ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማሳጣታቸው ተጠቁሟል
ቀደም ሲል የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር (አሁን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር) የቡና ጥራት ምርመራና ደረጃ ምደባ ማዕከል የብቃት ማረጋገጫ ቡድን መሪ የነበሩት አቶ ሁምኔሳ አብደታና የብቃት ማረጋገጫ ቡድን አባል አቶ ታምራት ኃይሌ፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ ተመሠረተባቸው። ከእነሱ ጋር በግብረ አበርነት የተጠረጠሩ የቡና ነጋዴዎች መሆናቸው የተገለጸው አቶ አብዱልቃድር ጀማል፣ ሰሚራ ተጃኒ፣ አህመድ ረታና ጀማል ሰይድ የሚባሉ ግለሰቦችም በክሱ ተካተዋል።
ሁለቱ የሚኒስቴሩ ባልደረቦች ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆንና የተሰጣቸውን ሥልጣን ያላግባብ በመጠቀም፣ አገሪቱ ከቡና ንግድ ገቢ ማግኘት የነበረባትን 828,352 ዶላር ወይም 15,243,514 ብር የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ ማድረጋቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል።
ሰሚራ የተባሉት አራተኛ ተከሳሽ የቡና ላኪነት የብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው፣ አብዱልቃድር የተባሉት ሦስተኛ ተከሳሽ ውክልና ሲጠይቁ የሚኒስቴሩ ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ መሥፈርቶችን ለመወሰን የወጣውን
መመርያ መተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል። ከመሥፈርቶቹ የተወሰኑት ለሥራው በቂ ካፒታል መኖሩንና ድርጅቱ የተሟሉ ሠራተኞች በቋሚነት መቅጠሩን የቅጥር ውል ማስረጃ ቀርቦ ሳይረጋገጥ፣ ኃላፊዎቹ ሁለት ሠራተኞች የተቀጠሩ በማስመሰል የትምህርት ማስረጃ ሰርተፊኬት ብቻ በማያያዝ የብቃት ማስረጃ እንዲሰጣቸው መፍቀዳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል።
የሚኒስቴሩ ሠራተኞች የፈጸሙትን ስህተት በመጠቀም ሰሚራ ተጃኒ (ሦስተኛ ተከሳሽ) ቡና ለመላክ ብቁ መሆናቸው ሲረጋገጥላቸው፣ ሦስተኛ ተከሳሽ አቶ አብዱልቃድር መሥፈርቱን ሳያሟሉ ንግድ ፈቃድ በማውጣት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገዙትን ቡና ወደ ውጭ መላክ ሲገባቸው፣ አገር ውስጥ በመሸጥ መንግሥት ማግኘት ይገባው የነበረውን 828,352 ዶላር ወይም 15,242,514 ብር የውጭ ምንዛሪ በማሳጣታቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል።
በመሆኑም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሳቸው ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውንና በሕጋዊ ነጋዴዎች ላይ የግብይት ፍትሐዊነት ላይ ተፅዕኖ በማሳደራቸው ክስ እንደ ተመሠረተባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል።