ባለፈው እሑድ በአሜሪካ በተካሄደው ቦስተን ማራቶን ኢትዮጵያውያን በሁለቱም ፆታ አልተሳካላቸውም፡፡ በተቃራኒው ኬንያውያን በሁለቱም ፆታ የአሸናፊነቱን አክሊል ደፍተዋል፡፡ በወንዶች ጂአፍሪ ኪሩይ በሴቶች ኢድና ኪፕላጋት አሸናፊ በሆኑበት 121ኛው ማራቶን የኢትዮጵያውያን የተፎካካሪነት አቅም መውረድ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በወንዶቹ ለሚ ብርሃኑና ሲሳይ ለማ ውድድሩን ማጠናቀቅ ካልቻሉት ተጠቅሰዋል፡፡
የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በወርቅ ደረጃ ከሚመድባቸው የጎዳና ሩጫዎች አንዱ እንደሆነ በሚነገርለት ቦስተን ማራቶን፣ ኢትዮጵያውያኑ ያስመዘገቡት ውጤት ለተቋሙና ለመሪዎቹ የማንቂያ ደወል ሊሆን እንደሚችል ጭምር የሚናገሩ በርክተዋል፡፡
ኬንያውያንን ያነገሠው የቦስተን ማራቶን ቀደም ሲል ምንም እንኳ እንደ ኬንያውያን ሁሉ ለኢትዮጵያውያንም ግምት ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በርቀቱ ብዙም ግምት ያልተሰጣቸው አገሮች በሜዳሊያ ሰንጠረዡ መካተት መቻላቸው ለአትሌቲክሱ እየሰጡ ያለውን ትኩረት እንደሚያመላክትም የሚናገሩ አሉ፡፡
ኬንያውያኑ በሁለቱም ፆታ አሸናፊ በሆኑበት ቦስተን ማራቶን ርቀቱን 2 ሰዓት 09፡ 37 ሰከንድ ያጠናቀቀውን ጂኦፈሪ ኪሩይን ተከትሎ አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ 2 ሰዓት 09፡ 58 ሁለተኛ ሲሆን፣ ጃፓናዊው ሉጉሩ ኢሳኮ 2 ሰዓት 12፡ 08 በሆነ ጊዜ አጠናቆ ሦስተኛ ወጥቷል፡፡ ከኢትዮጵያውያኑ ዲኖ ሰፍሮ 2 ሰዓት 14፡ 26 ሰባተኛና የማነ ፀጋዬ 2 ሰዓት 16፡ 47 በሆነ ጊዜ ርቀቱ አጠናቆ 12ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡
በሴቶች መካከል በተካሄደው ተመሳሳይ ውድድር እንደ ወንዶቹ ሁሉ ኬንያዊቷ ኢድና ኪፕላጋት 2 ሰዓት 21፡ 52 ሰከንድ አጠናቃ አንደኛ ስትሆን፣ ባህሬናዊቷ ሮዚ ኪሊሞ 2 ሰዓት 22፡ 51 ሁለተኛ፣ አሜሪካዊቷ ጆርዳን ሐሳይ 2 ሰዓት 23፡ 00 ገብታ ሦስተኛ በመሆን አጠናቃለች፡፡ ከኢትዮጵያኑ ለውድድሩ ትልቅ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው መካከል ብዙነሽ ዳባ 2 ሰዓት 30፡ 58 ሰከንድ አጠናቃ ሰባተኛ በመሆን ስታጠናቅቅ፣ ሩቲ አጋና አፀደ ባይሳ 2 ሰዓት 31፡ 26 እና 2 ሰዓት 40፡ 01 በሆነ ጊዜ ርቀቱን አጠናቀው 12ኛ እና 22ኛ በመሆን ማጠናቀቅ መቻላቸው ታውቋል፡፡