[ክቡር ሚኒስትር ለበዓል ከአሜሪካ የመጣ የቀድሞ ወዳጃቸውን የበዓል ምሣ ጋብዘውት እያወሩ ነው]
- ብላ እንጂ ምግቡ አልጣመህም እንዴ?
- ክብር ሚኒስትር ይኼ ካልጣመኝ ምን ሊጥመኝ ነው?
- ከጥሬውም፣ ከክትፎውም፣ ከዶሮውም፣ ከፍትፍቱም እያወጣህ ብላ እንጂ፡፡
- ምን ይኼ ብቻ? ጎድን ጥብሱ፣ አልጫውና ቀይ ወጡ፣ ከሽከሽ የሚለው ደረቅ ጥብስ፣ . . . ጉድ እኮ ነው፡፡
- አየህ በዓላትን የምናደምቀው በእነዚህ ምግቦች ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔማ የአንድ ቢሊየነር ድግስ ላይ የተገኘሁ ነው የመሰለኝ፡፡
- እኛም እኮ ሚሊየነሮችን እያፈራን ነው፡፡
- እርስዎም ሚሊየነሮች ተርታ ያሉበት ይመስላሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከዕድገቱ መቋደስ መብታችን ነው እኮ፡፡
- በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ነበር?
- ሕዝቡ ከልማቱ ተጠቃሚ አይደለም የሚባለው እውነት ነው?
- ዌል እንግዲህ በየደረጃው ተጠቃሚነት ይኖራል፡፡
- ማለት?
- ልማቱን ከደገፍክ ለአንተም አይጠፋም ማለቴ ነው፡፡
- እኔ እያልኩ ያለሁት ፍትሕዊ ተጠቃሚነትን ነው፡፡
- ፍትሕዊ ተጠቃሚ ለመሆን እኮ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል፡፡
- ለምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ልማታዊውን ኃይል ለማገዝ፡፡
- ዜጎች የልፋታቸውን ካበረከቱ እኮ መቀጠም አለባቸው፡፡
- ለውጤት መልፋትና ዝም ብለው ሲያዘጠዝጡ በመዋል እኩልነት አይመጣም፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ወዳጄ ይኼ የዳያስፖራ ጭንቅላትህን አሠራው፡፡
- እስኪ በግልጽ ይንገሩኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ይኼ ገበታ እንዲህ ሞልቶ የተንጣለለው ያለ ሥራ መሰለህ?
- በእርግጥ በዓይኔ ከማየው በላይም የገነቡዋቸው ሦስት ሕንፃዎች፣ የሚያንቀሳቅሱዋቸው የተለያዩ የግል ኩባንያዎች. . . ብዙ ይናገራሉ፡፡
- አሁን እየገባህ ነው፡፡
- ይህ ምን ያመለክታል ክቡር ሚኒስትር?
- ተጠቃሚ መሆን ከፈለግክ ውጤታማ መሆን አለብህ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- በጥሎ ማለፍ ነዋ!
- አሁንም አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- የጨዋታውን ሕግ ማወቅ ብቻ ሳይሆን. . .
- እህ?
- ሕጉን ለራስ በሚመች መንገድ መጻፍ መቻል፡፡
- ከዚያስ ክቡር ሚኒስትር?
- ከዚያማ ከሚሊየነርነት ወደ ቢሊየነርነት መሸጋገር፡፡
- እርስዎ ይህንን ተግባራዊ እያደረጉ ነው?
- ካርል ማርክስ ምን እንዳለ ታውቃለህ?
- ምን አለ ክቡር ሚኒስትር?
- ‹ፈላስፎች ዓለምን በተለያየ መንገድ ተርጉመውታል፣ ዋናው ቁም ነገር ግን ዓለምን መለወጥ ነው› ያለው፡፡
- ይኼ ምን ማለት ነው?
- ብዙ ከማውራት. . .
- እ?
- በትንሽ ድርጊት ራስን መለወጥ፡፡
- ምን የሚሉት መርህ ይሆን?
- ‹የበላ በለጠ የሮጠ አመለጠ› ይባላል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የምሣ ግብዣቸው ላይ ከተገኘ አንድ ባለሀብት ጋር የጦፈ ወሬ ይዘዋል]
- አንተ እንዲህ ጠፍተህ ለበዓል ትመጣለህ?
- ምን ይደረግ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የሚያጠፋ ምን ተገኘ?
- የጠፋሁበትን ምክንያት ሳያውቁት ቀርተው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምድንነው እሱ?
- የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሊያሳብደኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼማ የአገር ችግር ነው፡
- የአገር ችግር ቢሆንም ሲመራረጡበት እኮ ነው የሚውሉት፡፡
- እነ ማን?
- የተሻለ የሰጡና የተቀበሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ለምን አልነገርከኝም?
- ረሱት እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑን?
- ከአንዴም ሦስቴ ነግሬዎት ነበር፡፡
- እንዴት ረሳሁት እባክህ?
- ተሃድሶ ግምገማ ላይ ሆነው ምኑ ትዝ ይበልዎት?
- ልክ ነህ፡፡
- ግምገማው ጨከን ያለ ነበር ክቡር ሚኒስትር?
- ቢሆንም እንችለዋለን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የውጭ ምንዛሪው ጉዳይ እኮ በጣም እያሳሰበኝ ነው፡፡
- እንደምንም ይፈለግልሃል፡፡
- ያለበለዚያ ሞቴ እንደተቃረበ ይወቁት፡፡
- አይዞህ በእኔ ተወው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እሱ ከተሳካልኝ ሌላውን በእኔ ይተውት፡፡
- እሱ ድሮ ቀረ እባክህ፡፡
- ምን ማለትዎ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በአራዳ ቋንቋ ልንገርህ እንዴ?
- በአራዳ ቋንቋ?
- አዎ!
- እርስዎ እኮ አይቻሉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቀድመህ ታደርጋለህ፡፡
- ምኑን?
- በለመድከው የአራዳ ቋንቋ ልንገርህ ያልኩት እኮ ለዚህ ነው፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር አወሳሰቡኝ፡፡
- በል ወዳጄ ቶሎ ወደ አካውንቴ ትራንስፈር አድርገው፡፡
- ምን?
- ቀብዱን ‹ውረድ› አልኩህ፡፡
- ይኼ ደግሞ ከመቼ ወዲህ የመጣ ፈሊጥ ነው?
- ዘመኑ ተቀየረ እኮ?
- ወዳጅነት እንዲህ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እንካ በእንካ ነዋ፡፡
- ድሮ እኮ እንዲህ አልነበሩም?
- ‹በድሮ በሬ ያረሰ የለም› ሲባል አልሰማህም?
[የምሣ ግብዣው ላይ የተገኘ የክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ዘመድ እያነጋገራቸው ነው]
- አንተ እንዴት ነው እባክህ እንዲህ የተስማማህ?
- ዕድሜ ለአንተ ጋሼ፡፡
- እኔ እኮ ለመነሻ የሚሆን ነው የረዳሁህ፡፡
- አንተ ባሳየኸኝ መንገድ ሄጄ ነው ቀን የወጣልኝ ጋሼ፡፡
- ሥራ እንዴት ነው?
- ዕድሜ ለአንተ ስምህ ሲጠራ በሩ ሁሉ ይከፈታል ጋሼ፡፡
- እንዴት እባክህ?
- በስምህ የአገሩን በር ነው የበረጋገድኩት ጋሼ፡፡
- ከዚህ ሁሉ የእኔ ድርሻ የታለ ታዲያ?
- ጋሼ በእትዬ አካውንት እየገባ እኮ ነው፡፡
- እስካሁን ስንት ለቀቅክ?
- ሃያ ሁለት አካባቢ ገብቷል ጋሼ፡፡
- ሚሊዮን?
- አዎ ጋሼ፡፡
- በስንት ጊዜ?
- በዘጠኝ ወራት ውስጥ ጋሼ፡፡
- በዚህ ሁኔታማ አንተ ከሃምሳ በላይ ዘግተሃል፡፡
- ወደዚያ አካባቢ ነው ጋሼ፡፡
- የእኔ እንዴት ይኼ ብቻ ሆነ?
- የመጀመሪያ ስለሆነ ትንሽ ልቋቋም ብዬ ነው ጋሼ፡፡
- አዎ ቤት መሥራት፣ አሪፍ መኪኖች መግዛት፣ ትዳር. . . ያስፈልጉሃል፡፡
- ጋሼ?
- አቤት?
- የአንተ ስም እኮ ነው የጠቀመኝ፡፡
- ወደፊትም ይጠቅምሃል፡፡
- እሺ ጋሼ፡፡
- ግን. . .
- ግን ምን ጋሼ?
- ተጠንቀቅ!
- ከምን ጋሼ?
- ለእኔ የነገርከኝን ለማንም እንዳትናገር፡፡
- እኔ እኮ መቃብር ማለት ነኝ ጋሼ፡፡
- ካልሆንክ ግን ቀብርህን ፈጽምልሃለሁ፡፡
- ኧረ ጋሼ?
- አትንዸርዸር በቃ፡፡
[የበዓሉ የምሣ እንግዶች ተሸኝተው ክቡር ሚኒስትሩና ባለቤታቸው እያወሩ ነው]
- በጣም ምርጥ የሚባል መስተንግዶ ስለነበር አመሰግንሻለሁ፡፡
- ይገባኛል ክቡር ሚኒስትራችን፡፡
- ትንሽ ሲያሳዩሽ እኮ አትቻይም፡፡
- መመስገንና መወደስ ማን ይጠላል?
- እኔ ግድየለኝም፡፡
- አናውቅዎትም ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት?
- በሬዲዮ፣ በጋዜጣ፣ በቴሌቪዥን የእርስዎ ጥሩ ጥሩ ዜናዎች ሲቀርቡ እንዴት እንደሚፍለቀለቁ?
- ስተችም ያው ነኝ፡፡
- ባለፈው በግምገማ ሊነሳ ነው ተብሎ ሲወራብህ አብደህ አልነበር?
- ያ ሌላ ይህ ሌላ፡፡
- ለማንኛውም የምሣ ላይ ወሬህ ፍሬነገር ነበረው?
- በጣም እንጂ፡፡
- ምን አገኘህበት?
- ዳያስፖራውን አወዛገብኩት፡፡
- እሺ?
- ወዳጄ ኢንቨስተሩን ለፈጣን ክፍያ አቀባበልኩት፡፡
- እሺ?
- ያንን የአክስቴን የልጅ ልጅ ደግሞ አወጣጣሁት?
- ምኑን?
- በአካውንትሽ የለቀቀውን፡፡
- ይህቺም ገንዘብ ቁም ነገር ሆና?
- እስካሁን ለምን አልነገርሽኝም?
- አነስተኛና ጥቃቅን ጉዳይ አይመለከትህም ብዬ ነዋ፡፡
- ነው እንዴ?
- አዎ ምነው?
- የሺሕ ኪሎ ሜትር ጉዞ በአንድ ዕርምጃ የሚጀመር መስሎኝ?
- ይህቺም ገንዘብ ሆና በበዓል አትነጅሰኝ፡፡
- ሃያ ሁለት ሚሊዮን?
- አትቀልድ እባክህ፡፡
- ለማንኛውም?
- እሺ?
- ንገሪኝ፡፡
- ምን ልንገርህ?
- እያንዳንዷን ነጥብ፡፡
- ትንሽ ነገር ምን ያደርግልሃል?
- ትንሽ መስሎኝ ትልቁን የሚያጠፋው?
- ማለት?
- የመረጃ ትንሽ የለውም፡፡
- ምን ያደርግልሃል?
- አንቺ አይገባሽም እንዴ?
- ምኑ ነው የሚገባኝ?
- ስለ ጉንዳን ታውቂያለሽ?
- ጉንዳን?
- አዎ ጉንዳን?
- እና?
- ጉንዳን በጣም ትንሽ ፍጡር ነው፡፡
- እሺ?
- ሾልኮ ከገባ ግን. . .
- የት?
- ውስጣችን፡፡
- እሺ?
- አደባባይ ላይ ሱሪ ያስፈታናል፡፡
- ሆሆ. . .
- ስለዚህ?
- መርሀችን ነቃ በሉ ነው የሚለው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ሊተኙ ሲሉ ልጃቸው ከውጭ ሲገባ አገኙት]
- አንተ በበዓል ቀን የት ነው የምትዞረው?
- ጓደኞቼ ጋ ወጣ ብዬ ነበር ዳዲ፡፡
- እዚህ ስንት ተደግሶ ምን ያዞርሃል?
- አለ አይደል ዳዲ፡፡
- አንተ ጠጥተሃል እንዴ?
- በመጠኑ ዳዲ፡፡
- ምንድነው የጠጣኸው?
- አንድ ሁለት ሻት ነው ዳዲ፡፡
- ምንድነው እሱ?
- አለ አይደል ዳዲ፡፡
- ንገረኝ?
- ትንሽ ቮድካ ነው ዳዲ፡፡
- ከመቼ ጀምሮ ነው የምትጠጣው?
- ዳዲ አትቆጣ፡፡
- ሰክረህ እያየሁ እንዴት አልቆጣ?
- አለ አይደል አንዳንዴ ፈታ ማለት አስፈላጊ ነው ዳዲ፡፡
- ምን አልክ አንተ?
- ፈታ ነው ያልኩት ዳዲ፡፡
- ምኑ ነው የሚፈታው አንተ?
- ዘና ማለቴ ነው ዳዲ?
- ማን ነው የአስተማረህ?
- አንተ ነህ ዳዲ፡፡
- እንዴት አድርጌ?
- ሚኒስትርነቱንና ቢዝነሱን አንድ ላይ ማስኬድ እኮ የተለየ ስጦታ ነው ዳዲ?
- እና?
- እኔም ትምህርቱንና መዝናናቱን አንድ ላይ ማስኬድ ችዬበታለሁ፡፡
- ውይ. . . ውይ. . . ውይ. . .
- አገሪቱም እኮ እንዲህ ነው ግብግብ የምትለው ዳዲ፡፡
- ያንገብግብህ!