Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊግንባታ ሳያጠናቅቁ የተሰወሩት ሥራ ተቋራጭና አማካሪ እየተፈለጉ ነው

ግንባታ ሳያጠናቅቁ የተሰወሩት ሥራ ተቋራጭና አማካሪ እየተፈለጉ ነው

ቀን:

መንግሥት የቁም እንስሳት ለውጭ ገበያ ከመቅረባቸው በፊት የጤንነታቸው ሁኔታ የሚፈተሽባቸውና ጊዜያዊ ማቆያ በመሆን አገልግሎት እንዲሰጡ እያስገነባቸው ከሚገኙ አምስት የእንስሳት ኳራንታይኖች ውስጥ፣  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘውን ግንባታና የቁጥጥር ሥራዎችን ለማከናወን በገቡት የውል ስምምነት መሠረት ሳያጠናቅቁ ተሰውረዋል የተባሉ ሥራ ተቋራጭና አማካሪ እየተፈለጉ መሆኑ ተነገረ፡፡

ኳራንታይኖችን የሚያስገነባውና ግንባታቸውንም የሚቆጣጠረው የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር ሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ.ም ለፓርላማው ሪፖርቱን ሲያቀርብ እንዳስታወቀው፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአልመሃል የእንስሳት መፈተሻ ጣቢያን ገንብቶ እንዲያስረክብ ውል በመግባት ግንባታ ጀምሮ ሳያጠናቅቅ የተሰወረው ሥራ ተቋራጭና አማካሪ ድርጅት እየተፈለጉ ነው፡፡ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ይህን ያስታወቁት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከአባላት ተነስተውላቸው ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡

የሚኒስቴሩ የቁጥጥር ኮሚቴ የግንባታው መቆምን በተመለከተ ባደረገው ክትትል፣ ሥራ ተቋራጩና አማካሪው መጥፋታቸው መረጋገጡን ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሚኒስትሩ የአማራ ክልል የዲዛይን ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅትን በማነጋገር ግንባታው ከዕቅዱ በምን ያህል ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ምንስ ያህል እንደሚቀረው እየተጠና በመሆኑ፣ ከውጤቱ በኋላ ቀሪውን የግንባታ አካል ለማስጨረስ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ሳቢያ የተሰወሩትን ሁለቱንም አካላት አፈላልጎ ለሕግ ለማቅረብ፣ በመንግሥት በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ ሚኒስትሩ የተቋራጩንና የአማካሪውን ማንነት ሆነ የኮንትራቱን ዋጋ ባይገልጹም፣ ሪፖርተር ባደረገው ተጨማሪ ጥረት ሥራ ተቋራጩ ቱሊፕ ኮንስትራክሽን ድርጅት ሲሆን፣ አማካሪ ድርጅቱ ደግሞ በለስ አማካሪ እንደሚባል ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቁም እንስሳትንም ሆነ የሥጋ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በጥራትና በብዛት ለማቅረብ እንዲያስችሉ በማሰብ አምስቱ ኳራንታይኖችን ለመገንባት መንግሥት መወሰኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ የግንባታዎቹ ጥራት እንዴት እየተከናወነና በምን ደረጃ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ “ቀደም ብሎ ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ ከተያዘላቸው የጊዜ ዕቅድ ቢዘገዩም፣ ግንባታው ከተቋረጠው የቤኒሻንጉሉ ኳራንታይን ማዕከል በስተቀር ወደ መጠናቀቅ ደረጃ ላይ ተቃርበዋል፤” ብለዋል፡፡

በተለይ በአፋር ክልል ሚሌ ከተማ የሚገኘው ማዕከል ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ከመጠናቀቁ በላይ፣ የቁም እንስሳቱ ግብይት መዳረሻ ከሆኑ አገሮች የመጡ ባለሙያዎች ኳራንታይኑ አስፈላጊውን መሥፈርትና የጥራት ደረጃውን ገምግመው ዕውቅና ሰጥተው መሄዳቸውን ፕሮፌሰር ፍቃዱ አስረድተዋል፡፡ ለአብነትም ከሁለት ዓመት በፊት የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በኢትዮጵያ የቁም እንስሳትና የሥጋ ውጤቶች ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ በቅርቡ መነሳቱን፣ ከኳራንታይኖች ግንባታ ጋር በማያያዝ መሻሻል ስለመምጣቱ ጨምረው ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡

ሌሎቹ ግንባታቸው በቅርብ እንደሚጠናቀቁ የተገለጸው ኳራንታይኖች በጅግጅጋ፣ በሁመራና በመተማ እንደሚገኙም ተመልክቷል፡፡ የሦስቱም ኳራንታይኖች ግንባታ የውኃ መስመርና ዝርጋታ በከፊልና ሙሉ ለሙሉ የተከናወነላችው መሆኑን ጠቁመው፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እየተጠባበቁ ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዘርፉ የውጭ ገበያ መዳረሻን ለማስፋት በመንግሥት እየታየ ካለው ፍላጎት አንፃር በአገሪቱ ተመሳሳይ ሥፍራዎች ተጨማሪ ኳራንታይኖችን መገንባት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ በተለይ አሁን ያለው የውጭ ገበያ ተደራሽነቱ በመካከለኛው ምሥራቅ ብቻ የተወሰነ መሆኑን ያወሱት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከመጪው ዓመት ጀምሮ አገሪቱ ያላትን የቁም እንስሳት ሀብትም ሆነ የሥጋ ምርቶችን ወደ ሩቅ ምሥራቅ ለማድረስ ሰፊ የገበያ ዕድል መኖሩን ባደረግነው የገበያ ጥናት አረጋግጠናል፤” ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ሊገነቡ ይገባል ባሏቸው ኳራንታይኖች የግል ዘርፉም ሊሳተፍበት እንደሚችል ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

በዕለቱ እንደ ኳራንታይኖቹ ሁሉ ሚኒስቴሩ እያከናወናቸው በሚገኙ ሌሎች ዘርፎች ላይ ለተነሱላቸው ተመሳሳይ ጥያቄዎች ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በአገሪቱ በተለይም በቆላማና አርብቶ አደሩ በስፋት በሚገኝባቸው አካባቢዎች የቁም እንስሳትን እያጠቁ የሚገኙትን የቆላ ዝንብና የገንዲ በሽታን ለምን በተሻለ መንገድ መቋቋም እንዳልተቻለ፣ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ እያሰበ ያለው አዲስ ዕርምጃ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡

ሚኒስትሩ ሲመልሱ የተጠቀሱትን የከብት በሽታ ዓይነቶችን ሆነ የበሽታው አስተላላፊዎችን ለመቆጣጠር በፕሮጀክት ደረጃ በኑክሌር ሳይንስ በመታገዝ በቤተ ሙከራ የመከኑ የቆላ ዝንቦችን በማርባትና በአውሮፕላን በሽታው በተዛመተባቸው ሥፍራዎች በመርጨት፣ በተፈጥሮ የተፈለፈሉትን የቆላ ዝንብ ዝርያዎችን ለመቆጣጠር ሲደረጉ የቆዩ ተግባራትን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ በቤተ ሙከራ የሚከናወነው የማዳቀል ሥራዎችና ተደራሽነትን ለማስፋት እየተደረገ ያለው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም፣ የአገሪቱ የቁም እንስሳት የሚገኙባቸው ሥፍራዎች ከመስፋታቸውና የተለያዩ ክልሎችን የሚሸፍኑ በመሆኑ፣ በኑክሌር ሳይንስ የመከኑ የቆላ ዝንቦችን በብዛት እያራቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እነዚህን የተራቡና ከመደበኛው የዝንብ ዓይነቶች ፈጣንና ጠንካራ ዝርያዎችን በሚፈለጉባቸው ሥፍራዎች በአውሮፕላን ረጭቶ ለማዳረስ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ አዳዲስና ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገት የግድ ማስፈለጉን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህም አጋዥ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች አንዱ ያሉትን የድሮን (ሰው አልባ በራሪ ወይም አውሮፕላን መሰል ማጓጓዣ) ግዢ መፈጸሙን ቢገልጹም፣ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ስለሌለ መንግሥት በልዩ ሁኔታ እስኪፈቅድ እየተጠባበቁ እንደሆነ አክለዋል፡፡

ነገር ግን ከሚኒስትሩ ማብራሪያ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማወቅ ሪፖርተር የሚኒስቴሩን ሌሎች ኃላፊዎችን ባነጋገረበት ወቅት፣ ድሮኖቹ በኦስትሪያ የተመረቱና ከዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ በስጦታ የተበረከቱ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

 የድሮኖቹን አገልግሎት በተመለከተ ሲያብራሩ፣ በኑክሌር ኃይል በመታገዝ በቤተ ሙከራ የመከኑ የቆላ ዝንቦችን ለማስፈልፈልና ከአየር ላይ በመርጨት ለመቆጣጠር፣ ሥራው ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ጋር በትብብር እንደሚከናወንና ድሮኖቹን ከመደበኛ አውሮፕላኖች በተሻለ ጥራትና በአነስተኛ ወጪ ለመጠቀም ታስቦ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...