቶ ከሕግ በላይ መሆን አይችልም፡፡ እንዲሆንም ሊፈቀድለት አይገባም፡፡

ስለሆነም በደላችን ያለ ውሳኔ ተንጠልጥሎ እንዲቆይ በመደረጉ አድራጎቱን ስለምንቃወምና ስለማንቀበል ይህንኑ ለሚመለከታቸው የበላይ አካላትና ለመንግሥት ለማቅረብ እንድንችልና መሥሪያ ቤቱ ለአቤቱታችን የማያዳግም አፋጣኝ ምላሽ በጽሑፍ እንዲሰጠን አጥብቀን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

(አቶ ዳንኤል ካሳ፣ አቶ ተስፋ ነጋሽ፣ አቶ ታደሰ መሸሻ፣ አቶ አንተነህ ፈለቀ፣ እና አቶ ሥዩም ተፈሪ)

* * *

ሥነ ምግባር የስኬት ነጸብራቅ ነውና እንንከባከበው!

ሥነ ምግባር የአንድ ሰው እምነት፣ ስብዕናና እሴቶች ድምር ውጤት ነው፡፡ በባህርያችንና በተግባራችንም ይገለጻል፡፡ እጅግ ውድ ከሚባል ጌጣጌጥ በላይ ልንጠብቀው ይገባል፡፡ አሸናፊ ለመሆን ሥነ ምግባር ወሳኝነት አለው፡፡ ጆርጅ ዋሽንግተን በአንድ ወቅት ‹‹የአንድ ታማኝ ሰው ጽናትና ሰናይ ምግባራት ይኖሩኝ ዘንድ ሁሌም እተጋለሁ፤›› ብሏል፡፡ የታሪክን እሽክርክሪት የሚቆጣጠረው የሕዝብ አስተያየት (ድምፅ) ሳይሆን የመሪው ሥነ ምግባርና ባህርይ ነው፡፡ ወደ ስኬት የሚደረግ ጉዞ ብዙ እንቅፋቶች ቢኖሩትም በእነዚያ እንቅፋቶች ተሰናክሎ ላለመውደቅ ሰናይ ምግባርና ከፍተኛ ጥረት አስፈላጊ ናቸው፡፡ ተገቢ ባልሆነ ትችት ተሽመድምዶ ላለመውደቅ ጠንካራ ሆኖ መገኘት ግድ ይላል፡፡

አንድ ሰው በስኬት ከፍ ከፍ ባለ ቁጥር እሱን ጎትቶ ለማውረድ የሚሠለፉ በርካቶች ናቸው፡፡ በተራራ አናት ላይ የቆመ ሰው እዚያ ላይ የደረሰው እንደሁ በድንገት (በዕድል) ሳይሆን፣ ብዙ ተጋግጦና ታግሎ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በየትኛውም የሙያ መስክ ውጤታማ የሆኑ ሰዎች ስኬታማ ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ መንቋሸሻቸው የተለመደ ነው፡፡ ማንጓጠጥ ሥራ የማይሠሩ ሰዎች ባህርይ ነው፡፡ እጃቸውን አጣምረው በመቀመጥ የሚሠራውን ሰው ምንና እንዴት መሥራት እንዳለበት ሊነግሩት ይሞክራሉ፡፡ ዘለፋዎች ከግባችሁ እንዲያደናቅፏችሁ፡፡ አትፍቀዱላቸው፡፡ ለዘለፋና ለሒስ እጅ አትስጡ፡፡ ወቀሳን በመፍራት ሥራ ከመሥራት የሚታቀቡ ይኖራሉ፡፡  እየሠራችሁ በሄዳችሁ ቁጥር ግን ብዙ ተቺና ወቃሽ ሊያጋጥማችሁ ይችላል፡፡ ማንም ሰው መተቸትን አይወድም፡፡ ሆኖም ከቅን ልቦና ከሚመነጭ ሒስ ራሳችንን የምናሻሽልበትን ትልቅ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን፡፡ በትችት ላለመጎዳት ጠንካራ ልብ እንደሚያስፈልገን ሁሉ ጠቃሚ ትችትን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግም ጠንካራ ስብዕናን ይጠይቃል፡፡ የስኬታማ ሰው መለያም ይኼ ነው፡፡ ስኬታማ ሰው ራሱን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ተገቢ የሆነውንና ያልሆነውን መለየት አያዳግተውም፡፡ ስኬታማ ሰዎች ተዓምራትን አይጠብቁም፡፡ ቀላሉን አቋራጭ መንገድም አይሹም፡፡ ፍላጎታቸው እንቅፋቶቻቸውን የሚወጡበት ብርታትና ጥንካሬ ነው፡፡ የሚለኩት ምን ያህል እንደቀራቸው እንጂ ምን ያህል እንዳጡ አይደለም፡፡ ምኞት ብቻውን ዕውን አይሆንም፡፡ ምኞት ዕውን የሚሆነው ወይም ለውጤት የሚበቃው ከፅናትና ከጥረት ጋር ነው፡፡ ፀሎትም ቢሆን ተሰሚነት የሚኖረው ወኔ በተሞላበት ድርጊት ሲታጀብ ነው፡፡ ወኔና ሥነ ምግባር ለስኬት አስፈላጊ ቅመሞች ናቸው፡፡ ባህርይ በተለይም ፍትሐዊነትና ሀቀኝነት ያለ ወኔ ብቻውን ውጤታማ አይሆንም፡፡ ወኔም እንደሁ ያለ ባህርይ ከግብ አይደርስም፡፡ ስለዚህ መልካም ሥነ ምግባር ወኔና ጥረት ተጣምረው ስኬታማ ስለሚያደርጉን ይህ እንዲኖረን እንትጋ፡፡

(ተክልዬ ጀማነህ፣ ከምሥራቅ አዲስ አበባ)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...