Tuesday, April 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ተጠያቂነት ሲጠፋ የቆሉት ጥሬ ይሆናል!

 አገር የሚመራው በሕግ ብቻ ነው፡፡ ሕግ ደግሞ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን በግልጽ ይደነግጋል፡፡ የመንግሥት ሦስቱ ምሰሶዎች ሕግ አውጭው (ፓርላማው)፣ ሥራ አስፈጻሚው (የመንግሥትን ሥራ የሚያከናውነው) እና ሕግ ተርጓሚው (የዳኝነቱ አካል) እርስ በርስ እየተናበቡ መሥራት የሚችሉት፣ ተጠያቂነት የሚባለው መርህ በአግባቡ ሲሰፍን ነው፡፡ ሥርዓተ መንግሥቱ ጤናማ ሆኖ ሕዝብን ማገልገል የሚቻለው በሕጉ መሠረት አንዱ ለሌላው ተጠያቂነትን በተገቢው መንገድ እያሳየ፣ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት ሲችል ብቻ ነው፡፡ ይህ የእርስ በርስ ቁጥጥር የሚደረግበት ሥርዓት ደግሞ ሕግ ያከብራል፣ ያስከብራል፣ ሕገወጥነትን ጠንክሮ ይፋለማል፣ የሕዝብ ጥያቄን በአግባቡ ይመልሳል፡፡ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በተለያዩ ሕጎች የወጡ ድንጋጌዎችን መሠረት ያደረጉ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችን ከመጠበቁም በላይ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ይሠራል፡፡ ተጠያቂነት ሳይኖር ሲቀር ግን ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ያቅታል፡፡ ነጥብ በነጥብ እንነጋገር፡፡

የመንግሥትና የፓርቲ ሚና መደበላለቅ የሚፈጠረው ተጠያቂነት ሲጠፋ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ መንግሥትን የማስተዳደር ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ የፓርቲና የመንግሥት ሚና ዳር ድንበር ሊኖረው ይገባል፡፡ ለምሳሌ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስ ሠራዊትና የፀጥታ ኃይሉ ከፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ መሆን እንዳለባቸው በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ይህ ሕግ መጣስ የለበትም፡፡ የፓርቲ ተሿሚዎች በመንግሥት ሥራ ውስጥ ሲሳተፉ፣ የመንግሥትንና የፓርቲን ጉዳይ መደበላለቅ የለባቸውም፡፡ ተጠሪነታቸው ለፓርላማ የሆኑ ተቋማት የመንግሥት በጀት ተጠቃሚ ቢሆኑም፣ በአስፈጻሚው ተፅዕኖ ሥር ሊወድቁ አይገባም፡፡ ፓርላማውን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ሥራ አስፈጻሚውን ይቆጣጠራሉ እንጂ፣ አስፈጻሚ በተቃራኒው የበላይ መሆን የለበትም፡፡ በሕግም የተከለከለ ነው፡፡ የሕግ ተርጓሚውም ቢሆን ከአስፈጻሚው አካል ጫና ሊደርስበት አይገባም፡፡ ሕጉ አይልም፡፡ ተጠያቂነት በመጥፋቱ ብቻ ግን ከላይ የተዘረዘሩት በሙሉ ተግባራዊ አልሆኑም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይፋ በሚደረጉ ጥናቶች ጭምር የችግሩ ግዝፈት እየታየ ነው፡፡ ለሕግ የበላይነት ሲባል ተጠያቂነት የአገር ወግና ባህል ይሁን፡፡

የተጠያቂነት መጥፋት ሌላ ማሳያ ሕግ ለማስከበር በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሚታዩ መሰናክሎች ናቸው፡፡ ሙስና አገሪቱን እንደ ሰደድ እሳት እየለበለበ ነው፡፡ ለሙስና መስፋፋት ምክንያት የሆኑና ከፍተኛ የአገር ሀብት የሚዘረፍባቸው መስኮች በግልጽ ይታወቃሉ፡፡ የመሬት ወረራ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ከቀረጥና ከግብር ሥወራ ጋር የተያያዙ ሌብነቶች ይታወቃሉ፡፡ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችም እንዲሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹ጥልቅ ተሃድሶ› በሚካሄድበት በዚህ ወቅት ጉቦ መቀበልም ሆነ በየደረጃው ሙስና መፈጸም ተጣጡፎ ቀጥሏል፡፡ አገልግሎት በሚሰጡ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በተሰገሰጉ ጉዳይ አስፈጻሚዎች አማካይነት በአደባባይ የሚፈጸመው ሌብነት የተጠያቂነት ያለህ እያለ ነው፡፡ በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጀምሮ ፈጻሚዎች ድረስ የሚጠየቀው መማለጃ በሕግ የተፈቀደ ይመስላል፡፡ ቅሬታ ሲቀርብ የሚሰማ የለም፡፡ ይልቁንም ለሙስና የሚያበረታቱ ምክሮች ይለገሳሉ፡፡ ሕዝብ ደግሞ ‹መታደስ ማለት እንዲህ ነው ወይ?› እያለ ይጠይቃል፡፡ ተጠያቂነት በመጥፋቱ ብቻ ብዙ ነገሮች ከመስመራቸው እየወጡ ነው፡፡

ከፍተኛ የአገር ሀብት የወጣባቸው ንብረቶች ሲባክኑ ወይም ሲበላሹ የሚጠይቅ ስለሌለ በየመጋዘኑ፣ በየደረቅ ወደቡና በየመጠለያው ይወድማሉ፡፡ ለተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ በውጭ ምንዛሪ ጭምር የተገዙ ንብረቶች ሥራ ላይ ሳይውሉ እየቀሩ የትም ሲበላሹ ማየት አዲስ አይደለም፡፡ የብዙዎቹ መሥሪያ ቤቶች መጋዘኖች ፍተሻ ቢደረግባቸው አስደንጋጭ ነገሮች ያጋጥማሉ፡፡ ሰሞኑን የተሰማው በደረቅ ወደቦች የተከማቹ የመንግሥት ተቋማት ንብረቶች ጉዳይ እዚህ ላይ ሊነሳ ይገባል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባደረገው የመስክ ምልከታ፣ ከ61 ቀናት ጀምሮ እስከ ሦስት ዓመት ተኩል ድረስ ማንም ዞር ብሎ ያላያቸው በርካታ ኮንቴይነሮች በደረቅ ወደቦች ተከማችተዋል፡፡ መንግሥት በግል ድርጅቶች ላይ የሚወስደውን ዕርምጃ በራሱ ላይ መውሰድ ስላቃተው ብቻ፣ የአገር ጥሪት ሜዳ ላይ ይባክናል፡፡ የተጠያቂነት መጥፋት አንዱ ማሳያ ነው፡፡

የመንግሥት አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ መሥፈሩን መረዳት ያቃታቸው ሹማምንት ሳይቀሩ፣ መረጃ ሲጠየቁ ምላሽ ለመስጠት አይፈልጉም፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው ለምን  ተጠየቅን ይላሉ፡፡ የባሰባቸው ደግሞ ያስፈራራሉ፡፡ በሚዲያ ሥራ ውስጥ ጣልቃ በመግባት መሰናክል ይሆናሉ፡፡ ለተጠየቁት ግልጽ ጥያቄ በግልጽ ምላሽ መስጠት ሲገባቸው፣ ከጥያቄው ጀርባ የተደበቀ አጀንዳ አለ በማለት የመረጃ ነፃነት ሕጉን ይጋፋሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ አቅሙም ሆነ ተነሳሽነቱ ስለሌላቸው በተድበሰበሰ መንገድ ለማለፍ ይሞክራሉ፡፡ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በመጨፍለቅ ያደረሱት ጉዳት ምን ያህል አገርን ለአደጋ አጋልጦ እንደነበር እየዘነጉ፣ ዛሬም እዚህ ግባ በማይባል መሙለጭለጭ ችግር ይፈጥራሉ፡፡ የሕግ የበላይነት ማለት በሕጉ መሠረት ብቻ ኃላፊነትን መወጣት ማለት ነው፡፡ ይህ እየተዘነጋ ወይም ሆን ተብሎ እየታለፈ አገርን ችግር ውስጥ የሚከት አዙሪት ውስጥ ይገባል፡፡ ተጠያቂነት ሲጠፋ ራሳቸው ላይ ዘውድ ለመጫን የሚፈልጉ ይበረክታሉ፡፡

በአጠቃላይ ተጠያቂነት ሥራ አስፈጻሚውን መንግሥት፣ ሹማምንቱን፣ ፖለቲከኞችንና ሠራተኛውን ጭምር የሚመለከት ነው፡፡ እያንዳንዱ ተቋም በሕግ ተደንግጎ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ ሲደረግ፣ አሠራሩ ግልጽ ሆኖ ተጠያቂነቱም በዚያው ልክ ይታያል፡፡ አመራሩም ሆነ ፈጻሚው በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሲሠራ ሕግ ተከብሯል ይባላል፡፡ ተጠያቂነት ሳይኖር ግን የመንግሥትና የፓርቲ ሚና ይደበላለቃል፡፡ ሕግን ማክበር አይቻልም፡፡ ሕገወጥነትን መከላከል ዳገት ይሆናል፡፡ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይጣሳሉ፡፡ ሌብነት ይንሰራፋል፡፡ የአገር ሀብት ይባክናል፡፡ ፍትሕ ይደረመሳል፡፡ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል፡፡ ሰላም ይደፈርሳል፡፡ የአገር ገጽታ ይበላሻል፡፡ ብዙ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የፈለገውን ያህል መንገድ ቢገነባ፣ ሕንፃዎች ቢደረደሩ፣ ከተሞች ቢስፋፉና ልማቱ ቢመነደግ ግልጽነትና ተጠያቂነት የአገር ባህል መሆን ካቃታቸው ችግር ይፈጠራል፡፡ ለዚህም ነው ተጠያቂነት ከሌለ የቆሉት ጥሬ ይሆናል የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...