Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ተቋም ዓለም የሚጠቀምበት ዘመናዊ የጂን ባንክ በአዲስ አበባ መሠረተ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ለኢትዮጵያ እንስሳት መኖ አቅርቦትና ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ተስፋ ተጥሎበታል

ከመላው ዓለም የተሰባሰቡና አገሮች የተስማሙባቸው፣ ከ1,000 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች ያሏቸውን 19,000 ያህል ጂኖች ያሰባሰበና ለመላው ዓለም አገልግሎት የሚሰጥ ዓለም አቀፍ የእንስሳት መኖ ጂን ባንክና ባዮ ሳይንስ ማዕከል በአዲስ አበባ ተመሠረተ፡፡

ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (International Livestock Research Institute- ILRI) የገነባው ዘመናዊ የጂን ባንክና የባዮ ሳይንስ ማዕከል፣ ከኢትዮጵያ የ20 በመቶ የጂን አቅርቦት እንዳገኘ የተቀረውን ግን ከመላው ዓለም ማሰባሰቡን ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. የተቋሙ ሥራ መጀመር ይፋ በተደረገበት ወቅት ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ጄኔራል ተወካይ ሲቦኒሶ ሞዮ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ተቋሙ በሚገኝበት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባው አዲሱ ዘመናዊ የጂን ባንክ ለኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ለመላው ዓለም አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ በተቋሙ የተሰባሰቡት ዝርያዎች ንብረትነታቸው የዓለም ሕዝብ እንደሆነ እንዲሁም በምግብና በግብርና መስክ በተደረጉ ዓለም አቀፋዊ የተክሎች የጂን ሀብት ስምምነቶች መሠረትም ለመላው ዓለም በነፃ የሚቀርቡ የጂን ሀብቶች እንደተካተቱበት ሚስተር ሞዮ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የተክሎችን ውጤታማነትና ምርታማነት ለማሻሻል ብሎም ለረዥም ጊዜ ጠብቆ ለማቆየት በአዲስ መልክ የተገነባ ማከል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዕፅዋት ዝርያና ዓይነታቸውን በመሰነድ፣ ዕፅዋቱ ከአካባቢ ሁኔታዎች ጋር ስላላቸው ተዛምዶና ስለሌሎችም ጉዳዮች ምርምር በማካሄድ የመመዝገብና የመጠበቅ ሥራዎች ቀድሞም ተቋሙ ውስጥ ለዓመታት ሲተገበር የቆየ ሲሆን፣ ይህንን በማሻሻል በዘመናዊ መሣሪያዎችና በዘመናዊ ሕንፃ የተደራጃ ማዕከል በመገንባት ለሥራ ማብቃቱን ሚስተር ሞዮ ገልጸዋል፡፡

ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት አዲሱ ማዕከል፣ ለኢትዮጵያ የዕፅዋት ምርምርና ጥበቃ ላይ ስለሚያደርገው አስተዋጽኦ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳሬክተር መለስ ማሪዮ (ዶ/ር) እንደሚጠቅሱት፣ በኢትዮጵያ ሁለት የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ የሚሰጡ ተመሳሳይ የጂን ባንኮች መኖራቸውን ገልጸው በሦስተኛነት በተለይም በእንስሳት መኖ መስክ የሚሠራ የጂን ባንክ መምጣቱ የኢትዮጵያን የብዝኃ ሕይወት ሀብት ጥበቃ እንደሚያጠናክረው ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

በሙያቸው የአግሮ ባዮ ዳይቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዋና ዳይክተሩ፣ ኢንስቲትዩቱ በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ መስክ ከሚጠበቁበት ተግባራት መካከል ማንበር (ማቆየት)፣ ዘላቂ ቆይታ እንዲኖር ማድረግና መጠቀም እንዲሁም የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነትና የጥቅም ተካፋይነት አራት ትላልቅ ተግባራት ማከናወን ሲሆኑ፣ በእንስሳት፣ ለምግብነት በሚውሉ አዝርዕትና ሆርቲካልቸር እንዲሁም በማይክሮ ባዮሎጂካል ዘርፍ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ሥራዎች ላይ በማተኮር የሚሠራው የብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት፣ በዓለም አቀፉ የእስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት አዲስ የጂን ባንክ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው ዕድሎች መፈጠራቸው ተፈላጊ ዕፅዋትን ለመጠበቅ ብቻም ሳይሆን ለሚካሄዱ ልዩ ልዩ ምርምሮችም አጋዥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተክሎችና በዕፅዋት መስክ በከብቶች መኖነት የሚያገለግሉ ተክሎች ላይ በተለይ ድርቅ በሚመላለስባቸው አካባቢዎች ላይ ውኃ አጠር በሆኑ፣ በቶሎ የማይደርቁ ሰፋፊ ቅጠሎች ያሏቸውን የመኖ ዕፅዋት በመጠበቅ ብቻም ሳይሆን አልምቶ ለመጠቀም የሚረዱ ሥራዎችን ለማከናወን አዲሱ የጂን ባንክ ብዙ ጥቅም እንዳለው አቶ መለሰ አብራርተዋል፡፡

