Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትርጉም ተዛብቷል!

እነሆ መንገድ! ከሽሮ ሜዳ – ሜክሲኮ ወደ ጦር ኃይሎች ልንጓዝ ነው። “እዚህ ጋ ጠጋ! ጠጋ! ‘ማዘር’ እዚህ ተጠጉላቸው፤” ተለምዷዊ ቀጭን ትዕዛዝ ናት። ዛሬ ግን መብት አስከባሪ ገጥሞታል። “አልጠጋም! ለምድነው የምጠጋው? የከፈልኩህ ለአንድ መቀመጫዬ ብቻ መሰለህ?” ተጠጊ የተባለችው ወይዘሮ ብልጭ ብሎባታል። ከዓመት ዓመት ባርቆብን ግን እንዴት ልንሆን ነው? “ምናለበት በሁለቱም መቀመጫችን ተዘፍዝፈን ወያላና መንግሥትን ከማማት እርስ በርስ ብንተባበር? አይ ሐበሻ? ተቀምጦ ሰማይ ቀዶ መስፋት ብቻ?” ወያላው አጋዥ ለማግኘት አሳባሪ መንገዶችን በሙሉ በመጠቀም ላይ ነው። “ደግ አደረገ። እዚያ ያስለመዱህ ይጠጋጉልህ። ጊዜው የመጠጋጋት ነው ብለህ ከሆነ በጊዜ የማያምን ዜጋ አለ፤” ወይዘሮዋ እንደ እንዝርት ሾራለች። ሹረቷን ትክ ብሎ እያየ ያዞረው ደግሞ፣ “ምናለበት ብትጠጋና ብንንቀሳቀስ? ና ብሎ ከመደህየት ተጨናንቆ ማደግ አይሻልም? ይገርማል እናንተ?” ይላል አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት።

ከኋላችን ሦስተኛው ረድፍ ላይ ደግሞ “ይኼ ነው። በፍፁም እንዳትሰሚው፤” እያለ ኑሮ ጀምሮት መጠጥ እየጨረሰው ያለ ጎስቋላ  ጎልማሳ ያጉተመትማል። አጠገቡ ‘ማች በማች’ የለበሰች ዝንጥ ያለች ወጣት ቦርሳዋን እንቅ አድርጋ ታቅፋ አልሰማሁም፣ አላየሁም ጣቢያ ከፍታለች። መጨረሻ ወንበር አንድ አዛውንት፣ ሌላ አንድ ጎልማሳና ዕድሜያቸው በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገመቱ ወጣቶች ጎን ለጎን ተቀምጠዋል። ወያላው እልህ ይዞት አጠጋግቶ ሊያስቀምጣቸው የነበሩትን ተሳፋሪዎች አንዱን ጎማ ላይ አንዱን ከጋቢና ወንበር ጀርባና ሞተር ላይ አደላድሎ አስቀምጦ “ሳበው!” ብሎ በሩን ከረቸመ። ወይዘሮዋ በድል አድራጊነት ስሜት ፈገግ ብላ፣ “እኛን የሰለቸን ከእናንተ ጀምሮ ጉድለታችንና ክፍተታችንን ምክንያት አድርጎ ሙሴያችሁ ነኝ፣ ተቀበሉኝ፣ ተከተሉኝ፣ እመኑኝ የሚለን ሐሰተኛ ነብይ ብዛት ነው። ራሳችን ለራሳችን መብት ብንቆም መጀመርያውን መቼ በየአቅጣጫው ነጂ ይልክብን ነበር?” ብላ በራሷ ዓለም ጠፋች። ነገሩ ከምኔው የነጂና ተነጂ አተካራ ውስጥ እንደገባ ፈጣሪ ይወቀው!

ጉዟችን ተጀምሯል። ወያላው ሞተር ላይ ያስቀመጠው ተሳፋሪ ስልኩ ትጮሃለች። በስንት ስቃይ በስንት አሳር ካለችበት ታስሳ ወጣች። “ይኼ ሰውዬ ነዳጅና የከበሩ የተፈጥሮ ማዕድናት ላይ ቢሠራ ያው መጀመርያ ራሱን ከዚያ ምናልባት ራርቶ አገሩን ሊጠቅም የሚችል ሰው ይመስላል፤” ይላል ከጎኔ የተቀመጠው። ባለስልኩ፣ “ሃሎ!” የጆሯችን ታንቡር እስኪበሳ መጮህ ጀመረ። “ይሰማኛል። ቅድም እኮ ተቋረጠ። ምን ይታወቃል ሚሊዮን እያልኩ ሳወራ ቴሌ ትን ብሎት ይሆናላ! ሃሃሃ!” ገልመጥ ገልመጥ እያለ ያየናል። ቀጥሏል። “ስድስት ሚሊዮን እጄ ላይ አለ። ቀሪው እህል እጃችን ሲገባ በባንክ ትራንስፈር ይደረግልሃል ብለውኛል። አዎ ተፈራርመናል እንጂ፤” ስለሥራው ቀጠለ። ተሳፋሪው እያልጎመጎመ ወሬ ጀመረ።

“እህም ወይ ሚሊየን እንዲህ ሳናስበው አፋችን ይግባ?” አለች ከወያላው የተናቆረችው ወይዘሮ። “እኛ ያፋችን ነገር መቼ ቸገረን? የሆዳችን እንጂ የሚያንገዋልለን። እንይዘዋለን ባዶ። መቶ ብር ብን ስትል አትራራ። አብሮ በልቶ ጠጥቶ የሚንሸራተተው ወዳጅ በዛ ብለን ሳንጨርስ፣ በላባችን የምናመጣው ገንዘብ ረድኤተ ቢስ መሆኑ ባሰ፤” ትላለች አጠገቧ የተመቀጠች ደርባባ። ሦስተኛ ረድፍ ላይ ደግሞ ያ ጎስቋላ ጎልማሳ፣ “እኔ ግን  እንደ ምንም ብዬ ፌስታል ነው ማምረት ያለብኝ። አይመስልሽም?” ከመነጽር እስከ አልቦ በ‘ማች’ ያበደችውን ተሳፋሪ አስጨነቃት። ዞር ብላ፣ “አልገባኝም?” ከማለቷ፣ “በዚህ አያያዝ እንደ ዚምባቡዌ በዘንቢልና በፌስታል ገንዘብ ተሸክመን ጉልት መውጣታችን አይቀርማ! ዋናው ማደጋችን ነው፤” ሲላት እንሰማለን። ሰው ግን እንዴት አዙሮ ተኳሽ ሆኗል?!

ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። ወያላችን አንድ ሚሊየነር ሞተር ላይ አስቀምጦ እየተጓዘ መሆኑን ሲሰማ የባሰውን ተናደደ። “ወይ አይጠቀሙ ወይ አያስጠቅሙ፣ ወይ አይጠጉ ወይ አያስጠጉ፤” ይላል። ነጋዴው ስልኩን እንደ ቀጠለ ነው። ጋቢና የተቀመጡት ተሳፋሪዎች ሳይቀሩ ወያላውን ሰምተውት ኖሮ፣ “እባክህ በተጠጋጋ ብቻ አይደለም። ዕድል ያስፈልጋል። ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ሲሄድ የሚታለፍ አለ። የማይታይ። እንደኔ ያለው ደግሞ አለላችሁ በትንኝ የሚጋለጥ። ሌብነትም እኮ ‘ታለንት’ ይጠይቃል፤” አለ አንደኛው። “በቃ እኛ ግን መጠቃቀም፣ መጠጋጋት ስንባል የሚታየን ሌብነት ብቻ ነው? የሥራ ዕድል ማግኘት፣ በጎ በሆነ መንገድ መረዳዳት አይታየንም?” ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠችው አቋርጣ ገባች። “ሆሆ መጀመርያ ያለ ‘አይዲ’ የሚያስጠጋህ አለ እንዴ? የለም እኮ! እንደኛ ዓይነቱ ከምኑም የሌለበት ወይ ግንባር የለው ወይ የሚጋጨው ‘ቻፓ’ ዝርዝር ሳንቲሙን እያቃጨለ ዕድሜው በታክሲ ሠልፍ ያልቃል። ምናልባት ከቀናህ ደህሞ አገርህ በሀብት ከ184 አገሮች 171ኛ ሆነች የሚል ዜና ቢመረቅልህ ነው። በማትሞቀው እሳት አገርህ ደረጃ ስትመደብ አንተም ቶሎ ብለህ ምድብህን ማስተካከል ነው፤” ከጎኔ የተቀመጠው ይለፈልፍብኛል።

