Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፌደራል ፖሊስ ጣሊያናዊውን ባለሀብት አስሮ እንዲያቀርብ ታዘዘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በከባድ የማታለል ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉትን የሳፌት ኤስፒኤ (ጣሊያን) ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሰርጂዮ ዴሚ አስሮ እንዲያቀርብ ታዘዘ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው ትዕዛዝ፣ ሚስተር ሰርጂዮ ዴሚ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ ባለመፈጸማቸው ታስረው ይቅረቡ ሲል አዟል፡፡

ሉባር ኢንዱስትሪ የተባለው አገር በቀል ኩባንያ ያቀረበው ክስ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ 15 ዓመት እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲጠሩ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ተከሳሽ ባለመቅረባቸው በሌሉበት ክሱ ታይቷል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ሚያዝያ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፣ ተከሳሹ በሌሉበት የጥፋተኛነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በፍትሐ ብሔር በተመሠረተው ክስ ስምንተኛው የፍትሐ ብሔር ችሎት ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡  

ክሱን የመሠረተው አገር በቀል ኩባንያ የሆነው ሉባር ኢንዱስትሪ ነው የክሱ መነሻ ሉባር ኢንዱስትሪ በተፈቀደለት የውጭ ምንዛሪ ሌተር ኦፍ ክሬዲት በመክፈት፣ የማምረቻ ማሽኖችና ጥሬ ዕቃ ከጣሊያኑ ኩባንያ ሳፌት ኤስፒኤ ግዢ ፈጽሟል፡፡ ነገር ግን ሳፌት ኤስፒኤ መላክ የነበረበትን ማሽኖች ሳይልክ የላከ በማስመሰል፣ ሐሰተኛ ሰነዶችን ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በማቅረብ ዲክላራሲዮን እንዲሞላ በማድረግ፣ ትክከለኛ ያልሆነ ዕቃ እንዲገባ አድርጓል ተብሎ ነው፡፡

በዚህም ሉባር ኢንዱስትሪ 43,811.50 ዩሮ አጥቻለሁ በማለት ክስ መሥርቷል፡፡ ሉባር ይህንን ክስ በፍትሐ ብሔርና በወንጀል መሥርቷል፡፡

ሉባር ይህንን ክስ ከመመሥረቱ በፊት ጉዳዩን ወደ ቀድሞ ፍትሕ ሚኒስቴር ወስዶት ነበረ ሚስተር ሰርጂዮ ዴሚ አገር ውስጥ ስለነበሩ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሏቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የጣሊያን ኤምባሲ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 4 ቀን 2012 በጻፈው ደብዳቤ ኃላፊነት እንደሚወስድ በመግለጽ እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በወቅቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ ማስተር ሰርጂዮ ዴሚ የማያገለግል ማሽን ሸጠዋል ተብለው ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን የጣሊያን ኤምባሲ በደብዳቤ እንደገለጸለት አስታውሶ፣ ግለሰቡ ያለባቸው የጤና ችግር ከግምት ውስጥ እንዲገባና ኤምባሲው ኃላፊነት እንደሚወስድ በመግለጽ እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡

በዚህ መሠረት ፖሊስ በኤምባሲው ዋስትና ተጠርጣሪውን የለቀቀ ሲሆን፣ ተጠርጣሪው ወዲያው ከአገር ወጥተዋል፡፡

 በአሁኑ ወቅት በፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ የተባሉት ሚስተር ሰርጂዮ ዴሚ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡    

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች