Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሦስት ጉልቻ

ሦስት ጉልቻ

ቀን:

የኅብረተሰብ መነሻው ቤተሰብ ሲሆን፣ መሠረቱም በተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚፈጠረው  የጋራ ሕይወት ነው፡፡ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት፣ የአካላዊ አንድነትና መንፈሳዊ ዉሕደት መገለጫ የሆነው ጋብቻ በኅብረተሰብም ይሁን በጎጆ ወጪዎች ዘንድ መሠረታዊ ትርጉም ያለው፣ ሰዎች ከአንድ የዕድሜ ክልል ወደሌላ የዕድሜ ክልል መሸጋገራቸውን የሚያረጋግጡበት፣ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖራቸው ተግባርና ኃላፊነት፣ ከበሬታና ተቀባይነት ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚቀየርበት፣ በግላዊ ሕይወታቸው ውስጥ ከራሳቸው አልፈው የሌላን ሰው ሕይወት የሚጋሩበትና የራሳቸውን የሚያጋሩበት ልዩ ምዕራፍ ነው፡፡

በብዙዎች ዘንድ በወጥነት የሚከወን ማኅበራዊ ሥርዓትና ክንዋኔው  ከቦታ ቦታ፣ ከባህል ባህል፣ ከአገር አገር ይለያያል፡፡ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ በአመዛኙ ሠርግ በሚደገስበት ወርኃ ሚያዝያ አጋጣሚ የስልጤ፣ የሐድያና የአሪ ብሔረሰቦች የሦስት ጉልቻ ከፊል ገጽታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

የአንትሮፖሎጂና የፎክሎር ባለሙያዎች የኤፍሬም አማረና እታገኘሁ አስረስ ቡድን በሠራው ጥናት እንደተመለከተው፣ በደቡብ ኦሞ ዞን በሚኖረው አሪ ብሔረሰብ ጋብቻ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አንድ ማኅበራዊ ክዋኔ ነው፡፡ ጋብቻ በዋነኛነት የሁለቱን  ተጋቢዎች ቅድመ ጋብቻ ትውውቅ፣ ወንዱ የሚፈልጋትን ሴት ካገኘ ለቤተሰቡ ሁኔታውን የመግለጽና ልጅቷን በአሳቻ ቦታ ቀጠሮ ወደራሱ ቤተሰቦች መንደር ይዞ መሄድ፣ ቀጥሎም ከወንዱ ቤተሰብ ወደ ልጅቱ ቤተሰቦች ሰው ልኮ ድምፅ አሰምቶ ወይም ተጣርቶ የቤተሰቡ አባላት ሳያዩት ተሰውሮ መሄድን፣ ቀጥሎም የጥሎሽ ወይም ኮይታ አከፋፈል ላይ በሁለቱ ቤተሰቦች መካከል ውይይት ማድረግን፣ ቀጥሎም ከኮይታው መካከል በተለይ ለልጅቱ እናት የሚሰጠው ልብስ እንዲሁም ለአባትየው የሚሰጠው የበግ ስጦታ ተጠቃሽ ሲሆኑ ለእናትየዋ የሚሰጠው ልስብ ተምሳሌትነቱን ልጅቱን ስታሳድ በሽንት ውስጥ ተኝታና ተቸግራ መሆኑን ሲያመለክት የበጓ ስጦታ ደግሞ እነሱ ካሺ የሚሉትን ደንብ ለመፈጸሚያ ጉምዝ በሚል ነው፡፡

የካሺ ደንብን ለመፈጸም ጉምዝ የሚሉት እንሰት ይከተፋል፣ ከሙርሲ እንደሚመጣ የሚነገርለት አፈር ጉምዛው ላይ ይነሰነሳል ቀጥሎም የቡና ቅጠል ጨው ተነስንሶበት ይጨመርበትና ለበጓ ይሰጣል፡፡ ከዚያም ልጅቱ ለፍሬ እንድትበቃ ትመረቃለች አባትየውም በልጁ ላይ የያዘው ቂም ካለ ይቅር ይላል፡፡ የካሺ ደንብ ካልተፈጸመና አባትየው ቂም ከቋጠረ አፈር አንስቶ በመበተን እንደሚራገምና ይህ ከሆነ ደግሞ ልጅቱ በትዳር ሕይወቷ ውርዴ ያጋጥማታል ተብሎ ስለሚታሰብ ደንቡ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ በብሔረሰቡ ኮይታ ተከፍሎ እንደተጠናቀቀ የውጭሚ (መልስ) ጥሪ ይደረጋል፡፡ የልጅቷ እናትም ከራሷና ከዘመድ አዝማድ አሰባስባ ጎጆ መውጫ (በአሲ) ለልጅቷ ትሰጣለች እነዚህ በብሔረሰቡ ጋብቻ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ክስተቶች ናቸው፡፡

ስልጤ

በስልጤ ዳዊቱ ድረ ገጽ እንደተሰነደው፣ በብሔረሰቡ ዘንድ ብዙ የጋብቻ ሥርዓት ዓይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው በስፋት የተለመደው የስምምነት ጋብቻ ነው፡፡ ይህ የጋብቻ ዓይነት የአግቢው ቤተሰብ ሽማግሌ ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች በመላክ በተገቢዎች ቤተሰብ ስምምነት የሚፈጸም ነው፡፡ ሁለተኛው የጋብቻ ዓይነት “ኩል” ይባላል፡፡ በዚህ የጋብቻ ሥርዓት ልጅቱም ሆነች ቤተሰቦቿ ሳያውቁ አግቢው ፈረስ ላይ ተቀምጦ ከነፈረሱ ወደ ልጅቱ ቤት በመግባት አለንጋውን በቤቱ ምሰሶ ላይ አስሮ ልጅቱ እንድትሰጠው ቤተሰቧን የሚያስገድድበት ነው፡፡

ሦስተኛው የጋብቻ ዓይነት “ጠለፋ” ሲሆንሸ ወላጅ ከላይ የተጠቀሰውን የኩል የጋብቻን ካልተቀበለ ልጅቱ ወይም ቤተሰቦቿ ልጅን ካልፈለጉ ወይም አግቢው ወጪና ጋጋታን በመፍራት የሚወስደው ሌላ አማራጭ ነው፡፡ በዚህም ልጅቱን ይዞ በመኮብለል በመጨረሻም ሽማግሌ ልኮ ጋብቻው የሚፈጽምበት ሥርዓት ነው፡፡

አራተኛው የጋብቻ ዓይነት “ኦጋ” የሚባል ሲሆን፣ በዚህ የጋብቻ ሥርዓት ሴቷ የመረጠችው ልጅ አባት ቤት ሰተት ብላ በመግባት ምሰሶ ላይ ቅቤ ቀብታ እንዲያገባት የምትጠይቅበት ሥርዓት ነው፡፡

አምስተኛው የጋብቻ ዓይነት የውርስ ጋብቻ የሚባል ሲሆን፣ በዚህ የጋብቻ ሥርዓት ባል ሲሞት የሟች ታላቅ ወይም ታናሽ ወንድም ወይም የቅርብ ዘመድ የሟችን ሚስት የሚያገባበት ወይም የሚወርስበት ሥርዓት ነው፡፡

ሐድያ

የሐድያ ብሔር የጋብቻ ሥርዓት በተመለከተ የጻፉት መኰንን ኤጃሞ እንደገለጹት፣ በቀድሞው የሐድያ ባህል አራት ዓይነት የጋብቻ አፈጻጸም ይደረጋል።

አንደኛ በመተጫጨት በአብዛኛው ለሴቷ ትዳር የሚሆን ባል የሚመርጡላት/የሚፈቅዱላት ወላጆቿ ናቸው። ለወንዶቹም ቢሆን የእገሌን ሴት ልጅ እንድታገባ ብለው የሚፈቅዱለትና የሚያጩለት ወላጆቹ ናቸው። ተጋቢዎቹ ወጣቶች ሊተዋወቁ ወይም ከነአካቴው የዓይን ትውውቅ እንኳ ላይኖራቸው ይችላል። ለልጃቸው የሚሆነውን ይበልጥ ወላጆች ያውቃሉ ተብሎ ስለሚታሰብ የልጆቹ ቀልብ ወደ ሌላ ወጣት ቢሆንም የወላጅን ፈቃድ ለመሙላት ተብሎ ሳያንገራግሩ ይጋባሉ።

ከወንዱ ወላጆች ወደ ሴቷ ቤተሰብ ሽማግሌ/አማላጅ ተልኮ ፈቃድ ይጠየቃል። ከልጅቱ ቤተሰብ በመጀመርያ ጥያቄ የእሽታ መልስ አይሰጥም። ምክንያቱም ወደፊት መፍቀዳቸው እንኳ ላይቀር ትንሽ ማንገራገርና ማለማመጥ ደጅ ማስጠናት ያስፈልጋል። ሁለተኛውና ዋናው ምክንያት ደግሞ ረዥም የጊዜ ቀጠሮ ይሰጥና ልጃቸውን የተጠየቀለት ወንድ ምን ዓይነት ሥነ ምግባር እንዳለው ይጠናል፡፡ በተለይም ሥራ ወዳድነቱን፣ ራሱን ችሎ ለመኖር ያለውን ብቃት፣ ቤተሰብ ለማስተዳደር ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆኑን በተቻለ መጠን አጠያይቀውም ቢሆን ያጠናሉ። እንደሆነ ካወቁ የተላኩትን ሽማግሌዎች በሚቀጥለው ቀጠሮ ‹‹አትድከሙ ወፏ አልቀናቻችሁም›› ብለው ይመልሷቸዋል። ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልግ መስሎ ከታያቸው በአማላጅነት ተልከው ለመጡት ሽማግሌዎች ረዥም የጊዜ ቀጠሮ ከተሰጣቸው በኋላ ስለልጁ ማንነት በደንብ ያጠኑታል። ወላጆቿ አማላጅ ሽማግሌ ልኮ የጠየቃት ልጅ እንዲያገባት የሚፈቅዱለት ከሆነ የሠርጉ ጊዜ ለዓመት ሊቀጠር ይችላል። የተዘራው እህል ደርሶ ከታጨደ ከተወቃና ጎተራ ከገባ በኋላ አገሩ ጥጋብ ሲሆን ለሠርግ ድግስ ያመቻል ተብሎ ረዥም ቀጠሮ ይሰጣል። ካልሆነ እንደ ሁኔታው ወላጆቿ ከተስማሙ በወራት/አጭር ጊዜ ቀጠሮ ሊድሯት ይችላሉ።

ቤተሰቦቿ ተስማምተው ከፈቀዱ ልጅቱን ለትዳር የሚፈልጋት ወንድ በሽማግሌ አማካይነት ጥሎሽ ይልካል። ጥሎሽ መስጠት በሐድያ ባህል የተለመደ ነው። ጥሎሽ መስጠት ማለት አንዳንዶች እንደሚተረጉሙት ሴቷ በገንዘብ ትሸጣለች/ትገዛለች ለማለት አይደለም። ሲጀመር ጥሎሽ መስጠት ማለት አግቢው ወንድ ለሚያገባት ልጃገረድና ለቤተሰቦቿ ያለውን አድናቆትና ክብር መግለጫ መንገድ ነው። የጥሎሹ መጠን አንድ ዓይነት ሳይሆን አቅሙ በሚፈቅድለት መጠን ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ግን በሴቷም በኩል ይሁን በወንድየው በኩል “እኔስ ከማን አንሼ” በሚል አስተሳሰብ ከአቅም በላይ ዕዳ ሊሆንባቸው ይችላል። ለጋብቻ ቀጠሮ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ወንዱ የራሱን ጎጆ የሚወጣበት “እልፍኝ ቤት” ይሠራል፣ የእርሻ ሥራውን ወይም ሌላ መተዳደሪያ የሚሆነውን ሥራ ያጧጧፋል። ሴቲቷም በበኩሏ ከጓደኞቿ/ሚዜዎቿ ጋር እየተጋገዘች ለቤቷ የሚሆን ልዮ ልዮ የእጅሥራዎችን እየሠራች ታከማቻለች።

ሙሽራውም ሆነ ሙሽሪት የጋብቻቸው ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ ጊዜው እየተቃረበ ሲሄድ ሴቷ ቆንጆ ሹርባ ተሠርታ ልዮ ልዩ ዓይነት ጌጣ ጌጦቿን ደርድራ፣ ቅቤ በአናቷ ላይ ተደርጎላት በሴት ጓደኞቿ ታጅባ ባህላዊ ዘፈን እየተዘፈነ በገበያ ቀን ወደ ገበያ ትወጣለች። እግረ መንገዷን ወደፊት ለቤቷ ይዛ ምትሄደውን ዕቃ ለመግዛት ሲሆን፣ የሚመለከቷት ሁሉ ልጅቱ ከአለባበሷና ያጌጠችበትን ልዩ ሁኔታ ተመልክተው ለትዳር ሠርጓ መቃረቡን ያውቃሉ ማለት ነው። ሠርግ ሊደረግ አንድ ወር ሲቀረው ወይም ትንሽ ቀደም ብሎም ሊሆን ይችላል፤ በምትኖርበት አካባቢ ከሚዜዎቿ/ጓደኞቿ ጋር ታጅባ ቤት ለቤት እየሄደች የሠርጓ ቀን ስለተቆረጠ ቀን ጀምሮ እቤታችን (ወላጆቿ ቤት) እየመጣችሁ ተጫወቱ፣ ሥራም ታግዙናላችሁ ብላ ጥሪ ታስተላልፋለች። በእግራቸው የሚሄዱ ትናንሽ ልጆች እንኳ ሳይቀሩ የተደረገላቸውን ጥሪ በማክበር ከሥራ መልስ ማምሻውን ወደ ቤቷ እየሄዱ ባህላዊ ዘፈኖችን ይጫወታሉ፡፡

ለሠርግ ዝግጅት የሚሆን የሚፈጭ፣ የሚቦካና የሚጋገር በሐድያ ባህል ሠርግ ሲዘጋጅ ሁለት ዓይነት ዝግጅት ይደረጋል። አንደኛው ዓይነት “ኪፋ” የሚባለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓይነት “እልሞቻ” ይባላል። “ኪፋ” የሚደገሰው ብዙ ሀብት ያላቸውና ዝነኛ የሆኑ ሰዎች ልጆቻቸውን ሲድሩ የሚያዘጋጁት ዓይነት የሠርግ ድግስ ነው።

ሁለተኛው “እልሞቻ” የተባለው የሠርግ ድግስ እላይ ከተገለጸው “ኪፋ” ከሚባለው የሠርግ ድግስ በዓይነት/በመጠንና በውሎ የተለየ ይሆናል። ሠርገኞች የዕለቱ ለት ሙሽራዋን ይዘው ለመመለስ ይችላሉ‹ የአጃቢ ሠርገኛ ብዛትም የተመጠነ ይሆናል። የሀብት መተያያ ሳይሆን አብዛኛው ሰው የሚደግሰው ዓይነት እንደ ቤተሰቡ የሀብት መጠን የሚመጥን ድግስ ሊሆን ይችላል። ለሙሽራዋ የሚዘጋጀው የስጦታ ዓይነትና ሌሎች ነገሮች በሙሉ በመለስተኛ ደረጃ ይዘጋጃል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...