Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

መስከረም እና ደርጋውያን

ትኩስ ፅሁፎች

የመጨረሻውን ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) ከሥልጣን ያነሣው የጦር ኃይሎች የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ደርግ፤ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በመባል ሥልጣኑን ሲቆናጠጥ፣ ቆይቶም የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሆኖ እስከ 1979 ዓ.ም.፣ በይቀጥላልም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ሆኖ እስከ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ እስካስወገደው ድረስ ዘልቋል፡፡ ፎቶው ከመጀመርያው የደርግ ሊቀመንበር ሌተና ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም በኋላ መንበሩን የተረከቡት ብርጋዲየር ጄኔራል ተፈሪ ባንቲ (ከመሃል)፣ ከተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም (በግራ) እና ከምክትል ሊቀመንበር ሌተና ኮሎኔል አጥናፉ አባተ ጋር ሆነው በአብዮት አደባባይ ለዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘማቾች ክብር ሲሰጡ ያሳያል፡፡

******

  ሁሌም

 

ዓይንን የመሠለ

ምን አለ ምን አለ

ተንከባሎ ያያል

ወደላይ ይቃኛል

ወደታች ይቃኛል

ሁሉን ያስተውላል

ሁሌም ያያል

ሁሌም ያያል

እንደ ዓይን ያለ የልብ ካውያ

የአእምሮ ወንድም ከቶ የት ይገኛል

  • ኤፍሬም ገብረሥላሴ ‹‹የግጥም … ጥም›› (2003)

***

ከውጥረት ነፃ የሆኑ አሥር የዓለም ከተሞች

እ.ኤ.አ. በ2017 ውጥረት የማይታይባቸውና ውጥረት የበዛባቸው ከተሞች ይፋ መሆናቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ የትራፊክ ሁኔታ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ የአረንጓዴ ቦታ ምጣኔ፣ የዜጎች የፋይናንስ ሁኔታ ዕዳን ጨምሮ፣ አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነትንና እንዲሁም ከተሞቹ በዓመት ለምን ያህል ሰዓት የፀሐይ ብርሃን ያገኛሉ የሚለው የመወዳደሪያ መስፈርቶች ናቸው፡፡ ይህ መዝሙር ይዘመር የነበረው

በውድድሩ ከተካተቱ 150 ከተሞች መካከል ከውጥረት ነፃ ተብለው ከተመዘገቡ 10 ከተሞች መካከል አራቱ በጀርመን የሚገኙ ሙኒክ (ፎቶ)፣ ስቱትጋርት፣ ሀኖቨርና ሐምቡርግ ከተሞች ናቸው፡፡ ከነርሱ በተጨማሪ ከውጥረት ነፃ ተብለው የተመረጡት ሉክሰምበርግ፣ ቤም ስዊዘርላንድ፣ በርዴክስ ፈረንሣይ፣ ኢደንበርግ ካናዳ፣ ሲድኒ አውስትራሊያና ግሬዝ ኦስትሪያ ናቸው፡፡

በሌላ በኩልም ውጥረት ከነገሠባቸው መካከልም የኢራቋ ባግዳድ፣ የአፍጋኒሰታኗ ካቡል፣ የናይጄሪያዋ ሌጎስ፣ የሴኔጋሏ ዳካር፣ የግብጿ ካይሮ፣ የኢራኗ ቴህራን፣ የባንግላዴሿ ዲካ፣ የፓኪስታኗ ካራቺ፣ የህንዷ ኒውደሊሂና የፊሊፒኗ ማኒላ ከአንድ እስከ አሥር እንደየ ደረጃቸው ተቀምጠዋል፡፡

***

በዘረመል ምሕንድስና በቆሎ ያመረተው በነፃ ተለቀቀ

በዘረመል ምሕንድስና የበለፀጉ የግብርና ምርቶችን የማልማት ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በብዝኃ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ አለ የሚሉ ወገኖች ጄሞ እንዳይስፋፋ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በተቃራኒው ያሉት ደግሞ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል ጥናት አለመኖሩን በመጥቀስ ጄሞ የአገሮች የግብርና አውታር እንዲሆን በመደገፍ ይከራከራሉ፡፡

ዘ ዋሺንግተን ፖስት እንደዘገበው፣ ጣሊያናዊው አርሶ አደር ጆርጅዎ ፌዴንቶ ቴክኖሎጂውን ከሚደግፉት መካከል ነው፡፡ የአገሮችን ሕግ ተላልፎ በዘረመል ምሕንድስና የበለፀገ በቆሎ በማሳው ላይ በማልማቱ ለአውሮፓ ኅብረት ፍርድ ቤት ከሰውት ነበር፡፡ ይሁንና አርሶ አደሩ ሕጉን ተላልፎ ጄሞ ያለማ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ጄሞ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ስለመኖሩ መረጃ የለም በሚል ጆርጅዎን በነፃ አሰናብቶታል፡፡

***

የአፄ ቴዎድሮስ ችሎት

አንድ ሲራራ ነጋዴ መንገድ ሲሔድ ቆይቶ ቀን በምሳ ሰዓት ከአንድ ዛፍ ሥር አረፍ ብሎ ምሳውን ቆሎ ቆርጥሞና ውሃ ጠጥቶ ጉዞውን ሲቀጥል ሁለት መቶ ጠገራ ብር ረስቶ ሄደ።

አንድ ገበሬ አግኝቶለት ያንን ገንዘብ ሊሰጠው ከኋላ እየሮጠ ተከተለውና ‹‹ሰውዬ ቆም ብህ ጠብቀኝ፤ ጥለኸው የሔድከው ገንዘብህን አግኝቼልሃለሁ፤›› አለው። ነጋዴውም ‹‹ያገኘኸው ገንዘብ ስንት ነው?›› ሲለው ‹‹ሁለት መቶ ብር›› አለው።

ነጋዴው ግን ‹‹እኔ የጠፋብኝ ገንዘብ ሦስት መቶ ብር ነው። አንዱን መቶ ብር የት ደብቀህ ነው ሁለት መቶ ብር የምትሰጠኝ። ሞልተህ ካላመጣህ አልቀበልህም እከስሃለሁ። እንዲህ በዋዛ አንላቀቅም›› አለው።

ገበሬውም ገንዘቡን እንደያዘ ወደ ኋላ ተመለሰ። ነጋዴው የመሠረተው የውሸት ክስ በይግባኝ ተይዞ ወደ አፄ ቴዎድሮስ ሲቀርብ የሁለቱን አባባል ካዳመጡ በኋላ ነጋዴውን ምን ያህል ገንዘብ ነው የጠፋህ? ሲሉት ‹‹ሦስት መቶ ጠገራ ብር ነው›› አላቸው።

ገበሬውንም ‹‹ምን ያህል ገንዘብ አገኘህ?›› ሲሉት ‹‹ሁለት መቶ ጠገራ ብር ብቻ ነው›› አለ።

ከዚያ በኋላ ‹‹አንተ ነጋዴው ጠፋብኝ የምትለውን ሦስት መቶ ብር ከጣልህበት ቦታ ፈልገህ አግኝ። ሁለት መቶ ብር ያገኘኸው ገበሬ ደግሞ ሁለት መቶ ብር ጠፋኝ የሚል ሌላ ሰው እስከሚመጣ ድረስ ራስህ ልትጠቀምበት ትችላለህ›› ሲሉ ፈርደው ፋይሉ ተዘጋ።

  • መክብብ አጥናው ‹‹የአባቶች ጨዋታ›› (2005)

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች