Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

አዲሱ የደረቅ መኪና እጥበት

ሻይን ተንቀሳቃሽ የደረቅ መኪና እጥበት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በቅርቡ ወደ መኪና እጥበት ቢዝነስ የገባ ኢንተርፕራይዝ ሲሆን፣ መኪናን በግፊት ኃይል በሚሠሩ የመኪና ማጠቢያ ፕላስቲክ ማሽኖች ያለ ፈሳሽ ወይም በደረቅ የመወልወል አገልግሎት ይሰጣል፡፡ 106 የሚሆኑ ወጣቶች ተቀጥረው የሚሠሩበት ሲሆን፣ በአዲስ አበባ በሦስት ክፍለ ከተሞች በዋነኛነት በንግድ ማዕከል ሕንፃዎች እየሠሩ ነው፡፡ ስለ ማኅበሩ እንቅስቃሴ ምሕረተሥላሴ መኰንን የማኅበሩን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ይማም አነጋግራዋለች፡፡  

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ስለሚሰጠው የደረቅ መኪና እጥበት አገልግሎት ብታብራራልን?

አቶ ጥላሁን፡- የደረቅ መኪና እጥበት መሬት ላይ ውኃ ሳይፈስ መኪናን በማራስ ብቻ የሚደረግ የእጥበት ዘዴ ነው፡፡ አገልግሎቱ በተለያዩ አገሮች ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ  በአፍሪካ በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያና በሌሎችም አገሮች ይሰጣል፡፡ ሐሳቡን ያመጣነው በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተን ላቫጆ ሥራ በጠየቅንበት ወቅት ነበር፡፡ የቦታ ችግር ስላለ በመንግሥት በኩል በተወሰነ ደረጃ ላቫጆ መስጠት የተከለከለበት ጊዜ አለ፡፡ ይህንን በማየት ኢንተርኔት ላይ ሌላ አማራጭ ፈለግን፡፡ የመኪና እጥበት ውጭ አገር በአዲስ ቴክኖሎጂ እንዴት እንደሚሠራ አየንና ጀመርን፡፡

ሪፖርተር፡- የላቫጆ ሥራ ለመሥራት የቦታ እጥረት ችግር የሆነው እንዴት ነው?

አቶ ጥላሁን፡- ለላቫጆ ሥራ ቦታ የሚሰጠው ወንዝ ዳር ወይም ወጣ ያለ ቦታ ጥናት ተደርጎ ነው፡፡ ሒደቱ አሰልቺ ነው፡፡ እኛም ከተደራጀን በኋላ ቦታ ስለሌለን እንደ አማራጭ የደረቅ መኪና እጥበትን ወሰድን፡፡ ከዱባይ ያስመጣናቸው ማሽኖች ተንቀሳቃሽ ናቸው፡፡ ቦታም አይዙም፡፡ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት ብዙ ሒደቶች አልፈናል፡፡ ከኛ በፊት አንድ ከውጭ መጥቶ የጀመረ ልጅ ነበር፡፡ የሱ እጥበት አንድ የተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡ በላቫጆ ሥራ ባለመኪኖች  ወደ ላቫጆ ይሄዳሉ፡፡ እኛ ግን ወደ መኪናው እንመጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- የተደራጃችሁት ምን ያህል ሆናችሁ ነበር? ሒደቱስ ምን ይመስል ነበር?

አቶ ጥላሁን፡- መጀመርያ እኔና ጓደኛዬ ተደራጀን፡፡ ከዚህ በፊት የምንሠራው ሌላ ሥራ ነበር፡፡ ወደ መኪና እጥበት የመጣነው አዋጭነቱን በማየት ነው፡፡ ፕሮፖዛሉን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ጽሕፈት ቤት አስገባን፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የቢዝነሱን አዋጭነትና በሥሩ ብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች የመያዝ አቅም ያለው መሆኑን አየ፡፡ እንደ ማሳያ የወሰድነው ሦስት ክፍለ ከተሞችን ነበር፡፡ የካ፣ ቂርቆስና ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ያሉ ወጣቶች በኛ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ ሆነው የስምምነት ሰነድ ተፈራርመው አብረን እንድንሠራ ያቀረብነውን ጥያቄ የከተማ አስተዳደር ከተቀበለ በኋላ ሥራ ጀመርን፡፡

ሪፖርተር፡- መነሻ ካፒታላችሁ ስንት ነበር?

አቶ ጥላሁን፡- 100 ሺሕ ብር ነበር፡፡ አሁን እያደገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ስንት ወጣቶች ታቅፈዋል? አገልግሎቱን መስጠት ከጀመራችሁስ ምን ያህል ጊዜ ሆናችሁ?

አቶ ጥላሁን፡- በመጀመርያ ዙር በኛ ሥር ያሉ ወጣቶች ወደ 160 ናቸው፡፡ ከእነዚህ 90ዎቹ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከአንድ ሳምንት በኋላ ይጀምራሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት 160ውንም አስመርቀናል፡፡ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሆቴል ባካሄድነው የምርቃት ሥነ ሥርዓት ወደ 160 ወጣቶች ተገኝተዋል፡፡ በፕሮግራሙ ከትንሽ ቦታ ተነስተው ትልቅ ደረጃ የደረሱ እንደ ኢያሳያስ አድቨርታይዝመንትና አምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት ያሉ ሰዎችን ጋብዘን ለወጣቶቹ ምክር እንዲሰጡ አድርገናል፡፡ የጋበዝናቸው ሰዎች ስለ ሥራ ምንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥተዋል፡፡ የሦስቱ ክፍለ ከተሞች አመራሮች ተገኝተውም የማሽን ርክክብ ተደርጓል፡፡ ሥራውን ወደ መሬት ካወረድነው ወደ ሃያ ቀን ሊሆነን ነው፡፡ ጥናት ሠርተን ፕሮፖዛሉን ለመንግሥት እስክናቀርብ ስምንት ወር ገደማ ፈጅቶብናል፡፡ ሥራው ሁለት ዓይነት ነው፡፡ በሞሎችና መንገድ ለመንገድ እንሠራለን፡፡ ሞሎች ላይ ሠራተኞች ቀጥረን መኪኖች በቆሙበት እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ ቦሌና መርካቶ እየሠራንባቸው ያሉ ሕንፃዎች አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ሰው መኪና ለማሳጠብ ጊዜ የለውም፡፡ ላቫጆ ሲሄድ 30 ወይም 40 ደቂቃ ስለሚፈጅ በሳምንት አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ ይሄዳል፡፡ እኛ የሕንፃ አስተዳዳሪዎችን በማናገር መኪናውን ፓርክ ባደረገበት እንዲታጠብ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የደረቅ መኪና እጥበት በተለምዶ ከሚታወቀው የመኪና እጥበት ጋር ሲነፃፀር ፍሳሽ ውኃን ከማስቀረት ባሻገር ምን የተለየ አገልግሎት ያካትታል?

አቶ ጥላሁን፡- ሥራው አሁንም በዘልማድ ይሠራል፡፡ ዋናው ነገር የደረቅ መኪና እጥበት ጊዜ ቆጣቢ መሆኑ ነው፡፡ ባለ መኪናው ሳይንገላታ ሥራ ላይ እያለ መኪናው ይፀዳለታል፡፡ ሥራው ተንቀሳቃሽ ስለሆነ ብዙ ወጣቶችን ይዘን መሥራት እንችላለን፡፡ ከላቫጆ እጥበት የሚለየው መሬት ውኃ አለመፍሰሱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራውን ስትጀምሩ ከመንግሥት ምን ዓይነት ድጋፍ አገኛችሁ?

አቶ ጥላሁን፡- ሐሳቡን ይዘን ስንሄድ በሦስቱም ክፍለ ከተሞች ማሳያ እንድንሠራ ተደርጓል፡፡ በክፍለ ከተሞቹ ያሉ ወረዳዎችን አስተባብረው በዘልማድ ይሠሩ የነበሩ ወጣቶች በኛ ሥር እንዲሠሩ አድርገዋል፡፡ ሌላው ትልቅ ድጋፍ የመኪና መጨናነቅ የሌለባቸው አውራ ጎዳናዎች (ሃይ ዌይ) ያልሆኑ መኪና የሚቆምባቸው መንገዶች ላይ እንድንሠራ መፍቀዱ ነው፡፡ የከተማው የጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ቢሮ ያደረገልን ድጋፍ እንዳለ ሆኖ በእጃችን ያሉን ማሽኖች ግን የተወሰኑ ነበሩ፡፡ አዲስ ካፒታል ሊዝ ፋይናንስ የቢዝነሱን አዋጭነት በማየት እስከ 250 ሺሕ ብር የሚሆን ማሽን ሊያስገቡልን መሆኑ ነው፡፡ ከአንድ ወይም ከሁለት ወር በኋላ እጃችን ላይ ይደርሳል ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- አሽከርካሪዎች በአገልግሎታችሁ እንዲጠቀሙ በቂ ማስታወቂያ ሠርታችኋል ?

አቶ ጥላሁን፡- ሞሎች ላይ የቪአይፒ ኩፖኖች እንሰጣለን፡፡ ኩፖኖቹን የያዘ ሰው በምንሠራበት በማንኛውም ቦታ ይጠቀማል፡፡ በኩፖኑ ፓኬጅ አንድ ሰው ስምንት ቀን መኪናውን ካሳጠበ በወር 400 ብር ብቻ ይከፍላል፡፡ የአራት ቀን ፓኬጅም አለ፡፡ ሁለተኛው በበራሪ ወረቀት የሠራነው ማስታወቂያ ነው፡፡ የአቅም ጉዳይ ችግር ሆኖብን እስካሁን ባናደርገውም ለወደፊት በሬድዮና በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ለመሥራትም እናስባለን፡፡ በምንከራያቸው ሞሎች ባነሮች አሉን፡፡ መንገድ ላይ ለሚሠሩ ወጣቶች የኛን ድርጅት የሚገልጹ ተንጠልጣይ ባንዲራዎች ይኖሩናል፡፡ ሥራው አዲስ በመሆኑ አንዳንዶች መረጃው የላቸውም፡፡ እንዴት በደረቅ መኪና ይታጠባል? የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ግን በደረቅ መኪና እጥበት መኪናው ስፕሬይ ተደርጎ ርሶ በፎጣ ውስጡንም ውጪውንም ማፅዳት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከ400 ብር ፓኬጅ ውጪ አንዴ የሚያሳጥብ ሰው ስንት ይከፍላል?

አቶ ጥላሁን፡- ክፍያው እንደየቦታው ቢየለያይም አንዴ የሚያሳጥብ ሰው ቢበዛ 40 ብር ይከፍላል፡፡ ከሕንፃ አስተዳደሮች ጋር በጋራ ስለምንሠራ 60 በመቶውን ድርጅቱ 40 በመቶውን ደግሞ የሕንፃ አስተዳደሮች ይወስዳሉ፡፡ 40 ብር የምናስከፍለው መኪና ከላይ ብቻ ሲታጠብ ሲሆን፣ ውስጡም ሲጨመር 50 ብር ይከፈላል፡፡ የምንጠቀማቸው የተለያዩ ሻምፖዎችና የዳሽ ቦርድ ቅባቶች አሉ፡፡ ዋጋው እንደየመኪናው ዓይነትም ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ዶልፊንና ኮሮላ የሚታጠቡበት ዋጋ አንድ አይደለም፡፡ ዶልፊን የሚታጠበው 60 ብር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመንገድ እንዲሁም የሕንፃ ግንባታ እምብዛም የመኪና ፓርኪግን ታሳቢ ባለማድረጉ መኪና ማቆሚያ ቦታ በማጣት የሚቸገሩ አሽከርካሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ የእናንተ ቢዝነስ ፓርኪንግ ቦታን ያማከለ እንደመሆኑ ይህ ሥራችሁ ላይ እንቅፋት አይፈጥርም?

አቶ ጥላሁን፡- ሞሎች ላይ እንዲህ ዓይነት ችግር የለም፡፡ ነገር ግን የኛም ትልቁ ሥጋታችን ነው፡፡ መጀመርያ ጥናት ስንሠራ ለእጥበቱ የለየናቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህ የምንሠራባቸውን ቦታዎች በፎቶ አስደግፈን ለከተማ መስተዳድሩ ፕሮፖዛል አስገብተናል፡፡ ለምሳሌ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብሔራዊ ቴአትር ፊት ለፊት ብዙ መኪናዎች ይቆማሉ፡፡ የመኪና መጨናነቅ የሌለበት ዋና መንገድ ያልሆነም ቦታ ነው፡፡ እንደዚህ ዋና ዋና ብለን የለየናቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እንደዚህ ሆኖም ሥራው መሬት ሲወርድ ነው ችግሮቹ የሚታዩት፡፡

ሪፖርተር፡- ከፓርኪንግ ቦታ ውጪ በሥራችሁ የገጠሟቸሁ እንቅፋቶች አሉ?

አቶ ጥላሁን፡- ሥራውን ስንጀምር ሁለት ሥጋቶች ነበሩን፡፡ አንዱ ልጆቹ እኛ ካስቀመጥንላቸው ቦታዎች ወጥተው ከሠሩ የመኪና አደጋ ሊደርስባቸው መቻሉ ነው፡፡ ይኼ እስካሁን አልገጠመንም፡፡ ሆኖም ሊገጥመን ስለሚችል ከፍተኛ ክትትል ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው በዘልማድ ከሚሠሩት ልጆች አብዛኞቹ የክፍለ አገር ልጆች ስለሆኑ የአዲስ አበባ መታወቂያ የላቸውም፡፡ ስለዚህም ተደራጅተው መሥራት አይችሉም፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ቢሮ አሠራር እኛ የወሰድናቸው ልጆች ወረዳው የሚያውቃቸው የአዲስ አበባ ልጆች ናቸው፡፡ እንደነዚህ ልጆች ሁሉ መታወቂያ የሌላቸውንም ወደኛ መስመር አስገብተን የምንሠራው እንዴት ነው? የሚል ችግር ገጥሞናል፡፡ ሁለቱም ዜጎች ናቸው፡፡ ሁላችንም ስለምንሠራውም ለአገር ነው፡፡ እዚህ ላይ ወደኛ ሥርዓት አስገብተን የምንሠራበትን መንገድ ከየወረዳዎቹ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ በዘልማድ ለሚሠሩ ልጆች ዘመናዊ ማሽኖች አቅርበን ከኛ ጋር እንዲሠሩም እያመቻቸን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእጥበት አገልግሎቱ ሰዎች በአንድ ሕንፃ ውስጥ ገብተው የሚቆዩበትን ጊዜ ያማከለ ነው?

አቶ ጥላሁን፡- እጥበቱ የሚፈጀው ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ነው፡፡ አንድ ሰው መኪናውን አቁሞ ሲሄድ የኛ ሱፐርቫይዘር ምን ያህል ደቂቃ እንደሚቆይ ይጠይቃል፡፡ አምስት ወይም አሥር ደቂቃ ከሆነ መኪናው አይፀዳም፡፡ ካለን ተሞክሮ ሲኒማ ቤት፣ ካፌ ወይም ሱቅ የገባ ሰው የሚወጣው ቆይቶ ነው፡፡ አገልግሎቱን በሃይማኖት ተቋሞች አካባቢ የመስጠት ዕቅድም አለን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን አገልግሎቱን የምትሰጡባቸውን ቦታዎች ብትገልጽልን?

አቶ ጥላሁን፡- ኢንተርኮንቲነንታልና ኢሊሊ ሆቴል ጀርባ፣ ብሔራዊ ቴአትርና ስቴዲየም ፊት ለፊት፣ ሞርኒንግ ስታር ሞልና ቦሌ ሀይስኩል ጀርባና መርካቶ ድር የገበያ ማዕከልም እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ባላችሁ ተሞክሮ ከአሽከርካሪዎች ምን ዓይነት ምላሽ አገኛችሁ?

አቶ ጥላሁን፡- የኛ አገልግሎት ዋናው ጥቅም ጊዜ ቆጣቢነቱ ነው፡፡ ሁለተኛው አሽከርካሪዎች በፊት በየመንገዱ በሚያሳጥቡበት ወቅት የማያገኟቸውና በኛ አገልግሎት ውስጥ የተካተቱ እንደ መኪና ሽታ፣ የዳሽ ቦርድ ቅባትና የጎማ ቀለም ያገኛሉ፡፡ ዋጋችን መንገድ ላይ ካለው እኩል ነው፡፡ ስለዚህ በአገልግሎቱ የተጠቀሙ ደስተኛ ሆነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ቢዝነሱ እንዲያድግና የተጠቃሚዎች ቁጥርም እንዲጨምር ምን መደረግ አለበት?

አቶ ጥላሁን፡- በየሄድንበት ቢሮ ሥራው አያዋጣም ያለን ሰው አልነበረም፡፡ ከዚህ በኋላ እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙ ሺሕ ኢንተርፕራይዞች ይፈልቃሉ ብለን እናስባለን፡፡ ለላቫጆ የሚወጣው ውኃ ብዙ ስለሆነ  የሥራው ጥቅም ውኃ መቆጠቡም ነው፡፡ በየዓመቱ ብዙ መኪናዎች ወደ አገሪቷ ይገባሉ፡፡ ወጣቶች በዚህ ሥራ ቢሰማሩ አዋጭነቱ አያጠያይቅም፡፡ መንግሥትም ትልቅ ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?

አቶ ጥላሁን፡- ለወጣቶቹ መጀመሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንሰጣለን፡፡ ልምድ ባይኖራቸውም ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ወጣቶቹ ከሱስ ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ ልጆቹ ቁጠባም አላቸው፡፡ አንድ ልጅ በቀን ማጠብ ያለበት ዘጠኝ መኪና ነው፡፡ ከዘጠኙ ሁለቱ ቁጠባ ስለሆነ በቀን 80 ብር ይቆጥባል ማለት ነው፡፡ በዘልማድ የሚሠሩ ልጆች ቁጠባ ስለማይኖራቸው ሕይወታቸው አይለወጥም፡፡ በቀጣይ ብዙ መኪናዎች ባሉባቸው ክፍለ ከተሞች ሥራውን እንጀምራለን፡፡ ችግሮችን እየፈታን ስኬታችንን እያጠናከርን እንሄዳለን ብለን እናስባለን፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ትልልቅ ሕንፃዎች እየተሠሩ ነውና በሆቴሎች፣ በአፓርትመንቶችና በኮንዶሚኒየሞች አገልግሎቱን መስጠት እንፈልጋለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን

ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ውኃ የማከም ቴክኖሎጂ ሥራ የገባው በየጊዜው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውኃ ወለድ በሽታዎች መደጋገምን ዓይቶና ጥናት አድርጎ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ቢሻን...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...

ሕይወትን ለመቀየር ያለሙ የቁጠባና ብድር ማኅበራት

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ...