በስንታየሁ ግርማ
አሁን ያለንበት ዘመን ግሎባላይዜሽን ይሉታል፡፡ በአጭሩ ግሎባላይዜሽን ማለት በምርትና በገበያ በጥቅሉ የተሳሳረች ዓለም ለማለት ነው፡፡ ግሎባላይዜሽን ብሔራዊ ኢኮኖሚን ወደ ተያያዙና ተደጋጋፊ (ተመጋጋቢ) ወደ ሆነች ዓለም ኢኮኖሚ መቀየር ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ግሎባላይዜሽን ማለት ‘አሜሪካናይዜሽን’ ማለት ነው የሚሉ አሉ፡፡ አባባሉ አዲሱ የዓለም ሥርዓት ወይንም የአሜሪካ ሥርዓት ማለት ነው ይሉታል፡፡ ይሁንና በዚሁ ሥርዓት አሜሪካ ብቸኛ ተጠቃሚ ናት ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ከምንም ተነስታ በዓለም ቁጥር ሁለት ኢኮኖሚ በመሆን በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐችን ከድህነት ያወጣችው ቻይናም የግሎባላይዜሽን ውጤት ናትና፡፡
ግሎባል ገበያ
ግሎባላይዜሽን ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡፡ እነሱም ግሎባል ገበያና ግሎባል ምርት የሚባሉት ናቸው፡፡ ግሎባል ገበያ ማለት በታሪክ በተለያዩና በተነጣጠሉ ገበያዎች ወደ አንድ ትልቅ ገበያ የተለወጡበት ማለት ነው፡፡ በዓለም ላይ ሸማቾች የምርት ፍላጐታቸውና ምርጫቸው እጅግ ሁሉ የተቀራረበ በመምጣቱ ግሎባል ምርት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ግሎባል ገበያ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ በግሎባል ገበያ ተቀባይነት ካገኙ ምርቶች መካከል ኮካኮላ፣ ማክዶናልድ፣ ሊቫይስ ጂንስና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሜሪካ ኤክስፖርት ከሚያደርጉ ኩባንያዎች መካከለ 97 በመቶ ትንንሾች ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1987 እና በ1997 በአሜሪካ ከ100 በታች ያላቸው ሠራተኞች በእጥፍ አድረገው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በዘመነ ግሎባላይዜሽን በትልልቅ ብቻ ሳይሆን በትንንሽ ድርጅቶችም መወዳደር እንደሚቻል ነው የሚያሳዩት፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ወደ ቻይናና ሆንግ ኰንግ በ1990ዎችና ኤክስፖርት ካደረጉት መካከል 40 በመቶ ይሸፍናሉ፡፡
ብሔራዊ ገበያዎች ለግሎባል ገበያ ቦታቸውን እየሰጡ ናቸው፡፡ በብሔራዊ ገበያ አሁንም የተጠቃሚዎች ምርጫ፣ መለያየት፣ የሥርጭት ሁኔታ፣ በባህል ላይ የተመሠረቱ የእሴት ልዩነቶችና ብሔራዊ ገቢዎች ለግሎባል ገበያ ቦታቸውን እየሰጡ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በስትራቴጂክ ማርኬቲንግ ዕቅዳቸው እነዚህን ማጣጣም ችለዋል፡፡ ለምሳሌ የመኪና ፋብሪካዎች የተለያዩ ሞዴሎች ለተለያዩ አገሮች እንደ አካባቢው የነዳጅ ዋጋ የገበያ መጠን፣ የትራፊክ ሁኔታና የባህል እሴቶች ግምት ውስጥ በማስገባት ያቀርባሉ፡፡ ቻይና ለአፍሪካና ለአሜሪካ የምታቀርባቸው ምርቶች በሸማች የመግዛት አቅም ላይ ተንተርሰው እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡
በግሎባላይዜሽን ከፍተኛና የማይታመን ውድድር በመኖሩ ሸማቾች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ የሸማቾች ምርቶች የኢንዱስትሪ ዕቃዎችና የፋይናንስ አገልግሎት ዋነኛው ገጽታቸው ከአገር አገር ከፍተኛ ውድድር ማጋጠሙ ነው፡፡ ኮካ ኮላ ከፔፕሲ፣ ፎርድ ከቶዮታ፣ ቦይንግ ከኤርባስ፣ ወዘተ በሞት ሽረት ወድድር ላይ ናቸው፡፡ ለብዙ ኩባንያዎች የአሜሪካ የቻይና የእንግሊዝ ገበያ ማለት ትርጉም የለሽ እየሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም በግሎባል ገበያ እየተቀየሩ ስለሆነ ነው፡፡
ግሎባል ምርት
ግሎባል ምርት ማለት ምርትና አገልግሎትን የተለየዩ አገሮች ከብሔራዊ አዋጭነት አኳያ ሲያመርቱ ነው፡፡ አዋጭነቱ በዋናነኝነት በዋጋና በጥራት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አንዱ አገር የአንድን ምርት የተወሰነ ክፍል በማምረት በዋጋ አዋጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው አገር የተመሳሳይ ምርትን የተለያዩ ክፍሎች በማምረት ተወዳዳሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ኩባንያዎች ይህንን በማድረጋቸው አጠቃላይ ወጪያቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሱ ነው፡፡ የምርት አቅርቦታቸውንና ጥራታቸውንም ለማሻሻል እየረዱ ናቸው፡፡ ከዚያም በተቀናቃኛቸው ላይ የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል፡፡ ቦይንግ 777 ለምሳሌ ብንወስድ 132,500 ክፍሎች አሉት፡፡ በ545 አቅራቢዎች ይመረታሉ፡፡ የተለያዩ ክፍሎች በተለያዩ አገሮች የሚሠሩበት ምክንያት እነዚህ አቅራቢዎች የተለያዩ ክፍሎችን በማምረት በጣም የተሻሉ ስለሆኑና አዋጭ ስለሆነ ነው፡፡ ስምንት የጃፓን አቅራቢዎች የቦይንግ በርን ሲያመርቱ፣ ሦስት የጣሊያን አቅራቢዎች የቦይንግ ክንፍ ሊፍት ያመርታሉ፡፡ በሲንጋፖርም የሚመረት ክፍል አለ፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን ብራንዱ የአሜሪካ ቢሆንም ቦይንግ የአሜሪካ ምርት ሳይሆን የዓለም ምርት እየሆነ ነው ማለት ነው፡፡
የተለያዩ ምርቶችን በተለያዩ አገሮች ማምረት ለትልልቅ ምርቶች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ የአነስተኞቹም ጭምር እንጂ፡፡ ለምሳሌ ስዋን ኦፕቲካል የዓይን መነጽር አምራች ድርጅት ነው፡፡ መቀመጫው አሜሪካ ነው፡፡ ዓመታዊ ሽያጩ ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የስዋን መነጽሮች የተለያዩ ክፍሎች በሆንግ ኮንግ፣ በቻይና፣ በጃፓን፣ በፈረንሣይና በጣሊያን ይመረታሉ፡፡ ይህንን በማድረጉ ስዋን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ችሏል፡፡ በአጠቃላይ የስዋንም ሆነ የቦይንግ 777 ልምድ የሚያሳዩን ስለአሜሪካ ምርት ሳይሆን ስለዓለም ምርት ነው፡፡
ምንም እንኳን ዓለም በምርቶችና በገበያዎች በጥብቅ እየተሳሰረች ቢሆንም፣ አሁንም የሚያገጥሙ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች አሉ፡፡ መደበኛ የሆኑና ያልሆኑ የንግድ መሰናክሎች አሁንም በአገሮች መካከል ይታያሉ፡፡ የትራንስፖርት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መዋዠቅ፣ የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ መሠረታዊ ችግሮች አለመፈታት፣ ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ሥጋቶች፣ እንደ ትራምፕ ዓይነት መሪዎች በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በቀኝና በግራ ክንፍ ፓርቲዎች የበላይነት ማግኘታቸው፣ በበለፀጉት አገሮችና በደሃ አገሮች መካከል ያለው የገቢ ልዩነት እንደታሰበው እየጠበበ አለመምጣት፣ በምዕራቡ ዓለም ያለው በድሆችና በሀብታሞች መካከል ያለው የገቢ ልዩነት እየሰፋ መሄድ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የግሎባላይዜሽን መንስዔዎች
ለግሎበላይዜሽን ማደግና መስፋፋት የተለያዩ ምሁራን የተለያዩ ትንታኔዎች ይሰጣሉ፡፡ በአብዛኛው ግን ስምምነት የተደረሰባቸው ምክንያቶች ሁለት ናቸው፡፡ አንዳቸው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በምርቶችና በአገልግሎቶች ላይ ተጥሎ የነበረው ቀረጥ፣ ኰታና የመሳሰሉት የንግድ መሰናክሎች በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሱ መምጣታቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ የቴክኖሎጂ ዕድገት በተለይም የኮሙዩኒኬሽን በኢንፎርሜሽን ፕሮሰሲንግና በትራንስፖርት የታየው የቴክኖሎጂ ለውጥ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1920ዎቹ እና በ1930ዎች ብዙ አገሮች በዓለም ንግድና ኢንቨስትመንት ላይ ከባድ መሰናክሎች አድርገው ነበር፡፡ መሰናክሎቹም በከፍተኛ ቀረጥና በኰታ መልክ የሚገለጹ ነበሩ፡፡ ዓላማው የአገር ውስጥ ምርትን ከውድድር ለመከላከል ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አገሮችን ከፍተኛ ቀረጥ ወደ መጣል ውድድር ውስጥ አስገብቷቸው ነበር፡፡ ይህም በዓለም ላይ ከፍተኛ የፍላጐት መቀነስን በማምጣት የ1930ዎቹን የኢኮኖሚ ውድቀት አስከትሎ ነበር፡፡
ከዚህ የኢኮኖሚ ድቀት በመማር በአሜሪካ መሪነት አገሮች የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅፋቶች በሒደት ለመቀነስ ተስማሙ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1993 በኡራጋይ የዓለም የንግድ ድርጅትን አቋቋሙ፡፡ ድርጅቱ የዓለም ንግድን በተመለከተ ፖሊሲዎችን ያወጣል፡፡ 125 አገሮችም ድርጅቱን ተቀላቅለዋል፡፡ በአገሮች መካከልም ያሉ የንግድ አለመግባባቶችንም ይፈታል፡፡ በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ አገሮች መካከል ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚገድቡ ተግባራትን ለመቀነስ (ለማስወገድ) ስምምነት አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት ምርቶች የዓለም ገበያን ማደግ አፋጥነውታል፡፡ የዓለም ገበያና የምርት መስፋፋት የዓለም ንግድንና ምርትን በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ ግሎባላይዜሽን አገሮችን በጥብቅ አስተሳስሯል፡፡
ግሎባላይዜሽን ምርትንና አገልግሎትን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ ቢሆንም፣ አሁንም በጥርጣሬ የሚያዩት አሉ፡፡ ግሎባላይዜሽን ማለት አዲሱ የዓለም ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓትም የአሜሪካ ነው፡፡ ሥርዓትም ሳይሆን ሥርዓተ አልበኝነት ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ በኢራቅ ያደረገችውን ጣልቃ ገብነትን በማስታወስ (ያለ ተመድ ዕውቅና መሆኑ) ልብ ይሏል፡፡
ያም ሆነ ይህ ግሎባላይዜሽን የዓለማችን እውነታ እየሆነ ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ እንዳሉት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የሥርዓት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ቻይና ያሉ ዝሆኖችን ያሳደገ ሥርዓት ኢትዮጵያን የማያሳድግበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ራሳቸው እንደሚሉት ከግሎባላይዜሽን ሥርዓት ውጭ መሆን ከእግር ኳስ ሜዳ ቀርቶ በፎርፌ መሸነፍ ነው፡፡ ከግሎባላይዜሽን ውጪ መሆን እንደ ሰሜን ኮሪያ ተመፅዋች መሆን ነው፡፡ ሰሜን ኮሪያ ያላትን የኔክሌር ኃይል ለማስፈራሪያነት በመጠቀም በዓመት በነፍስ ወከፍ ከደቡብ ኮሪያ ከ3,000 ዶላር በላይ ዕርዳታ ታገኛለች፡፡
በግሎባላይዜሽን ማደግ እንደሚቻል ቻይና በተግባር ስላሳየች፣ ከእንግዲህ ስለጉዳዩ መነጋገር የትወራ እንጂ የትግበራ አይደለም፡፡ ስለዚህ በግላባይዜሽን አዋጭነታችን በመለየት በጥብቅ መሳተፍ ይኖርብናል ብለው የነበሩት አቶ መለስ ናቸው፡፡ ”የእስያ ነብሮች” ከሚባሉትም የምንማረው ይኼንኑ ነው፡፡ እነዚህ በዓለም አስደማሚ የሆነ ዕድገት ያስመዘገቡ የእስያ አገሮች ለዕድገታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረገው መካከል፣ ኤክስፖርት መር ፖሊሲ መከተላቸው ነው፡፡ እንደ ኮሪያ የመሳሰሉት አገሮች ለባለሀብቱ በየዓመቱ የኤስክፖርት ኰታ ይሰጡት ነበር፡፡ ኮታውን ካሳካ የተለያዩ ማበረታቻዎች ይሰጡ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ለአገር ውስጥ ምርቶች የተፈቀዱትን ጭምር ለኤስክስፖርት አድራጊዎች ሰጡ፡፡ ኰታውን ካላሳኩ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቅጣቶች ተገበሩ፡፡ ኮሪያም ስኬታማ ሆነች፣ ታይዋንና ሌሎች እሷን ተከትለው አደጉ፡፡
ኢትዮጵያን ይህንን ፈለግ መከተል ትችላለች፡፡ አሰሱንም ገሰሱንም ወደ ውጭ መላክ ሳይሆን በጥናት ላይ ተመሥርቶ አንፃራዊ ብልጫችንን በመለየት መወዳደር ነው፡፡ ለምሳሌ በዓለም ላይ 90 ከመቶ የሚሆነውን ጤፍ እናመርታለን፡፡ ጤፍ በንጥረ ነገር የበለፀገና የተለየዩ የጤና ጥቅሞች እንዳሉት በምዕራባውያን ተመራማሪዎች ሳይቀር እየተረጋገጠ ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም በሚመገቡት ምግብ ምክንያት ከልክ ያለፈ ውፍረት የጤና፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ችግር እየሆነ ነው፡፡ ሸማቾች ስኳር በበዛባቸው ምግቦች ምክንያት የራሳቸውና የልጆቻቸው ጤንነት አደጋ ላይ እየወደቀ ስለሆነ፣ መንግሥት በማስታወቂያ ላይ አዲስ ሕግ እንዲያወጣ እየወተወቱ ነው፡፡ ከፍተኛ ቀረጥም በእነዚህ ምርቶች ላይ እንዲጣል የመብት ተሟጋቾች እየወተወቱ ነው፡፡ አሜሪካ በዚህ ምክንያት በየዓመቱ ከ147 እስከ 210 ቢሊዮን ዶላር እያወጣች መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እነ ቪክቶሪያ ቤካም የመሳሰሉት ዝነኞች ጤፍ ካለው ጠቀሜታ አንፃር ምርጫቸው እየሆነ ነው፡፡
ጋርዲያንና ኒዮርክ ታይምስም ስለጤፍ ጠቀሜታዎች እያተቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ኒዮርክ ታይምስ እ.ኤ.አ. ኦገስት 16 ቀን 2016 “is Teff the New Super Grain?” በሚል ርዕሰ አንቀጽ ስለጤፍ ጠቀሜታዎች አስነብቧል፡፡ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የማስተዋወቅ አቅማችንን ማሳደግ ይገባል፡፡ በመጀመሪያ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች ያሉበት ቡድን ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያ ያላትን አንፃራዊ ብልጫ በጥናት እንዲለዩ መደረግ አለበት፡፡ በመቀጠል የጥንካሬ፣ የድክመት፣ የመልካም አጋጣሚዎችና የሥጋቶች ትንተና በመካሄድ ወደ ሥራ መግባት ይኖርበታል፡፡
የኢትዮጵያን መለያ ወይንም ብራንድ ለማስተዋወቅ የሚዋቀረው ቡድንና የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚከተሉት ቢሆኑ ይመረጣል፡፡
- ከመንግሥት፣ ከባለሀብቶች/ኤክስፖርተሮች፣ ከአርት፣ ከትምህርት ተቋማት፣ ከሚዲያ . . . ሰዎች ቢሰባሰቡ፣
- ብራንዱ በውጭ ዓለም እንዴት እንደሚታይ የተለያዩ የጥናት ዘዴዎችን በመጠቀም ማወቅ፣
- የአገሪቱን ገጽታ ጠንካራና ደካማ ጐኖች ለመለየት ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና አጋሮች ጋር አቀፍ ምክክር ማካሄድና ስምምነት ላይ መድረስ፣
- ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ የሚረዳ ማዕከላዊ ሐሳብ ከባለሙያዎች ጋር በመሆን መለየት፣ ሌሎች ፕሮግራሞችም የሚመሩበት ማድረግ፣ ዋናው ሐሳብ የኢትዮጵያ የተለየ መለያ ባህሪ የያዘ መሆን አለበት፣
- ዋነኛው ሐሳብ የሚተዋወቅባቸውን ዘዴዎች ሎጐን ጨምሮ በመለየት ማስተዋወቅ፣
- ቱሪስቶችን ለመሳብ፣ ኢንቨስተሮችን ለመማረክ፣ የኤክስፖርት ምርቶች በውጭ ገበያ ተቀባይነት እንዲያገኙ እንደ ተቀባዮች ባህሪ መልዕክቶች በማዘጋጀት አቀናጅቶ ማሠራጨት፣ የአሠራሩን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ አገናኝ ቡድን ማቋቋም ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡
- ፡- ጸሐፊው የፌደራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