በተለይም በጂን ጥበቃ ረገድ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገሮች የተፈጸሙ ስርቆቶችንና የተወሰዱ የጂን ሀብቶችን በማስመለስ ረገድ ተቋማቸው፣ ከአንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩቱ ጀምሮ እንደ ጀርመን ባሉ አገሮች የተወሰዱትን ሲያስመልስ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዓለም አቀፍ ተቋም እንደመሆኑ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ልዩ ልዩ የብዝኃ ሕይወት ሀብቶችን አገር ውስጥ በማላመድ፣ ከኢትዮጵያ ሥነ ምኅዳር ጋር በመስማማት የኢትዮጵያ ሀብት ሆነው መመደብ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል እንደሚኖርም ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ ወራሪ ዕፅዋትን የመከላልና የመቆጣጠር ሥራዎችን በመሥራት ያልታሰቡ ጉዳቶች እንዳይደርሱ የሚደረጉ ጥበቃዎች እንዳሉም አብራርተዋል፡፡ 

ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ በደረሰባት ጉዳትና ዘረፋ ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የብዝኃ ሕይወት ሀብቶችን ለመጠበቅ ተብሎ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ሀብቶቿን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳትሆን መቅረቷን አቶ መለስ አውስተዋል፡፡ በሰሜናዊ ንፍቅ ግዙፍ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ የሚደረግባት ማዕከል ቢቋቋምም፣ ኢትዮጵያ በማዕከሉ ሀብቶቿን ለማስቀመጥና ለማስጠበቅ የቀረበላትን ጥያቄ ሳትቀበለው ቀርታለች ብለዋል፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በሰሜናዊ ንፍቅ ጫፍ ጥበቃ በሚደረግበት የጂን ባንክ ውስጥ ሀብቶቿን ከማስቀመጥ ይልቅ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የጂን ባንክ አምሳያ በፍቼ ከተማ መመሥረቱን ያብራሩት አቶ መለስ፣ ይኽም ያልታሰበ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ አደጋዎች ተከስተው አንደኛው የጂን ባንክ ውስጥ የተሰባሰቡት ሀብቶች ጉዳት ቢደርስባቸው በሌላው የሚገኙት ተመሳሳይ ሀብቶች ምትክ እንዲሆኑና ከጥፋት ለመታደግ በማሰብ አምሳያው ማዕከል መተከሉን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ሀብት ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ጌትነት አሰፋ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ በተቋሙ የተከፈተው አዲሱ የጂን ባንክ ለኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በቅርብ የማይገኙ የነበሩ ቴክሎጂዎችን በቀላሉ ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡ 

የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥርና የእንስሳት ሀብቱ ብዛት በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ለዚሁ ቁጥር የሚመጥን የዕፅዋትና የተክሎች አቅርቦት መኖር እንደሚያፈልግ ሲያረዱም፣ በተለይ በአገሪቱ በሰፊው ለሚገኙት እንስሳት የሚውል መኖ በብዛትና በጥራት ለማቅረብ በምርምር የተደገፈ ልማት ለማካሄድ አዲሱ የጂን ባንክና የባዮ ሳይንስ ማዕከል መመሥረቱ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ገበሬዎች ከዚህ ቀደም ሲያከናውኑ ከነበረው የመኖ አመራረት በተጓዳኝ በሰፊው ለማልማት የሚችሉበት መደበኛ የመኖ እርሻ መጎልበት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡

በአቶ ጌትነት ሐሳብ የሚስማሙት ሚስተር ማዮ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ተኮር የእንስሳት መኖ እርሻዎች መለመድ እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡ በእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩቱ የማይክሮ ባዮሎጂቱ ክሪስ ጆንስ (ዶ/ር) እንዲሁም የመኖና የመኖ ሀብት ፕሮግራም ኃላፊ ሲሆኑ፣ የአዲሱ ማዕከል ተግባራ ከሆኑት ውስጥ ለገበሬው ተስማሚ የመኖ ዝርያዎችን በማቅረብ እንዲጠቀሙ ዕድል መፍጠር የሚለው ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች