የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ዘመናዊ የንግድ ማዕከላት ግንባታ ለማካሄድ ፕሮጀክት ቀረፀ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የተቀረፀውን የንግድ ሪፎርም በጥልቀት ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላሉ ያላቸውን የገበያ ማዕከላት ለመገንባት ከአቃቂ ቃሊቲ፣ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ከኮልፌ ቀራኒዮና ከቦሌ ክፍላተ ከተሞች ቦታ ተረክቧል፡፡ በመረከብም ላይ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገመቺስ መላኩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የከተማው አስተዳደር በ2003 ዓ.ም. የንግድ ሪፎርም ከቀረፀ በኋላ ለውጦች መጥተዋል፡፡
‹‹በሪፎርሙ የተገኙትን ውጤቶች የበለጠ ለማስፋትም በአሥሩም ክፍላተ ከተሞችና በማስፋፊያ አካባቢዎች ዘመናዊ የግብይት ሥፍራዎችን ለመገንባት ታቅዷል፤›› ሲሉ አቶ ገመቺስ አስረድተዋል፡፡
በተለይ በአሁኑ ወቅት በመሳለሚያ አካባቢ ተወስኖ የሚገኘው እህል በረንዳ፣ በሌሎችም አካባቢዎች በተደራጀና በዘመናዊ መንገድ ለማስፋት ታቅዷል፡፡ ፒያሳ የሚገኘውን አትክልት ተራም እንዲሁ እዚያው አራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ ወደ ዘመናዊ የንግድ ማዕከል ለማዛወር፣ ከዚያም በተጨማሪ በንፋስ ስልክና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍላ ከተሞች፣ እንዲሁም በሌሎች ክፍላተ ከተሞች ለማስፋፋት መታቀዱን አቶ ገመቺስ ተናግረዋል፡፡
በተወሰኑ ቦታዎች ተከማችቶ የሚገኘው የዕርድ እንስሳት ፋብሪካ በዋና ዋና የገበያ ማዕከላት የማስፋት ዕቅድም እንዳለ ተገልጿል፡፡
‹‹የገበያ ማዕከላቱን ማስፋፊያ አስተዳደሩ ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር የሚያካሂደው ነው፤›› ሲሉ አቶ ገመቺስ ተናግረው፣ ‹‹በተያዘው በጀት ዓመት ብዙ ሥራዎች ይከናወናሉ፤›› ሲሉ አቶ ገመቺስ አስረድተዋል፡፡
ንግድ ቢሮው ከመደበኛ ንግድ በተጨማሪ መደበኛ ባልሆነው የንግድ ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት ፖሊሲና ደንብ አዘጋጅቷል፡፡
አቶ ገመቺስ እንዳሉት በጎዳና ንግድ፣ ወቅት እየጠበቁ በሚካሄዱ የንግድ ሥራዎች (እሸት በቆሎ)፣ እንዲሁም የባልትና ውጤቶችን ጨምሮ በአምስት የንግድ ዓይነቶች ላይ ሥርዓት ለማስያዝ ታቅዷል፡፡
እነዚህን ሥራዎች ለማካሄድ ፖሊስ፣ ፍትሕ፣ እሳት አደጋን ጨምሮ ዘጠኝ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
‹‹ሁለቱም ዘርፎች መደበኛንና ኢመደበኛን የሚገፉ ሳይሆኑ፣ የሚደጋገፉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩን የሚመራ ራሱን የቻለ መዋቅር ይቋቋማል፤›› በማለት አቶ ገመቺስ ገልጸዋል፡፡