Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ካሩቱሪ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ጠቅልሎ መውጣቱን ይፋ አደረገ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የኩባንያው ባለቤት ‹‹ተስፋ ቆርጫለሁ ተሸንፌያለሁ›› አሉ

   ለሰባት ዓመታት ያህል በጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ከመቶ ሺሕ ሔክታር  በላይ መሬት የእርሻ ቦታ በመያዝ የሜካናይዝድ ግብርናን ለማካሄድ ሲሞክር የቆየው የህንዱ ካሩቱሪ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ለቆ መውጣቱንና ኢንቨስትመንቱን ማቋረጡን ለሪፖርተር ይፋ አደረገ፡፡

  የኩባንያው ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ራም ካሩቱሪ ማክሰኞ መስከረም 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን ለሪፖርተር ከህንድ በላኩት የጽሑፍ መልዕክት፣ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ የነበረውን ኢንቨስትመንት በማቋረጥ መውጣቱን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በመሸነፋችንና ተስፋ በመውቁረጣችን ከኢትዮጵያ ለመውጣት ወስነናል፡፡ በቅርቡም መግለጫ እናወጣለን፤›› የሚል መልክዕት ቢያስተላለፉም፣ ዝርዝር ሁኔታውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ‹‹እንድታውቁት ያህል ነው . . .›› በሚለው መልዕክታቸው ራም ካሩቱሪ፣ ‹‹ተስፋ ቆርጫለሁ ተሸንፌለሁ፤›› በማለት ከኢትዮጵያ ለመውጣት ስለመወሰናቸው ተናግረዋል፡፡

  ስለጉዳዩ መንግሥት የሚያውቀው ጉዳይ እንዳለ ለማወቅ ለጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ጋት ሉዋክቱት፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ እንዲሁም ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ስልክ በመወደል መረጃ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

  ካሩቱሪ ለመጨረሻ ጊዜ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ 70 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ የሥራ ማስኬጃ ብድር በጋምቤላ የሚገኘውን መቶ ሔክታር የእርሻ መሬት በዕዳ ማስከበሪያነት መያዙ ያሳደረባቸውን ከፍተኛ ቅሬታና የደረሰባቸውን ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ አስታውቀው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

  ንግድ ባንክ የመጀመሪያውን የ25 በመቶ የብድር ማራዘሚያ ክፍያ በመቀበል ቀሪውን በድርድር እንዲከፍሉ ማድረጉን፣ ከፍርድ ቤት ዕገዳ በማስወጣት የባንኩ የሐራጅ ማስታወቂያ እንዲገታ ሲከራከሩ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህኑና በወቅቱ በግብርና ሚኒስቴር ሥር የነበረው የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የካሩቱሪ ይዞታ ከነበረው መሬት ውስጥ ከ98 ሺሕ ሔክታር በላይ መንጠቁን ማስታወቁንም መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

  ራም ካሩቱሪ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ቆየት ብለው እንደነበር ሲታወቅ፣ በመጀመሪያ ተሰማርተው የነበረውም በአበባ እርሻ መስክ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ሁለት የአበባ እርሻ ኩባንያዎችን በመክፈት ሲንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት ከጋምቤላ ክልል ባለሥልጣናት በቀረበላቸው ግብዣ መሠረት 300 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደተሰጣቸው፣ እሳቸው ግን ‹‹አቅሜ አይችልም›› በማለት መሟገታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይህም ሆኖ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት አንድ መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት ሊሰጣቸው እንደቻለ ይታወቃል፡፡

  ከንግድ ባንክ በተጨማሪ ዘመን ባንክን ጨምሮ ከሌሎች የግል ባንኮችም ብድር በመደበር የሚታወቀው ካሩቱሪ፣ በተለይ ከዘመን ባንክ ጋር የነበረው ግንኙነት በፍርድ ቤትና በሽምግልና ጭምር ሲታይ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የነበራቸውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አስቸጋሪ ያደረጉት የኢትዮጵያ መንግሥት የበታች ሹማምንት ናቸው በማለት ክፉኛ የወረፉት ካሩቱሪ፣ መሬታቸውን ቢነጠቁ በህንድ መንግሥት በኩል መብታቸውን እንደሚያስከብሩ፣ ‹‹ንኩኝና የህንድን ኃያልነት ታያላችሁ፤›› በማለት ጭምር ብስጭታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና በላኩት ጽሑፍ ‹‹ተሸንፍሁ›› ያሉት፣ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተሟግተው ይሁን አሊያም፣ ‹‹እስካሁን የሞከርኩት ይበቃኛል ከእንግዲህ አልችልም፤›› ለማለት ፈልገው እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም፡፡

  የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ቀድሞ ግብርና ሚኒስቴር ይባል በነበረበት ወቅት ስለወሰደው ዕርምጃ ሲገልጽ፣ ባለሀብቱ ከሚጠበቀው በላይ ፕሮጀክቶቻቸውን በማዘግየታቸውና ውጤት ሊያሳዩ አለመቻላቸው፣ ለኢንቨስትመንት ማበረታቻ ተብሎ በተጣቸው ከቀረጥ ነፃ ዕድል የገቡ ማሽነሪዎችን ሲሸጡ መገኘታቸው፣ ወዘተ ዕርምጃ ለመውሰድ እንዳበቃው፣ የካሩቱሪ እህት ኩባንያ የሆነው ካሩቱሪ ግሎባል ኩባንያም ህንድ ቀውስ ውስጥ መግባቱ፣ በተለይም በኩባንያው ባለድርሻ ቤተሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሳቢያ ችግር ውስጥ መግባቱን መንግሥት እንደተገነዘበ በወቅቱ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

   

   

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች