Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይተናነቀናል እኮ!

እንሆ መንገድ ከመገናኛ ወደ ኮተቤ ልንጓዝ ነው። እልፍ አዕላፍ ታረኮች በህላዌ መንደር ዛሬም እየተኖሩ ይተረካሉ። እዚህ የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ መካከለኛው የጥንዶች ረድፍ ላይ አባት የልጁን ፈተና ወረቀት ዘርግቶ ‘ኤክሶቹን’ ይቆጥራል። ልጅ አብዛኞቻችን የዕድሜ ልክ ደመወዛችን ቢደመር የማይሸምተው፣ ከፍሬው ቀድመን ያወቅነውን አፕል ስልክ የመጨረሻ ምርት ይዞ ‘ከረሜላ ማፍረስ’ ይጫወታል። ‹‹እንዴት ይኼን ትሳሳታለህ?›› አባት በድንገት ወደ ልጁ ተቆጥቶ ዞረ። ልጅ ቀናም አላለ። ‹‹የቱን?›› ከረሜላ በከረሜላ እያፋጨ፣ በለስ ከቀናው ቦምብ እያፈነዳ የቸኮሌት ‘ቦነስ’ ይለቅማል። ‹‹እስኪ አሁን ከረሜላ መሃል ቦምብ እያፈነዱ አድገው ነው ለሰው የሚመለሱት?›› ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ደርባባ ወይዘሮ ትጠይቀኛለች። ‹‹ይኼ ‘ካንዲ ክራሽ’ የሚሉት ጌም የስንቱን ትዳር በተነው መሰለህ? ታውቃለህ የጋሼ (ማን ነበር ስማቸው?) ልጅ ከባሏ ያፋታት እኮ ይኼ ‘ጌም’ ነው፤›› መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ጓደኛማቾች ያወጋሉ።

‹‹አንተን እኮ ነው የማናግረው! ይኼን እንዴት ‘ኤክስ’ ልትሆን ቻልክ?›› አባት ብስጭቱ ጨምሯል። እግዜር ባርኮለት ምንም እንኳ በሁለተኛው ዙር ቢሆንም ልጁም ደነገጠለት። ‹‹መቼ ያሳፍራል የእሱ ስጦታ ከሆነ?›› ብሎ ያጉተመተመውን ተሳፋሪ ልለየው አልቻልኩም። ‹‹ልክ ነኝ። አስተማሪው ነው የተሳሳተው፤››  በኩራት ልጅ አባቱን ያስረዳዋል። ‹‹ጥያቄው ‘ገፀ ባህሪያት ቀርፀን ታሪክ ስንጽፍ ስንት ዓይነት የግጭት ዓይነቶችን መጠቀም እንችላለን?’ ነው የሚለው። መልሱ ‘ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋርና ሰው ከመኪና ጋር’ ነው። አስተማሪው ግን ‘ሰው ከመኪና ጋር’ አልክ ብሎ ‘ኤክስ’ ሰጠኝ፤›› ብሎ እንዳበቃ ተሳፋሪው ‹‹ተባረክ! ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ። ስንቷ በመኪና አደጋ ቆማ እየቀረች፣ ስንቱ ሚስቱን በመኪና አደጋ እያጣ፣ ያለ እናት ልጁን እያሳደገ ቤተሰብ እየተበተነ እያየ ይኼን ‘ኤክስ’ ካደረገህ መገምገም አለበት፤›› ብላ ወይዘሮዋ ደነፋች። ‘ኤክስ’ ወይ ‘ራይት’ አንድ ነገር ነው፡፡ ግምገማን ምን ዶለው? ለሰው ‘ኤክስሬይ’ ማዘዝ ስንወድ ግን!

ጉዟችን ተጀምሯል። ሾፌራችን እንደ ሰደድ እሳት ጨዋታ ተጀምሮ ሲቀጣጠል፣ ‹‹ታክሲ ውስጥ በህቡዕ መደራጀት ሳይጀመር›› እያለ ለወያላው የሬዲዮኑን ድምፅ ጨመር ያደርገዋል። አንጀት የሆነ የስፖርት ትንታኔ እናደምጣለን። ‹‹ክርስቲያኖ ሮናልዶና ሜሲ እንደ አሜሪካና ሩሲያ ተፋጠዋል፤›› ይላል ጋዜጠኛው። ‹‹አሜሪካና ሩሲያ ተፋጠዋል እንዴ? ለመሆኑ እነሱም እንደ እኛ የሚያስፈጥጥና የሚያፋጥጥ ጉድ ያውቃቸዋል እንዴ?›› ትላለች ከኋላችን ቆንጂት። ወይዘሮዋ ቀበል አድርገው፣ ‹‹ኧረ ዝም በይው። ይኼ አንቺን አይመለከትም። የኮስሞቲክስና የፀጉር መሥሪያ ዋጋ የሚያሳስባችሁ አልበቃ ብሎ ጭራሽ የሩሲያና የአሜሪካ ፍጥጫ ይጨመርባችሁ?›› ስትላት ተሳፋሪዎች ተደናገጡ። ወዲያው ግን፣ ‹‹በተመሳሳይ ሰዎች መሀል የተነሳ ‘ክሪቲሲዝምን’ የሚዳኝ ሕግ እስኪወጣ ምን ማድረግ ይቻላል?›› ብሎ ጋቢና የተቀመጠው ወጣት ቀልባችንን ወደ ሜሲና ሮናልዶ ፍጥጫ መለሰው።

አፍታም አልቆየ ‘ሜሲ ይበልጣል ሮናልዶ’ ክርክሩ ጦፈ። ‹‹ደግሞ ሜሲ ጀግና ይባላል? በስንት ተጋዳይ ሰማዕታት ላብና ደም እኮ ነው እዚህ ያደረሰው፤›› ሲል አንዱ ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ስለኳስ ተጫዋቹ ሜሲ ነው የሚያወራው? ወይስ ሜሲ የሚባል ታጋይ ነበረ?›› ይላል ሌላው። ‹‹ሮናልዶንማ የሚያክለው የለም አይገርማችሁም? (ኧረ ማንም አልተገረመም ወንድም) ምናልባት ራሱ ስለራሱ ችሎታ አዳንቆ ሜሲን እበልጠዋለሁ ማለቱ ቢያስተቸውም…›› ብሎ ሌላው ንግግሩን ሳይጨርስ ደግሞ ጋቢና ያለው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹እኔ እኮ የእኛ ሰው ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡ በእኔ እበልጥ በእኔ እሻል የሚዳማው። የእኔ አስተዳደር፣ የአገር ግንባታ፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ ወዘተ ካለፈውና ከሚመጣው ይለያል የሚል የእኛ ሰው ብቻ ይመስለኝ ነበር። ለካ ፈረንጅም ራሱን ያንቆለጳጵሳል?›› ብሎ ታኬታ ለባሽን ዘውድ ከሚጭነው ያመሳስላል። በተረፈ ተሳፋሪዎች ‘የሜዳን ለባለ ሜዳው! የዙፋንን ለባለ ዙፋኑ!’ ቢባሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ባይ ሆነው ይኼው ሁለት ሺሕ ዓመት ድረስ እየተጓዙ ነው።

 ወያላችን የተቀዳደች ሸሚዝ ደርቦ ሲንጎማለል መተሃራ የሚጓዝ አውቶቡስ ረዳት ይመስላል። ‹‹አንተ እንዲያው ይህቺን ጥብቆ ለብሰህ አይበርድህም?›› ይሉታል ከሾፌሩ ጀርባ ከጎኔ የተቀመጡ አዛውንት። ‹‹አያዩትም እንዴ ይኼን የዝናብ ፀሐይ? ደግሞስ ደርበን መቼ ሞቆን ያውቃል? ዘንድሮ እኮ ብርዱና ሙቀቱ ተቀላቅሏል፤›› እያለ ይመልሳል። ብልህና አስተዋይነት ጎልቶ የሚነበብባቸው እናት ‹‹ነገረኛ›› ብለው ፈገግ አሉ። ጆሮዬ በከፊል እዚህ ከፊል ጋቢና ወደ ተቀመጡት ወጣቶች ነው። ሾፌሩ ቆየት ያለ የሙዚቃ ስብስቦቹን እያጫወተ መንገዱንም ተሳፋሪዎችንም የረሳ ይመስላል። ‹‹እንቅልፌን ደርበህ ተኛልኝ እባክህ…›› ትላለች በዛወርቅ አስፋው። ‹‹እስኪ ትንሽ ድምፁን ከፍ አድርገው፤›› ይላል አንደኛው። ‹‹ሰምቼው አላውቅም እባክህ…›› ሲል መልሶ፣ ‹‹መስማት ሲፈጥርብን አይደል?›› ይለዋል ከጎኑ የተቀመጠው። የፊተኛው ግጥሙን አጣርቶ ሰምቶ ሲያበቃ ከት ብሎ እየሳቀ፣ ‹‹እንኳን እንቅልፍ ደርበን ሳንደርብብም ቅዠቱን አልቻልነው፤›› ብሎ ሳቁን ቀጠለ።

‹‹ምን ማለትህ ነው ዘፈኑ እኮ የፍቅር ነው። ተኙልኝ አላለች፣ ያለችው ተኛልኝ ነው። በሰው አደራ ምን አገባን እኛ?›› ብሎ አጠገቡ ያለው ነጀሰው። ነገር ቆስቋሹ ተሳፋሪ ንጀሳውን ችላ ያለ መስሎ፣ ‹‹ብቻ ሥልጣንና ፍቅር የማያሳብደው የለም። የሁለቱ አንድነት ታዲያ በእብደት መሀል ደርብ የሚሉህ ነገር ብዛት ነው። ከእንቅልፍ እስከ ችጋር አምጥተው አንተ ጋ መቆለል ነው። አስተኝተው ማሸት ሲችሉበት…›› ብሎ አብሮ ማዜም ጀመረ። ‹‹በቃ ሰው በሰበብ አስባቡ በመንግሥት ካልተነጫነጨ አይሆንለትም?›› ስትል ከኋላዬ አንዷን ደርባባ አዳምጣለሁ። ‹‹ከእንቅልፉ ሲቀሰቀስ የማይነጫነጭ ሰው አለ ብለሽ ነው?›› የሚላት ደግሞ ካጠገቧ ‘ፌስቡክ’ ላይ ‘ሎግ ኢን’ ብሎ ያቀረቀረ ተሳፋሪ ነው። የሱሳችን ብዛትና ተለዋዋጭነት አይገርምም ግን?

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላችን ሒሳብ ተቀብሎ መልስ ያቀባብላል። ጎልማሶቹ ወደ ግል ጨዋታቸው ዞረዋል። ‹‹አንተ ባለፈው ያን ጉዳይህን ጨረስክ ወይስ እስካሁን እያመላለሱህ ነው?›› ይጠይቃል አንደኛው። ‹‹ኧረ ተወኝ። ሳምንት ሲቀጥሩኝ ወር ስመላለስ ቆይቼ፣ ይኼው አሁን ደግሞ የዛሬ ሁለት ሳምንት ያልቃል ብለውኝ ተቀምጫለሁ፤›› ይመልሳል በብስጭት። ‹‹አይ ቢሮክራሲና የባለጉዳይ አበሳ?›› አለች ሳታስበው ከኋላቸው የተቀመጠች ወጣት፡፡ ‹‹ቢሮክራሲ ብቻውን ቢሆን እስካሁን በመልካም አስተዳደር ዕጦት የምንሰቃይ ይመስልሻል? አይ ሞኝት። ዋናው ቢሮክራሲ እኮ የሚያስተናግዱሽ ሰዎች ቀናነት ማጣት፣ ለሥራ ያላቸው የተነሳሽነት ስሜት መቀዛቀዝ፣ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ስለሚበዙ ጭምር እኮ ነው፤›› አለና መስኮቱ ጥግ የተቀመጠ ወጣት ተሳፋሪ ቀጠለ።

‹‹ለምሳሌ ባለፈው አንድ ስም አይጠሬ መሥሪያ ቤት ለሆነ ጉዳይ ሄጄ አንዱ ቁም ስቅሌን አሳየኝ። እዚያ ቢሮ ግባ ይለኛል። ስገባ የለም እዚህ አይደለም፣ እዚያ ነው ስባል፣ ብቻ ምን አለፋችሁ እሄዳለሁ ቀኑ ይመሻል። ማልጄ እሄዳለሁ ሲመሽ እመለሳለሁ። ሲመረኝ፣ መቼም ሲመረን ሁላችን አለን ቀን አይደል? ሄድኩና ያ ሰውዬ ላይ ስጮህ እየሳቀ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‘አንተ ማን ስለሆንክ ነው እኔ ተቀምጨ አንተ ቆመህ አዘኸኝ የማስተናግድህ? ገና እንደመጣህ እዚህ ተቀምጬ አሳንሰህ እንዳየኸኝ ገብቶኛል።’ አለኝ። ይታያችሁ እስኪ። ‘ተቀምጬ አንተ ቆመህ ቁልቁል እያየኸኝ ጉዳይህ እንዴት ቶሎ ሊያልቅ ትፈልጋለህ?’ ብሎ ነገር አለ?›› ብሎ ገጠመኙኝ ሲነግረን ፈጠራ እንጂ እውነት ያጋጠመው አልመስለን ብሎ እርስ በርስ ተፋጠጥን። በመፋጠጥ የአፈጻጸምና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የምንቀርፍ ይመስል? ጉድ አሉ የባሰባቸው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹እስኪ እስከዚያች መንደር ጫነኝ የእኔ ልጅ። እዚያች ፉካዋ ጋር ታወርደኛለህ? በሞቴ…›› ይማፀናሉ ዕድሜ ሽቅብ ሲሮጥ እያንኳተተ የሚያሰቃያቸው አዛውንት። ‹‹ኧረ የምን ሞት አመጡ ደግሞ በትንሳዔው? ይግቡ ግድ የለም!›› ወያላው የልጅነት ስሜትና ሥልጣን እየተፈራረቁበት ቸርነቴን እዩልኝ ይለናል። ‹‹ተባረክ! እሱስ አንተ ሆነህ አይደል በነፍስ የተለመንክ? አንዱ ይኼውላችሁ ግቢ እሸኝሻለሁ ብሎ አሳፍሮ ሲያበቃ መሀል መንገድ ትራፊክ ያየኛል ብሎ አባረረኝ። ዋ ሰው! በደጉ ጊዜ በቅሎ ጭነን፣ ፈረስ ለጉመን ስንቱን ያለ ሳንቲም ያለ ሴራ የትናየት እንዳልሸኘን፣ ዛሬ መኪናው ለሚወስደን ጊዜ ለሚያሳፍረን ሞልቷል ይሉናል፤›› ብለው አዛውንቷ ቆዘሙ። ‹‹ወዴት እየሄዱ ነው?›› ጠየቀቻቸው ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመች ወይዘሮ።

አዛውንቷ የመንገዱን ዙሪያ ገባ ቃኝተው፣ ‹‹ምኑን አውቄው ልጄ? ተኝተሽ ስትነሺ የነበው እንዳልነበረ ሆኖ ታገኚዋለሽ። ቴሌቪዥኑ ልማት፣ ልማት፣ ጥልቅ ተሃድሶ ይላል። አሮጌ አስተሳሰብ ሳይፋቅ ተሃድሶ ብሎ ነገር። ዘንድሮስ ይውጋሽ ብሎ ይማርሽ ሆነ ሥራችን። መንገድ በመንገድ ላይ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሆነ። መንገዴም ጠፋኝ፤›› እያሉ በራሳቸው ሳቁ። ‹‹ምንድነው እሱ በፌስታል የያዙት?›› ጠየቃቸው ከአጠገቤ የተቀመጠው ጎልማሳ። ‹‹ለፋሲካው ከተረጠብኩት ለዳግማይ ትንሳዔው የቆጠብኩት ፍርፋሪ፤›› አሳጥረው መልሰው ረጀም ትካዜ ውስጥ ገቡ። መልሰው፣ ‹‹ብዙ እህል ታቅፈህ መቀመጥ፣ ባትበላውም ጉልበት የተበላ ቀን ሕመሙ ከቁንጣን ይብሳል። ዘመኑ የማከማቸት ሆነ። ሚሊዮን መቆለል ባይቀናን ፍርፋሪያችንን ማሻገት ማን ይከለክለናል?›› አሉትና ያቋረጡዋቸውን አጫጭር ሳቆች አርዝመው ስቀው ጨረሱዋቸው። ዓይኖቻቸው መሀል የታከታቸውና ተስፋ ያጡ እናቶች ሲቃ ጎልቶ ተሰማን መሰል ተናነቀን። ‘ተናነቀኝ እንባ…’ ነበር ያለው ዘፋኙ? ይተናነቀናል እኮ፡፡ ወርደናል። መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት