በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ሰርባ መስኖ ተፋሰስ ፕሮጀክት ላይ የሽብር ጥቃት በማድረስ፣ ሁለት ሠራተኞችን በመግደልና በአምስት ሠራተኞች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ 14 ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው አቶ ደረጀ በላይ፣ አቶ ቸርነት ሀብቴ፣ አቶ እሸቱ መከተ፣ አቶ መሀሪ አዲስ፣ አቶ ማስረሻ ማንደፍሮን ጨምሮ 14 ተከሳሾች ሁሉም የሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ፣ የጫሂትና ቆላድባ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ማሞ ግን ጎንደር ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ነጋዴ መሆናቸውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ያቀረበው ክስ ያሳያል፡፡ ከነጋዴው በስተቀር ሁሉም ያልተማሩና አርሶ አደሮች መሆናቸውን ለፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡
ተከሳሾቹ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት አባልና ታጣቂ በመሆን፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ ‹‹መንድባ ጫካ›› ውስጥ ወታደራዊ ቤዝ በመመሥረትና ሙሉ የጦር መሣሪያ በመታጠቅ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሥልጠና ከኤርትራ በመጡ አመራሮች መውሰዳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ አቶ ደረጀ፣ አቶ ቸርነትና አቶ እሸቱ የተባሉት ተከሳሾች በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. በመንድባ ጫካ ውስጥ ከተሰበሰቡ በኋላ ባደረጉት ምክክር፣ መንግሥት በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ ውስጥ በቻይና ኮንትራክተሮች እያስገነባ ባለው የሰርባ የመስኖ ተፋሰስ ፕሮጀክት ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም መስማማታቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ መጋቢት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ በሠራተኞች መኖሪያ ቤት ላይ ተኩስ በመክፈት፣ አቶ ተሻለ ተስፋሁንና አቶ መንግሥቴ አበበ የተባሉ ሠራተኞችን መግደላቸውን ገልጿል፡፡ አቶ አደገ ጌትነት፣ አቶ ሸጋው ቢክስ፣ አቶ ሀብታሙ እሸቱ፣ አቶ እውነቱ መሀሪና አቶ ጊዜ አዲስ አስማማው በተባሉት ሠራተኞች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጋቸውን አክሏል፡፡ ጠቅላላ ግምቱ 1,933,760 ብር በሚገመት ንብረት ላይ የማውደም ተግባር መፈጸማቸውንም ጠቁሟል፡፡
ተከሳሾቹ በተጨማሪም ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ ጉራምባ ቀበሌ ውስጥ፣ የልማት ሥራ በማከናወን ላይ በነበሩት የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሠራተኞችና ማሽኖች ላይ ጥቃት በመፈጸም ግምቱ 134,686 ብር የሆነ ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡
ተከሳሾቹ ስዊድን ከሚገኘው አስማረ ብሩ ከሚባል የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር ጋር በስልክ በመገናኘትና የተለያዩ ተልዕኮዎችን በመቀበል፣ ከነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ወር 2009 ዓ.ም. ድረስ በሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ በመዟዟር ከ23 በላይ አባላትን መመልመላቸውንና ጫሂት ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ጫካ ውስጥ የማደራጀት፣ የማስታጠቅና ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ ተከሳሾቹ በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. ጫሂት ከተማ ውስጥ አመፅ እንዲነሳ በማድረግ የከተማው ቀበሌ ጽሕፈት ቤት በእሳት እንዲወድም ማድረጋቸውንም በክሱ ጠቅሷል፡፡ ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው 350 ብር በመያዝ በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም. ለሥልጠና በሁመራ በኩል ወደ ኤርትራ መሄዳቸውን፣ በተመሳሳይ ወር አስማረ ብሩ የተባለው የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር ከስዊድን 350,000 ብር ልኮላቸው በበለሳና በአርማጭሆ ወረዳ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት የቡድኑ አባላት ጋር በመሆን የሽብር ተግባር ድርጊቱን እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡
ተከሳሾቹ በጎንደር ከተማ አካባቢ ለጊዜው ካልተያዙና ስማቸው ያልታወቁ ስምንት ሰዎችን ለሽብር ተግባር በመመልመል የፖለቲካና ወታደራዊ ሥልጠና እንዲሰጣቸው ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ቃፍታ ሁመራ ወረዳ በማድረግ ወደ ኤርትራ መላካቸውን፣ መሠረተ ልማቶችን ለማውደም ተልዕኮ መቀበላቸውንና በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀእናለ)፣ 35፣ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 (1፣4እና6) የተደነገጉትን በመተላለፍ የሽብር ተግባር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ዓቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ለተከሳሾቹ ክሱን በችሎት አንብቦላቸው፣ ጠበቃ ማቆም አለማቆማቸውን ወይም መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው መፈለግ አለመፈለጋቸውን ለመጠባበቅ ለጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