Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዋና ኦዲተር በጂቡቲና በደረቅ ወደቦች የተከማቹ ንብረቶችን የተመለከተ ምርምራ እንዲያከናውን ተወሰነ

ዋና ኦዲተር በጂቡቲና በደረቅ ወደቦች የተከማቹ ንብረቶችን የተመለከተ ምርምራ እንዲያከናውን ተወሰነ

ቀን:

  • የምርመራ ውጤቱ የሚለያቸው አጥፊዎች በሕግ ይጠየቃሉ
  • በሜቴክና በስኳር ኮርፖሬሽን መካከል ያለው አለመግባባት እንዲመረመር ታዘዘ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በጂቡቲና በደረቅ ወደቦች የተከማቹ ንብረቶችና ባለቤቶች ላይ የኦዲት ምርመራ እንዲያከናውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ውሳኔ አሳለፉ፡፡ የምርመራ ውጤቱ በተጠያቂነት የሚለያቸው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ ፓርላማው ለመንግሥት እንደሚያቀርብ አፈ ጉባዔው አስታውቀዋል፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ ውሳኔያቸውን የተናገሩት የፓርላማው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአፋር ክልል በሚገኙ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ላይ ያደረገውን የመስክ ምልከታ አስመልክቶ፣ ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ምልከታውን ያደረገው በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት የሰመራ ደረቅ ወደብ፣ በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የተንዳሆ ከሰም የስኳር ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም በአዋሽ ወልዲያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት ላይ ምርመራ ተደርጓል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመስክ ምልከታው ወቅትም በውርስ ከጅቡቲ ወደብ ለኢትዮጵያ የተላለፉ በርካታ ንብረቶች በሰመራ ደረቅ ወደብ ተከማችተው ለብልሽት እየተዳረጉ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው በትዝብቱ አስፍሯል፡፡

የተከማቹ የእርሻ መሣሪያዎች፣ ማቀዝቀዣዎችና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ለትልልቅ ግንባታዎች የሚያገለግሉ ብረቶች፣ ለውኃ ሥራዎች የሚያገለግሉ ቱቦዎች፣ ለመንገድ ግንባታ ሊውል የሚችል ሬንጅ፣ የቤት መኪናዎች፣ ለፋብሪካ ግብዓትነት የሚውሉ ኬሚካሎች በደረቅ ወደቡ ለዓመታት ተከማችተው እንደሚገኙ በፎቶግራፍ የተደገፈ ማስረጃ ቋሚ ኮሚቴው አቅርቧል፡፡

ከእነዚህ ንብረቶች መካከል አምስት የመንግሥት ድርጀቶች በባለቤትነት ተጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ትምህርት ሚኒስቴር በ17 ኮንቴይነሮች የታሸገ ንብረት ቢኖረውም፣ ከሁለት ዓመት በላይ በሰመራ ወደብ ተከማችቶ ይገኛል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ከሰመራ ውጪ ለተመሳሳይ ጊዜ ያልተነሱ አሁንም በደረቅ ወደቦች የሚገኙ 35 ኮንቴይነሮች እንዳሉት የቋሚ ኮሚቴው ምርመራ ያሳያል፡፡ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ደግሞ በቃሊቲና በሞጆ 27 ኮንቴይነሮች ለ572 ቀናት ሳይነሱ ተከማችተው እንደሚገኙ ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪ ኃይል ስድስት ኮንቴይነሮች ለ121 ቀናት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ንብረቶች ለ61 ቀናት በሞጆ ደረቅ ወደብ ተከማችተው እንደሚገኙ የቀረበው ሪፖርት ይገልጻል፡፡

በምርመራ የተገለጹትን ግኝቶች አስመልክቶ ምላሽ ለመስጠት የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ምክትል ሥራ አስፈጻሚና የደረቅ ወደብና ተርሚናል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወት፣ ችግሩ ከድርጅታቸው አቅም በላይ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ድርጅት የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ሲሆን፣ በሰመራ ወደብ የሚገኙት አብዛኞቹ ዕቃዎች ባለቤቶች በራሳቸው ምርጫ በዩኒ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓት ያስመጧቸውና ጂቡቲ ላይ ተከማችተው የአገሪቱ መንግሥት ሊወርሳቸው ሲል በድርድር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሥልጣን ሳይኖረው በመንግሥት ትዕዛዝ እነዚህን ንብረቶች ለባለቤቶቹ እንዲያስረክብ ወይም በሐራጅ እንዲሸጥ መታዘዙን አስረድተዋል፡፡

ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ጥሪ ቢደረግም የ13 ኮንቴይነሮችና 16 ተሽከርካሪዎች ባለቤቶች ብቻ መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ወደ ሐራጅ ሽያጭ ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ ንብረቶች ባለቤቶች መካከል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል፡፡

የድርጅቱ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራ በበኩላቸው፣ ችግሩ ያለው በዩኒ ሞዳል የሚገባው ንብረት ላይ መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ወቅትም በጂቡቲ ወደብ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የተከማቹ በርካታ ንብረቶች እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓት የሚገቡ ንብረቶችን ድርጅቱ ቢበዛ በስምንት ቀናት ውስጥ ከጂቡቲ አንስቶ በሞጆና በሌሎች ደረቅ ወደቦች ቢያቀርብም፣ አስመጪዎች ግን በሚሰጣቸው የሁለት ወራት ገደብ ውስጥ ንብረታቸውን እያነሱ አለመሆኑንም  ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መነሳት ያልቻሉ 8,755 ኮንቴይነሮች በደረቅ ወደቦች በዋናነትም በሞጆ ደረቅ ወደብ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 7,725 የሚሆኑት የግል ባለሀብቶች ያስመጧቸው ሲሆን፣ 1,030 የሚሆኑት ደግሞ በመንግሥት ድርጅቶች የገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ችግሩ ያለው የንግድና የፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ ነው፤›› የሚሉት አቶ መስፍን፣ መንግሥት ትኩረቱን በዚህ አካባቢ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ስለተገኘ ብቻ አስመጪዎች ዕቃ እንዲይዙ ወይም ገበያ ሳይኖር የውጭ ምንዛሪ ስላለ ብቻ አስመጪዎች ዕቃ እንደሚያዙ አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዕቃው ጂቡቲ ወደብ ከደረሰ በኋላ የዕቃው ሰነዶችን (Bill of Lading) ከባንክ ለማውጣት ቀሪውን (70 በመቶ) ለባንክ መክፈል የሚጠበቅባቸው በመሆኑ እንዲሁም የትራንስፖርት፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ታክስና ቀረጥ ወጪ ስለሚጠብቃቸው የውጭ ምንዛሪ የተከፈለበትን ንብረት በሰው አገር እንደሚተውት ገልጸዋል፡፡

የሚገለጸውን ውስብስብ ችግር በጥሞና ያዳመጡት አፈ ጉባዔ አባዱላ፣ ‹‹ይኼ ኃላፊነት የጎደለው አሠራር ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹እባካችሁ ይህንን አስተካክሉ ብለን የምናልፈው አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡

አገሪቱ ባላት አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ እየተገዛ ንብረቱ ግን እየበሰበሰ መሆኑ አገራዊ ኪሳራ ነው ያሉት አፈ ጉባዔ አባዱላ፣ በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደሌለበት አስታውቀዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ የኦዲት ምርመራ አካሂዶ ሙያዊ ሪፖርት እንዲያቀርብ እንደሚደረግና በሪፖርቱ ላይ ተመሥርቶ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህንን የምናደርገው ለማጋለጥና ለማብጠልጠል አይደለም፡፡ አንድ ቦታ ልንቆርጠውና ልንማርበት ስለሚገባ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው በሪፖርቱ የቀረበው የስኳር ኮርፖሬሽን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካና የከሰም ስኳር ፋብሪካ አፈጻጸም ጉዳይ ነው፡፡

ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከተጀመረ አሥር ዓመት ቢሞላውም እስካሁን ሙሉ በሙሉ አለመጠናቀቁን፣ የሠራተኞች መኖሪያ ቤት መገነጣጠሉን (በዲዛይን ችግር)፣ ከፋብሪካው የሚለቀቅ ቆሻሻ ማጣሪያ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን የሚሠራ) ያልተጠናቀቀ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተገዙ ሲኖትራኮች፣ ግሬደሮች፣ ፓወር ፕላስ ማሽነሪዎችና የሙከራ ማሽነሪዎች በመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ችግር በየቦታው ቆመው እንደሚገኙ ቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት አድርጓል፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ሜቴክ ላቀረባቸው ማሽነሪዎች፣ አገር ውስጥም ሆነ ቻይና ድረስ ተጉዘው መለዋወጫ ቢያስፈልጉም ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሜቴክ የተወከሉት የሥራ ኃላፊ መኮንኖች በበኩላቸው የስኳር ኮርፖሬሽንን ወቀሳ አልተቀበሉም፡፡ ተሽከርካሪዎቹና ማሽነሪዎቹ መቆማቸውን እንደሚያውቁና በመጋዘናቸውም በቂ መለዋወጫ መኖሩን፣ ነገር ግን ስኳር ኮርፖሬሽን ዋጋው ተወደደ በሚል ሰበብ ለመግዛት እንዳልፈለገ አስታውቀዋል፡፡

‹‹በኃላፊነት የተቀመጣችሁ ሁላችሁም ችግር እንድትፈቱ እንጂ ተሸክማችሁ እንድትሄዱ አይደለም፤›› ያሉት አፈ ጉባዔው፣ በሜቴክና በስኳር ኮርፖሬሽን መካከል መለዋወጫን አስመልክቶ የተፈጠረውን አለመግባባት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አጣርቶ ለፓርላማ በጽሑፍ ሪፖርት እንዲያደርግ አዘዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...