ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎች ያላንዳች እንግልት ወደ ቀያቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም፣ የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ተቀናጅተው እንዲሠሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ጠየቁ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. የተመላሾች ማስተባበሪያ ብሔራዊ ኮሚቴ በሚኒስትሩ መሪነት በመሰብሰብ፣ በጉዳዩ ላይ እስካሁን የተከናወነውን ሥራ ገምግሟል፡፡
የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ሕገወጥ የውጭ ዜጎች ወደ አገራቸው በሰላም እንዲወጡ በቅርቡ የ90 ቀናት የምሕረት አዋጅ ያወጣ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመውን ግብረ ኃይል እንቅስቃሴ በመገምገም በቀጣይነት ሊሠሩ ስለሚገቡ ጉዳዮች ዕቅድ አውጥቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደሚሉት ብሔራዊ ኮሚቴው እስካሁን ለተመላሾች መረጃ በመስጠት፣ በአካባቢው የማስተባበሪያ ቢሮዎች በመክፈትና ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አከናውኗል፡፡
መረጃን ተደራሽ በማድረግ በተደረገው እንቅስቃሴ እስካሁን በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ አገራቸው መምጣታቸው ታውቋል፡፡
ብሔራዊ ኮሚቴውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚያስተባብሩት ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤርፖርቶች ድርጅት፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ፖሊስንና ክልሎችን ያቀፈ ነው፡፡
በዚሁ ስብሰባ ኦሮሚያና አማራን ጨምሮ አንዳንድ ክልሎችም ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዜጎች ወደ አገራቸው በሰላም እንዲገቡ፣ ከዚያም ወደ ቀያቸው እንዲደርሱና እንዲቋቋሙ ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ ለዚሁ ዓላማ የተቋቋሙ ቢሮዎችንም በሰው ኃይል ለማጠናከር ተወስኗል፡፡
በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የምሕረቱ ተጠቃሚ ሆነው አገራቸው ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በቅርቡ ኢትዮጵያውያኑ በዕድሉ እየተጠቀሙ ባለመሆናቸው መንግሥትን እንዳሳሰበው መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ ከሚገኙ የሪያድና የጅዳ ኤምባሲዎች በተጨማሪ ሰባት ማስተባበሪያ ቢሮዎች ለዚሁ ዓላማ መቋቋማቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