Thursday, November 30, 2023

የጥልቅ ተሃድሶው አካሄድና ያልፈታቸው ችግሮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጣሊያን የኢትዮጵያን ምድር ለመውረር ሙከራ አድርጎ አልሳካለት ሲለው ወደ አገሩ ከሸሸበት ማግሥት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብዙ ለውጦች ታይተው እንደነበር ይነገራል፡፡  የቅኝ ግዛት ፍላጎት የነበረውን ጣሊያንን ያባረረ ሕዝብ በአገሩ እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ ይመቻችለት ዘንድ ጥያቄዎችን ማቅረብ እንደ ጀመረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ከ1942 እስከ 1944 ዓ.ም. ድረስ ባሉ ጊዜያትም ንጉሠ ነገሥቱ አያሌ የኢኮኖሚና አስተዳደራዊ ለውጦችን ወይም ተሃድሶዎችን እንዳደረጉ መረጃዎች ይቁማሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የጦር ሠራዊትና የፖሊስ መኮንኖች ቋሚ የወር ደመወዝ እንዲቆረጥላቸው ተደርጓል፡፡ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክልል አንድ ወጥ የሆነ የግብር ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ እነዚህና ሌሎች የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች በንጉሡ ሥርዓት ጊዜ የኅብረተሰቡን ወቅታዊ ችግር ይፈታሉ ተብለው የተወሰኑ ዕርምጃዎች እንደነበሩ ይጠቀሳል፡፡

መንግሥታት ሥልጣናቸው ከእጃቸው እንዳይወጣ ሲሉ የተለያዩ የማባበያና የማግባቢያ ቃል ኪዳኖችን ለሕዝቡ ይገባሉ ሲሉ የተለያ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ምንም እንኳ ደርግ አምባገነን ሥርዓት የነበረ ቢሆንም፣ የተለያዩ ተሃድሶዎችን እንዳደረገ ይነገራል፡፡ ከሕዝብ ጋር ለመግባባትና ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል ለሕዝቡ ቃል ይገባ እንደነበር የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡

አምባገነኑ የደርግ ሥርዓት ተወግዶ የኢሕአዴግ መንግሥት በትረ ሥልጣን ከጨበጠ በኋላም ቢሆን ተሃድሶዎችን በተለያየ ጊዜ አድርጓል፡፡ ኢሕአዴግ በድርጅት ውስጥ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት በ1993 ዓ.ም. ተሃድሶ አድርጎ ነበር ይታወሳል፡፡ ከዚያ ወዲህም ቢሆን የተለያየ የተሃድሶ ንቅናቄዎችን ያደረገ ቢሆንም፣ በ2009 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ያደረገው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ግን ሰፋ ያለና ሁሉንም አመራርና የመንግሥት ሠራተኞችን  ጭምር ያሳተፈ ነው፡፡

ከ2008 እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም. በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በርካታ አካባቢዎች ሁከቶች ተቀስቅሰው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በኦሮሚያ በ15 ዞኖችና 91 ወረዳዎችና ከተሞች ውስጥ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የመብት ጥሰት፣ ሥራ አጥነት፣ የልማት ፕሮግራሞች መዘግየት፣ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ጥቅም በሕግ ተደንግጎ ተግባራዊ አለመደረግ፣ ወዘተ የሚሉ ምክንያቶች ለሁከትና ለግጭቱ መነሻ እንደነበሩ ሪፖርተር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በአማራ ክልልም ተከስቶ የነበረው ግጭትና ተቃውሞ መንስዔም በተመሳሳይ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ፍትሕ ማጣት፣ የቦታ አሰጣጥ ችግር፣ ኢፍትሐዊ ግብር አጣጣልና የኑሮ ውድነት እንደነበሩ ተዘግቧል፡፡

ይህ ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም. የነበረው አገራዊ ተቃውሞና ረብሻ በኢሕአዴግ ታሪክ ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ሰፊውና ብዙ ውድመትና ኪሳራ ያስከተለ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ አገራዊ ግጭትና ሁከት ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት መውደሙን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገልጿል፡፡

ለዚህ አገራዊ ቀውስና ተቃውሞ መንስዔ የሆነውን ጉዳይ ለመለየትና ለማወቅ ኢሕአዴግ ባደረገው ግምገማ የመንግሥት የአሠራር ብልሹነት እንደሆነ ተገንዝቦ፣ ይህንን ለማረምና ለማስተካከል ደግሞ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በመጀመር አመራሩና የመንግሥት ክንፍ የሚባለው ሠራተኛው በጥልቅ ተሃድሶው እንዲያልፍ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

 አንዳንድ ግለሰቦች ለዚህ ችግር መንስዔው የኢሕአዴግ ውስጣዊ ችግር ስለሆነ፣ በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ማለፍ የነበረባቸው ኢሕአዴግና አባላቱ ብቻ ነበሩ ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

በዚህ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በዋናነት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች የተደፈቁበት እንደነበር የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከታኅሳስ 22 እስከ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ እንዳረጋገጠ፣ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ መግለጫው፣ ‹‹በየደረጃው በተካሄዱ የግምገማ መድረኮች፣ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እስከ ታችኛው ድረስ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር፣ እንዲሁም ሥልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል አመለካከትና ተግባር ድርጅቱን፣ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንዲሆን፣ የህዳሴያችን አደጋዎች መሆናቸው እንዲጋለጡና በየደረጃው ብቁ ትግል የተካሄደባቸው መሆኑን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ተግባብቶበታል፤›› ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡

ሥራ አስፈጻሚው ይህንን ቢልም የኢሕአዴግ የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ ግን የተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በዋናነት ችግሩ ስለተፈጠረ አይደለም ጥልቅ ተሃድሶ የተደረገው፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው በ15 ዓመታት ውስጥ ከሦስቱ መሠረታዊ ነገሮች አንዱ የነበረውን መስመር የማጥራት ጉዳይ ለመገምገም ሊካሄድ የነበረ ነው፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ከዘመናት የጭቆናና የግፍ ሥርዓት አውጥቶ ሰላም የሰፈነባት አገር መገንባት መቻሉን ቢናገርም፣ እስካሁን ድረስ በልማትና በዴሞክራሲ ግንባታ እክሎች እንዳሉበት ይህን መግለጫና ሌሎች መረጃዎችን አባሪ አድርገው የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ የአገሪቱን ድንበር ከአሸባሪዎች የመጠበቅ አቅሙ የዳበረውን ያክል በዴሞክራሲያዊና በመልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ ብዙ ሥራዎችን እንዳልሠራ ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ከወጣቱ የሥራ ፈጠራ ውስንነት፣ ከሙስናና ከብልሹ አሠራር፣ ከመልካም አስተዳደር ዕጦትና የመንግሥት ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል፣ ወዘተ ችግሮች የኢሕአዴግ መገለጫዎች እንደሆኑ አንዳንድ ባለሙያዎች ሲገልጹ ይሰማል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሥራ ዕድል ያልተፈጠረለት ወጣት በርካታ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የባሰ እንዳደረገው በመጥቀስ፡፡ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በ2009 ዓ.ም. ሁለቱን ምክር ቤቶች ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ባሳለፍነው ዓመት በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት የአገራችን ወጣቶች ነበሩ፤›› ብለው ነበር፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ኢሕአዴግ የሚነግሩትን አይሰማም ይላሉ፡፡ የሚነገረውን ቢሰማ በ2008 ዓ.ም. የተከሰተው ግጭትና ሁከት ባልተከሰተ ነበር ይላሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት ባልወደመ ነበር እያሉ ሲሞግቱ ይሰማል፡፡  

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በ2009 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባቀረቡት የመክፈቻ ንግግር ‹‹ባሳለፍነው ዓመት ያጋጠመንን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረግን በነበረበት ወቅት የተከሰተው ሌላው አገራዊ  ችግር፣ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ሁከትና ግጭት መቀስቀሱና አንፃራዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት መታየቱ ነበር፡፡ ለሁላችንም ግልጽ እንደሚሆነው በልዩ ልዩ የአገራችን ክፍሎች በተለይ ደግሞ ወጣቶች የተሳተፍባቸው ሁከቶችና ግጭት ተቀስቅሰዋል፡፡ በእነዚህ ግጭቶች ሳቢያ በአሳዛኝ ደረጃ የወጣቶችና ሌሎች ዜጎች፣ እንዲሁም የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ቀላል የማይባል ንብረትም ወድሟል፡፡ በተጨማሪ የዜጎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ደፋ ቀና ብለው ሠርተው ኑሯቸውን ለማሸነፍ የሚንቀሳቀሱ ዜጎች ለፈተናዎች ተዳርገዋል፤›› ብለው ነበር፡፡

ይህ የሚያመለከተው ደግሞ የችግሩ ጥልቀትና ስፋት ምን ያህል እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት የችግሩን መኖር ያመነበት፣ ጥልቀትና ስፋቱን የተቀበለበት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በተለይ ይህ ሁሉ ችግር የመነጨው የሕዝብ አገልጋይ መስለው በተቃራኒው ሕዝብን ሲጎዱና ሲበድሉ የነበሩ አመራሮች በስፋት እንደነበሩ በመጠቆም፡፡ በዚህ የተነሳ ኢሕአዴግ ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ አመራሮችን ከሥልጣን ማገዱን መግለጹ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ኤሪክ ብሌር (በብዕር ስሙ ጆርጅ ኦርዌል) የተባለው እንግሊዛዊ ጸሐፊ ‹‹1984›› በተሰኘው መጽሐፉ፣ ‹‹በአንድ ሥርዓት ውስጥ ሙሰኛ አመራር ካለ ብዙ ነገሮች ፍፃሜያቸው አያምርም፤›› ይላል፡፡ ጆርጅ ኦርዌል ለዚህ ድምዳሜ ያደረሰው ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ1917 ጀምሮ በቀድሞው የሶቭየት ኅብረት፣ በአንዳድ የምሥራቅ አውሮፓና እስያ አገሮች ተነስራፍቶ ነበረው ኢፍትሐዊ አሠራርና ሙስና እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ፍፃሜያቸው ግን ሳያምር እንደቀረ በመጽሐፉ አብራርቷል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ውጤቶች በአገሪቱ እንዳይፈጠሩ ኢሕአዴግ በ2009 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› የሚል ንቅናቄ መጀመሩን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አቶ ሰለሞን ካሳ፣ ‹‹መታደስ ስንል ከዚህ ቀደም የነበረውን መጥፎ አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ አመለካከት ወይም አሠራር፣ ባህል፣ ወደ ጥሩ ሒደት መለወጥ ነው፤›› ይላሉ፡፡ የኢሕአዴግ የመታደስ ንቅናቄም የነበሩ መጥፎ አመለካከቶችና አስተሳሰቦች ወደ ጥሩ የመለወጥ ዓላማን አንግቦ የተካሄደ የንቅናቄ መድረክ እንደነበር አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡ በትክክል እነዚያ መጥፎ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች በአሁኑ ጊዜ ተወግደዋል? ተስተካክለዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ አሁንም በተለያዩ ባለሙያዎች እየተነሳ ያለ ቢሆንም፣ ይህን ጥልቅ ተሃድሶ ኢሕአዴግ ማካሄዱ ተከስተው ለነበሩ ችግሮች ላይ ባለቤት ለመስጠትና ችግሩን ለመቀልበስ እንደሆነ አንዳንድ ግለሰቦች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አባልና ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሙሼ ሰሙ ‹‹ኢሕአዴግ በድርጅቱ ውስጥ ያካሄደው ወይም ጥልቅ ተሃድሶ ብሎ የሚጠራው እንቅስቃሴ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ሲያደርጋቸው የነበሩና የቆዩ ባህሪያቶቹ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ አንድ ችግር ባጋጠመው ጊዜ ማኅበረሰቡ ችግሩ እንዲፈታለት ጥያቄ ባቀረበበት ጊዜ፣ መጀመሪያ እንቅስቃሴውን ቀልብሶ ለችግሩ ባለቤት ለመፈለግ የመጠመድ ባህሪ አለው፤›› ይላሉ፡፡

የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊው አቶ ፈቃዱ ግን ከዚህ የተለየ ሐሳብ ነው የሚያቀርቡት፡፡ ‹‹የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞው የኢሕአዴግ መስመርን በማስተካከል በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳች ላይ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየትና ለእነዚህም ትክክለኛ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ኢሕአዴግ በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት ያደረገው የአመራር ሽግሽግ የግልጽነት ችግር አለበት የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ አቶ ሰለሞን ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ‹‹አዲስ የተሾሙ አመራሮች የማስፈጸም አቅማቸው እስከ ምን ድረስ ነው? በተጨማሪም ከተፅዕኖ ውጪ ሆነው ይሠራሉ ወይ የሚለው መጤን አለበት፤›› ይላሉ፡፡

ስለአፍሪካ ታላላቅ ጉዳዮች ሰፋ ያለ መረጃና ትንታኔ የሚሰጠውና ‹‹ዲስኮርስ›› የተሰኘው መጽሔት ዋና አዘጋጅና የፐብሊክ ፖሊሲ ተንታኙ አቶ ዳደ ደስታ በበኩላቸው፣ ‹‹ኢሕአዴግ አጠቃላይ የአገሪቱ ሀብትና ንብረት ከሕዝቡ ቁጥር ጋር ተመጋጋቢ ሆኖ እንዲሄድ የማድረግ ውስንነት አለበት፡፡ ከሕዝቡ ጋር ያለው ግንኙነት የላላ ነው፡፡ በዚች አገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሙስና ተንሰራፍቷል፡፡ መንግሥትም ይህንን እንደ ችግር አይቶ ለመፍታት ሲንደፋደፍ ይታያል፡፡ ግን ሲፈታ አይታይም፤›› በማለት ያለውን ክፍተት ጠቁመዋል፡፡

ጥልቅ ተሃድሶ ማድረግ የኢሕአዴግ የተለመደ ባህሪና ከዚህም ብዙ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል የገለጹት አቶ ሙሼ፣ ‹‹ከዚህ በፊት ኢሕአዴግ  የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አድርጌያለሁ ብሏል፡፡ እነዚህ ተሃድሶዎች መሠረታዊ ችግሩን ቀልብሰው ቢሆን ኖሮ ወደዚህ ተሃድሶ መግባት አስፈላጊ ባልነበረ፡፡ ምክንያቱም እንደ ድርጅት ከአንዱ ችግር ተምሮ ሌላ ችግር የማይፈጠርበትን ሁኔታ አረጋግጦ ማለፍ ሲገባው እንደተለመደው ለተፈጠረው ችግር ባለቤት ፈልጎ፣ ለዚያ ባለቤት መጠሪያ ሰጥቶ የሄደበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሙሼ አክለውም፣ ‹‹ከአንዱ ተሃድሶ ወደ ሌላው ሲሄድም ባህሪያቸው እየተለወጠ አልመጣም፡፡ ሕዝቡን መድረክ አመቻችቶ በስፋትና በጥልቀት የማወያየት ነገር ለም፡፡ ኢሕአዴግ መርጦ ባወጣቸው ጥያቄዎች ላይ ውይይት ይካሄዳል፡፡ ለግምገማ መነሻ መሆን ያለባቸው ግን ከሕዝቡ የመነጩ ችግሮች ነበሩ፡፡ የችግሩ ባለቤት እሱ፣ አወያይም እሱ፣ ተወያይም እሱ ሆኖ ምን ዓይነት መፍትሔ ነው ሊመጣ የሚችለው?›› በማለት ኢሕአዴግን ኮንነዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢሕአዴግ በእርግጥም ውስንነቶች  እንዳሉበት ጠቁሟል፡፡ አቶ ፍቃዱ፣ ‹‹ዕድገታችን የፈጠረው የፍላጎት አለመጣጣም አንዱ ችግር ነው፡፡ የጥራትና የተደራሽነት ችግር፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ወዘተ በድርጅቱ ጉዞ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ዳደ፣ ‹‹በሁላችን ኪስ ያለው ገንዘብ ተደምሮ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንደሚባለው ሁሉ፣ የሁላችንም ሐሳብ ተደምሮ ነው የዚችን አገር  ዕጣ ፈንታና መሠረት መጣል ያለበት፡፡ ሐሳቦች ከየጓዳው ነው መገኘት ያለባቸው፡፡ ከአንድ ፓርቲ ብቻ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሙሼ ባሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ሲያባራሩ፣ ‹‹የፍትሕ ዕጦት፣ የሥራ አጥነት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር፣ ወዘተ በሕዝቡ ዘንድ ያሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እያንዳንዱን ኢትጵያዊ መንገድ ላይ አቁመህ ብትጠይቀው ሁሉም ብሶትና ቁጣ አለው፡፡ ስለዚህ እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች መጀመሪያ ተነቅሰው መውጣት ያለባቸው ከማኅበረሰቡ ነው፤›› ይላሉ፡፡

አቶ ሰለሞን በበኩላቸው፣ ‹‹የተነሱና የተሸጋሸጉ አመራሮች የት እንደ ደረሱ ለሕዝቡ መታወቅ አለበት፡፡ እነሱ የሚቀጥሉ ከሆነም ሕዝቡ ማወቅ አለበት፡፡ አለበለዚያ እሳት ማዳፈን ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ በአብዛኛው የተሠራው ሥራ የፓርቲውን የውስጥ ብዥታ ማከም ነው የሚመስለኝ፡፡ ይህንን ስል ምክንያት አለኝ፡፡ አንደኛ የአካሄድ ችግር አለ፡፡ ለምሳሌ አመራሮችን የማሸጋሸግ ሥራ ከሕዝቡ የመነጨ አይደለም፡፡ ፓርቲው ጥልቅ ተሃድሶ አድርጎ የራሱን ግምገማ አካሂዶ፣ ችግሮቹን በራሱ መመዘኛ አውጥቶ ተቀበሉኝ የሚል አካሄድ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ የሕዝብ አመኔታ አይፈጥርም፡፡ ሁለተኛው የማለባበስ ችግር አለ፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ፡፡ የዴሞክራሲ ጥያቄ ችግር አለ፡፡ የኢኮኖሚ ፍትሐዊነት ችግር አለ፤›› በማለት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

አክለውም፣ ‹‹የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ እየተሠራ አይደለም፡፡ የፍትሕና የፀጥታ ኃይሎች በአስፈጻሚው እጅ እንዳይወድቁና ራሳውን ችለው እንዲሠሩ ምን ዓይነት ሥራ ሠርቷል ብለን ብንጠይቅ እዚህ  ግባ የሚባል መልስ አናገኝም፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አቶ ሙሼ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ያደረገው አስተዳደራዊ ዕርምጃ በእኔ እምነት ፋይዳ የለውም፡፡ ምክንያቱም በኢሕአዴግ አባላት ዘንድ የሚታየው ባህሪ አንዱ ከአንዱ ተወራራሽነት አለው፡፡ ይኼ ተወራራሽ ባህሪ ሁሉም ዘንድ ያለ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ሰዎችን በሰዎች በመተካት ለየት ያለ ነገር ማምጣት ይቻላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ለእኔ ከባድ ነው፡፡ ይህ ችግር ከአስተዳደራዊ ለውጡ ባሻገር ወንጀልም አለበት፡፡ ፍትሕን ያዛቡ፣ የማኅበረሱን ሀብት የዘረፉ፣ መሬቱን ያራቆቱ ሰዎች እንዳሉ በሕዝቡ ዘንድ እሮሮ ይቀርባል፡፡ ስለዚህ አስተዳደራዊ መፍትሔ አይደለም የሚፈልጉት፡፡ ሕጋዊ ውሳኔ ይፈልጋሉ፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ ጥልቅ ተሃድሶ ጋር ተያይዞ የሚነሳው መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለውይይት መጋበዝ መቻሉን እንደ መልካም አጋጣሚ  የሚቆጥሩ ወገኖች ቢኖሩም፣ አቶ ሙሼ ግን በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠ ጉዳይ እያለ መደራደርን እንደ ሌላ አማራጭ  አድርጎ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ ይኼ ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በመጠቆም፡፡ የሕዝብን ጥያቄ ተደራሽ ለማድረግ ከሆነ ደግሞ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቅምና ጉልበት አላቸው ወይ? የሚለው መፈተሸ አለበት ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ አባል የሌለው፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሌለው፣ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዶ የማያውቅ ተቃዋሚ ፓርቲ ሕዝብን ሊወክል አይችልም ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማለታቸው እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ፍቃዱ ደግሞ ከዚህ ሐሳብ በተቃራኒ የቆሙ ናቸው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲጠናከር የኢሕአዴግ አንዱ አቋም እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ሲባል በአሁኑ ወቅት ከ21 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር በመጀመር በአገሪቱ ያለውን የኃይል ሚዛን ሊያስተካክል የሚችል ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

 ከዚህ በተቃራኒ ግን ይህ ጥልቅ ተሃድሶ ይዟቸው የመጡ ብዙ በጎ ጎኖች እንዳሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

