Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊጅማ ዩኒቨርሲቲ አግሪቢዝነስን በሁለተኛ ዲግሪ ሊሰጥ ነው

  ጅማ ዩኒቨርሲቲ አግሪቢዝነስን በሁለተኛ ዲግሪ ሊሰጥ ነው

  ቀን:

  ጅማ ዩኒቨርሲቲ በእርሻ ውጤቶች ቢዝነስ (አግሪቢዝነስ) ላይ የሚያተኩር የድኅረ ምረቃ ትምህርት ሊጀምር ነው፡፡ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በአግሪቢዝነስ ማኔጅመንት የሥራ መስክ ተቀጥረው በመሥራት ላይ ለሚገኙ ባለሙያዎች የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱ ቅድሚያ እንደሚሰጥ፣ አጫጭር ሥልጠናዎች የሚሰጥበት አግሪቢዝነስ ሊደርሽፕ ኢንስቲትዩት ለማቋቋም መታሰቡንም የፕሮጀክት አስተባባሪው ዶ/ር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡

  ጉዳዩን አስመልክቶ በኔዘርላንድ ኤምባሲ አስተባባሪነት የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በአገሪቱ ከፍተኛ የአግሪቢዝነስ ማኔጅመንት ችግር አለ፡፡ ዘርፉ የሚመራው የአግሪቢዝነስ ማኔጅመንት ዕውቀት በሌላቸው የግብርና ሳይንስ ምሩቃን ነው፡፡ ይህም ሴክተሩ እንዳይዘምን፣ የግብርና ምርት ከአገር ውስጥ ገበያ አልፎ በተገቢው መጠን ለውጭ ገበያ እንዳይቀርብ ማነቆ ሆኖበት ቆይቷል፡፡

  ለዚህም ትምህርቱ በአገር ውስጥ አለመሰጠቱ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ድርጅቶች አሠራራቸውን ለማሻሻልና ቢዝነሳቸውን ለማስፋት የተማረ የሰው ኃይል ከማግኘት ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥማቸው በጥናቱ ተገልጿል፡፡ ፍላጎትና አቅርቦት የማመጣጠን፣ የመረጃ ክፍተት፣ የደንበኛ አያያዝ፣ ሠራተኛና ኃላፊዎችን አስተባብሮ የማሠራት፣ ውሳኔ የመስጠት እንዲሁም የሴልስ፣ የማርኬቲንግና የፋይንስ አስተዳደር ችግሮች በስፋት መኖሩ በጥናቱ ተብራርቷል፡፡

  ‹‹ጥናቱ የእንስሳት መኖ፣ አግሪ ቢዝነስ፣ የእንስሳት ዕርባታ፣ የእንስሳት ተዋፅዖ ምርትና የመሳሰሉትን የግብርና ዘርፎች ይዳስሳል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የሚሠሩ አመራሮች የአመራር ዕውቀት የሌላቸው የእርሻ ምሩቆች ናቸው፡፡ ትክክለኛ ማኔጀር መሆን አልቻሉም፤›› ያሉት ዶ/ር ወንዳፈራሁ በአገሪቱ የአግሪቢዝነስ ትምህርት የሚሰጡ የትምህርት ተቋማት ባለመኖራቸው የተፈጠሩ ክፍተቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

  ባለሙያዎች ለአጫጭር ሥልጠና ወደ ጎረቤት አገር ኬንያና ወደ እንግሊዝ ተልከው የቢዝነስ አመራር ክህሎቱን እንዲያዳብሩ የሚደረግበት አሠራር ቢኖርም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ውጤታማ መሆን አለመቻሉን ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ላሉ የሥልጠና ፕሮግራሞች ከፍተኛ ወጪ እንደሚወጣ፣ ነገር ግን በአገር ውስጥ መሰጠት መጀመሩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስቀርም አክለዋል፡፡

  ከመስከረም 2010 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ አበባ በሚገኘው የዩኒቨርሲቲው ሳተላይት ካምፓስ  ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ይጀምራል፡፡  ትምህርቱ በሁለት ዓመት የሚጠናቀቅ መሆኑን፣ በአግሪቢዝነስ የማኔጅመንት፣ የፋይናንስና የኢኮኖሚክስ ባህሪ ያላቸውን 18 ኮርሶች ይሰጣሉ፡፡ አጠቃላይ ክፍያውም 5000 ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ዶ/ር ወንዳፈራው ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለሴት ተማሪዎች ከአጠቃላይ ክፍያው ሦስት አራተኛውን ብቻ ከፍለው የሚማሩበት ዕድል መመቻቸቱንም ተናግረዋል፡፡

  ፕሮግራሙ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንደሚሰጠው ታውቋል፡፡ በዘርፉ ያሉ ቁልፍ ችግሮችን ለይቶ በማውጣት ሰፊ የተግባር ትምህርት ለመስጠት መታሰቡንም ይናገራሉ፡፡

  ዩኒቨርሲቲው ኔዘርላንድ ከሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቀረፀው ሥርዓተ ትምህርቱ ዙሪያ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

  በፕሮግራሙ ላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ እንዳሉት፣ የፕሮግራሙ መጀመር አገሪቱ ያልተጠቀመችበትን የአግሪቢዝነስ ሴክተር እንዲጎለብት ያደርገዋል፡፡ በቂ ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ በማድረግ ለግብርና ምርቶች ጥሩ የገበያ ዕድል እንዲፈጠር ይረዳል፡፡ ግብርና መር የሆነው የአገሪቱ ፖሊሲም ለፕሮግራሙ መጎልበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img