ይኼን ሲል የሰማው ቀጭኑ ጎልማሳ “ማስተካከል ካልቻልክስ? ምድቡ የሞት ምድብ ከሆነስ?” ብሎ መጣብን። “አሁን ይኼ ጥያቄ ነው? ልማታዊ ኑሮ ካቃተህ ልማታዊ ሞት መሞት ነዋ፤” ብሎ የተሳፋሪውን ወሽመጥ በጠሰው። “ልማታዊ ኑሮን እያየነው ነው፣ ልማታዊ ሞት ደግሞ እንዴት ያለ ነው?” ሲሉ አዛውንቱ፣ “መንግሥት ሳያሳሙ ቀባሪ ሳያስቸግሩ ‹ሳይለንት› ሆኖ ማለፍ ማለት ነዋ። ሌላ ምን ይሆናል? ወይ ስም ሳያስነሱ መመንተፍ ወይ ተረስቶ ማለፍ ነው፤” ብትል ቆንጂት ተሳፋሪው ተገርሞ እየተገላመጠ አያት። ብሶት በተዘራና በተጠማ ብቻ ነው ያለው ግን ማን ይሆን?

ወያላችን መልስ መመለስ ጀምሯል። “ሙጀሌ ለበላሽ ፎክች ፎክች ላለሽ፣ ሸፋፋው መንገድ ነው ገዳዳው ትያለሽ’ አሉ። እንዲያው እኮ፤” ይላሉ ጠና ያሉ ሴት ከሾፌሩ ጀርባ ቦታ እየያዙ። “ሙጀሌ ደግሞ ምንድነው?” ይላል አጠገባቸው የተቀመጠ ልጅ እግር። “ምን ይሠራልሃል ካልበላህ? ዕድሜ ለቻይና ጫማና መንገድ እናንተ የዛሬ ልጆች እኮ በአስተሳሰብ እንጂ በሙጀሌ አካሄዳችሁ አይበላሽም፤” ይሉታል። “አይ እማማ ያው ያለፈው መጪውን በቀና መንፈስ የማየት ‘ፎብያ’ ኖሮበት እንጂ እንደየዘመኑ፣ ገዳዳነት የሚያጣው ትውልድ አለ?” ሲላቸው፣ “ለነገር ሲሆንማ ለመልስ አንደኞች ናችሁ። ምናለበት ታዲያ በነካ እጃችሁ የዚህችን አገር ቋጠሮ መፍታት ብትሞክሩ? እ? ሞክሩ እስኪ! ቅዱስ ያሬድ አንዲት ትል ወድቃ ስትነሳ ወድቃ ስትነሳ አተኩሮ እያየ ከሙከራና ከጥረት ብዛት ስኬት እንዳለ ገባው። እህ የእሱ ወገን ሆናችሁ ሳለ በሰው ወርቅና ዜማ ካልደመቅን እያላችሁ በእሳት መንኮራኩር ካልተነጠቅን ከምትሉ፣ ምናለበት ከትል አብዝቶ ከሚበልጠው የሰው ልጅ ታሪክ ተምራችሁ ለአገር ብትጠቅሙ?” ብለው እንደ መማፀንም እንደ መቆጣትም አሉ።

“መቼ እንቢ አልን ብለው ነው? ከብልሆችና ከጠቢባን ታሪክ ልንማር ስንታትር የአሸናፊዎች ሽለላ፣ የአርበኞች ቀረርቶ እየበጠበጠ አስክሮን እኮ ነው የተሳከረብን፤” ብላ መሀል መቀመጫ ላይ ከእጮኛዋ ጋር የተቀመጠች ደመ ግቡ እንደ ዘበት ጣልቃ ገባች። ወይዘሮዋ ዘወር ብለው ዓይተዋት ፊታቸውን ሳይመልሱ ሦስተኛው ረድፍ አጠገቤ የተቀመጡ አዛውንት፣ “ቢቀና ባይቀና ምን ገዶኝ ለመንገድ፣ ደግ አበጀው ብሎ ክፉ ሊረግጥበት፤” ብለው ገጠሙ። በዕድሜ በጥቂት እንደሚያንሱዋቸው የሚያስታውቁት ወይዘሮ፣ “ክፉማ ክፉ ነው ውለታ መቼ ያውቃል፣ መንገድ እየሄደ በደግ ይራመዳል፤” አሉና ታክሲያችን የቅኔ ቤት ቢያስመስሉት፣ የገባውም ያልገባውም ግራ የተጋባውም ጭምር አጨበጨበ። ሽፍፍ ሽፍፍ ከሚል ጨዋታ ደግሞ አንደኛውን ሙጀሌን ማከክ ይሻላል መሰል?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ሾፌራችን ነገራችን ስልችቶት ድምፁን ከፍ ባደረገው  ራዲዮ የቢራ ማስታወቂያ ከእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ጋር ይንጋጋል። “በዓሉ አላለፈም እንዴ?” ትላለች አንዷ። “መቼ መጣ? ገና ዓመት ይቀረው የለም እንዴ?” ባዩ ጎልማሳው ነው። ጠያቂያ ፈገግ ብላ፣ “ይኼ ነው ጨዋታ፤” ስትለው፣ “አላጫውተን ብለው እንጂ ስንጫወትማ ኤል ክላሲኮን እናስንቅ ነበር፤” አላት። “ምን ክላሲኮ ነው ያልከው?” አዛውንቷ ጠየቁ። “ኤል ክላሲኮ!” አለ ወያላው ጣልቃ ገብቶ። “አንተን ማን ጠየቀህ? ሆሆ። ምንድነው ግን እንዲህ ይኼ ዘመን ሳይጠሩዋቸው አቤት በሚሉ ሰዎች የተጨናነቀው?” ሲሉ ጎልማሳው ለስለስ ብሎ፣ “ምናልባት አንዳንዴ ኔትወርኩ ‘ክላሽ’ ስለሚያደርግ ይሆናል፤” አላቸው። “ጉድ ፈላ! ኔትወርኩም ታጣቂ ነው እንዴ? እኔኮ ሲቪል ነበር የሚመስለኝ?” ሲሉ አዛውንቷ ‘ክላሽ’ ጠመንጃ መስሏቸው ታክሲያችን በሳቅ ወጀብ ተንቀጠቀጠች። ወያላው ስለሜሲና ሮናልዶ ሊያወራ እንደቋመጠ፣ ጎልማሳው ‘ተጫዋች ሽማግሌ አንቱ ሳይባል ያረጃል’ የሚሉት ተረት ለእሱ እንደ ተተረተ ሊያሳየን የጀመረው የጨዋታ አገባብ እንደከሸፈ፣ አዛውንቷ እንግሊዝኛና አማርኛ ተጠላልፎባቸው ትርጉም እንዳዛቡ ‘መጨረሻ’ ተብለን ወረድን። ትርጉም ሲዛባ መልሱን መንገድ ላይ ፈልጉ። መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት