Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ ጉባዔ በዘላቂ ቱሪዝም ላይ መምከር ጀምሯል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ለሦስት ቀናት የሚካሄደውና በአፍሪካ የዘላቂ ቱሪዝም ልማት ላይ ያተኮረው 59ኛው ከፍተኛ ጉባዔ፣ ከሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ 

ከ300 ያላነሱ የውጭና የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙበት የሚጠበቀው ጉባዔው፣ በአፍሪካ ቀጣና የቱሪዝም ጉዳዮች ላይ በማተኮር ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ ዓበይት ሥራዎችን የተመለከቱ ሪፖርቶችም እንደሚቀርቡበት ይጠበቃል፡፡ በሪፖርት ይቀርባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል በጥቅምት ወር መግቢያ በሞሮኮ የተፈረመው ቻርተር ይገኝበታል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በየጊዜው መካሄድ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከዚሁ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በተጓዳኝ፣ በሞሮኮ ተካሂዶ በነበረው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ስብሰባ ወቅት በርካታ የአፍሪካ አገሮች ያፀደቁት የቱሪዝም ቻርተር በአብዛኛው ዘላቂነትና ኃላፊነትን መርህ ያደረገ የዘርፉን ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት ያለመ እንደነበር ከዓለም ቱሪዝም የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሞሮኮ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አንጎላ፣ ቤኒን፣ ካሜሩን፣ ጊኒ ቢሳው፣ ካቦ ቬርዴ፣ ቡሩንዲ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኮትዲቯር፣ ጋምቢያ፣ ጋቦን፣ ኬንያ፣ ማሊ፣ ማውሪታንያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ናይጄሪያ፣ ኒጀር፣ ሴኔጋል፣ ሲሼልስ፣ ሱዳን፣ ዚምባብዌ፣ ቱኒዝያ እንዲሁም ቻድ የቱሪዝም ቻርተሩ ፈራሚዎች ሲሆኑ፣ በቱሪዝም ሚኒስትሮቻቸው አማካይነት ቻርተሩን በማጽደቅ ወደ ተግባር ለመወለጥ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡

ከ25 በላይ አገሮች ባጸደቁት የቱሪዝም ቻርተር ስምምነት መሠረት፣ ዘላቂነት ያለው የቱሪዝም ዘርፍን፣ ተጠያቂነት ያለባቸውን አሠራሮች ለመተግበር የጋራ ማዕቀፍ ተደርጎ እንደሚጠቀስም የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ሪፖርት ይጠቅሳል፡፡ በዚህ መሠረት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ከቱሪዝም ልማት ጋር ተሰናስሎ መልካም የሚባሉ የቱሪዝም ዘርፉ ልምምዶች ከአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በእያንዳንዱ አገር ውስጥ ከሚገኘው ከብዝኃ ባህል አኳያ ተጣጥሞ የሚተገበርበት፣ ወጥ የሆኑ የቱሪዝም ሥራዎች መተግበሪያ መሣሪያ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ቻርተሩን የፈረሙ አገሮች የየራሳቸውን አገር አቀፍ የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ማስፈጸሚያ ዕቅዶችንም ይፋ ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት የሚተገበር የቱሪዝም ማስተር ፕላን ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያዘጋጀው ይህ ማስተር ፕላን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ከጉብኝት ሥራዎች ጋር በተዛማጅነት ወደፊት ያስመዘግባቸዋል የተባሉ ዝርዝር ዕቅዶች የተካቱበት ነው፡፡ በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በ2024 በየዓመቱ የ4.8 በመቶ ዕድገት በማስመገዝብ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስገኝ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ፣ ከአገሪቱ ኢኮኖሚም የ3.6 ከመቶ ድርሻ የመያዝ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ባሻገር አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ የሥራ ዕድል በአሥር ዓመት ውስጥ መፍጠር የሚችልበት አቅም እንዳለው በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠንቶ ለመንግሥት የቀረበው የአሥር ዓመት ማስተር ፕላን ይጠቅሳል፡፡ ማስተር ፕላኑ እንዲተገበር ታሳቢ የሚደረገው ከካቻምና ጀምሮ ቢሆንም አብዛኞቹ የማስተር ፕላኑ ዕቅዶች ወደ ተግባር ለመሻገር ዳዴ እያሉ ይገኛሉ፡፡

በአሥር ዓመት ውስጥ አሥር ዋና ዋና የተግባር መስኮች የተለዩለት የኢትዮጵያ ዘላቂ የቱሪዝም ማስተር ፕላን፣ የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ቁጥር ወደ አምስት ሚሊዮን እንዲሆን፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢም 180 ቢሊዮን ብር የማድረግ ትልም አስቀምጧል፡፡ አሥር ዋና ዋና ሥራዎች የተለየው ማስተር ፕላኑ ዘላቂና ተወዳዳሪ የቱሪዝም ዘርፍ በአገሪቱ እንዲፈጠር ለማስቻል መንግሥት የ5.3 ቢሊዮን ብር ወጪ መመደብ እንዳለበትም አስፍሯል፡፡

በሌላ በኩል ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄደው ጉባዔ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን ተሞክሮም ይቃኛል፡፡ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ካከናወናቸው ሥራዎች መካከል በኢትዮጵያ የሚጠቀሰው ከሁለት ዓመታት በላይ ሲተገበር የቆየው የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ነው፡፡ ከዓለም ባንክ በተገኘ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር፣ በዓለም ቱሪዝም ድርጅት ባለሙያዎች አማካይነት የሆቴሎች የደረጃ መሥፈርት ዝግጅት፣ ምዘና እንዲሁም ምደባ የተካሄደበት አሠራር የሚጠቀስ ነው፡፡

በዚሁ የምዘናና ምደባ ሥራ አማካይነት 600 ያህል የኢትዮጵያ ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን አሟልተው እንደሚመዘኑ ቢጠበቅም፣ ደረጃዎች የሚጠይቋቸውን መስፈርቶች ማሟላት እንደሚችሉ የታመነባቸው ሆቴሎች ብዛት ከ400 በታች ሆነው መገኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡ የምዘናው ዓላማ የሆቴሎችን ዓለም አቀፍ ደረጃ ከማውጣት፣ አዳዲስ የሆቴልና መስተንግዶ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ሁሉ እንዲመሩበት የሚያስችል መሥፈርት ከማዘጋጀት ባሻገር፣ ደረጃ ያገኙ ተቋማት ጤናማ የንግድ ውድድር ሥርዓት እንዲከተሉ ለማድረግ እንደሚያስችል የዓለም ቱሪዝም አስፍሯል፡፡

ከእነዚህ ነጥቦች እኩል የአገሪቱ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዓለም አቀፍ ደረጃና ጥራትን ያሟሉ አገልግሎቶችን እንደሚሰጡ ይህንንም የዓለም የቱሪዝም ማኅበረሰብ አገሪቱ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉ አገልግሎት መስጫዎች እንዳሏት ለማስገንዘብ ጨምር እንደሚያግዝ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

በአፍሪካ የቱሪዝም ዘርፉን ዘላቂነትና ተጠያቂነት ያለበት አድርጎ ለማጎልበት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የሚመክረው የአዲስ አበባው የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጉባዔ፣ ከቻይና አኳያ የመወያያ አጀንዳውን ቀርጿል፡፡ የቻይና የውጭ ቱሪዝም ፍሰት በየጊዜው በአፍሪካ እያሳየ ያለውን ዕድገት መነሻው ያደረገው ይህ ጉባዔ፣ የአገር መሪዎች፣ ሚኒስሮችና ሌሎችም በተዋረድ የሚገኙ ልዑካን የሚሳተፉበት ከፍተኛ ጉባዔ ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች