Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ የፕሮጀክት ብድሮችን ወደ ልማት ባንክ ማዞሩ ድንጋጤ ፈጠረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለግል የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚሆኑ የብድር ጥያቄዎችን እንደማያስተናግድ ያስተላለፈው ውሳኔ ድንጋጤ ፈጠረ፡፡ የፕሮጀክት ብድር ጥያቄዎችም ወደ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንዲዛወሩ ተወስኗል፡፡

ባንኩ ባለፈው ሳምንት ሲመለከታቸው የነበሩትን ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የሚውሉ የብድር ጥያቄዎችን ላለማስተናገድ መወሰኑ ታውቋል፡፡ ሆኖም እነዚህ የብድር ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ እየተጠበቀባቸው፣ ሳይታሰብ አቋርጧል መባሉ የፕሮጀክት ብድር ጠያቂዎችን አደናግጧል፡፡

እንዲህ ያሉ የብድር ጥያቄዎች የሚስተናገዱት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አማካይነት እንደሆነ ከተገለጸላቸው የፕሮጀክት ብድር ጠያቂዎች አንዳንዶቹ፣ በተባሉት መሠረት ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ እያመለከቱ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተገኘው መረጃ መሠረት ለፕሮጀክቶች የሚውሉ የብድር ጥያቄዎች በልማት ባንክ በኩል እንዲስተናገዱ መወሰኑ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በመንግሥት ውሳኔ መሠረት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ እንዲያደርግ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ እንዲያበድር ነው የሚፈለገው፡፡

ይህ ውሳኔ ቀደም ብሎም የሚታወቅ እንደነበር ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ሆኖም አሠራሩ በጥልቀት ያልተሠራበት በመሆኑ፣ ክፍተቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡ የሰሞኑ ውሳኔም ውዥንብር የፈጠረው በዚህ ሳቢያ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለፕሮጀክቶችም ሆነ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆነውን የብድር ጥያቄ እንዳላቆመ ገልጾ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰሞኑን የጠራ መረጃ ይሰጥበታል ብሏል፡፡

ይህ የባንኩ ውሳኔ ተላለፈ ከተባለበት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከባንኩ ብድር ለማግኘት ከጠቅላላ የኢንቨስትመንት ወጪያቸው 30 በመቶ የሚሆነውን አሟልተው፣ ቀሪውን በባንኩ ብድር ለመሸፈን የሚያስችል ጥያቄ ያቀረቡ ናቸው ግራ የተጋቡት፡፡ ለንግድ ባንክ ላቀረቡት የብድር ጥያቄ አዎንታዊ መልስ እየጠበቁ፣ ባንኩ ጉዳያቸውን ወደ ልማት ባንክ መምራቱ አስደንግጧቸዋል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ በሆቴሎች፣ በተለያዩ ሕንፃ ግንባታዎችና የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች ላይ የተሰማሩ የንግድ ባንክን ብድር የሚሹ ኢንቨስተሮች ውሳኔው ውዥንብር ውስጥ እንደከተታቸው እየገለጹ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ብዙዎቹ ሆቴሎችና ትልልቅ ሕንፃዎች በፕሮጀክት ብድሮች የተገነቡ ሲሆን፣ አሁን በጅምር ላይ ያሉ ግንባታዎችም በ70/30 የፕሮጀክት ብድር አሰጣጥ መሠረት ከንግድ ባንክ ብድር ለማግኘት ጥያቄ ያቀረቡ ናቸው ተብሏል፡፡

የባንኩ ውሳኔ የሚፀና ከሆነ በርካታ ፕሮጀክቶች በእንጥልጥል ላይ ይቀራሉ የሚል ሥጋትም አሳድሯል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እነዚህን በቢሊዮኖች ግምት ያላቸውን የብድር ጥያቄዎች ለማስተናገድ አቅም ላይኖረው ይችላል ተብሎ መነገሩ ጉዳዩን አሳሳቢ ሳያደርገው አልቀረም፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገኘ መረጃ እንደሚለው ደግሞ፣ ንግድ ባንኮች ማበደር ያለባቸው ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ ነው፡፡ ለፕሮጀክቶች የሚሆነውን  ደግሞ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነው ማበደር ያለበት፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአንድ የግል ባንክ የሥራ ኃላፊ ንግድ ባንክ ከመነሻው የፕሮጀክት ብድር ማቅረብ አልነበረበትም ይላሉ፡፡ ባንኩ ከአወቃቀሩ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ያለበት እንደማንኛውም ንግድ ባንክ ለሥራ ማስኬጃ ብድር ነው፡፡ የፕሮጀክት ፋይናንስ ማቅረብ ያለበት ደግሞ የልማት ባንክ ነው፡፡ ልማት ባንክ እንደ ኢንቨስትመንት ባንክ ስለሆነ የሚሠራው፣ ይህ ቀድሞ ተግባራዊ መደረግ የነበረበት አሠራር ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አሁን ከንግድ ባንክ በመጠየቅ ላይ ያሉ የፕሮጀክት ብድሮችን ወደ ልማት ባንክ በፍጥነት ማዘዋወር፣ ብድር እየተሰጣቸው ያሉትን ባለሀብቶች ባለው ሁኔታ እያስተናገዱ ቀስ በቀስ ከልማት ባንክ ጋር ማቆራኘት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ልማት ባንክም ቀልጠፍ ብሎ ለመስተንግዶ መዘጋጀት እንዳለበት አክለዋል፡፡ በሌላ በኩል አሠራሮች ሲቀየሩ ግራ መጋባትና ውዥንብር ውስጥ የሚከቱ ድርጊቶችን መፍጠር ተገቢ ባለመሆኑ፣ ሒደቱ ፍፁም የተረጋጋ መሆን አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች