አቶ መሐመድ አህመዲን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ
የዚህን ዓመት የትምህርት ልማት ሥራን አስመልክቶ ከመስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የትምህርት ንቅናቄ ፕሮግራም በመካሄድ ላይ ነው፡፡ ፕሮግራሙንም ምክንያት በማድረግ አቶ መሐመድ አህመዲን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በተወሰኑ የመማር ማስተማር ሥራዎች ዙሪያ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ ይህንንም ቃለ ምልልስ ታደሰ ገብረማርያም እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡
ጥያቄ፡- የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ሥርዓት ከቁጥጥር የወጣ ይመስላል፡፡ በየዓመቱ ጭማሪ ማድረጋቸው እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ዓይነቱን አካሄድ ለማስቀረት ምን እየተሠራ ነው?
አቶ መሐመድ፡- የግሉ ዘርፍ ልማታዊ በሆነ አግባብ የሚሠራባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ሲገባ ግን ዝም ብሎ ተነስቶ አይደለም፡፡ የሚገባበት አሠራርና ሥርዓት አለው፡፡ ከገባ በኋላ ግን ሥራውን ሲያንቀሳቅስና ወይም አተገባበሩ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹም መካከል አንዱና ዋነኛው የክፍያ ሥርዓት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ችግሩን በመገንዘቡ የተነሳ የክፍያውን ሥርዓት የሚገልጽ መመርያ በ2007 ዓ.ም. አውጥቷል፡፡ መመርያውን በመተግበር ረገድ አንዳንድ የታዩ ወይም ብቅ፣ ብቅ ያሉ መልካም ነገሮች የነበሩ ሲሆን ደካማ ችግሮችም ተከስተዋል፡፡ በዚህ ዓመት ላይ ግን የደረስንበትን ተጨባጭ ሁኔታ ስናየው ብዙዎቹ ችግሮች የተቀረፉበት ነው፡፡
ጥያቄ፡- የተቀረፉት ችግሮች ምንድናቸው? እንዴትስ ተቀረፉ?
አቶ መሐመድ፡- በግል ትምህርት ቤቶች ወላጆች በክፍያው ጉዳይ ላይ ከባለሀብቱ ጋር ለመደራደር የሚያስችላቸው አሠራርም ሆነ አደረጃጀት ከአሁን በፊት አልነበራቸውም፡፡ ከዚህ ችግር በመነሳት የግል ትምህርት ቤት መምህር፣ ተማሪና ወላጅ ሕብረት (ወተመሕ) ተቋቁሟል፡፡ ወተመሕ ትምህርት ቤቱ የሚያቀርበውን ጥያቄ በራሱ ብቻውን ሳይሆን የትምህርት ቤቱን ልጆች ወላጆችን ይዞ በጥያቄው ላይ ይደራደራል፡፡ አንድ ትምህርት ቤት ጭማሪ ሲያስብ ለጭማሪው የሚያበቁ ምክንያቶችን ይለያል፡፡ እነዚህም ምክንያቶች ውስጥ ለቀጣይ ዓመት ጭማሪ ሊያመጣልኝ ይችላል የሚለውንም ማረጋገጫ ለሰጠው ወይም ፈቃዱን ላደሰለት ተቋምና ለወተመሕ ያቀርባል፡፡ ከእነዚህም አካላት ምላሽ ሲያገኝ ጥያቄውን ይዞ በቀጥታ ወደ ሕዝብ ይቀርባል፡፡ በትምህርት ቤቱ ልጆች ካላቸው መካከል 50 ከመቶና ከዛም በላይ የሆኑ ወላጆች ካገኘ ውይይት ያደርጋል፡፡
ጥያቄ፡- ይህ ዓይነቱ አካሄድ ውጤታማ መሆኑ እንዴት ይታወቃል?
አቶ መሐመድ፡- አሁን እየታየ ያለው አካሄድ የሚያሳየው ነገር ቢኖር 25 በመቶ ጭማሪ ማድረግ አለብኝ ብሎ ያቀረበ ትምህርት ቤት፣ ስምንት በመቶ ብቻ ይበቃሃል ብሎ የወሰኑ ወላጆች መኖራቸውን ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ለሕግ የመገዛት፣ ዕቅዳቸውን የማቅረብ፣ ሲፈቀድላቸው ወላጆችን የማወያየት፣ በተወያዩበት መሠረት ደግሞ ሲወስንና መግባባት ላይ ሲደረስ የመጨመር አዝማሚያዎችና ለሕግ ተገዢ የመሆን ነገር እየታየ መጥቷል፡፡ በወላጆችም በኩል የመደራደርና የመደራደር አቅምን ተጠቅሞ መብታቸውን የማስጠበቅ ጉዳይ እያጎለበተ የመጣበት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከክፍያ ጋር ተያይዞ ያለው ጉዳይ ከቁጥጥር ውጪ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወላጆችም ትምህርት ቤቶችም እየተደራደሩ፣ እየተግባቡና በተስማሙትም ልክ ክፍያዎች እየተፈጸሙ ነው፡፡
ጥያቄ፡- የመምህራን ምዘና ላይ አሥር ከመቶ ያህሉ ሲያልፍ የቀረው 90 ከመቶ የሚሆነው መምህር ደግሞ ወድቋል ይባላል፡፡ በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ ቢሰጡን፡፡
አቶ መሐመድ፡- መምህራን የሙያ ብቃታቸውን ታሳቢ ያደረጉና የሙያ ብቃትን ማረጋገጫ የሚሰጥ የሙያ ብቃት ምዘና አለ፡፡ የመምህሩን የምዘና ሥርዓት ሁለት ዓይነት ፈተናዎች አሉት፡፡ አንዱ በጽሑፍ ፈተና እንዲያልፍ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የግል ማህደሩ ላይ በየጊዜው የሚሠሩት ሥራ ተመዝኖ ውጤት የሚሰጥበት ነው፡፡ በምዘናው አካሄድ አኳያ የጽሑፍ ፈተናውን ያለፈ መምህር ወደ ግል ማኅደር ፈተና የሚገባበት አሠራር ነው ያለው፡፡ ይህ አሠራር ግን እንደ አገር ብዙ የተለመደ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው የአገራችን ትምህርት ምናልባት ከቄስና ከቁርአን ትምህርቶች አንስቶ ዘመናዊ ትምህርት እስከተጀመረበት ድረስ ስድስተኛ፣ ስምንተኛና አሥረኛ ክፍል የተማረ ሰው መምህር ሆኖ የመጣበት ሒደት ነው ያለው፡፡ ከሠርተፊኬት ተጀምሮ ወደ ዲፕሎማና ዲግሪ ሲመጣ ወይም ዘመናዊ የሆነውንና ያደገውን የትምህርት ሥርዓት እየተከተልን ስንመጣ ግን እያደጉ የመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ዛሬ ግን መምህርነት በትልቅ ሙያነቱ ሰርቲፋይ ተደርጎ በብቃት መመዘን አለበት የሚለው አስተሳሰብ እየመጣ ነው፡፡ ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ምዘና ትልቁ ፋይዳው ለማሠልጠኛ ተቋሞቻችን ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የመጀመርያው ምዘና ተሰጥቷል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ አምስት ሺሕ መምህራን የሙያ ብቃት ምዘና ቢወስዱም ውጤቱ ግን ብዙ የምንኩራራበት አይደለም፡፡ ነገር ግን ለማሠልጠኛ ተቋማት ጥሩ ግብረ መልስ የሰጠ ነው፡፡
ጥያቄ፡- የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መምህራንን በሥራቸው ላይ የማቆየት ወይም ሊያስቆያቸው የሚያስችል ማበረታቻ (ኢንሴንቲቭ) በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ መሐመድ፡- ትልቁና መሠረታዊ የሚሆነው ነገር በሥልጠና ሥርዓታችን ውስጥ በቂ መምህራንን ወደ ገበያው የማምጣቱ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥትና የግል ትምህርት ዘርፎች (ሴክተሮች) መምህር ይፈልጋሉ፡፡ መምህሩ ደግሞ በመምህርነት ሙያ ብቻ ላይቆይ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ቢያንስ በመንግሥት የትምህርት ተቋም ውስጥ እንዲቆይ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ሥራዎች አንዱና ዋነኛው የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ መምህሩ ሊኖር የሚችልበትን ቤት የማግኘትና የመማር ማስተማሩን ሥራ እንዳይወጣ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች የመፍታት ጉዳዮች የኅብረተሰቡ ችግር ሲሆን፣ የኅብረተሰቡን ልጆች የማስተማሩ ተግባር ደግሞ የመምህሩ ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ መሠረተ ሐሳብ በመነሳት መምህሩ የመኖርያ ቤት እንዲያገኝ የተደረገበት ሁኔታ እንዳለና ይህም ሁኔታ ቀጣይነት እንደሚኖረው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም ሌላ መምህሩ ወደ ትምህርት ቤቱ በጊዜ መድረስ ካልቻለ ከጊዜ ጋር ተያያዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በማየት ትራንስፖርት የሚያገኝበትን መንገድ ለማመቻቸት የተሠሩ ሥራዎች እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ጥያቄ፡- የትምህርት ጥራት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር መቀናጀትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የጥራቱ ጉዳይ እንዴት እየታየ ነው?
አቶ መሐመድ፡- በትምህርት ጥራት ዙሪያ መሠራት ያለባቸው በርካታ ሥራዎች ናቸው፡፡ እንደ ዘርፍ የውስጥም የውጭም ጉዳዮች ይኖሩታል፡፡ የትምህርት ጥራት ሥራ መሠረታዊ የሆኑ ጠቋሚዎች ያሉት ተግባር ነው፡፡ አንድ ወቅት ሠርተነው የምናበቃ አይደለም፡፡ ወይም ውስን ተግባራትን በመሥራት የሚፈለገው ነገር ይመጣል ተብሎ የሚወሰድ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ የበቃ መምህር በበቂ ሁኔታ የማቅረብና የመምህር ተማሪ ጥመርታ ጉዳይ አንዱ የትምህርት አመላካች ተብሎ የሚወሰድና ለጥራት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ያለው ነው፡፡ የክፍል ተማሪ ጥመርታም በተመሳሳይ መልኩ የመጽሐፍ ተማሪ ጥመርታ እንደ አንድ መነሻ ይመሰዳል፡፡ በመሠረቱ ሁሉም መምህራን የቅድመ ሥልጠና የወሰዱ ናቸው፡፡ በሥራ ላይም የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ይወሰዳሉ፡፡ በዚህ መልኩ በበቁና ልምድ ባዳበሩ መምህራን ልጆችን ማስተማር ለጥራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ጥራትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ተከታታይነት ያለው ሥራ መሠራት እንዳለበት ግድ ይላል፡፡
ጥያቄ፡- በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ዴስኮችና ወንበሮች ተሰባብረው ይታያሉ፡፡ ከጥገናውና ከግብዓት አቅርቦት አኳያ ምን እየተሠራ ነው? የመማርያ መጻሕፍት ሥርጭት ላይ እጥረት እንዳለ ይታያል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን ጥረት ተደርጓል?
አቶ መሐመድ፡- ከግብዓት አቅርቦት አንፃር በአንድ ወቅት ሠርተን የምናበቃው ነገር አይደለም፡፡ ዛሬ የተጠገነ ፕላዝማና ወንበር ነገ ሊበላሽ ይችላል፡፡ ይህንን በመገንዘብ ሰፋ ባለ መልክ ጥገናዎችን ለመሥራት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በመገንባት ላይ ያሉ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም በነባር ትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነቡ ሕንፃዎች አሉ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ የሚውል በጀት ተይዞ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው፡፡ ከመጻሕፍት አቅርቦት ወይም ሥርጭት አንፃር ሲታይ ደግሞ ከውስን የትምህርት ዓይነቶች በስተቀር በሌሎች ላይ መቶ በመቶ የመጻሕፍት አቅርቦት አለ፡፡ የሥርጭት ሒደቱ ላይ መጻሕፍቱን ለተማሪዎቹ በትክክል ከመስጠቱ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎችን ለማሟላት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ባለድርሻ አካላትንም አሳውቀናል፡፡
ጥያቄ፡- አንዳንድ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሲቋቋም ተሰጥቷቸው የነበረው ስያሜ በቀድሞ ሥርዓት በሌላ እንዲለወጥ ተደርጎ እስካሁን እየተጠሩበት ነው፡፡ አሁን ግን ያ የቀድሞው ስያሜያቸው እንዲመለስላቸው ወይም በቀድሞው ስማቸው እንዲጠሩ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ መሐመድ፡- የትምህርት ቤት ስያሜ ያጣላናል ብዬ አላስብም፡፡ ትልቁ ነገር ትምህርት ቤት ወፍጮ ነው፡፡ እዚህ ወፍጮ ውስጥ ገብቶ የሚወጣው አካል የተፈለገውን ቅርጽ ይዞ አገር ሊገነባ የሚችል አካል ይወጣል፣ አይወጣም የሚለው ነው መሠረታዊ ጉዳይ፡፡ ጊዜ የምናጠፋ ከሆነ ማጥፋት ያለብን በዚህ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ስያሜው ግን ፋይዳ ካለው ባለቤቱ ማኅበረሰቡ ነው፡፡ ይህ እስከሆነ ድረስ ደግሞ የሚፈጽመውም ማኅበረሰቡ ነው፡፡ ትናንትም የሰየመው ማኅበረሰቡ ነው፡፡ ዛሬም ስያሜው ላይ ተስማምቶ ሊያፀድቀው የሚችለው ማኅበረሰቡ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ሕፃናትን ወደ ትምህርት ቤት የማምጣት፣ ከደሃ ቤተሰብ የወጡ ተማሪዎችን በምግብ ሥርዓት ለማቀፍ፣ የደንብ (ዩኒፎርም) ልብስ፣ የትምህርት ግብዓቶችንና ቁሳቁሶች በነፃ ሊያገኙ የሚችሉበት አካሄድ ምን ይመስላል?
አቶ መሐመድ፡- ሰባት ዓመት የሞላው ሕፃን፣ በተለያየ ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ፣ እንዲሁም መማር ሲገባቸው ያልተማሩ ጎልማሶች፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሕፃናትን ጭምር ቤት ለቤት መዝግበንና ኩፖን ሰጥተን ትምህርት ቤት ጋር የማገናኘት ሥራ በስፋት ሠርተናል፡፡ ይህም ሥራ በጥሩ ሁኔታ ከመከናወኑ የተነሳ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት እየመጡ ነው፡፡ ይህ አንድ ጥሩ ገፅታ ሲሆን የምገባ፣ ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁሶችን በነፃ እንዲያገኙ ማድረግ ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በተለያዩ ምክንያቶች የትምህርት መሣሪያ የማያገኙ ተማሪዎችን ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የትምህርት ቁሳቁሶችን እናቀርባለን፡፡ እንደ መንግሥትም የምገባ ሥርዓቱን በበለጠ የመደገፍ ሥራ እናከናውናለን፡፡ በዚህ ዓመት ቢያንስ ምግቡን ማቅረብ ባንችል ለምግብ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የማቅረቡ ጉዳይ በጀት ይዘን እየሠራን ነው፡፡ ተማሪዎችን የሚመግቡ አካላትም እንዲበረታቱ፣ እንዲደገፉ ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረግን ነው፡፡