አቶ ሰለሞን በተሃድሶው የመጡ ለውጦችን ሲገልጹ፣ ‹‹የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሲባል የአመራር ለውጥ ተደርጓል፡፡ ለውጡ ደግሞ ትምህርትን መሠረት ያደረገ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሰለሞን አክለውም በዚህ ንቅናቄ የአመለካከት ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ሌላው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር ጥልቅ ተሃድሶው ያመጣው ጅምር ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት የተሄደበት መንገድ ጥሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አቶ ሙሼ በበኩላቸው፣ ‹‹ይኼ ተሃድሶ እንበለው ግምገማ አንዱ የማስታረቂያ መንገድ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አንተም ተው፣ አንተም ተው የማለት ነገር ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን የሕዝብን አደራ ለተቀበለ መንግሥት በቁርጠኝነት የሕዝብን ችግር ከግምት ውስጥ አስገብቶ ለመፍታት የሚያስችል ሥልት ነው ብዬ አልቀበለውም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዳደ በጥልቅ ተሃድሶው የመጡ ለውጦችን ሲያብራሩ ደግሞ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ይኼ ፅንፈኞች ያመጡት ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ጥሩ ነን፡፡ እኛ መቶ ፐርሰንት የፓርላማ ወንበር ያገኘንና የተጎናፀፍን ፓርቲ ነን፡፡ ስለዚህ ችግር የለብንም አለማለቱ እንደ ትልቅ ነገር ይወሰዳል፡፡ እኛ የፈጠርነው ችግር ነው፡፡ ሌሎች ሊጠቀሙበት ሞክረው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ዋናው በእኛ ውስጣዊ ድክመት የመጣ ነው የሚለውን መነሻ እንደ መልካም ነገር አየዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ፍቃዱ ደግሞ፣ ‹‹ይህ እንቅስቃሴ በየደረጃው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ መሪ ድርጅቱ በመምራት፣ ኅብረተሰቡ ደግሞ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ጉልህ ሚና ነበራቸው፤›› ብለዋል፡፡

የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቀሴው ከተጀመረ ከስድስት ወራት በላይ ያቆጠረ ቢሆንም፣ ገዥው ፓርቲ ቃል በገባው ልክና መጠን አለመፈጸሙን የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ የመጀመሪያ ጉዳይ አድርገው የሚወስዱት ደግሞ መንግሥት ዘላቂ በሆነ መንገድ ከሕዝቡ ጋር ያለመሥራት ችግር እንዳለበት ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ዳደ፣ ‹‹ሕዝቡ ከአገሪቱ ሀብትና ፀጋ ጋር ተያያዥ እንዲሆንና የዕድገቱም ተጠቃሚ ማድረግ ተገቢ ነው፤›› ይላሉ፡፡

አቶ ሰለሞን በበኩላቸው፣ ‹‹ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሲባል የግል ሴክተሩን በሚያቀጭጭ መንገድ መንግሥት ለእነዚህ እሴት ለማይጨምሩ ወጣቶች ከግል ባለሀብቶች ነጥቆ የመስጠት አሠራር አለ፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ድርጊት ደግሞ ከጥልቅ ተሃድሶው መርህና እንቅስቃሴ ጋር የሚፃረርና ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል ሊጎዳ የሚችል ድርጊት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሌላው አቶ ሰለሞን የጠቀሱት ጉዳይ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴው ከመካሄዱ በፊት ከአገሪቱ ምሁራን ጋር ውይይት አለመደረጉ፣  ችግሮችን በተገቢው መንገድ ለመፍታት እንቅፋት እንደሆነ ነው፡፡

ጥልቅ ተሃድሶው አገሪቱን ወደ ሰላምና መረጋጋት እንደመለሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሚያዚያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት  መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ማንኛውም የፓርቲ ሒደት አስተማማኝ መሆኑ የሚለየው በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በመረዳት እንደሆነ መናገራቸውን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ‹‹መቀልበሳቸውን የምናረጋግጠው ከሕዝባችን አመለካከት እንጂ ረብሻውን ከሚፈጥሩ ጥቂት ኃይሎች ተነስተን አይደለም፡፡ በዚህ ግምገማችን እናምናለን፡፡ ምክንያም ሕዝባዊ መንግሥት እንደ መሆናችን መጠን መነሻችንም መድረሻችንም ሕዝቡ ነው፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው ሕዝባዊ እንዳልነበር የሚናገሩ ወገኖችም አሉ፡፡ አቶ ሙሼ በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ‹‹የተደረጉ ግምገማዎች ዝግ ናቸው፡፡ ግምገማው ለምን እንደተካሄደ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ዋናውና ወሳኙ ጉዳይ የዚች አገር ባለቤት ሕዝቡ ነው የሚለውን ኢሕአዴግ መጀመሪያ ማመን አለበት፤›› ብለዋል፡፡

አገሪቷን ስሟንና ክብሯን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ ሳይባል በአገር ጉዳይ ላይ ብሔራዊ መግባባት መፈጠር እንዳለበት ብዙ ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ከዚህ በፊት ተከስቶ እንደነበረው አገራዊ ቀውስና ግጭት ሁለተኛ እንዳይደገም ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ያሳስባሉ፡፡

ከዚህ በፊት የነበሩትን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ በመፍታትና የነበረውን ብሔራዊ አንድነት የበለጠ አጠናክሮ መሄድ ተገቢ እንደሆነ በመጠቆም፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚደርስበትን መንገድ መቀየስ አንዱ ስትራቴጂ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ ደግሞ ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር  እያደረገ ያለውን ድርድር የበለጠ ማጠናከር እንዳለበት በመጠቆም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ዳደ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ያለው የተቃዋሚ ድርጅቶች ሁኔታ በሚፈልገው ደረጃ ከፍ ያለ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይህንን ችግር መፍታት ኃላፊነቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጥልቅ ተሃድሶውና ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች የነበራቸው ክፍተት ታርመውና ተስተካክለው ወደፊት የተሻለች አገር መገንባት ተገቢ መሆኑን ባለሙያዎች አክለው አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ሰለሞን፣ ‹‹ኳሱ ያለው በገዥው ፓርቲ እጅ ነው፡፡ የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ችግሮችን ኢሕአዴግ መፍታት አለበት፡፡ የይድረስ ይድረስ ሳይሆን በተጠናና አስተማማኝ በሆነ ዘዴ መሥራት አለበት፡፡ ተነሳሽነቱና የሕዝቡን ብሶት ጆሮ ሰጥቶ የማዳመጥ ሒደቱ ላይ በደንብ ቢሠራ መልካም ነው፤›› የሚል የመደምደሚያ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ ሙሼ ደግሞ፣ ‹‹በዚች አገር ላይ በርካታ አማራጮች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ ጉዳይ ላይ ያለውን አማራጭ ይዞ መቅረብና ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ራስህን ብቸኛ ተመራጭ  አድርገህ የምትወስድ ከሆነ ሌሎች አማራጮችን ለማቅረብ ዕድል አይኖርህም፡፡ ኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመጣጣኝ ጉልበትና አቅም ተሰጥቷቸው ሕዝቡ እንዲመርጣቸው መደረግ አለበት፡፡ ሁሉም ሰው በዚች አገር የራሱን አሻራ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ስለዚህ ይህንን ደግሞ በቀናነትና በቁርጠኝነት ኢሕአዴግ መቀበል አለበት፡፡ ዜጎች አማራጭ መስማት ከቻሉ፣ ከአማራጮች መካከል ደግሞ ያመኑበትን መምረጥ ከቻሉ፣ በጋራ ስለአገር መሥራት ቀላል ይሆናል፡፡ ውድቀትም ቢኖር ያንን ውድቀት የጋራ አድርጎ ለመቀበል ችግር አይኖርም፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

አቶ ዳደ በበኩላቸው፣ ‹‹የወጣት ሥራ ፈጠራ ትልቅ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ኢሕአዴግና መንግሥት ትልቅ ትኩረት እየሰጡት ነው፡፡ እኔ ግን ከዚያም በላይ የሆነ ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ በገጠሩ አካባቢም ቢሆን ብዙ ሥራ አጥ ማኅበረሰብ አለ፡፡ የተወሰነ ወራት ይሠራሉ፣ የተወሰነ ወራት ደግሞ ቁጭ ይላሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮች ላይ መንግሥትና ኢሕአዴግ ትኩረት አድርገው ቢሠሩ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል ባይ ነኝ፤›› የሚል የማጠቃለያ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

የኢሕአዴጉ አቶ ፍቃዱ ደግሞ፣ ‹‹ስለእያንዳንዱ ችግር ምንጭና መንስዔ ከኅብረተሰቡ ጋር መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ የጋራ መግባባቱ እንደ ድርጅት ከተደረሰ በኋላ ሳይዛነፍ ወደ ሕዝቡ መውረድ አለበት፡፡ ከዚህ በኋላ በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮችን ለይቶ ከሕዝቡ ጋር መሥራት ተገቢ ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -