በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ማብሰሪያ የሆነው ችቦ በዋና ዋና ከተሞች ከተዘዋወረ በኋላ መድረሻው ባዘጋጁ ከተማ ላይ እንዲያደርግ ተወሰነ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ችቦ›› አዘጋጅ ክልል ከመድረሱ በፊት በቅብብሎሽ ሒደት በበርካታ ከተሞች እንዲዞር መደረጉ፣ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋጋሪነቱን በኅብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ችቦ ማዛወር የሚጀመረው ቀጣዩን 6ኛው ጨዋታዎች አዘጋጅ በሆነችው ትግራይ ነው፡፡ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በሳምንቱ መገባደጃ ከክልሉ መስተዳድርና ስፖርት ተቋም ጋር ታውቋል፡፡
የኦሊምፒዝምን መርህ መሠረት ያደረገው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ የተጀመረው በ1999 ዓ.ም. ሲሆን፣ እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ አምስት ጊዜ ተካሂዷል፡፡ የመጀመርያዎቹ ሁለቱን አዲስ አበባ፣ ሦስተኛውን አዳማ፣ አራተኛውንና አምስተኛውን ባሕርዳር እና ሐዋሳ ማስተናገዳቸው ይታወቃል፡፡