Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የግል ባንኮች ከ4.9 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፉ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የአገሪቱ የግል ባንኮች ለዓመታት በአትራፊነታቸው የዘለቁ መዝለቅ የቻሉ ሲሆን፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም በጠቅላላው ከታክስና ከሌሎች ተቀናሽ ወጪዎች በፊት ከ4.9 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገባቸው ታውቋል፡፡

  የባንኮችን የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን የሚያሳየው የመጀመርያ ደረጃ ግርድፍ ሪፖርት፣ 16ቱም የግል ባንኮች ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያስመዘገቡት፣ የትርፍ መጠን ከዓምናው ዘጠኝ ወራት ይልቅ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ያመለክታል፡፡

  እንደ መረጃው ከሆነ፣ 16ቱም ባንኮች አትራፊ ቢሆኑም አራት ባንኮች በዘጠኝ ወራት ያስመዘገቡት ትርፍ፣ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ካገኙት ትርፍ ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ አሳይቷል፡፡

  ባንኮቹ ከስድስት ሚሊዮን እስከ 248 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ጭማሪ ትርፍ እንዳስመዘገቡ መረጃው ይጠቁማል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ያስመዘገቡት ግን ባንኮች አዋሽ፣ ዳሸንና አቢሲኒያ ናቸው፡፡

  እንደ ሪፖርቱ ከሆነ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ከ986 ሚሊዮን ብር፣ ዳሸን ባንክ ከ814 ሚሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ ባንክ 502 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፍ ችለዋል፡፡ ሦስቱ ባንኮች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ያስመዘገቡት የትርፍ መጠን ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ በተለይ ዳሸን ባንክ ከ248 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ትርፍ ማግኘቱን ያሳያል፡፡ አዋሽ ባንክ ያገኘው ትርፍ ከዓምናው ዘጠኝ ወራት ጋር ሲነፃፀር ከ183 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳሳየ ለመረዳት ተችሏል፡፡ አቢሲኒያም የ129 ሚሊዮን ጭማሪ ትርፍ አግኝቷል፡፡

  ከሦስቱ ባንኮች ባሻገር፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገበው፣ ወጋገን ባንክ ነው፡፡ ወጋገን ባንክ በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከታክስና ከተቀናሾች በፊት ከ467 ሚሊዮን ብር በላይ አትርፏል፡፡

  ይህ የትርፍ መጠኑ ከዓምናው ይልቅ ከ166 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው የሚጠቁም ነው፡፡ ይህም ከዳሸንና ከአዋሽ ቀጥሎ የትርፍ መጠኑን በማሳደግ በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡

  የትርፍ መጠናቸውን ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ማሳደግ የቻሉት ሌሎቹ ባንኮች ብርሃን፣ ሕብረትና ንብ ናቸው፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ፣ ሕብረት ባንክ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 352 ሚሊዮን ብር፣ ንብ 435 ሚሊዮን እንዲሁም ብርሃን 351 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻላቸውን ይኸው ግርድፍ ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

  የአገሪቱ የግል ባንኮች በ2008 ሙሉውን በጀት ዓመት በጠቅላላው ያስመዘገቡት ትርፍ ከ6.05 ቢሊዮን ብር በላይ እንደነበር ይታወቃል፡፡

  በዚህ ዓመት ሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ድረስ የግል ባንኮች ጠቅላላ ሀብት መጠን ከ220 ቢሊዮን ብር በላይ ሊደርስ መቻሉ ታይቷል፡፡ ከፍተኛ ሀብት ካስመዘገቡት ውስጥ አዋሽ ባንክ በቀዳሚነት ሲቀመጥ፣ አጠቃላይ ሀብቱም 36.8 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ዳሸን 32.3 ቢሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ 23.4 ቢሊዮን ብር፣ ወጋገን 20.5 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ሕብረት ባንክ 20.8 ቢሊዮን ብር ያስመዘገበ ሀብት ማፍራት መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡

  እነዚህ ባንኮች በሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ያሳዩት የብድር ክምችትም ማደጉ ታይቷል፡፡ አዋሽ ባንክ 21.2 ቢሊዮን ብር ሲያስመዘግብ፣ ዳሸን 17.8 ቢሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ 13.4 ቢሊዮን ብር፣ ወጋገን 10.12 ቢሊዮን ብር፣ ሕብረት 11.01 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ንብ ባንክ 10.6 ቢሊዮን ብር ያስመዘገበ የብድር ክምችት እንዳላቸው ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡  

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -