Friday, September 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት ከሕዝብ ጋር ይናበብ!

የአገሪቱ የሥልጣን ባለቤት ነው የሚባለው ሕዝብ የመንግሥት ቀጣሪ እንደሆነም ይታሰባል፡፡ ይህ አባባል በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እውነት ሲሆን፣ በተግባር ግን በተቃራኒው ነው፡፡ የአገሪቱ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ የተለያዩ ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ተግባራዊ የሚደረጉት በአስፈጻሚው አካል ወይም መንግሥት ነው፡፡ በየትም አገር መንግሥት የሕዝብን አደራ ተቀብሎ ሲያስተዳድር ከአገር ዘላቂ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጋር ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ኃላፊነት ተግባራዊ የሚደረገው ደግሞ አስፈጻሚው አካል ከሕግ አውጭውና ከሕግ ተርጓሚው ጋር በሕጉ መሠረት ሲጣጣም ነው፡፡ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ ሕግ በማስከበር፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በዲፕሎማሲ፣ በመሠረተ ልማቶች ግንባታ፣ በመሬት አስተዳደርና ልማት፣ ወዘተ የሚደረስባቸው ውሳኔዎችና የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ደግሞ ከሕዝብ ፍላጎትና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር መጣጣም አለባቸው፡፡ ይህ በተግባር ሲረጋገጥ መንግሥትና ሕዝብ እየተናበቡ ነው ይባላል፡፡

ከዚህ ቀደም ሕዝብና መንግሥትን ያቀያየሙና ለግጭት የዳረጉ ጉዳዮች በዝርዝር ሲታዩ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መጓደልና በሙስና ምክንያት ብቻ ነው ብሎ መደምደም ተገቢ አይደለም፡፡ ይልቁንም የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የአፋኝነት ባህሪ ያላቸው ሕጎች፣ የሕዝብን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያሰናክሉ አጓጉል ድርጊቶች፣ በሕዝብ መሀል ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ውሳኔዎች፣ የአቅምና የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ተሿሚዎች መብዛት፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር መበለሻሸት፣ የሕገወጥነት መስፋፋት፣ የሕግ የበላይነትን መጋፋትና የመሳሰሉ መሠረታዊ ምክንያቶች በስፋት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች በፍጥነት በማረም የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ ሲቻል፣ በስህተቶች ላይ ስህተቶች እየተደመሩ የሕዝብን ቁጣ አንረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥትና ሕዝብ ተቃቅረው አገሪቱን አደጋ ውስጥ የከተተ ብጥብጥ ሊከሰት ችሏል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞተው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ለአካል ጉዳትና ለተለያዩ እንግልቶች ተዳርገውና ከፍተኛ የአገር ሀብት ከወደመ በኋላ ነው እሳት የማጥፋት ሥራ ውስጥ የተገባው፡፡ በጣም ከዘገየ፡፡

መንግሥት ሕዝብ በሚፈልገው መንገድ አገር መምራት ሲኖርበት፣ ባልተፈለገ አቅጣጫ መንጎዱ ያንን ሁሉ ጥፋት በማድረሱ አገሪቱ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተዳርጋለች፡፡ የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሁለተኛ ጊዜ ለአራት ወራት ተራዝሟል፡፡ አዋጁ አንፃራዊ ሰላም ለማስፈንና መረጋጋት ለመፍጠር ቢጠቅምም፣ ለአገሪቱ ዘለቄታዊ ህልውና ሲባል ግን መሠረታዊ ለውጦች ያስፈልጋሉ፡፡ መንግሥት ሕዝብን ከልቤ አገለግላለሁ ሲል ሕዝቡ የሚያምንባቸውና የሚተማመንባቸው ሹማምንት ሊኖሩ ይገባል፡፡ ራሳቸውን በትምህርት፣ በሥራ ልምድና በሥነ ምግባር ያበለፀጉና የአገር ፍቅር ያላቸው ዜጎችን ማግኘት የሚቻለው ከፓርቲ ፖለቲካ ውግንና በላይ ማሰብ ሲቻል ነው፡፡ በዚህ መንገድ ማሰብ ሲቻል የመንግሥትና የሕዝብ መናበብ ይጨምራል፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ የሚመራው መንግሥት ‹ጥልቅ ተሃድሶ› ከጀመሩ ወዲህ የትኛው ሹም ነው በጥፋቱ ተፀፅቶ ሥራውን በገዛ ፈቃዱ የለቀቀው? ሌላው ቀርቶ ‹‹ቆሼ›› በሚባለው ሥፍራ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት በቀጠፈው አደጋ ሳቢያ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ለምን ከኃላፊነታቸው አልተነሱም? በበርካታ ችግሮች ምክንያት ተጠያቂነት ያለባቸው መቼ ነው ከኃላፊነታቸው የተነሱት? በታችኛው እርከን ላይ የተወሰደው መጠነኛ ዕርምጃ ወደ ላይ መሄድ ለምን አቃተው? ሕዝብ በደንብ ይመለከታል፡፡

ምርጫን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ ጀምሮ በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን መንግሥት ጥረት ቢያደርግ እኮ፣ ከሕዝብ ጋር መጣላትም ሆነ ሁከትና ብጥብጥ ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ መንግሥት የሕዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ የሚያቅተው በውስጡ ችግር ሲኖር ነው፡፡ ውስጡ ገብተው የሚቦጠቡጡትና የግልና የቡድን ጥቅም ላይ ብቻ በማሰፍሰፍ ሕገወጥነትን የሚያበረታቱ ሲበዙ፣ የሕግ የበላይነት ይደረመሳል፡፡ የግለሰቦች ፍላጎት ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅና እንኳን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊገነባ አገር የሚበትን ችግር ይፈጠራል፡፡ ሐሰተኛ ሪፖርቶች እየተቀባቡ እየወጡ የሕዝቡን ደም ፍላት ያባብሳሉ፡፡ በሕዝብ ስም የሚነግዱ ራስ ወዳዶች በሚዲያ ብቅ እያሉ መሬት ላይ የማይታይ ውዥንብር ያሠራጫሉ፡፡ በየመድረኩ ‹ጥልቅ ተሃድሶ› እየተካሄደ ነው እየተባለ ተሃድሶውን የማይገልጹ ዲስኩሮች ይበረታሉ፡፡ ሕዝብም ለካ እነዚህ ሰዎች አይታረሙም እያለ ያቄማል፡፡

መሆን የነበረበት ግን በሕግ የበላይነት ሥር ለሕዝብ ታዛዥ የሆነ መንግሥት የሚኖርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር መሠረቱን ካሁኑ መጣል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት ራሱን በራሱ እየተቆጣጠረና አገርን ወግ ማዕረግ እያሳየ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ያጠናክራል፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል ያሰፍናል፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ያስከብራል፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥርጊያውን ያመቻቻል፣ የሙያና የሲቪክ ማኅበራት በብዛትና በጥራት እንዲያብቡ ይረዳል፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ያረጋግጣል፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የአገር ባህል እንዲሆኑ ያግዛል፣ የአገር ባለቤትነት መንፈስን ያፀናል፡፡ በዚህ መሠረት የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረቱ ሲጣል ድንጋይ ወርዋሪ ሳይሆን ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ለማፍራት ይረዳል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ይህንን ነው፡፡

እንደሚታወቀው አገራችንን ጨምሮ በበርካታ አገሮች በሕዝብና በመንግሥት መካከል መቃቃር የሚፈጠረው፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ ሲነጥፍና የመንግሥት የአገልጋይነት ሚና ሲኮላሽ ነው፡፡ መንግሥት ሰፋፊ የልማት ዕቅዶችን ዘርግቶ የፈለገውን ያህል ቢማስን የሕዝብ ተሳትፎ ካልታከለበት ፋይዳ የለውም፡፡ መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ አካል መሆኑ ማረጋገጫው፣ የሥልጣኑ ባለቤት ነው ለሚባለው ሕዝብ በሚኖረው ታዛዥነት መጠን ነው፡፡ እስካሁን የተመጣባቸው መንገዶች ችግር ፈጣሪ፣ የአገርንና የሕዝብን ሰላምና ህልውና የሚፈታተኑ መሆናቸው ከተረጋገጠና ወደ ‹ጥልቅ ተሃድሶ› ከተገባ በኋላ በፍፁም ወደኋላ ማለት አያስፈልግም፡፡ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ታዛዥ የሚሆን ሥርዓት በመመሥረት የመንግሥት ሥልጣን በነፃና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ እንዲያዝ ጥርጊያው ይመቻች፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በግልጽና በነፃነት እንዲሰሙና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ማንኛውም ዓይነት መስዕዋትነት ይከፈል፡፡ ሥልጣን በጉልበት ሳይሆን በምርጫ ካርድ ብቻ ይገኝ፡፡ ሁሉም መሠረታዊ መብቶች ይከበሩ፡፡ ለነውጥና ለጥፋት የሚዳርጉ ጊዜ ያለፈባቸው ኋላቀር ድርጊቶች ይገቱ፡፡ ሕዝብ የሥልጣን ዋነኛ ባለቤት መሆኑ በተግባር ይረጋገጥ፡፡ የሕግ የበላይነት ይስፈን፡፡ ያኔ ሕዝብና መንግሥት እየተናበቡ ነው ይባላል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...