Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጥረት ኮርፖሬት የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ለመጠቅለል 35 በመቶ ክፍያ ፈጸመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኘው የኢንዶውመንት ኩባንያ ጥረት ኮርፖሬት፣ የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ለመጠቅለል የሚያስችለውን 35 በመቶ ክፍያ ፈጸመ፡፡ በዚህም መሠረት የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅን ለመግዛት ካቀረበው አጠቃላይ 315 ሚሊዮን ብር 35 በመቶ የሚሆነውን መክፈሉ ተገልጿል፡፡

ጥረት ኮርፖሬት የባህር ዳርና የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበራትን ለመግዛት የሚያስችለውን ሙሉ ክፍያ ለማጠናቀቅ፣ የሦስት ወራት ጊዜ እንዲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ ተፈቅዷል፡፡

ከአሁን ቀደም ድርጅቱ በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር በወጣው ጨረታ፣ ለሁለቱ አክሲዮን ማኅበራት 765 ሚሊዮን ብር ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሰጠው ውሳኔ ፋብሪካዎቹ ለጥረት እንዲተላለፉ ተወስኖ ነበር፡፡

ሚኒስቴሩ ጨረታውን ካወጣ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጣልቃ ገብነት ተጠይቆ ነበር፡፡ ይህም የሆነው በወቅቱ ጥረት ለሁለቱም ፋብሪካዎች አቅርቦት የነበረው ዋጋ ሚኒስቴሩ አቅርቦ ከነበረው ዋጋ በታች ሆኖ ስለተገኘ ነበር፡፡ በጊዜው ጥረት ለኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ 450 ሚሊዮን ብር፣ ለባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ደግሞ 315 ሚሊዮን ብር ነበር ያቀረበው፡፡

ከሚኒስቴሩ በተገኘ መረጃ መሠረት ባለፈው ሳምንት ሁለቱ አካላት ማለትም ጥረት ኮርፖሬትና ሚኒስቴሩ ስምምነት መፈራረማቸው ታውቋል፡፡ ስምምነቱም በሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ መሰለች ወዳጆና በጥረት ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ካሳ ተፈርሟል፡፡

በመቀጠል የንብረት ርክክብ እንደሚደረግ የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድአፍራሽ አሰፋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከአራት ዓመታት በፊት የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አጠቃላይ ቋሚ ሀብት 401 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጊዜ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የፋብሪካውን አቅም ለማሳደግ በመንግሥት ወጪ ተደርጓል፡፡ በ1970ዎቹ የተመሠረተው ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ባለፈው ዓመት ከወጪ ንግድ 1.95 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡

በተመሳሳይ ጊዜ የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሀብት 505 ሚሊዮን ብር ገደማ ነበር፡፡ በ1953 ዓ.ም. የተመሠረተው የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ከአሥር ዓመታት በፊት በቻይና ባለሀብቶች በኪራይ ለ18 ወራት ተይዞ ነበር፡፡ በ2004 ዓ.ም. መንግሥት 500 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ በማውጣት ፋብሪካውን አሻሽሎታል፡፡

በዚህም መሠረት ጥረት ባቀረበው ዋጋ ፋብሪካዎቹን እንዲረከብ ተፈቅዶለታል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ሚኒስቴሩ እንዲረከብ የጠየቀ ቢሆንም፣ ጥረት ግን የሦስት ወራት ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

በቀጣይ ጥረት ኮርፖሬት የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅን ለመግዛት የሚያስችለውን ክፍያ ይፈጽማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ጥረት ኮርፖሬት በ1987 ዓ.ም. ከብአዴንና ከ25 መሥራች አባላት በተገኘ 26.1 ሚሊዮን ብር ነበር የተመሠረተው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሥሩ ዳሸን ቢራን ጨምሮ 18 ኩባንያዎች ይገኛሉ፡፡

ከወራት በፊት እስከ ሦስት ወራት ድረስ ለጥረት እንደሚሰጠው አቶ ወንድአፍራሽ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ጥረት ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ሰባት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የምርት ሽያጭ ማከናወኑን ተገልጾ ነበር፡፡ የተጣራ 442.8 ሚሊዮን ትርፍ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡

በ700 ሚሊዮን ብር ገደማ ከመንግሥት የገዛቸውን የባህር ዳርና የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጨምሮ፣ ሌሎች የታቀዱ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ እ.ኤ.አ. በ2017 ለማስገባት እየተዘጋጀ መሆኑ ተነግሮ ነበር፡፡

ጥረት ሁለቱን ኩባንያዎች በሥሩ ለማድረግ ፋብሪካዎቹ ያለባቸውን ዕዳ አብሮ ይረከባል፡፡ ከአሁን ቀደም ሚኒስቴሩ ሁለቱን ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ ባወጣው ጨረታ፣ የግል ባለሀብቶች ጥረት ካቀረበው ያነሰ ዋጋ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህም አቶ ድንቁ ደያሳ የተባሉ ባለሀብት ሁለቱን ፋብሪካዎች ለመግዛት 606 ሚሊዮን ብር አቅርበው የነበረ ቢሆንም ሚኒስቴሩ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

አቶ ድንቁ ከሁለት ሳምንት በፊት የሶደሬ ሪዞርትን በመንግሥት ተይዞ የነበረውን 30 በመቶ ድርሻ በ90 ሚሊዮን ብር መጠቅለላቸው ይታወሳል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅት ሚኒስቴር ሒልተን ሆቴል ጨምሮ ሁለት ሆቴሎችን በመንግሥት ሥር እንዲቆዩ ወስኗል፡፡ በአልኮል መጠጥ፣ በወረቀት፣ እንዲሁም በእርሻና በትራንስፖርት የተሰማሩ አራት ድርጅቶችን ወደ ግል እንዲተላለፉም ለይቷል፡፡

ባለፈው ዓመት በነበረው አፈጻጸም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር 1.2 ቢሊዮን ብር ገቢ በሥሩ ካሉ የልማት ድርጅቶች ማግኘቱን መግለጹ አይዘነጋም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች