መርሐ ግብሩን እንዲታደሙ ለተጋበዙ ሰዎች በተላከው መጥሪያ ወረቀት ላይ የሴቶችና የወንዶች አለባበስ ምን መምሰል እንዳለበት ተገልጻል፡፡ ተመሳሳይ የሽልማት ዝግጅቶች ሲሰናዱ የታዳሚን አለባበስ የሚጠቁሙ መግለጫዎች መመልከት ስለተለመደ የኢትዮ ዞዲያክ ሽልማት የተለየ ላይሆን ይችላል፡፡
የሽልማት ሥነ ሥርዓቱን የሚታደሙ ተጋባዦችም መርሐ ግብሩን ይመጥናል ያሉትን አለባበስ እንዲከተሉ በአዘጋጆቹ ተጠይቀዋል፡፡ መደበኛ አለባበስ በሚል ብዙኃኑ የተስማሙበት አለባበስ የማይዋጥላቸውና መደበኛ የሚለውን አገላለጽ ከራሳቸው ዕይታ አንፃር የሚተረጉሙ መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮ ዞዲያክ ሽልማት የመጀመርያ ዙር መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በተካሄደበት ወቅት ብዙዎቹ ታዳሚዎች መደበኛ ባሉት አለባበስ ተገኝተዋል፡፡
የሽልማት ሥነ ሥርዓቱን ለመታደም ወደ 11 ሰዓት ገደማ በቦታው ተገኘን፡፡ መግቢያው ላይ የሚፈትሸው፣ ሰዎች የጥሪ ወረቀት ይዘው መገኘታቸው ብቻ ሳይሆን በጥሪ ወረቀቱ የተመለከተውን አለባበስ መከተላቸውም ጭምር ነበር፡፡ ‹‹አለባበሳቸው ለመርሐ ግብሩ አይመጥም›› የተባሉ ሰዎች ወደ አዳራሹ መግባት የተከለከሉ ሲሆን፣ በሁኔታው ቅሬታቸውን ያሰሙ ነበሩ፡፡ በአንፃሩ የመርሐ ግብሩ ታዳሚ ኪነ ጠቢባን ወደ አዳራሹ ከመዝለቃቸው በፊት በተዘጋጀላቸው ቦታ ፎቶ ይነሳሉ፡፡
በኢትዮ ዞዲያክ ሽልማት በ12 ዘርፎች ለውድድር ከቀረቡ 60 ዕጩዎች መካከል ለ12ቱ አሸናፊዎች ተበርክቷል፡፡ ባለፉት ሳምንታት በ8251 የስልክ መስመር ለዕጩዎቹ ድምፅ ይሰጥ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ሽልማቱ የተጀመረው በያዝነው ዓመት ሲሆን፣ ከዕጩዎቹ መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኙ ለሽልማት በቅተዋል፡፡ መርሐ ግብሩ የመጀመርያው ቢሆንም በሌሎች የሽልማት ሥነ ሥርዓቶች እንደሚታየው ብዙ ስህተቶች አልተስተዋሉም፡፡
መድረክ መሪዎቹ ታዳሚዎችን ዘና በሚያደርግ ንግግር ዝግጅቱን የመሩ ሲሆን፣ በመርሐ ግብሩ መቆራረጥም አልተስተዋለም፡፡ በእርግጥ ሽልማቱ ይጀመራል ከተባለበት ሁለት ሰዓት ዘግይቶ መጀመሩ ታዳሚዎችን ያስቀየመ ነበር፡፡ የሽልማቱ አዘጋጆች ጋዜጠኞችና ፎቶ ጋዜጠኞችም ካሜራ ይዘው ወደ አዳራሹ መግባት እንደማይችሉ ገልጸውልን ነበር፡፡ አዘጋጆቹ ለፎቶግራፍ ከመደቧቸው ባለሙያዎች ፎቶ እንድንወስድ ቢጠይቁንም፣ እያንዳንዱ ሚዲያ አንድን መርሐ ግብር የሚሸፍንበት የራሱ መርህና መንገድ ስላለው የሚዲያችን ፎቶ ጋዜጠኛ ፎቶ ማንሳት እንዳለበት አስረድተናቸው ወደ አዳራሹ እንድንገባ ተፈቀደ፡፡
የኢትዮ ዞዲያክ ሽልማት መጠሪያ ኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበብ ከዋክብትን እንደሚያመለክት አዘጋጆቹ ይናገራሉ፡፡ በኪነ ጥበቡ የላቀ የሠሩ ባለሙያዎችን ለማበረታታት ሽልማቱ መጀመሩንም ያክላሉ፡፡
በመዚቃ፣ በፊልምና ሌሎችም የኪነ ጥበብ ዘርፎች ሽልማት የሚሰጡ ተቋሞች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል፡፡ በዘርፉ ጤናማ የሆነ ፉክክር ለመፍጠር፣ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉ ባለሙያዎችን ዕውቅና ለመስጠትና የላቀ ጥበባዊ ሥራ ያበረከቱትን ለማወደስ ሽልማት አስፈላጊ ነው፡፡ ባደጉ አገሮች በጉጉት የሚጠበቁና አሸናፊዎች ብቻ ሳይሆን ዕጩዎችም በመካተታቸው የሚኩራሩባቸው ሽልማቶች አሉ፡፡ ክብርና ዝናቸውን ጠብቀውም ለዓመታት ዘልቀዋል፡፡ በአገራችን በተለያዩ ተቋሞች ተነሳሽነት ተጀምረው መቀጠል የቻሉና ደብዛቸው የጠፋም ሽልማቶች አሉ፡፡ በዕውን ለኪነ ጥበብ በመቆርቆርና ጥበብን ለማሳደግ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት ሽልማት የጀመሩና ጊዜያዊ ጥቅምን ለማሳደድ ዘርፉን የተቀላቀሉትን ጊዜ እንደሚለያቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የኢትዮ ዞዲያክ የመጀመርያው ዙር በተካሄደበት ዕለት በየዘርፉ ላሸነፉት ሽልማት እንዲያበረክቱ የተጋበዙ አንጋፋ ባለሙያዎች ሽልማቱ ዘላቂነት እንዲኖረው ጠይቀዋል፡፡ አሳስበዋልም፡፡ ውድድሩ በ2009 ዓ.ም. የወጡ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች የተፎካከሩበት ሲሆን፣ አሸናፊዎች 24 ካራት ወርቅ ቅብ ዋንጫ እንደተበረከተላቸው አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ በዓመቱ ምርጥ አዲስ ድምፃዊት ዘርፍ፣ ሰላማዊት ዮሐንስ ‹‹ሰናይ››፣ መሳይ ተፈራ ካሳ በ‹‹ብርቄ ነሽ››፣ ጂ መሳይ በ‹‹አገኘኋት››፣ ብስራት ሱራፌል በ‹‹ወጣ ፍቅር›› እና ዳዊት ዓለማየሁ በ‹‹ኢትዮጵያ›› ታጭተው፣ ብስራት ሱራፌል አሸንፏል፡፡
ዮዲት ጌታቸው በ‹‹እንቆጳ››፣ ዘለዓለም ብርሃኑ በ‹‹አፄ ማንዴላ›› እና ብሩህ ምንዳ በ‹‹79›› የተወዳደሩት በምርጥ ተስፋ የተጣለበት/ባት ተዋናይት ዘርፍ ሲሆን፣ ዘለዓለም ብርሃኑ አሸንፏል፡፡ ሽልማቱን የሰጠችው ተዋናይት ፍቅርተ ደሳለኝ፣ ኪነ ጥበብ ዋጋ ተሰጥቶት ባለሙያዎች የሚሞገሱበት ዘመን ላይ በመድረሷ የተሰማትን ደስታ ‹‹ሙያችን ይህን ያህል ክብር አልነበረውም፡፡ አሁን ኪነ ጥበብ አሸንፋ ዓለምን በቁጥጥሯ ሥር አውላለች፤›› በማለት ገልጻለች፡፡
በዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍ የተወዳደሩት አምስት ዕጩዎች ጌትሽ ማሞ በ‹‹ተቀበል››፣ ወንዲ ማክ በ‹‹እጅ ወደ ላይ››፣ አማኑኤል የማነ በ‹‹መኣረየ››፣ ሳሚ ጎ በ‹‹ኢትዮ ሼክ›› እና ይርዳው ጤናው በ‹‹ሠራችልኝ›› ሲሆኑ፣ ጌትሽ ማሞ አሸንፏል፡፡ ተሸላሚው ድምፃዊ ‹‹የሸለማችሁኝ እናንተ ናችሁ፤›› ብሎ ሕዝቡን ሲያመሰግን፣ ሽልማቱን ያስረከበው ሚካኤል በላይነህ፣ ‹‹ዕውቅና የሚሰጥ ሲኖር ባለሙያ ይበረታታል፡፡ ጀምረው የቀጠሉ ትንሽ ናቸው፡፡ እናንተ እንደምትቀጥሉ አምናሁ፤›› ሲል ለአዘጋጆቹ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ቃልኪዳን ጥበቡ በ‹‹ምዕራፍ 2››፣ ሰላም ተስፋዬ በ‹‹79››፣ ፀጋነሽ ኃይሉ በ‹‹እግዜር ድልድይ››፣ ዘሪቱ ከበደ በ‹‹ታዛ›› እና ፍርያት የማነ በ‹‹ማያ›› በዓመቱ ምርጥ መሪ ተዋናይት ዘርፍ ተወዳድረው ሰላም ተስፋዬ አሸንፋለች፡፡
በምርጥ የቪዲዮ ክሊፕ ዘርፍ ለውድድር የቀረቡት አምስት ዕጩዎች ያሬድ ነጉ በ‹‹ያጉቴ››፣ ሙሉ ዓለም ታከለ ‹‹እኔ እሻልሻሁ››፣ ልጅ ሚካኤል በ‹‹አንቺ ለኔ››፣ ዚጊ ዛጋ በ‹‹በሲማ ዬ›› እና አቡሽ ዘለቀ ‹‹ኤ ማላዌ›› ነበሩ፡፡ አሸናፊው ልጅ ሚካኤል፣ ‹‹የሽልማት ሥነ ሥርዓት ደርሼም ተመልሻለሁ፡፡ ሰዎች እንዲመርጡኝ ቅስቀሳ ባደርግም ይህንን ሽልማት አገኛለሁ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፤›› ብሏል፡፡
ሽልማቱን ያቀበለችው ፀደንያ ገብረማርቆስ የሌሎቹን ሸላሚዎች አስተያየት ተጋርታለች፡፡ ጥበቡ አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንዲራመድ ባለሙያዎች እርስ በርሳቸው መከባበር እንዳለባቸው ተናግራለች፡፡ ‹‹እኛው ራሳችንን ካላከበርን ጥበቡ ሌላ ርቀት የመሄድ ጉልበት አይኖረውም፡፡ ብዙ ሸላሚዎች መጥተው ሄደዋልና፤ የዛሬ አምስትና አሥር ዓመት ያገናኘን፤›› ብላም ለሽልማቱ መቀጠል ያላትን ተስፋ ገልጻለች፡፡
በዓመቱ ምርጥ መሪ ተዋናይ ዘርፍ ሔኖክ ወንድሙ በ‹‹የእግዜር ድልድይ››፣ ሚካኤል ሚሊዮን በ‹‹ባለ ጉዳይ››፣ ታሪኩ ብርሃኑ በ‹‹እንደ ቀልድ››፣ ግሩም ኤርሚያስ በ‹‹79››፣ አማኑኤል ሀብታሙ በ‹‹ታዛ›› እና ካሳሁን ፍሥሐ በ‹‹ማያ›› ተወዳድረው ግሩም ኤርሚያስ አሸንፏል፡፡ በተያያዥ በዓመቱ ምርጥ ፊልም ዘርፍ ለውድድር ከቀረቡት ታዛ፣ የእግዜር ድልድይ፣ ምዕራፍ 2፣ አፄ ማንዴላና 79 በብዙኃኑ የተመረጠው ታዛ አሸንፏል፡፡
የሙዚቃና ፊልም ዘርፎችን በማዋሃድ የተሰጠው ሽልማት፣ ሌላው የውድድር ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ ሙዚቃ አቀናባሪ ነው፡፡ ካሙዙ ካሳ፣ ጊልዶ ካሳ፣ ታምሩ አማረ፣ አቤል ጳውሎስና ሚካኤል ኃይሉ የዘርፉ ተወዳዳሪዎች ሲሆኑ፣ ጊልዶ ካሳ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ዞዲያክ ሌላው ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሲሆን፣ የዘርፉ ሽልማት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ደማቅ አሻራ ካኖሩ ድምፃውያን አንዷ ለሆነችው አስቴር አወቀ ከአንጋፋው ድምፃዊ አሊ ቢራ እጅ ተበርክቷል፡፡ ድምፃዊቷ ከአገር ውጪ በመሆኗ ፕሮዳክሽን ማናጀሯ ሽልማቱን ተቀብላለች፡፡
አንተነህ ኃይሌ በ‹‹እግዜር ድልድይ››፣ ቅድስት ይልማ በ‹‹ታዛ››፣ ፍቅረኢየሱስ ድንበሩ በ‹‹ምዕራፍ 2››፣ ሙሉዓለም ጌታቸው በ‹‹አፄ ማንዴላ›› እና ተካበ ታዲዮስ በ‹‹79›› ፊልም በዓመቱ ምርጥ አዘጋጅ ዘርፍ ተወዳድረው ቅድስት ይልማ አሸንፋለች፡፡ በተለያየ ዘርፍ የታጨው ፊልሙ በሁለት ዘርፍ ያሸነፈ ሲሆን፣ አዘጋጇ በፊልሙ ሥራ ወቅት የተሳተፉትን ባለሙያዎች አመስግና ‹‹ሽልማቱ የናንተ ነው፤›› ብላለች፡፡
በዓመቱ ምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ዘርፍ መለከት፣ ሞጋቾች፣ ዘመን፣ ወላፈንና ዋዜማ በዕጩነት ቀርበው ዘመን ሽልማቱን አኝግቷል፡፡ ከተፈሪ ዓለሙ እጅ ሽልማቱን የተረከበው ሰለሞን ዓለሙ ‹‹ሽልማት ከየትም ይምጣ ከየት ያስደስታል፤›› ብሎ ሸላሚዎቹ ዘላቂነት እንዲኖራቸው ተመኝቷል፡፡
የውድድሩ የመጨረሻ ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ አልበም ሲሆን፣ የኢዮብ መኰንን ‹‹እሮጣለሁ››፣ የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ኢትዮጵያ››፣ የኤደን ገብረሥላሴ ‹‹ወስን››፣ የቃቆ፣ የብስራትና የሙሌ ‹‹መንገደኛ›› እና የኃይልዬ ታደሰ ‹‹በዘመኔ›› ዕጩዎች ነበሩ፡፡ ያሸነፈው የቴዎድሮስ ካሳሁን አልበም ሲሆን፣ ማናጀሩ ‹‹ቴዲ ከባንዱ ጋር ከፍተኛ ጥናት ላይ ነው፤›› ብሎ ሽልማቱን ተቀብሎለታል፡፡ ‹‹ዓመቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፍትሐዊነት እኩል የሚኖርበት ይሁን፤›› ሲልም ታዳሚው ድጋፉን አሰምቷል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ለዘለዓም በክብር ትኑር›› በሚል ኃይለ ቃልም የኢትዮ ዞዲያክ የ12 ዘርፎች ሽልማት ተገባዷል፡፡ አዘጋጆቹ እንደገለጹት፣ በዕለቱ ከተሰጡ የዋንጫ ሽልማቶች በተጨማሪ ባለሙያዎችን የሚያበረታታ የገንዘብ ሽልማትም ይሰጣል፡፡