Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትድብልቅ ስሜት ያስተናገደው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት

ድብልቅ ስሜት ያስተናገደው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት

ቀን:

በዓመታዊ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጎልተው ለሚታዩ ስፖርተኞች የተለየ ሽልማት የሚበረከትላቸው መድረክ የውድድር አንድ አካል እየሆነ መምጣት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በተለይ በዓለም የብዙኃኑን ቀልብ በገዛው የእግር ኳስ ጨዋታ የዋንጫ ባለቤት የሚሆነውን ክለብ ከማወቅ ባልተናነሰ፣ የዓለም ምርጥ ተሸላሚ ተጨዋቾችን ለማወቅ የሚደረገው ጥረትና ጉጉት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

የዓመቱ ምርጥ እግር ኳስ ተጨዋች፣ ምርጥ ግብ አስቆጣሪ፣ ምርጥ አትሌት፣ የክብረ ወሰን ባለቤትና ምርጥ ስፖርተኛ በማለት በተመልካች ድምፅ፣ በባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ምርጫ ሽልማት ማበርከት ከተለመደ ረዥም ጊዜ አስቆጥሯል፡፡

በተለይ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የሚዘጋጀው የባላንዶር ሽልማት በቴሌቪዥን መስኮት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ተመልካች በዓለም ዙሪያ ይከታተለዋል፡፡ የዓመቱ ምርጥ የስፖርት ሽልማት ዝግጅትን የቴሌቪዥን አውታሮች፣ ሬዲዮኖች፣ የኅትመት ሚዲያዎችና የድረ ገጽ የስፖርት የመረጃ አውታሮች የአሠልጣኞችን፣ የጋዜጠኞች፣ የአምበሎችና የተመልካቾችን ድምፅ በመጠቀም የተመረጡትን ስፖርተኞችን የመሸለም ሥነ ሥርዓት የዝግጅታቸው አንዱ አካል አድርገውታል፡፡

በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ በተለያዩ የውድድር መድረኮች ላይ ውጤታማ መሆን የቻሉ ስፖርተኞችን በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የመሸለም ባህል እየተለመደ መጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ውድድር ካጠናቀቁ በኋላ በተለያዩ ዘርፎች በመከፋፈል ሽልማት ከማበርከት ባሻገር፣ የራሱ የሆነ ጊዜ ሰጥተውና የሕዝብ አስተያየትን ተቀብለው የመሸለም ልምድ አልነበራቸውም፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በውድድሩ መጨረሻ ቀን በሁለቱም ፆታ ኮከብ ተጨዋች፣ ኮከብ ግብ አግቢ ብሎ ከመሸለም ባሻገር ዓመታዊ የሽልማት ሥነ ሥርዓት አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስም ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በአትሌቲክሱ ወርቅ ላመጡ አትሌቶች የገንዘብና የመሬት ሽልማት ከማበርከት ውጪ በዚህ ረገድ እምብዛም ሲንቀሳቀስ አይስተዋልም፡፡

መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. የመጀመርያ የሆነው የስፖርት ሽልማት ‹‹የኢቢሲ ሽልማት›› በሚል ስያሜ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ማቅረቡ አከናውኗል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር ከተፈጠረበት ቅራኔ በኋላ በቴሌቪዥን መስኮት ዕጩዎችን በማስተዋወቅ፣ የተመልካቹን ምርጫ በማስተናገድ የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኞችን በሁለቱም ፆታ አሳውቆ ሸልሟል፡፡

ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ እግር ኳስና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ሽልማቱን በጋራ ከማዘጋጀትና ከገቢ አንፃር ጥያቄ ማንሳታቸው ክርክር አስነስቶ ነበር፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተጨዋቾችን የሽልማት ሥነ ሥርዓት ይፋ እንደሚያደርግ የገለጸው ፌዴሬሽኑ፣ ኢቢሲ ያሰናዳውን ፕሮግራም በጋራ ለማሰናዳት ስምምነት ላይ ቢደርስም አዘጋጁ አካል በቀጥታ ወደ ሥነ ሥርዓቱ መግባቱ እንዳስቆጨው የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወንድምኩን አላዩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ከሆነ፣ ‹‹ማንም አካል የሽልማት ፕሮግራም የማዘጋጀት መብት ቢኖረውም ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ ለማዘጋጀት መስማማት የውድድሩን ታሪካዊ ዳራና የፌዴሬሽኑን የገቢ አቅም ማጎልበት ያስችላል፤›› በማለት አቶ ወንድምኩን አክለዋል፡፡

በመጀመርያ የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት መክፈቻ ወቅት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሥዩም መኰንን በበኩላቸው፣ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ በየዓመቱ የሚቀጥልና ሁሉንም ስፖርተኛ የሚያነቃቃ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የምርጫ ሥነ ሥርዓቱ እንደሚከናወን ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የቅሬታና የድጋፍ አስተያየትን ሲያስተናግድ የነበረው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት ሥነ ሥርዓት ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩልም ቅሬታ አስነስቷል፡፡ ፌዴሬሽኑ በተለይ ዕጩ አትሌቶችን የመምረጥ ድርሻው በባለሙያዎች መሆን በጋራ በመሥራትም ፌዴሬሽኖቹ ተጠቃሚ መሆን እንደነበረባቸውም ያስረዳል፡፡

አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ቅሬታ እንዳለው ፍንጭ ያሳየ ቢሆንም፣ የምርጫ ሥነ ሥርዓቱም እንደማንኛውም አካል እንደተመለከተው ገልጿል፡፡

በሸራተን አዲስ በተዘጋጀው የአቢሲ ስፖርት ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የቀድሞ አትሌቶች፣ አሠልጣኞች፣ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች፣ የፌዴሬሽን አመራሮችና ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ተገኝተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የቀድሞ የስፖርት ጋዜጠኞች የአዘጋገብ ሁኔታና ያበረከቱት አስተዋጽኦ በዘጋቢ ፊልም ቢቀርብም፣ ነባርና በአገሪቱ ስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ መሠረት የሆኑት እነ ሰሎሞን ተሰማ፣ ይንበርበሩ ምትኬና ፍቅሩ ኪዳኔ አለመጠቀሳቸው ትችት ሲሰማ ነበር፡፡

በ2009 ዓ.ም. በተከናወነው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሴቶች ዕጩ ሎዛ አበራ፣ ሰናይት ቦጋለና ወይንሸት ፀጋዬ ሲሆኑ፣ በወንዶች ሳላሃዲን ሰይድ፣ ጌታነህ ከበደና አስቻለው ታመነ ነበሩ፡፡ ባገኙት ድምፅ መሠረትም በሴቶች እግር ኳስ ሎዛ አበራ አሸናፊ ስትሆን፣ በወንዶች አስቻለው ታመነ በመሆን ሽልማቱንም ተረክበዋል፡፡

በአትሌቲክሱ ታምራት ቶላ፣ ሙክታር እድሪስና ዮሚፍ ቀጄልቻ ዕጩ ሲሆኑ፣ በሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ፣ አልማዝ አያናና ሰንበሬ ተፈሪ ነበሩ አልማዝ አያናና ሙክታር እድሪስ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ሁሉም አሸናፊዎች የ75 ሺሕ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

  

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...