Thursday, March 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሊዝ አዋጁን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ማሻሻያ አቀረበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ (ሊዝ አዋጅ) ቁጥር 721/2004 በድጋሚ ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ፣ በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ አቀረበ፡፡

በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ባለቤትነት የተዘጋጀውን የሊዝ አዋጅ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከራሱ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ሰነድ አዘጋጅቶ እሑድ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ለውይይት አቅርቧል፡፡

በቀረበው ሰነድ ላይ በተለይ የሊዝ አዋጁ በኅዳር 2004 ዓ.ም. ከፀደቀ ጊዜ ጀምሮ አጨቃጫቂ ሆነው የቆዩ ሦስት ጉዳዮች ላይ የድንጋጌ ለውጥ አድርጓል፡፡

የመጀመርያው የማስፋፊያ ፕሮጀክት መስተንግዶ፣ ሁለተኛው የግዙፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ የቦታ ጥያቄ በድርድር እየተስተናገደ አለመሆኑን፣ ሦስተኛው ደግሞ በአንድ ግቢ ውስጥ የግልና የቀበሌ ቤት ተቀላቅሎ ሲገኝ የሚሰጠው ተነፃፃሪ ካርታ፣ በርካቶችን ወደ ልማት ማስገባት አለመቻሉ ላይ የተወሰዱት ዕርምጃዎች ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ነባር ፕሮጀክቶች የተሰጣቸው ቦታ በቂ ሳይሆን ሲቀር ለቀጣዩ ግንባታ የማስፋፊያ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ የሊዝ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት እነዚህ የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄዎች የሚስተናገዱ ሲሆን፣ ከ2004 ዓ.ም. በኋላ ግን በአዋጁ ምክንያት አገልግሎት ማግኘት ተቋርጧል፡፡

በዚህ ምክንያት ባለሀብቶች ፕሮጀክታቸውን ለማስፋፋት ሳይችሉ ከመቆየታቸው በላይ፣ ለመልካም አስተዳደር ዕጦት ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ግን ለማስፋፊያ ፕሮጀክቶች መሬት የሚቀርብበት ዕድል መፈጠሩ ተመልክቷል፡፡

ሁለተኛው በከተማው ውስጥ ለባለአምስት ኮከብ ሆቴል፣ ለግዙፍ የገበያ ማዕከላት፣ ለሪል ስቴቶች፣ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለጤና ተቋማት መሬት የማቅረብ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ የከተማው ከንቲባ ፕሮጀክቶቹ አገራዊ ፋይዳ አላቸው ብለው ካመኑ መፍቀድ የሚችሉ ቢሆንም፣ አዋጁን ለማስፈጸም በወጡ ደንብና መመርያዎች እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚስተናገዱት በልዩ ጨረታ እንደሚሆን ይደነግጋሉ፡፡

በዚህ ምክንያት በቢሊዮን የሚቆጠር ካፒታል ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ ያቀረቡ በርካታ ፕሮጀክቶች፣ መስተንግዶ ማግኘት ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ እነዚህን ፕሮጀክቶች ለመገንባት ፍላጎት ያላቸው አልሚዎች በአካባቢው የጨረታ ዋጋ፣ ቦታውን በድርድር (በምደባ) ማግኘት የሚችሉበት ዕድል መፍጠሩ ተመልክቷል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የተነፃፃሪ ካርታ (ፕሮፖርሽናል) አሠራር ነው፡፡ ይህ አሠራር በአንድ ግቢ ውስጥ የቀበሌም የግልም ይዞታ ተቀላቅሎ ሲገኝ፣ ባለይዞታው የሚሰጠው ካርታ ተነፃፃሪ ይሆናል፡፡፡

ይህ ባለይዞታ የራሱን ይዞታ ማልማት የማይፈቀድለት በመሆኑ ባለይዞታዎች በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጨዋታ ውጭ የሚሆኑበት አጋጣሚ በመኖሩ ከፍተኛ ቅሬታ ሲነሳ ቆይቷል፡፡

ነገር ግን በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ የግል ባለይዞታው ከአጠቃላዩ ይዞታ ከ50 በመቶ በላይ የያዘ ከሆነ የቀበሌ ቤቱን የመጠቅለል ዕድል እንደተፈጠረለት ታውቋል፡፡ እነዚህ ሦስት ጉዳዮች ጎልተው ቢወጡም፣ ረቂቅ አዋጁ በግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜ ገደብና በተለዋጭ ቤት ጉዳይ ላይ ማሻሻያ አቅርቧል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ባለፈው እሑድ ውይይት አድርገዋል፡፡ የመሬት ሥሪት ባለሙያዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት ግን፣ ውይይቱ መደረግ ያለበት ከአደረጃጀቶች ጋር ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ባለሙያዎቹ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም በእሑዱ ስብሰባ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ከተገኙት ከተለያዩ አደረጃጀቶች የመጡ ነዋሪዎች ይበዛሉ፡፡

ነገር ግን ሊታወስ የሚገባው ጉዳይ በ2004 ዓ.ም. ይህ የሊዝ አዋጅ ከመፅደቁ በፊትና ከፀደቀ በኋላ፣ በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች ጭምር መነጋገሪያ መሆኑ ነው ይላሉ አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡

በዚህ መሠረት በመሬት ሥሪት ጉዳይ ላይ ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ሰዎችና ባለሀብቶች ጭምር ሊወያዩ ይገባል በማለት ገልጸዋል፡፡

ከዘጠኙም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደር አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎች አዋጁን ለማሻሻል ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ጥናት ጎን ለጎንም ከሊዝ አዋጁ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ኦዲት የተደረጉ ሲሆን፣ በኦዲት ግኝቱም አዋጁ መሻሻል እንዳለበት ታምኖበታል፡፡ ረቂቅ አዋጁ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የተለያዩ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎች ውይይት አድርገውበታል ተብሏል፡፡

ከሕዝብ የተገኘው ሐሳብ እስከ መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ተሰብስቦ ለኮሚቴው ከተሰጠ በኋላ፣ ኮሚቴው በድጋሚ ረቂቁን ተመልክቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች