Tuesday, February 27, 2024

መሻሻሎችን አሳይቷል የተባለው የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ጉዳይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከል ተቀስቅሶ የነበረውን ግጭት ለማብረድ፣ ባለፈው ሳምንት የፌዴራሉ መንግሥት የፀጥታ አካላት ወደ ሥፍራው መሄዳቸው ይታወቃል፡፡

በዚህ ግጭት በርካቶች ሕይወታቸውን ሲያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ለዚህ ግጭት ዳግመኛ መቀስቀስ ምክንያት እስካሁን ድረስ ቁርጥ ያለ አስተያየት ባይሰጥም፣ ግጭቱ ከዚህ የባሰ አደጋ እንዳያደርስና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መንግሥት ሰሞኑን አስታውቀዋል፡፡

ስለግጭቱ መቀስቀስና ስለተፈናቀሉ ዜጎች፣ እንዲሁም ግጭቱ ከዚህ የባሰ ጉዳት እንዳያደርስ ሲባል የሁለቱ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አቻቸው አቶ አብዲ መሐመድ በሰጡት መግለጫ፣ ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች መካከል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ በጠፋው የሰው ሕይወትና ንብረት ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማቸውም ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የደረሰው ጉዳት የአንዱ ክልል ብቻ ሳይሆን፣ በሁለቱም ክልሎች ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አቶ አብዲ በበኩላቸው በግጭቱ ምክንያት የሞቱትም ሆነ የተፈናቀሉት ዜጎች የሁለቱም ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ግጭቱ በሁለቱ ክልል ሕዝቦች መካከል እንዳልነበረ ርዕሳነ መስተዳድሮች ጠቁመው፣ ይህንን ድርጊት አውግዘውታል፡፡ ሁለቱ ሕዝቦች የአንድ ኢትዮጵያ አካል ብቻ ሳይሆኑ ዘመናትን የተሻገረ የጋራ እሴትና ባህል ባለቤቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ በበኩላቸው፣ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የኦሮሞ ሕዝብ ሶማሌዎችን፣ ሶማሌዎችም የኦሮሞ ተወላጆችን ለመከላከል መሞከራቸውን አስታውቀው፣ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍ፣ አካባቢያቸውን ማረጋጋትና በግጭቱ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው መመለስ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ይኼንን ድርጊት የፈጸሙ አካላት እነማን እንደሆኑ እስካሁን እንዳልታወቀና እየተጣራ እንደሆነ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጽ ተሰምቷል፡፡ የሁለቱ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮዎችም እርስ በራሱ የሚጣረስ መረጃ ሲያወጡ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የሁለቱ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በዚህ ድርጊት ተሳታፊ የነበሩ አካላትን ለሕግ ለማቅረብ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ቃል ገብተዋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔም፣ ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ከሁለቱ ክልሎች እጃቸው አለበት የተባሉ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት ተይዘው ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ከዚህ በፊት የተገለጸ ሲሆን፣ ወደፊትም በዚህ ድርጊት ተሳታፊ ሆነው የተገኙ አካላት በቁጥጥር ሥር ውለው ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል፡፡  

የግጭት አካባቢዎች በፌዴራል መንግሥት እንዲጠበቁ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ከወሰን አካባቢዎች ርቀው ሕዝባቸውን እንዲያረጋጉ፣ ዋና ዋና መተላለፊያ መንገዶች በመከላከያና በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ የተላለፈው ውሳኔ መተግበር እንዳለበትም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮችም ሁለቱ ሕዝቦች ለዘመናት አብረው የኖሩ በመሆናቸው ሰላማቸውን በጋራ እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፣ የተቀሰቀሰው ግጭት ዳግመኛ እንዳይፈጠርና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ ከሁለቱ ክልል ከተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎችና ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፣ ይህን ግጭት ለማስቆም የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላት ወደ ሥፍራው ሄደዋል፡፡ በዚህ ድርጊት ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦች በአፋጣኝ ለሕግ እንደሚቀርቡና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዕርምጃ እንደሚወስድባቸው ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ በተከሰተባቸው የድንበር አካባቢዎችና ቀጣናዎች የፌዴራል መንግሥት ማንኛውንም የጦር መሣሪያ ወይም ትጥቅ የሚያስፈታ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ድርጊት በሁለቱም ክልሎች መካከል ያሉ ልዩ ኃይሎች ተሳታፊ እንደነበሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለመፍታት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ኃይል ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል፡፡ አይከፈለውን ከፍሏል፡፡ ለዚህም ታላቅ ምሥጋና ይገባዋል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ግጭት አንዳንድ የልዩ ኃይል አባላት ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ይኼን አጣርተን በሕግ እንጠይቃን፡፡ በሶማሌ ክልልም ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ እነሱንም አጣርተን ዕርምጃ እንወስዳለን፤›› ብለዋል፡፡ 

ይህ ግጭት ወደባሰ ደረጃ እንዲሄድ የሁለቱ ክልሎች መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ እንደነበረም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ድርጊት ከአሁን በኋላ መቆም እንዳለበት ማሳሰቢያ የሰጡ ሲሆን፣ ይህን ድርጊት የማያስተካክሉ ከሆነ ግን ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል፡፡

‹‹የዜጎች ሰላም የማይዋጥላቸው ፀረ ሰላም ኃይሎች ችግሩ ወደ ከፍተኛ ሁኔታ እንዲሄድ በማድረጋቸው መንግሥት በሚያደርገው የማጣራት ሥራ ሁሉም ዜጋ ከመንግሥት ጎን በመቆም ትብብር ሊያደርግ ይገባል፤›› በማለት ያሳሰቡ ሲሆን፣ ችግሩን በሚያባብሱ ሚዲያዎች ላይ መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡

ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በግጭቱ ወቅት የደረሰን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ፣ እጃቸው ያሉባቸው አካላት ከየትኛውም ወገን ይሁኑ የማያዳግም ዕርምጃ መንግሥት እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሁለቱም ክልሎች በተለይም ግጭት በተከሰተባቸው አወዳይና ሌሎች አካባቢዎች መረጋጋት እየታየ እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ተፈናቅለው የነበሩ ግለሰቦች ወደ ቀያቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይም ሁለቱ ክልሎች ከፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየሠሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከቀን ገቢ ግምት ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባና በአማራ ክልሎች ተቃውሞ ሲነሳ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ከበደ ጫኔ፣ በቅርቡ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡ የቀድሞውን የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንን የተኩት አቶ ከበደ፣ ይህንን ችግር  ለመፍታት ትልቅ የቤት ሥራ ከፊታቸው እንዳለ እየተነገረ ነው፡፡

በዚህም የተነሳ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችን በጋራ አገናኝቶ የጋራ መግለጫ እንዲሰጡ ከማድረግ ባሻገር፣ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ተመልሰው በሚቋቋሙበት ላይ ከሁለቱ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ከመስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ ባሉት ቀናት በየቀኑ ውይይት እያደረጉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሚኒስትሩ፣ ብአዴን በባህር ዳር ከተማ ዓመታዊ ጉባዔውን እስከ መስከረም 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ያካሄደ ቢሆንም፣ በዚህ ጉባዔ ላይ ከመስከረም 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንዳልተሳተፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ኤምባሲ ማክሰኞ መስከረም 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይም በሐረርጌ የጎሳ ግጭትንና የበርካታ ሰዎችን መፈናቀል አስመልክቶ በሚወጡ አሳሳቢ ዘገባዎች ተረብሸናል፤›› ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ግልጽ በሆነ አካሄድ ጉዳዩን እንዲያጠራና አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲሹ ማበረታታት እንዳለበትም አሳስቧል፡፡

አገሪቱ ግልጽና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት፣ ግልጽ የመንግሥት አሠራር፣ እንዲሁም የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማትን በማጠናከር ስትችል የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር ልትሆን እንደምትችልም አመልክቷል፡፡ የሰሞኑን ሁነቶች በተጠቀሱ ዘርፎች ይበልጥ ፈጣንና ተጨባጭ ለውጥ አስፈላጊ እንደሆነ አመላካች መሆናቸውንም በመግለው አስታውቋል፡፡

ሰሞኑን በሁለቱ ክልሎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ የፖለቲካ ተንታኙ ንጋት አስፋው (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ለዚህ ግጭት መከሰት ዋነኛ መንስዔው በሁለቱ ክልሎች አመራሮች በኩል የጋራ ስምምነት ባለመደረሱ ነው፡፡ ‹‹ለፈሰሰው ደም ተጠያቂው የሁለቱ ክልሎች አስተዳዳሪዎች ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሰኛል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ መፍታት ሲገባ በሚዲያ ላይ በሁለቱ ወገኖች በኩል አላስፈላጊ ነገሮች መወራወር ከአመራር ብስለት ጉድለት የመጣ ነው ይላሉ፡፡

ሁሉም በፌዴራል ጥላ ሥር እስካሉ ድረስ መወያየትና ጉዳዩን በውስጥ ወደ በመያዝ መፍትሔ መምጣት ይገባ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ወደ ሕዝቡ ዘለቅ ብሎ በመግባት የጉዳዩን መነሻ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አጥንቶ መፍትሔ መስጠት እንጂ፣ መዘላለፍ እንደ አርዓያ የሚታይ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያለው ፖለቲካ ውጥንቅጡ የወጣ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኖች ይናገራሉ፡፡ በሶማሊያ፣ በሊቢያ፣ በሶሪያ፣ በየመንና በሌሎች አገሮች ያለው ሁኔታ ምስቅልቅሉ የበዛና በሺሕ ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞትና ስደት ምክንያት እንደሆነ ሲነገር ይሰማል፡፡ ዶ/ር ንጋት ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የቤት ሥራዋን በትክክል መሥራት እንዳለባት ይናገራሉ፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለንን የቤት ሥራ በትክክል መሥራት የሚቻለውና አሸናፊ የምንሆነው በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ያለው ግጭት ሲፈታ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ቀልድ እንደማያስፈልግ የገለጹት ዶ/ር ንጋት፣ ሕዝብና መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ግጭቶች እንዳይከሰቱ መሥራት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ግጭቶች በአገሪቱ መደጋገማቸውን አስታውሰው፣ የዚህ ችግር ዋነኛ መፍትሔ ደግሞ በአመራር አካላት ባለ ችግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  በአሁኑ ወቅት ሕዝቡን ያስመረሩና ለመልካም አስተዳደር ችግር የሆኑ አካላት እንዳሉ ተናግረው፣ ዛሬ ነገ ሳይባል ዕልባት እየሰጡ መሄድ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ባለፈው ሳምንት ለተቀሰቀሰው ግጭት ዋነኛ ተጠያቂዎችን በመለየት፣ አሁንም ቢሆን ግን ሌላ ግጭት እንዳይከሰትና የተፈናቀሉ ዜጎች የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው  መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡   

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሰሞኑን ‹‹የሕዝቦች የቆየ ወንድማማችነት በጊዜያዊ ችግር ሳይገታ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤›› በሚል ርዕስ መግለጫ አውጥቷል፡፡

‹‹አገራችን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ገና ጨቅላ ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ባለፈባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ አንፀባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለ ነው። ከአሁኑ ለሌሎች አገሮች ልምዶችን እያካፈለ የሚገኝም ሥርዓት ሆኗል፡፡ አገራችን ሰላም በራቀው የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ እየኖረች፣ የራሷን ሰላም አስተማማኝ ከማድረግ አልፋ ለአካባቢውና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሰላም ዘብ ለመሆን የበቃችውም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወደውና ፈቅደው በመሠረቱት ፌዴራላዊ ሥርዓት አማካይነት ውስጣዊ ሰላሟን በአስተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥ በመቻላቸው ነው። ኢትዮጵያውያን እነዚህና ሌሎች በርካታ አንፀባራዊ ድሎችን ማስመዝገብ የቻሉት ግን መንገዳቸው ሁሉ አልጋ በአልጋ ስለሆነላቸው አልነበረም። በየወቅቱ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ሁሉ በፌዴራል ሥርዓታቸው ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው በፅናት እየፈቱ በማለፋቸው እንጂ፤›› ይላል መግለጫው፡፡  

በቅርቡ ካጋጠሙ ፈተናዎች መካከል አንዱ በአንዳንድ አካባቢዎች ከወሰን ጋር ተያይዘው ይነሱ የነበሩት ችግሮች እንደሆኑ፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የፌዴራሉና የሚመለከታቸው የክልል አመራሮችና ወንድማማች ሕዝቦች በጋራ ሲሠሩ መቆየታቸው፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ ተፈጥረው የነበሩትን ችግሮች በመፍታት ረገድ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል ብሏል፡፡ ‹‹በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በተካሄደው እንቅስቃሴ አበረታች ሥራዎች ቢከናወኑም፣ አሁንም ቀሪ ሥራዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ መሀል ግን ለዘመናት አብረው የኖሩትን የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ወንድማማች ሕዝቦችን ፈጽሞ ሊወክል የማይችል ግጭት ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ለወገኖቻችን ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ ግጭት ሳቢያ ሕይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሁሉ የኢፌዴሪ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን ይመኛል፤›› በማለት ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

ችግሩ ወደ ከፋ አደጋ እንዳይሸጋገር ለመቆጣጠር ሲባል የአገር መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት ግጭቱ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ከክልሎቹ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በትብብር በመሥራት፣ ሁኔታውን በመቆጣጠርና በማረጋጋት ላይ እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡ ግጭቱን በማነሳሳትና በማባባስ የተሳተፉ ወገኖችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በሚከናወነው የቁጥጥር ሥራም በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም፣ አስቀድሞ ለመከላከል ሲባል የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች በሥፍራው ተገኝተው ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ ናቸው ብሏል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በጊዜያዊ ማረፊያ ቦታዎች በማቆየት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ በመደረግ ላይ መሆኑን፣ በቀጣይም ወደ ቀድሞ መኖሪያ አካባቢዎቻቸው ተመልሰው የተረጋጋ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

ችግሩን ከማረጋጋት ባለፈ በዘላቂነት ይፈታ ዘንድ መንግሥት ከክልሎቹ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሕዝቦች ጋር በጋራ በመሆን ከአሁን በፊት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በጊዜያዊ ግጭት ሳይረበሹ ችግሩን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ ለዘለቄታው ለመፍታት ሲያካሂዱት የነበረውን ጥረት አጠናክረው በመቀጠል፣ ለችግሩ ዘላቂ ዕልባት በመስጠት ላይ አተኩረው እንዲሠሩ መንግሥት ጥሪውን ያቀርብላቸዋል ብሏል፡፡ ‹‹የአገራችንን ሰላም፣ ልማትና ብልፅግናን የማይወዱ አንዳንድ ኃይሎች ጊዜያዊ ግጭቶችን በመቆስቆስና በማፋፋም አገራችንን ወደ ጥፋትና ውድመት ለመክተት እያደረጉት ያለው ማንኛውም እንቅስቃሴ ከሕዝቦቻችን ዕይታ የተሰወረ ባለመሆኑ፣ የአገራችንን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ስትጫወቱት የነበረውን የመሪነት ሚና አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉም መንግሥት ጥሪውን ያቀርብላችኋል፤›› በማለት በመግለጫው አትቷል፡፡

‹‹የአንዱ ወይም የሌላኛው ሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል፣ በሶሻል ሚዲያና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች አማካይነት ችግሩን በማራገብና በማጋነን፣ በሽብርና የጥላቻ ቅስቀሳ እኩይ ተግባር ላይ የተሰማራችሁ አካላት ሁሉ ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ መንግሥት ያስጠነቅቃል፤›› ካለ በኋላ አንዳንድ አካላትም፣ በተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር በመደናገጥ በደመ ነፍስ እየሰጡት ያለው መረጃና እርስ በርስ የመወነጃጀል ተግባር ችግሩን ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ የሌለው በመሆኑ ከዚህ መሰሉ አድራጎት እንዲታቀቡ መንግሥት እንደሚያሳስብ አስታውቋል፡፡ ‹‹በዚህ መሰሉ ተግባር ላይ መሳተፍ የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ከባድ ወንጀል እንደሆነም መንግሥት ማስገንዘብ ይወዳል፤›› ሲል የአቋም መግለጫው ደምድሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -