Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ምንም ዓይነት ድርድር አላደረገም››

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ምንም ዓይነት ድርድር አለማድረጉንና የአቋም ለውጥ እንዳላደረገ፣ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ለሪፖርተር ጋዜጣ በላከው መግለጫ አስታወቀ::‹‹የማዕድን ቦታ እንዲያስረክቡ የታዘዙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከኦሮሚያ ጋር በመደራደር ይዞታቸውን አስከበሩ›› በሚል ርዕስ በሚያዚያ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ዕትም በወጣው ዘገባ፣ ለጥሬ ዕቃ ማውጫ የሚገለገሉባቸውን የማዕድን ሥፍራዎች እንዲያስረክቡ የታዘዙት ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ ከክልሉ መንግሥት ጋር ባካሄዱት ረዥም ጊዜ የወሰደ ድርድር ተጨማሪ ገንዘብ በመክፈል ይዞታቸውን ማስከበራቸውን መናገራቸው ይታወሳል::

 

‹‹ለሲሚንቶ ግብዓት የሚውሉ የማዕድን ቦታዎችን በተመለከተ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሁለት መሠረታዊ ዕርምጃዎች ተወስደዋል::አንደኛው ዕርምጃ የሲሚንቶ ማምረቻ ፋብሪካ ሳይኖራቸው የማዕድን ቦታዎችን በተለያየ መንገድ ይዘው ምንም እሴት ሳይጨምሩ አሸዋና ፑሚስ እያፈሱ ሲሸጡ የነበሩ ‘ባለሀብቶች’ ላይ የተወሰደ ዕርምጃ ነው::እነዚህ ‘ባለሀብቶች’ ከዚህ ዘርፍ እንዲወጡ ተደርጓል::ሁለተኛው ዕርምጃ በክልላችን የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሲሚንቶ ምርት የዕሴት ሰንሰለት ለሲሚንቶ ግብዓት የሚውለውን የማዕድን ጥሬ ዕቃ ከማውጣት ጀምሮ ያለውን ሁሉንም ሥራ ራሳቸው ኩባንያዎች ጠቅልለው ይሠሩ ስለነበረ፣ ከእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ ማዕድን የማውጣቱን ሥራ ለተደራጁ ወጣቶች እንዲለቁ የማድረግ ነው::በዚህም መሠረት ከሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ባለሀብቶችና የማኔጅመንት አካላት ጋር በተደረገ ውይይት የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ከእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ ጥሬ ዕቃን የማቅረብ ጉዳይ ለወጣቶቹ በመልቀቅ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው በመስማማት፣ ወጣቶቹ የሚያመርቱተን ጥሬ ዕቃም ገዝተው ለመጠቀም ተስማምተው በይፋ ውል ተፈራርመው ወደ ተግባር ገብተዋል::በውላቸው መሠረትም መገበያየት ጀምረዋል፤›› ሲል መግለጫው ያብራራል::

‹‹ከሲሚንቶ ጥሬ ዕቃ ግብዓት አቅርቦት አንፃር የተወሰዱት ዕርምጃዎች ሦስት መሠረታዊ ዓላማዎች አላቸው::አንደኛው ለሲሚንቶ አምራች ኩባንያዎች አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው ግብዓት እንዲያገኙ በማስቻል ምርታማነታቸው እንዲያድግ ማገዝ ነው::ሁለተኛው መሠረታዊ ዓላማ በሲሚንቶ የእሴት ሰንሰለት በግብዓት አቅርቦት የወጣቶቻችንን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው::ሦስተኛው ትልቅ ካፒታልና ዕውቀት ያላቸው ‘ባለሀብቶች’ ምንም እሴት ሳይጨምሩ፣ አሸዋና ፑሚስ አፍሰው እየሸጡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ከአቅም በታች ከመተወን ይልቅ ከዚህ ዘርፍ ወጥተው እሴት ወደ ሚጨምሩና ከአቅማቸው ጋር ተመጣጣኝ ወደ ሆኑ ዘርፎች እንዲሄዱ ታስቦ ነው፤›› በማለትም የውሳኔውን ዓላማ ያስረዳል::

በዚህም መሠረት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከባለድርሻ አካላት ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ ወደ ተግባር እንዳመራም መግለጫው ጠቁሟል::‹‹በዘርፉ የተደራጁ ወጣቶች ለሲሚንቶ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናትን አምርተው ለፋብሪካዎቹ በመሸጥ ላይ ይገኛሉ::የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹም ከወጣቶቹ ጋር በገቡት ስምምነት መሠረት የሲሚንቶ ማምረቻ የማዕድን ግብዓቶችን ከወጣቶች ገዝተው እየተጠቀሙ ነው፤›› በማለትም ያክላል::

‹‹የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከላይ ከተጠቀሰው ውሳኔና ስምምነት በኋላ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ምንም ዓይነት ድርድር አላደረገም::ከአሁን በኋላም ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን ወደኋላ ሊመልስ የሚችል ድርድርም አያደርግም፤›› ሲልም የክልሉን መንግሥት አቋም ግልጽ አድርጓል:: 

‹‹ይህ ጉዳይ ተግባራዊ በመደረጉ ጥቅማቸው የሚነካባቸው አካላት እንደሚኖሩ በጣም ግልጽ ነው::ጥቅማቸው የተነካባቸው ግለሰቦች የፕሮፓጋንዳ ዘመቻና ከዚያም ያለፈ ነገር ለማድረግ መሞከራቸው አይቀርም::በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የወጣው ዘገባም የዚህ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አካል እንደሆነ ይሰማናል፤›› ያለው መግለጫው፣ የክልሉ መንግሥት ድምፅ ሳይካተት ዘገባው ይፋ መሆን አልነበረበትም ብሏል::

ሪፖርተር በዘገባው ደርባ፣ ዳንጎቴና ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ባካሄዱት ድርድር የጥሬ ዕቃ ማውጫ የማዕድን ሥፍራቸውን ማስጠበቅ እንደቻሉ፣ በዚህም በአንድ ሜትር ኪዩብ ፑሚስ 20 ብር ለመክፈል እንደተስማሙና ከቁጥጥራቸው ውጪ ሊሆኑ የነበሩትን የማዕድን ሥፍራዎች ዳግም በይዞታቸው ሥር እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ገልጾ ነበር::

የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ፣ ‹‹እኛ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በተነደፈው የሥራ ዕድል ፈጠራ የመፍትሔው አካል መሆን እንፈልጋለን::ስለዚህ በአንድ ሜትር ኪዩብ ተጨማሪ ክፍያ ለመፈጸም ተስማምተናል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር መናገራቸው አይዘነጋም::

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች